Tidarfelagi.com

ሸውራራ ፌሚኒዝም

ወደ ኋላ ስናይ!

አባት እናቶቻችን ባለ ብዙ ስህተት ነበሩ።እንደ አብዛኛው ህዝብ።በብዙ ጉዳዮች ላይ የነፃነት አስተሳሰብን አልተከሉልንም።ትልቁ የጥሩነት መለኪያቸው፣ ለታላላቆች ቃል መገዛት፣ባህል እና ልማድን መጠበቅ ወዘተ እንጂ የልጆቻቸውን intellect በመገንባት ላይ ደካማ ነበሩ። የሚያከራክረን አይመስለኝም።
ወደ ኋላ ስናይ፣ ከአሉታዊ ማህበረሰባዊ ጠባያችን አንዱ ማህበረሰቡ ሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጭቆና ነው። ከቤት ውስጥ ጭቆና ጀምረን፣ ሴቶች እንዳይነግሱ እስከሚደነግገው ክብረ ነገስት ማንሳት እንችላለን።ጉዳዩ በታሪክ ብቻ የቀረ ሳይሆን፣ አሁንም ያለ ነው። በእርግጥ ስለ ሴት ባለው እይታ ማህበረሰባችን ከአሁኗ ሳውዲ፣ አባት ልጁን ይሸጥ ይለውጥ ከነበረባት ህንድ፣ ሴት ተወግራ ከምትገድልባት ፓኪስታን… መሸላችን አይጠፋንም። ጥያቂው ግን የመሻል አይደለም!!

በኢትዮጵያ ውስጥ እንስታዊ እንቅስቃሴ ብዙ አልተለፋበትም። አውሮፓ እና አሜሪካ ላይ ለዓመታት የተደረጉትን ትግሎች በማንፀሪያ ብናይ ይበራልናል። አንድ ሁለት ብለን የምንጠራቸው ፌሚኒስቶች አሉ? አልተለፋበትም! ማለት ካለብን እንበልና፣ «ምስጋና ለሶሻሊስም» ብዙ መንገድ አሳጥሮልናል። ያ ትውልድ ኮርጆ ባመጣው ርእዮተ ዓለም፣ «ሴቶችም ወንዶችም በሶሻሊዝም አንድ ሆናችኋል»በሚል መንፈስ፣ ቢያንስ ፖለቲካዊ መብቶቹን በእኩል ተቋድሰዋል።ማህበረሰቡ ጋር ይቀራል።

ጎበጠም ተቃና ያለፈው ያለፈ ነውና ወደ ዛሬው እንለፍ። በርግጥ ይሄ ነው የሚባል የፌሚኒስት እንቅስቃሴ የለም። ያለውም ገና ጡት ያልጣለ ነው። ሲነኩት ግን ወዲያ ለንቦጩን የሚጥል ነው። ቢሆንም፣ በበጎ ይጥና እያልን ስህተት ያልነውን እንከትብ። ምን አይነኬ አለ?

አይነኬ (?)

ጭቆናውን ባንክድም፣ ጥቂት ፌሚኒስቶች ግን እኛ እንጂ እናንተ ስታወሩት አይነት አዝማሚያ ሲሰጡት አይተናል። ከዛ በላይ፣ ፍፁም ተከላካይ ሆነው ፌምኒዝምን ጭራሽ የማይነካ ሊያደርጉት ይጥራሉ። አንዳንድ ጉዳዮችን አይነኬ በማድረግ ለውይይት የመዝጋት ልማድ አለ። የቆየ ነው።ለፈለገው አዋጭ ስልት ነው!
በተለይ እኛ አይነኬ ለማድረግ የሚደርስብን ያለ አይመስለኝም። ሁሉ ነገር አይነኬ ነው። ባህሉ፣ እምነቱ የብሔር ጉዳይ እና የፆታ ጉዳይ አይነኬ ከተደረጉት ናቸው።

ነገሮች አይነኬ በሆኑ ቁጥር፣ ፈትኖ ለማሻሻል፣ አሽቶ ለማቃናት የማይመቹ ይሆናሉ። አራማጆቹ ግን የአትንኩብን ባነራቸውን ይዘው ይጓዛሉ። ይህም፣ እኔ ካልኩት ውጪ ያለው መፍትሄ የማይረባ ነው ከሚል መነሻ ነው። ወዲህም፣የጉዳዩ ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ ከሚል፣ ራስን የጉዳዩ ሐዋሪያ አደርጎ ከማየት ነው።

የመንካት ፍርሃት!

በብልጭ ድርግሙ የፌሚኒስቶቻችን ቁጣ ውስጥ የሚታየው አንዱ ችግር፣ መርጦ መንካት እና ፈርቶ መተው ነው። ስለ ሌላው ሀገር ፌሚኒዝም ሳይሆን፣ ስለ ደጃችን ፍመና ነው የማወራው።

ፌሚኒስትነታቸውን አምነን፣ አሳምነውን ሳለ… «ወንዳዊ ጥቃቱን አድነው የሚያዩበትን አይን» እያደነቅን ስንዘልቅ፣ በሴቶች ላይ ፓለቲካዊ በደል ሲፈፀም ድምፃቸው ይጠፋል።ድምፃቸው ብቻ አይደለም ትንፋቸውም ይጠፋል። ለምን? ለሚለው መልሱ የሚታወቅ ይመስለኛል።

ፓለቲካውን ብቻ አይደለም። ሃይማኖቱን፣ ወጉን፣ ልማዱን የመጋፈጥ ወፍራም ፍርሃትም አለ። እነ Simone de Beauvoir እነ Elizabeth Cady Stone … ሌሎችም ሲፅፉ ሃይማኖቱን፣ ባህሉን፣ ልማዱን ነክተው ነው። ኤልዛቤት ካዲ ስቶን እና ጓደኞቿ ለፌሚኒዝሙ ካደረጉት አስተዋፅኦ ጎን ለጎን «The women’s Bible» የሚል መፅሐፍ እስከመፃፍ ደርሰዋል።
ተቃውሟ የማያስነሳው ነገር ላይ እየተረባረቡ፣ መስሎ ለማደር ጠንካራዎቹን ማነቆዎች ዘሎ ማለፍን አደርባይነት ከሚለው ቃል ውጪ የሚገልፀው ያለ አይመስለኝም። በዚህ መንገድ ሼም ኢን ኢዝም እንጂ ፌሚኒዚም አይሰራም።

ምንጩን መሳት!

ምናልባት ፌሚኒስት ነን ያሉን ልጆች፣ የብሔር ጭቅጭቅ ካለበት ምድጃ ስር ስላደጉ ይሆናል፣ጠላት መስራትን እንደ ስልት ያዩታል። ወይም ከሱ ውጪ ማየት አልቻሉም።በድንጋጌያቸው መፅሐፍ፣ ወንድ እና ሴት አጥቂ እና ተጠቂ ናቸው። ሴት ሴትን ልታጠቃ/ልትጮቅን አትችልም። ያው መቼም victim role መውሰድ ጥሩ መላ ሆኗል በብዙ ቦታ። ይሁን። መሰረታዊ ሰህተቶቹን ግን አይጋርዳቸውም።

ሴቶች ተጨቁነዋል ስንል፣ ጨቋኙ ማነው? ማህበረሰቡ አይደል?! ማህበረሰቡ ደግሞ ከግማሽ በላይ በሴቶች የተገባ ነው። ጉዳዩ የቁጥር እንደማይሆን ይገባኛል። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። የልጆችን ባህሪ በመቅረፅ ደረጃ፣ ከወንዱ በላይ ትልቁ ስልጣን ለሴቶች የተሰጠ ነው። የስነ ልቦና ባለሞያዎች እንደሚነግሩን፣ በልጅነት የታነፀ ባህሪ ዘላቂ እና ለመንቀል ከባድ ነው። ልጆችን ከማንም ቀድሞ በማግኘት እና ባህሪያቸውን በመስራት ደግሞ፣ ከእናቶች ማንም አይቀድምም።እናቶች ልጃቸውን ሲያሳድጉ፣ ስለ ሴት ያለውን አመለካከት ይቀርፁታል? በተለምዶ «የወንድነት ባህሪ» የሚባለውን የባህሪ ልባስም አይደል የሚያለብሱት? ምን ያህሉ ወንድ፣ በእናቱ እጅ ሴትን ስለማክበር ተምሯል፣ በጎረቤቱ ወይዘሮ ተነግሮታል? ወንዱስ ትሉ ይሆናል። ወንዱማ ነገሮቹ ባሉበት ቢቀጥሉ ነው የሚመርጠው፣ ይመቸዋላ። ስህተት እንደሆነ አውቃለሁ። ግን፣ ዛሬም እናቶችም ሆኑ ሴቶች ወንዱ የሰራውንና የሚፈለገውን ልማድ ነው በታናናሾቻቸው የሚተክሉት። እንደምን ያሉት የሚል ካለ በዝርዝር ማንሳት እንችላለን።ስላልተማሩ ነው ሊባል ይችላል። አንድ ሰው መመታቱን ለማወቅ፣ መማር ያለበት አይመስለኝም። ሳይ ያደኩት፣ እያየሁም ያለሁት ወንዶች ሴቶችን እንደማያከብሩ ብቻ ሳይሆን፣ ሴቶችን ሴቶችን አንደማያከብሩ ጭምር ነው! ፈመኞቻችን ይሄን ማየት አይፈልጉም።

ማህበረሰቡ ጨቋኝ ነው ስንል፣ ሴቶቹን አልጨመረም? በልጆቻቸው ላይ ብዙ መለወጥ ሲችሉ፣ እንዲቀጥል ዝም ካሉ ጭቆናው ላይ አስተዋፅኦ አላደርጉም? ወዳ ጭቆናን የምትቀበል ሴት የለችም ይባላል። ችግሩ፣ ማህበረሰብ የሚመረውን ሲጣፍጥ እንድትል ያደርግሀል። ማህበረሰብ ከተቀበለው የሚመረው ይጣፈጣል፣ እብደቱ ጤንነት፣ ትክክሉ ስህተት ይሆናል።

ይሄ ብቻ አይደለም፣ ወንዱስ ተጠቂ አይደለም ወይ? ማህበረሰብ ሃይለኛ ነው፣ ሳትወድ ባህሪን ይሰራል ካልን፤ ወንዱ እንደ ወንድ አክት እንዲያደርግ ወይም ስለሴቶች አሉታዊ አተያይ እንዲያዝ የሚያደርገውም ማህበረሰቡ ነው። ስለዚህ፣ ወንዱም የማህበረሰቡ ተጠቂ ይሆናል። ማህበረሰብ ወንዱን፣ ወንዱ ሴቷን ያጠቃል። ሴቷም «ወንድ እኮ ነው… በሴት አያምርም…የታባቷ አንዴ በደገማት» ስትል ጥቃቷን እያቀፈች ነው። ማህበረሰቡ አውሬ እንድትሆን ቢያደርግህ፣ አንተም በአውሬነትህ የምታጠፋቸውም ተጠቂ ናችሁ። በፆታም ጉዳይ፣ የመጨረሻ እና የከፋው ውጤት ሴቷ ላይ ቢያርፍም ሁለቱም ተጨቋኝ ናቸው። This is not logic,it is a fact. ካልተማመን፣ የሶሻላይዜሽንን ኪስ መፈተሽ ነው። የአቲቲውድ ምህንድስናው በማን ቁጥጥር ስር እንዳለ ማየት ነው። ማህበረሰቡ ከተበላሸ፣ ውስጡ የሚፈለፈሉት ግለሰቦችም የተበላሹ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። አሳዛኙ ነገር፣ ሁሉም ማህበረሰብ ለራሱ ቅዱስ ነው!!

አንዲት ሴትን መቃወም፣ ሴትነትን ከመቃወም መሳ ሊያደርጉት የሚፈልጉ ሥዮመ ሶሻል ሚዲያ ፌሚኒስቶችንም እያየን እንቆዝማለን

ሰው እኩል አቅም የለውም (በተለያየ ምክንያት) እኩል ነፃነት እና መብት ግን ይገባዋል። ነፃነት ግን፣ ነፃ ካልወጣ አስተሳሰብ አይጨለፍም።

ያልተሳካ ፌሚኒዝም መጨረሻው የፍቅር ስሜትን መነጠቅ ነው። አንዳንዶቹ ፌሚኒስቶች ብቸኝነትን እንደ ስኬት ይቆጥሩታል። እያንዳንዱ ዘርፍ ሉዘር የሚያስብል የራሱ መስፈርት አለው።ያልተሳካ የፍቅር ታሪክ መያዝ አሸናፊነትን አይመሰከርም። የሚመሰክረው በፍቅር ጉዳይ loser መሆንን ነው።

የአመለካከት ልዩነቶች ይኖራሉ። እድሜ ይስጣቸው። የተሳሳቱ ሃሳቦች ሲኖሩ ግን፣ አስተሳሰቡን እንጂ የሃሳቡን ተሸካሚ በመጥላት ሸራፊ ውጤት አይመጣም።

በአጠቃላይ፣ የሴቶች ጭቆና ማህበረሰብ ደርሶት ወንድ እየተወነው እዚህ የደረሰ አይደለም። መመድረኩም ሆነ ትወናው ላይ ሴቷም ወንዱም ተሳታፊ ናቸው። የችግሩ ስር አስተሳሰቡ እንጂ አሳቢዎቹ ጋር አይደለም። አሳቢዎቹ የአስተሳሰቡ ተጠቂዎች ናቸው።ችግሩን ትቶ፣ ክስተቶችን እየተከተለ «እህህ» የሚል እንስታዊነት አንዳች አይለውጥም። ጊዜ በስልጣኑ ከሚለውጠው ውጪ። እስከዛ በድፍረት የበሽታውን ዋልታና ማገር ማየትንእንመክራለን።

በመጨረሻም፣ የሌላውን ባላውቅም ወንድ ሆኖ ሴትን አለመውደድ በጣም የሚከብድ ይመስለኛል።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

2 Comments

 • aterefmelaku29@gmail.com'
  Ateref Melaku commented on September 27, 2016 Reply

  ሸፋፋ ፌሚኒዝም::

  አሁንም ጻፍ ለምን? ይመቻል ያስተምራል ሸፋፋ የፌሚኒዝም አስተሳሰብ ያላቸውን ያስተካክላል. ግን ብዙ ሴቶች ወንድ የሚሰራውን ሁሉ ትሰራለች ይላሉ፡፡ይህን አሳብ ከተፈጥሮ እና ከ ሳይንስ አንጻር በተለይ ሥፖርት ዘርፍ በመብት እንጂ በመስራት እኩል እንዳልሆንን ያሳያል፡፡ ምን ትላለህ?

 • betelhemhailu7@gmail.com'
  ቤተልሔም commented on April 5, 2017 Reply

  ያነሳኸው ሃሳብ ጥሩ ነው፡፡ መልካም አተያይ… ነገር ግን ሁሉም ሠው የሚያንፀባርቀው በማህበረሰቡ እና በአስተዳደጉ የገነባውን ሀሳብ ነው፡፡ ጥሩ ነገርን ሳትመለከት አና በሴቶች ላይ አሳዛኝ ድርጊቶች እየተመለከተች ዝም ማለት መፍትሔ ነው? ወንዶችንም ብትጠላ ልክ ባትሆንም አይፈረድባትም…. ጥላቻን ያስተማረ ህብረተሰብም ጥሩ እይታን ሊጠብቅ አይገባም፡፡ ሴቷ በወንዶችም በሴቶችም ብትበደል እንኳን ሴቶቹም የችግሩ ተካፋይ ናቸው ይሄንን አስተሳሰብ እንዲይዙ ያረጋቸው እድገታቸው ነው፡፡ እናም በአንተ እይታ መፍትሔው ምን ይመስልሀል?? እንደ እኔ አስተያየት አሁን በሚያድጉት ልጆች (በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ)የአስተሳሰብ ለውጥ ስራዎች መስራት ካልቻልን የማንወጣው ችግር ውስጥ የሚከቱን መንገዶች ይፈጠራሉ፡፡ እናም የኛን ማንነት የማያማክል እና የሌሎቹን ሳናስተካክል እንደወረደ በመውሰድ የተሳሳተ የፌሚኒስት አስተሳሰብ እንይዛለን ወይም ለመያዝ እንገደዳለን…. ለማንኛውም ያነሳኸው ሀሳብ ጥሩ ነው፡፡ በርታ….

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...