Tidarfelagi.com

ሸሌ ነኝ

‹‹ነይ እዚህ ጋር ልብስሽን አውልቀሽ ውስጥ ሳትገቢ…ብርድልብሱ ላይ ተኚ›› ሲለኝ፤ ልማድ ሆኖብኝ መግደርደር ዳድቶኝ ነበር፡፡
ድሮ፤ ልጃገረድ እንዳለሁ ጊዜ መሽኮርመም፡፡
ሰው እንጂ ሴት ያልሆንኩ መስሎኝ፡፡
ስጋ ሸጬ እንጀራ ልገዛ ያልመጣሁ መስሎኝ፡፡
ገንዘብ ተቀብዬ ደስታን ልሰጥ ያልመጣሁ መስሎኝ፡፡
አንገቴን እንደሰበርኩ ወደ አልጋው ሄድኩ፡፡ ሲያገኘኝ እሄድ እንደነበረው አይደለም አካሄዴ፡፡ ሰበር ሰካ የለውም፡፡ እዩኝ እዩኝ የለውም፡፡ ተገዝቶ ወደ ሚታረድበት ቦታ እንደሚሄድ በግ ነው አካሄዴ፡፡
ገዢዬ፣ የማያውቀኝ ሰው ፊት ልብሴን ሳወልቅ የመጀመሪያዬ እንደሆነ አያውቅም፡፡
ገዢዬ፣ በገንዘብ ተገዝቼ ከወንድ ለመተኛት ስመጣ የመጀመሪያዬ እንደሆነ አያውቅም፡፡
ገዢዬ፣ ለዚህ ስራ ድንግል እንደሆንኩ አያውቅም፡፡
ልብሴን ማውለቅ ሳልጀምር እየፈራሁ፤ ‹‹ይቅርታ…መብራቱን ታጠፋው?›› አልኩት፡፡፡
ዞር ብሎ አየኝና ፤ ‹‹ሃሃ! ታሾፊያለሽ እንዴ…! ለምንድነው የማጠፋው…!›› አለኝ፡፡ ይስቃል፡፡
ፈራሁ ብለው አያምንም፡፡ በሰቀቀን ዝም ብዬ ማውለቅ ጀመርኩ፡፡ የአልጋው ጫፍ ላይ ኩምትር እንዳልኩ ድንገት እስካሁን መኖሩን ያላወቅኩት ብርድ አንዘፈዘኝ፡፡ ሳል ጀመረኝ፡፡ ይሄን ጊዜ ሰውየው ዞር ብሎ አየኝና፤ ‹‹ምነው…ብርድ…ቲቢ ምናምን አለብሽ እንዴ?›› አለኝ፡፡
‹‹አይ…በርዶኝ ነው…አያመኝም…አሁን በርዶኝ ነው….›› ብዬ ብርድ ልብስ ውስጥ ገባሁ፡፡
‹‹ኖኖ! ከላይ ሁኚ…አትግቢ …››አለኝ ቶሎ ብሎ፡፡ ቀጭን ትእዛዝ ነበር፡፡
እምቢ ብዬ መሄድ እንደማልችል ማወቁ አስከፋኝ፡፡
እሺ ብዬ ስለመጣሁ እምቢ ብዬ እንደማልሄድ እርግጠኛ መሆኑን ሳውቅ ከፋኝ፡፡
ከነሳሌ ከብርድልብሱ ወጣሁ፡፡
መጥቶ አጠገቤ ተኛ፡፡ሰውነቴ በፍርሃት ተንዘፈዘፈ፡፡ የውስጥ ሱሪ ብቻ ሲቀረው እርቃኑን ነው፡፡
እግዜር በሚያውቀው፤
ከማላውቀው ሰው ቤት ለማደር መምጣት አልፈለግኩም ነበር፡፡
የማላውቀው ሰው እጆቹን ጭኖቼ መሃል አስገብቶ እንዲፈነጭ አልፈለግኩም ነበር፡፡
የማላውቀው ሰው ጆሮዬን ተጠግቶ እንዲያቃትትብኝ አልፈለግኩም ነበር፡፡
ግን ሰውየው አስገድዶ አላመጣኝም፡፡
አልደፈረኝም፡፡
ያስገደደኝ ኑሮ ነው፡፡
የደፈረኝ ድህነት ነው፡፡
ሲነጋ እና ከኔ ጋር ያለውን ጣጣውን ሲጨርስ የሰጠኝን አምስት መቶ አዳዲስ ብሮች እንደያዝኩ በትእዛዝ ያወለቅኩትን ልብሴን በከፍተኛ ፍጥነት ለበስኩ፡፡ ያወለቅኩት ክብሬ ግን አልጋው ላይ ቀርቷል፡፡
‹‹ቅዳሜ እመጣለሁ..ማን ብዬ ላስጠራሽ ?›› አለኝ በተኛበት፡፡
እንድሄድ ፈልጓል፡፡ አገልግሎቴ አብቅቷል፡፡
አሁን እንደተፋቀ የሞባይል ካርድ ነኝ፡፡
አሁን እንደተጫረ የክብሪት እንጨት ነኝ፡፡
በድጋሚ በጉጉት የሚያየኝ በሚቀጥለው ቅዳሜ መጥቼ እፎይ ማለት ሲያምረው ነው፡፡
ስሜን ነግሬው ዞር አልኩና ቦርሳዬን አንጠልጥዬ ለመሄድ ስዞር፤
‹‹ማነሽ…እ…በሩን በደንብ ዝጊው›› አለኝ አልጋው ላይ ተገላብጦ ጀርባውን እየሰጠኝ፡፡
ፊት እንኳን የማይገባኝ ሰው መሆኔን ሲነግረኝ ነው በጀርባው የሚያናግረኝ፡፡
የሚታወስ ስም እንደሌለኝ ሲነግረኝ ነው ማነሽ ያለኝ፡፡
ይሄን ሳስብ ተዛባሁ፡፡
ተዛነፍኩ፡፡
ካለ አጥንት እንደተፈጠረ ሰው ሰውነቴ ለመቆምም ለመሄድም እምቢ እያለ ወደ ታክሲ ተራው ሄድኩ፡፡
ተኝቶ የነጋለት ሰው ይተራመሳል፡፡
ታክሲው ውስጥ ገብቼ መስኮቱን ደገፍ አልኩና ያለ እቅድ ስቅቅቅ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ ከአይኔ ግድብ የሚፈሰው እምባ ጉንጬቼ ላይ የሚደርቅ ሳይሆን አዋሽ ወንዝ ለመግባት ያልም ይመስል ይንዠቀዠቃል፡፡ ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው የአንገት ልብሴ ላይ ያርፋል፡፡ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው ጃኬቴ ላይ ያርፋል፡፡ ከክብሬ ጋር አውልቄው የነበረው ሱሬዬ ላይ ያርፋል፡፡
በለቅሶዬ መሃል፤ ‹‹አይዞሽ….ሁሉም ያልፋል›› የሚል ድምፅ ሰማሁና ዞርኩ፡፡
ከእኔ በእድሜ የምታንስ ልጅ ናት፡፡
‹‹ሁሉም ያልፋል›› የሚል የታክሲ ጥቅስ አንብባ የምትደለለው ለዚያ ነው፡፡ ትንሽ ልጅ ስለሆነች፡፡ በቂ ስላልኖረች፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንደኔ ላለው ሰው እንደማያልፉ የሚያስተምራት የሕይወት ልምድ ስለሌላት፡፡ ቀልደኛ!
ዝም ብዬ አየኋትና በእሺታ ጭንቅላቴን ነቅንቄ ተመልሼ ወደ መስኮቱ ዞርኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ ዛሬ እዚህ ታክሲ ውስጥ እያለቀስኩ ባልተቀመጥኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ ለአምስት መቶ ብር አምስት መቶ ቦታ ባልተሰባበርኩ፡፡
ሁሉም ቢያልፍ ኖሮ እኔ ትርሲት የአቶ ከለላው እና ወይዘሮ ስምረት ሴት ልጅ፣ የብሌን ታላቅ እህት፣ የዳዊት ታናሽ እህት፣ የዳግም ፍቅረኛ ሆኜ በቀረሁ፡፡
አሁን ግን ትርስቲት ሸሌዋ ነኝ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡
ሸሌ ብቻ፡፡
ይህንን ሰውየው አይን ውስጥ አይቼዋለሁ፡፡
ይሄንን ሰውየው ትእዛዝ ውስጥ ሰምቼዋለሁ፡፡
ይሄንን ሰውየው ‹‹በሩን በደንብ ዝጊው›› ንግግር ወስጥ አድምጨዋለሁ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡
ለማንበብ ደቂቃ የሚፈጅ ስም በመስጠት የኔን ስራ ቅዱስ ማድረግ አይቻልምና ፤‹‹ የለም፤ አንቺ እኮ ‹በወሲብ ንግድ የተሰማራች ሴት› ነሽ!›› ብላችሁ አታፅናኑኝ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ሸሌ ነኝ፡፡
በረሃብ እያዛጋሁ ቤቴ ገባሁና ከሰል አቀጣጠልኩ፡፡ ሳልበላ ውሃ ላፈላ፡፡ ሳልበላ በፈላ ውሃ ልታጠብ፡፡ ሳልበላ በፈላ ውሃ ገላዬን ልታጠብ፡፡ ሸሌነቴን በፈላ ውሃ ሙልጭ አድርጌ ልታጠብ፡፡
ውሃው እስኪፈላ ልብሶቼን አውልቄ ከሌሎቹ ልብሶቼ ጋር እንዳይቀላቀሉ በቤቴ አንዷ ማእዘን ላይ ሰብስቤ ጣልኳቸው፡፡ ብዙ ልብስ የለኝም ግን እነዚህን ልብሶች መልሼ እለብሳቸው አይመስለኝም፡፡
ራቁቴን የሰመጠች አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ውሃው እስኪፈላ እየጠበቅኩ ቤቴን አየሁት፡፡ ለሰው የሚነገር ነገር ስለሌለኝ እንትኑ እዚያ ጋር፣ እንትኑ ደግሞ እዚያ ጋር አለ ብዬ ላወራችሁ አልፈልግም፡፡
በዋጋ ከተሰላ፤ አሁን ያለኝ ዋጋ የከፈልኩበት አምስት መቶ ብር ብቻ ነው፡፡ አልጋዬ ላይ የተቀመጠው አምስት መቶ ብር፡፡
ምናልባት ካልገመታችሁ፤ እንዲህ ያለውን ዋጋ ያልከፈልኩበት ብር ለማግኘት ሞክሬ ነበር፡፡ ማለቴ ዘልዬ ሸሌ አልሆንኩም፡፡
አሳጥሬ ልንገራችሁ እና ምንም ስራ ሰርቻለሁ፡፡ ግን እኔን እና እኔን የሚጠብቁ ቤተሰቦቼን ሆድ ፀጥ የሚያደርግ፣ አንገት ቀና የሚያደርግ፣ ደረት አስነፍቶ የሚያስሄድ ስራ አላገኘሁም፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ፤ እንጀራ ፍለጋ ሴት የሆንኩት ሰው ሆኜ ስላልተሳካልኝ ነው፡፡
ልድገመው፡፡
እንጀራ ፍለጋ ሴት የሆንኩት ሰው ሆኜ ስላልተሳካልኝ ነው፡፡
የስጋ ለስጋ ኑሮን የመረጥኩት ሌላ ነገር ሆኜ መኖር ስላልቻልኩ ነው፡፡
ለምሳሌ የሆነ ሰሞን የሆነ ኤን ጂ ኦ ሸሌ የመሆን አዝማሚያ ያሳየነውንም፣ ገብተው የተንቧቹበትንም ሴቶች ሰበሰበና፤ ‹‹ከዚህ አስነዋሪና ቆሻሻ ስራ ነፃ እናውጣችሁ፤ ያልገባችሁበትንም እናድናችሁ›› አለን፡፡
‹‹አልጋ አንጣፊ ስለሆነች ከአልጋ ለመውደቅ ቅርብ ናት›› ብለው ነው መሰለኝ ፕሮጀክቱ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ደስ ብሎኝ ገባሁ፡፡ ኤን ጂ ኦው ‹‹አማራጭ የገቢ ማግኛ ዘዴዎች›› በሚል ለግማሻችን ጥልፍ፣ ለግማሻችን ዳንቴል ስራ አስተምሮ ‹‹በሉ እንግዲህ ሂዱና ንፁህ ስራችሁን እየሰራችሁ በብልፅግና ኑሩ>> ብሎ አንድ ኮንቴነር ቤት ተከራይቶልን ሄደ፡፡
እኔ ከጥልፎቹ መሃል ነበርኩ፡፡
እንደተማርኩት እየጠለፍኩ አዲሱንና ንፁሁን ስራዬን ነፃ መውጫዬ፣ መልካም እጣ ፈንታዬ፣ የእግዜር ካሳዬ አድርጌ ተቀብዬው ስራ ጀምሬ ነበር፡፡
ብዙዎቻችሁ ‹‹አንዴ ሸሌ የሆነች ወይ ለመሆን ያኮበኮበች ሴት ሁሌም ሸሌ ናት›› ብላችሁ እንደምታስቡ አውቃለሁ፡፡
በሚኒ ስከርት መንገድ መቆም የለመደች ሴት በ‹‹እስከ ጉልበት›› የስራ ቀሚስ ቢሮ መቀመጥ አትችልም ብላችሁ እንደምታምኑ አውቃለሁ፡፡
የራሳችሁ ጉዳይ!
እኔ ግን በዛ ሰሞን እፎይታ ተሰምቶኝ ነበር፡፡
ሳልጠፋ ስለተገኘሁ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
ሳልሰበር ስለተጠገንኩ እፎይ ብዬ ነበር፡፡
ሸሌ መሆን የሚያጓጓኝ ሰሞን፣ የከጃጀለኝ ሰሞን፤ አልጋ አንጣፊ ሆኜ የምሰራበት ቡና ቤት ውስጥ ያሉ የሚቀርቡኝ ሸሌዎችን ገድል እና እሮሮ በታላቅ ትኩረት፣ በቀን በቀን እሰማ ነበር፡፡ አይ ነበር፡፡
በመሸ ቁጥር በ‹‹ኮንዶም አድርግ አታድርግ›› ጭቅጭቅ በጭንቅላቱ ሳይሆን በእንትኑ ከሚያስብ ወንድ ጋር እየተጣሉ በፖሊስ መዳኘት አለ በሚሉት የማስፈራሪያ ወሬዎች ተሰላችቼ ነበር፡፡
‹‹በጥፊ ካልመታሁሽ ደስ አይለኝም›› እያለ ከላይም ከታችም ከሚደበድበኝ ወንድ ጋር አድሬ የከፈለኝን ገንዘብ በድብደባ ያበጠ ፊቴን ለመታከም ማዋሉ መረረኝ በሚሉ ሴቶች ዋይታ ተማርሬ ነበር፡፡
እሺ…ዝርዝሩ ይቅርባችሁና እንዲያው በደፈናው ፤ በጨለመ ቁጥር ባለተራ ወንድ እላዬ ላይ ስለማይንደፋደፍብኝ የእውነት ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
ከዚህ እጣ ፈንታ ለጥቂት ስላመለጥኩ፤ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡
እናም፤ ቀን ቀን እየጋለ አቅልጦ እንደ ውሃ ሊያፈሰኝ በሚዳዳው ሙቀት ፣ ሲመሽ ሲመሽ ጥፍር አውጥቶ ሰውነቴን በሚቧጭቀኝ ብርድ ሳልማረር፣ እዛች ኮንቴነር ውስጥ ቁጭ ብዬ ጥልፌን እጠልፍ ነበር፡፡
በየወሩ ‹‹አሁንስ በቃኝ…እንኳን ትርፍ ሊያመጣ ለሚያከስር ስራ ደግሞ!› እያሉ ከጥልፉም ከዳንቴሉም ጎራ ወጥተው ሸሌነትን የመረጡ፣ ወይም ወደ ሸሌነት የተመለሱ ጓደኞቼን እያየሁ እንኳን በንፅህና ጎዳና ለመቀጠል ብዙ ለፋሁ፡፡
ብዙ ታተርኩ፡፡ ብዙ ወጣሁ፡፡ ብዙ ወረድኩ፡፡
ንፁሁ ስራዬ ግን ከሰው በታች አደረገኝ እንጂ ከፍ አላደረገኝም፡፡
ሱቄን የሚጎበኙ ወንዶች ሁሉ፤ ጥልፍ ጠለፍኩበትን አልጋ ልብስ ከመግዛት ይልቅ እኔን ጠልፈው አልጋ ውስጥ ማስገባት ነበር የሚታትሩት፡፡
በአምስተኛው ወር የከሸፈውን ፕሮጀክት ተከትሎ የከሸፈውን ህልሜን ኮንቴነሩ ውስጥ ጥዬ ወደ ‹‹ሰጥቶ የመቀበል›› አለም መጣሁ፡፡
የዛሬው ሰውዬ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ ‹‹ሀ›. ዬ፣ አንደኛ ክፍሌ፡፡
ሳልዋረድ መብላት ብፈልግም፣ ሳልገላመጥ መኖርን ብሻም የሞከርኩት ሁሉ አልሳካ ብሎኝ ሸሌ ሆንኩ፡፡
ባላያችሁትና ባልኖራችሁት ሕይወቴ ፈርዳችሁብኝ ብትሰድቡና ብትረግሙኝም፤
አለም ስትፈጠር ፣ ገና ያኔ ——ከገበሬነት በፊት፣ ከአናጢነት በፊት፣ ከአስተማሪነት በፊት…ከምንም አይነት ስራ በፊት ‹‹ሲወርድና ሲዋረድ›› እዚህ የደረሰውን ስራዬ ግን በእርግማንና በስድብ ወጀብ ከምድረ ገፅ እንደማይጠፋ ታውቁታላችሁ፡፡
ምክንያቱም፤
በጨለማ በጨለማ ዝቅ ብዬ ያገኘሁት ገንዘብ እጄን የሚጠብቁ ቤተሰቦቼን ከፍ እንደሚያደርግልኝ አውቃለሁ፡፡
ቀን የተጠየፉኝ ሰዎች ማታ እንደሚያመልኩኝ አውቃለሁ፡፡
ቆሻሻው ስራዬ ንፁህ እንጀራ እንደሚገዛ አውቃለሁ፡፡
ስለዚህ፤ ወንድ ሊሆን የሚመጣን ወንድ ሴት ሆኜ እያስተናገድኩ እንደ ሰው እኖራለሁ፡፡
ሸሌ ነኝ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ሸሌ ነኝ፡፡
ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

6 Comments

 • chombe@hotmail.com'
  ቾምቤ commented on September 22, 2017 Reply

  ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ። ህይወታችሁን የምትቀይሩበት ጥሩ ስራ ይስጣችሁ ከሁሉም የሚከፋው የኑሮ ድህነት ሳይሆን የህሊና ድህነት ነውና በተቻለ መጠን “ይቻላልን” ለአዕምሮአችሁ ንገሩና አሳምኑት

  • helinaberhane26@gmail.com'
   Helina berhane commented on December 14, 2017 Reply

   don’t u think u r missing the moral of the story which is being less judgmental!

 • value commented on January 12, 2018 Reply

  እባክሽ ከዚ ስራ ዉጪ ሴትነትሽን እግዚአብሄር በማይፈቅደው መልኩ አታጋልጪዉ Please

 • ጌትነት commented on May 24, 2018 Reply

  ደውይና አስተያየት እሰጥሻለሁ0925839186

 • Anonymous commented on March 4, 2019 Reply

  ena nje deglnase yewsedkut

 • ባቦ commented on August 5, 2019 Reply

  እናቱን የሚወድ ሴት ልጅ አያሰቃይም

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...