Tidarfelagi.com

ሶማሊ እና ኦሮሞ ወንድማማቾች ናቸው!

ታሪካችን የመረዳዳት እንጂ የግጭት አልነበረም። ታሪካችን የአብሮ መኖር እንጂ የመበላላት አልነበረም። ታሪካችን የመፋቀር እንጂ የመናቆር አልነበረም። እጅግ በሚገርም ሁኔታ አንዳችን ለሌላው መብትና ጥቅም መከበር ስንል አብረን ተዋግተናል። ህይወታችንን ሰውተናል። ለምሳሌ ታዋቂ የኦሮሞ አርበኞች የሆኑት ኤሌሞ ቂልጡ (ሐሰን ኢብራሂም)፣ እና ሁንዴ (አሕመድ ተቂ) ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር ሲሉ በሀብሮ አውራጃ፣ ጢሮ በምትባለው ቀበሌ በተሰውበት ውጊያ ላይ ከሞቱት አምስት ሰዎች አንዱ “ሱለይማን” የሚባል የሶማሊ ተወላጅ ነው። ሱለይማን ባለፈው ሳምንት ግጭት ተፈጥሮበታል በተባለው የዳሮለቡ ወረዳ ነበር የተወለደው።
—–
በቀድሞ ዘመናት በሶማሊና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የብሄረሰብ ግጭት የተፈጠረበት ሁኔታ የለም። ከ1983 በፊት በምስራቅ ኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች መካከል አልፎ አልፎ የታዩ ግጭቶች በውሃና በግጦሽ መሬት ሳቢያ የተፈጠሩ እንጂ የብሄረሰብ መልክ የነበራቸው አይደሉም። ግጭት ሲፈጠር ደግሞ ሽማግሌዎች በቶሎ ገብተውበት ያበርዱት ነው። በመሆኑም ከብቶችን ከመዘራረፍ በተረፈ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በግጭቶቹ የሰው ህይወት አይጠፋም።

በግጭት ሳቢያ የአንድ የሰው ህይወት ሲጠፋ ደግሞ ደሙን ለማድረቅ ሲባል በሁለቱም ማህበረሰቦች የሚኖሩት ጎሳዎች የተለየ ባህላዊ ስነ ስርዓት በማዘጋጀት ለሟች ቤተሰቦች 101 ከብቶችን ቆጥረው ያስረክቡት ነበር!! አዎን! የሰው ነፍስ ሲጠፋ 101 ከብት ነበር ጉማው (የሰው ህይወት እጅግ በጣም ውድ ስለሆነ ነው የካሳ ክፍያው እንዲህ የበዛው)።
—–
ከ1983 ወዲህ ግን ነገሩ ሙሉ በሙሉ መልኩን ቀይሯል። ብሄረሰቦችን እያጋጩ የአገዛዝ ዘመናቸውን ማራዘም የሚፈልጉ “ማጅራት መቺዎች” ወንድማማቾችን ደም በማቃባት እኛ የማናውቀውን ልማድ አምጥተውብናል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተከሰቱት አሳዛኝ ትራጄዲዎች በነዚህ ማፊያዎች ደራሲነት፣ አዘጋጅነት እና ተዋናይነት የተፈፀሙ ናቸው።

ማጅራት መቺዎች በአንድ በኩል የብሄር መብት አስከባሪዎች ነን በሚል “ብሄር ብሄረሰቦች” የሚል ሽለላ ይደጋግማሉ። ይሁንና የብሄረሰቦች ግጭት በኢትዮጵያ ምድር እንደ አሁኑ በዝቶ አይታወቅም። ለምሳሌ “አፋኝ ስርዓት” በሚባለው ዘመነ ደርግ በብሄረሰቦቻችን መካከል ሰላምና ፍቅር ነው የነበረው። በዘመኑ የብሄር ጭቆና መኖሩ እርግጥ ነበር። በብሄረሰቦቻችን መካከል ግን ግጭት አይታወቅም። ጨቋኙ ስርዓቱ ነው እንጂ ብሄረሰቦች አይደሉም።
—–
አሁን በሶማሊና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የታየውን ችግር ያመጡብን ገዥዎቻችን ናቸው። ዓላማቸው ምን እንደሆነም እናውቃለን። መፍትሄውንም በትክክል እናውቃለን። እነርሱ እጃቸውን ከሰበሰቡልን ችግሩን በአጭር ጊዜ መቅረፍም እንችላለን።

ይሁን እንጂ እነርሱ እጃቸውን የሚሰበስቡ ዓይነት አይደሉም። ታዲያ እጃቸውን ካልሰበሰቡልን እኛ በየጊዜው እየተጋጨን ልንኖር ነው?

በጭራሽ! ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የራሳችን ዘዴ በመፍጠር ይህንን አስቀያሚ፣ አስነዋሪና አሳፋሪ የሆነ የግጭት አባዜ በፍጥነት ማስቆም አለብን።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...