Tidarfelagi.com

ስግር ልብወለድ፣ ሕጽናዊነት (ክፍል 1)

‘I see the world in a grain of sand
And a heaven in a wild flower…. ‘ (1803)

እንግሊዛዊው ገጣሚ ዊሊያም ብሌክ

የሰፈራችን ልጅ ቴንሳ እንዲህ የሚል ግጥም አለው፤

‘አለምን በደቃቃ ጤፍ አያታለሁ
አገሬንም በቁራሽ እንጀራ’

የዋህነት እንዴት ያደክማል? ከተባለው የግጥም መድብሉ (2003)

***
እንደ መግቢያ
አዲስ የአጻጻፍ ስልት፤ ለምን?

ከአንድ አጻጻፍ ስልት ወደ ሌላ አይነት የአጻጻፍ ስልት ለመሻገር ገፊው መንፈስ የሚመጣው ከውስጥ ወይም ከውጪ ወይም ከሁለቱም ይሆናል።

ውስጥ ማለት ደራሲው፤ውጪ ማለት ደግሞ ደራሲው ልምድ የሚቀስምበት አውድ ወይም ቁሳዊ አለም ማለት ነው።

የሕጽናዊነት አጻጻፍ ስልት የመጀመርያው መቆስቆሻ ጠብታ የወረደው ከታላላቅ ደራሲያን ሰማይና ከደራሲው የምናብ እርጥበት ሳይሆን እንጀራ የተባለ ቁስን ኦንቶሎጂያዊ ሕልውና ከመጠየቅ በመጣ አጋጣሚ ነው።

እንጀራ ውብ እና ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ሁሉም ሰዎች ቢያምኑም ስለአስፈላጊነቱ እንተንትን ወይም እንረዳ ሲባል ግን ከጸሎት ያሳንሱታል። የመንፈስ ታናሽ ያደርጉታል።

(‘ሊነግዱብሽ ይሯሯጣሉ፡ ሊግባቡብሽ ግን ይድሃሉ። ተበዳይነትሽን ለማን ልንገረው?’ እንዳለችው ሲስተር አልታዬ (2000)

ሳብጀክት (ሰው) በገነነበት ፍልስፍናችን፤ ቁስ (የሰውንም ገላ ጨምሮ) ሁልጊዜም ከሰው ሃሳብ ያነሰ፣ የሃሳብ ትራፊ ወይም ታዛዥ ነው። በዚህ አይነት ዘንባላ ፍልስፍናችን፤ በሚያሳድረን እንጀራ ላይ እንኳን እናድማለን።

ፍራንሲስ ፖንጅ፤ በቁሶች(Things) ሕልውናና አስፈላጊነት ከመርካቱ የተነሳ ‘ነጋ ጠባ ስለ ሃሳቦች ማውጣትና ማውረድ የማቅለሽለሽ ስሜት ያሳድርብኛል፤ በተቃራኒው ግን ተጨባጩ ዓለም ውስጥ ያሉ ቁሶች ደስ ይሉኛል’ ይላል።

ይሄ በደረቅ ቁስ ጸባይ ተገፋፍቶ የኪን ወይንም የአጻጻፍና የመጻፍን ቅርጽ በአዲስ አቅጣጫ ለማየት መጣር ኦብጀክት ፌኖሚኖሎጂስቶችን ደስ የሚያሰኝ ነው።

***
ሥግር … ሥግር ልብወለድ / ሽግግር

ይሄንን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀምኩት በ 2009 ዓ.ም በታተመው ‘አማሌሌ’ በተባለው የአጭር ታሪክና የመጣጥፎች መድብል ውስጥ ‘አማሌሌ’ በተባለው ኖቬላ መጨረሻ ላይ ነው። እዛም ‘ሥግር’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከዚህ በታች ያለው የመሰለ ነገር ብዬአለሁ፤

‘አንዳንድ የተክል ዓይነቶች ለምሳሌ ቀጋ፣ ጌሾ፣ ድንች፣ ዝንጅብል ወይም ጽጌረዳ ከዋናው ግንዳቸው ተቆርጠው ወይንም ተቀንጥሰው ቁራጩ ወይንም ቅንጣሹ ራሱን ችሎ እንዲያድግ ወይንም እንዲጸድቅ ማድረግ ‘ማሥገር’ ይባላል። ድርሰቱ (አማሌሌ) ሶስት ክፍሎች አሉት። የመጀመርያው ክፍል ሥግር ሲሆን የቀሩት ሁለቱ ከዚህ ከመጀመርያው ክፍል የበቀሉ ወይም የጸደቁ ናቸው።’

ቶማስ ኪን በመዝገበ ቃላቱ (1990) ሠገረ/አሠገረ የሚለውን በእንግሊዝኛ to transmit, to transfer, to hlep, to crossover ብሎ ይተረጉመዋል። ደስታ ተክለወልድ ደግሞ በሀዲስ መዝገበ ቃላታቸው ማለፍ፣ መራመድ፣ አለፈ፣ ተራመደ፣ በሚሉ ቃላት ይፈቱታል።

በነዚህ ሁሉ ፍቺዎች የመሻገር ጽንሰ ሀሳብ በቀጥታም ሆነ በውስጥ አዋቂነት አለ። ሽግግሩ ከነባር ቦታ ወደ አዲስ ቦታ ወይም አውድ የሚከናወን ነው።

***
አንድ ሰሞን (አሁንም ድረስ) ሕጽናዊነት ያልኩትን የአጻጻፍ ስልት ኦንቶሎጂካል መሰረት ለመስጠትና እሱን የመሰለ ወይንም ወደዛ የሚወስደኝ የባዕድና አገርኛ የአጻጻፍ ስልት ሳስስ፤ ራይዞም (Rhizome) የተባለ የእንግሊዝኛ ቃል (ፅንሰ ሃሳብ) አጋጠመኝ።

ራይዞም የተባለው ቃል ጊለስ ድሉዝ እና ፌሊክስ ጓታሪ የተባሉ የፈረንሳይ ፈላስፎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1976 በጻፉት Thousand Plateaus በተባለው መጽሃፋቸው ውስጥ ቃሉን እንደ ፅንሰ ሃሳብና አልፎ አልፎም እንደ ልዋጭ ተጠቅመውበታል።

በመፅሀፉ መግቢያ ላይም ራሱን የቻለ ምዕራፍ ፅፈውለታል። ይሄም ብቻ ሳይሆን ከ 600 ገፅ በላይ ያለው ይሄ መፅሀፍ በራይዞም ስልት የተጻፈ ነው።

ኡምቤርቶ ኤኮ እንደሚለው፤

‘The rhizome is so constructed that every path can be connected with every other one. It has no centre, no periphery, no exit, because it is potentially infinite. The space of conjeture is a rhizome space.’
Umberto Eco(1984) The Open Work

(ለምለም ትርጉም – ‘ራይዞም አንዱ መስመር ከሌሎች መስመሮች ጋር የተያያዘ ነው። ማዕከልም ደርዝም የለውም። ወሰን የለሽ ስለሆነ መውጫም የለውም። የግምት ዓለም የራይዞም ዓለም ነው።’)

ታዲያ ይሄንን ጽንሰ ሃሳብ የሚተረጉም የአማርኛ ቃል እየፈለግኩ እያለሁ፤ ማግኘትም በመቸገሬ በአንድ ውይይት መሃል ነገሩ ተነሳና አንድ ሰው ‘ሥግር’ የሚለውን ቃል አመጣ። የቃሉን ትርጉም ፎርማላይዝ ማድረግ ስለነበረብኝ ከላይ እንደጠቀስኩት መዝገበ ቃላት አማከርኩ።

ቀድሞ መሰየሙ ቢከብደኝም አንዳንዴ በሆነ መዛነቅ ከፈረሱ ጋሪው ሊቀድም ይችላልና ፍቺውን እየተጠቀምኩበት ወይም እየጻፍኩበት ስለነበር ቃሉ የሳበው ነገረ ጉዳይ እንግዳ ጉዳይ አልሆነብኝም። ምናልባት ቀድሜ እጽፍበት በነበረው ስልት መጻፍ እንደማልችል በስውር ልቡናዬ የተረዳሁት ግን አውጥቼ ልናገረው ያልቻልኩት ከቋንቋ በታች ያረበበ ስሜት ለረጅም ጊዜ ተጣብቶኝ ኖሮ ይሆናል።

***

ሥግር ድርሰት

አንድን ድርሰት ቀርቦ ሥግር መስራት ማለት ከድርሰቱ ውስጥ የሆነ ኩነት (event) ወስዶ ወደተፈለገው ወይም ወደሚችልበት እልፍ አቅጣጫዎች መውሰድ ማለት ነው።

በአንድ ነጠላ የመሰለ ጉዳይ ውስጥ ብዝሃነት (multiplicity) ወይም ያልተከፈተ እምቅ ሃይል (potential) አለ።

መሆን (becoming) ማለት አንድ ሁኔታ ሃሳብ ወይም ኩነት በወሰን አልባነት ሲተረተር ወይም በስልት ሲከፈት ማለት ነው። ሁልጊዜም ‘በአላቂው’ ጉዳይ ውስጥ ወሰን የለሽ ነገር እናያለን።

‘በአንድ ጥሬ የዕብነበረድ ሰሌዳ ውስጥ ሕልቆ መሳፍርትእምቅ ነገር አለ’ እንዳሉት አንዳንድ ፈላስፋዎች። አንዱ የዕብነበረድ ሰሌዳ የተለያዩ ባለሙያዎች እጅ ሲገባ ቀራጩ፣ ቤት ሰራተኛው፣ ሰአሊው፣ ደራሲው፣ ዘመድ የሞተበት ወዘተ የተለያየ ባህሪ ወዳላቸው ነገሮች ሊለውጠው ይችላል።

ኩነት ማለት እንደ ሌይብኒዝ አንዲት ነጥብ ጽንፍ የለሽ ነገሯ ለአፍታ ሲቋረጥ ነው። (አንዱ መረዳት ይሄ ነው) በአጭሩ ኩነት መርጠን ይሄንንም በአፍታ ግታት (finite interrruption) እምብርየለሽ (infinite) መስክ መፍጠር ማለት ነው። (ይሄኛው ሌላኛው መረዳት ነው።)

ያ እምቁ ሃይል በሁኔታዎችና በነገሮች መሃል ያለው የማያልቅ ግንኙነት ወይም ትስስር ነው።

‘Each text is trapped in a network of relations, between the different parts that constitute it, between that text and those which precede it or those that came after it, or even those which never were’

ያልነበረው ገና የሚጠበቀው ቴክስት በቦርገስ ስያሜ ሃሳዌ ቴክስት (pseudo-textuality) ይባላል። ይሄ ‘አፍ’ ወደ አንባቢ-ደራሲ ሲወረወር (‘እንካ’ ሲባል) እነዛ ሃሳዊ ቴክስቶች ይኖራሉ ብዬ ተስፋ በማድረግ ነው።

***

ከ ኤልዛቤል እስከ አፍ

በግራጫ ቃጭሎች ስለ ሕፅንና ሕፅናዊ አጻጻፍ ማውራት የጀመርኩት ከፍልስፍና ተነስቼ ሳይሆን ቅደም ተከተላቸውን ልብ ባልልም በሁለት ምክኒያቶች ነው።

አንደኛው የአገራችንን መሰረታዊ ቀለብ፤ ማለት እንጀራን በድጋሚ ማግኘት (rediscover) ማድረጌ ሲሆን ሁለተኛው በድርሰት ስራ ውስጥ አንድን ኩነት ወይም event አንስቼ problematize ከማድረግ ነው።

ይሄም ወደተያያዘና እርግጠኛ ወዳልሆነ የተለያየ አቅጣጫ የሚበተን አተራረክ አሳየኝ። ኑባሬ መረባዊ እንደሆነ በድጋሚ፣ በተደጋጋሚ፣ ላመልጠው በማልችል መንገድ በልቦናዬ ሳልኩት። ይሄ ግዴታ መሆን (becoming) እንጂ ግልብ አንጻራዊነት አልነበረም። በትክክል ያለሁበትን ሁኔታ ለመረዳት ቃል ማቀናበር ነበረብኝ።

ከጥቂት የግል ንትርክ በኋላ ‘ሕጽናዊነት’ አልኩት።

ሕጽናዊነት የሚያተኩረው የነገሮች ውስጣዊ የማይለወጥ ማንነት (essence) ላይ ሳይሆን ግንኙነት ላይ ነው።

አንድ ጉዳይ፣ አንድ ቁስ፣ አንድ ሃሳብ፣ ወዘተ ከሌሎች ነገሮች፣ ቁሶች፣ ሃሳቦች ወዘተ ጋር ያለውን ዳይናሚክ ግንኙነት መግለጽ መቻል ያንን ነገር ማወቅ ነው። ወደ እውነትም የሚወስደን ይሄ አይነት ቁስአካላዊነት ነው።

ይሄ ግንኙነት ደግሞ ሁልጊዜ መረባዊ ነው። ለነገሮች የተሟላ ዕውቀት እንዲኖረን ወሰን የለሽ የሆነውን የግንኙነት መርበብት ሁሉ አስሰን ማግኘትና ማወቅ አለብን። ይሄ ግን አይቻልም፤ ባለመቻሉም የሰው ልጅም ይሁን ደራሲው ከድንቁርና አያመልጡም።

ባህላዊና (የሃይማኖት ገድሎች) እና ዘመናዊ የምንላቸው ብዙ ድርሰቶች ግን ከተቀነበበ፣ መልሱ ከሚታወቅ ወይም ከሚጠረጠር፣ ክፉና ደጉን ለየሁ ከሚል ስርዓትና ካበጀ ርዕዮት ስለሚነሱ ትረካቸው መስመራዊ፤ መልሳቸው ደግሞ ብዙ ጊዜ አንድ ወጥና አጨራረሱ የሚታወቅ ወይም የሚጠረጠር ነው።

‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ በተባለው በመጠኑ ሕጽናዊ አገነባብ ባለው ልብ ወለዴ ውስጥ፣ በ ‘ኩሳንኩስ’ ምዕራፍ፣ ‘ሊጥ’ በተባለው ንዑስ ምዕራፍ ውስጥ ገለታ እና ሰናይት የተባሉ ፍቅረኛ ገፀ ባሕሪያት አሉ። እነዚህ ወጣቶች በመለያየታቸው ፍቅራቸው ይፈርሳል። (ቢያንስ ከላይ እንደዛ ነው)። ሲለያዩ የልጅቷን መዳረሻ እዛ ውስጥ ባለ ሌላ ቀጣይ በሆነ አጭር ታሪክ ውስጥ ስናይ፤ የልጁ (የገለታ) ታሪክ ግን የወዳጁ አይነት አጨራረስ አልተሰጠውም።

በስሎ በተቋቋመ የተጠየቅ ጎዳና ላይ የተገነባ፣ ‘ሚዛናዊ’ የተባለ፣ ክላሲክና ዘመናዊ ስራ የለመዱ አንባቢዎች ‘የገለታን ነገር አንጠልጥለህ ተውከው’ ብለው ደራሲውን ሊሞግቱት ይችላሉ። በቀቢጸ ተስፋነቴ ሊያማኝ የለፋም አለ።

ገለታ እንደተሰደደ እናውቃለን። ምን እንደደረሰበት ግን አንባቢው በግልጽ እንዲነገረው ይፈልጋል።

በመጀመርያ ጥያቄው ቢነሳም ልክ ነው ማለት አይደለም። ግን ይሄ ጠያቂ ልማድ ጋርዶት እንጂ፤ ገለታን በተሰደደበት ተከትዬ የደረሰበትን ብጽፈው እንኳን ድርሰቱ ሊያልቅ አይችልም። ገለታ ቢሞት እንኳን ተረኩ ከተፈለገና በምናብ ከታጠቀ አያልቅም። ስጋና አጥንቱ ወደ አፈር ከተለወጠ በኋላ እንኳን በልብወለድ ሞሌኪዩላር ሕልውናውን ማስቀጠል ይቻል ነበር።

በዚህ አፍ በተባለው ልብወለድ ውስጥ፤ ውዴ፣ ገለታ፣ ሰናይት፣ ቹቹና ሰላማዊት ቀድመው ከነበሩ ድርሰቶቼ ማለትም ከኤልዛቤል፣ ከ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ ከስንብት ቀለማት ወዘተ ተቆርጠው የተዘሩበት ወይም የተተከሉበት መስክ ነው።

እንኳን ድርሰቱ ደራሲውና ጠያቂውም ጅምር ናቸው። ቴክስት ቢሆኑም ኑባሬ ናቸው።”

***

 

ስግር ልብወለድ፣ ሕጽናዊነት (ክፍል 2)

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...