Tidarfelagi.com

ስኳር መች ይጣፍጣል?!

በዚህ እጅ ያልነካው ወዳጅ በማይገኝበት ክፉ ዘመን ሰላሳ አራት አመት እስኪሞላት ድረስ የማንም እጅ ሳይነካካት ከወር በፊት የተሞሸረች ልጃገረድ ወዳጅ አለችኝ።

‹‹ያላገባኝ አይነካኝም!›› ብላ….
‹‹ወንድ ልጅ ወተቱን በነፃ ካገኘ ላሚቱን አይገዛም›› ብላ…
ስንቱን የወንድ ፈንጂ በጥንቃቄ እንጣጥ ብላ፣ ስንቱን አማላይና አታላይ አምልጣ፣ እሷም እንደማንም ግጣሟን አገኘችና ጎጆ ወጣች። ተሰበሰበች። አገባች….ተነካች።

በቃል እና በእምነቷ መሰረት፣ ክብር እና ንፅህንናዋን ጠብቃ ኖረ ተዳረች። ከባሏ ተኛች።

በዚህ ዘመን ቀረ ብለን የምንገረምበት ወግ አጥባቂነቷ የአስናቀች ወርቁን ዘፈን ያስታውሰኝ ነበር። አስናቀች ቀኑን ሙሉ ከምታፈቅረው ልጅ ውላ ልክ ሲመሽ ሌላ እንዳያስብ ‹‹ልሂድ›› ስለምትል ወዳጄን የምትመስል ሴት ዘፍናልን ነበር።

‹‹ፍቅርዬ- ፍቅርዬ ደህና ሁን
ሊመሽ ስለሆነ መሄዴ ነው አሁን…..
…እኔ እንደምወድህ – ፍቅሬ ሆይ ውደደኝ
በህጋዊ ስርአት ማልድና ውሰደኝ…
አፍቅረኝ ላፍቅርህ ኑሯችን ባንድ ይሁን
እስከዚያው ድረስ ግን- ፍቅርዬ ደህና ሁን›› እያለች ዘፍናልን ነበር።

እናም…የ34 አመቷ ወዳጄም በህጋዊ ስርአት፣ በአማላጅና በምልጃ የፈለገችውና የፈለገችውን አገኘችና፣ ወሰዳትና አገባች። ተነካች።

ሰርጉ ተከናውኖ…
ጫጉላው አብቦ…
ከስንት ያመለጠው ብር አምባር ተሰብሮ ጥቂት ቀናት ካለፉ በኋላ አሁንስ ይበቃታል ብዬ ደወልኩላት። እንዴት ሆንሽ….አጥሚትና ገንፎ የት ይዘን እንምጣ ልል እና ላጫውታት ደወልኩላት።

ብዙ ሳይጠራ አነሳች።

(በቅቷታል ማለት ነው…)

ሰላምታችን ሲያልቅ ወደ አንገብጋቢውጉዳይ ገባሁና..
‹‹እህስ…ነገሩስ? እንደጠበቅሸው አገኘሽው ወይስ ቅር አለሽ?›› አልኳት።
‹‹ቅር አለሽ ወይ? ወይ ጉድ…አንቺ….ስኳር መች ይጣፍጣል?!›› ብላ መለሰችልኝ።

ከአንጀቴ ሳቅሁ።

እንዲህ ትላለች ብዬ ስላልጠበቅኩም፣ ያ ከአመታት በፊት የሰማሁት ታሪክ ላይ ያለችው ልጅንም አስታወሰችኝና ሳቅሁ።

(ታሪኩ እንዲህ ነው። ልጅቱ ለስኳር ያላት ፍቅር የትዬሌሌ ነው። ‹‹ከስኳር የሚጥም፣ ከስኳር የሚጣፍጥ ነገር በአለም ላይ…አንዳችም ነገር የለም›› የምትል አይነት። እጮኛዋ ‹‹ተይ ተጋብተን ፍቅር ስንሰራ ኋላ ሃሳብሽን ትለውጫለሽ›› ቢላትም እሷ ግን ወይ ፍንክች! በኋላ ጋብቻው ተከናውኖ ባልና ሚስት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር እየሰሩ ወደ ማገባደዱ ሲደርሱ የሚስቱን ሁኔታ ያየው ባል በእጁ የጨበጠውን ስኳር በተከፈተ አፏ ውስጥ ሙጅር ያደርጋል። ይሄን ጊዜ የስኳር ነገር የማይሆንላት ሚስቱ ምን አለች? ‹‹ውይ ውዴ…! የምን አፈር ነው አፌ ውስጥ የጨመርከው?!››)

‹‹ወይ አንቺ…እና ታዲያ ይሄን ያህል ጊዜ በመቆየትሽ ትንሽ አልተቆጨሽም ታዲያ?›› አልኳት
ለመመለስ ሰከንድ አልፈጀባትም።
‹‹በጭራሽ! መቆየቴ መቼም አይቆጨኝም….ግን እንዲህ መሆኑን ግን ነገራችሁኝ አታውቁም….››
‹‹ ብንነግርሽስ ኖሮ?››
‹‹እሱስ ምንም ለውጥ አያመጣም ነበር…ያው ምናልባት ትንሽ…ይበልጥ ልጓጓ ግን እችል ነበር……..››

ወሬያችን አልቆ ስልኩን ስዘጋ በዚህ ሁሉም ሰው ሁሉንም ሰው ለመምሰል በሚሮጥበት ጊዜ፣ ለግል አቋምና እምነቷ ባላት ታማኝነት እንዳዲስ ተደነቅኩባት። ቀናሁባት።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን (በእኔ እና በአለም ስሌት) ዘግይታም ቢሆን አዳሜ የአለምን ምሬት የሚያጣፍጠው ፍቅርን በመስራት ስኳር መሆኑን በማወቋ ተደሰትኩላት።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...