Tidarfelagi.com

ስንቴ ገረዝኩት?

“አንቺማ አትገርዢኝም። በስመአብ! ” አለ እያማተበ ለመቀመጥም ለመነሳትም በቀረበ አኳኋን አየሩ ላይ ተንጠልጥሎ።

“አየር ላይ ነህ፣ አረፍ ትል?” አልኩት አኳኋኑ ሳቄን እያመጣው

“የታለ ዶክተሩ ከምር? ” አለኝ ወንበሩ ላይ ተስተካክሎ እየተቀመጠ

“እኔ ነኝ!!” አልኩት ምን እንደሚያስብ ለመገመት እየሞከርኩ

ካርዱ ላይ የተፃፈው እድሜ 33 ይላል። ወጣት ነው፣ ማንም ሴት አይታው የምትደነግጥለት ዓይነት ቁመናና መልክ፤ በራሱ የሚተማመን የሚመስል ገፅታ ፤

“አንቺማ አትገርዢኝም። ይዤው አረጃታለሁ እንጂ………” አለኝ ለኔ ሳይሆን ለራሱ የሚያወራ በሚመስል ድምፅ

“ለምን? ሴት ስለሆንኩ?”

“አወና ፣ ሴት ብቻ አይደለሽም። ህልም የመሰልሽ ቆንጆ ሴት ነሽ። ሆ!!”

“እሱ ከስራዬ ጋር ምን አገናኘው?”

“ላንቺ ነዋ ስራ…………” ቀጥሎ ያልሰማሁትን ነገር አጉተመተመ

“ይቅርታ አቶ ሲሳይ ብዙ አገልግሎት ፈላጊዎች ውጪ ተሰልፈዋል። ስራችንን እንቀጥል?”

“እህ ስለተቆጣሽ ይሰማሽ መሰለሽ እንዴ?” አለ ወደሱሪው ዚፕ አይኑን እየላከ። መሳቅ አምሮኛል ግን መሳቅ የለብኝም።

“እንዴት ሳትገረዝ ……….?” ጥያቄዬን የምጨርስበት ቃል ስፈልግ

“አረጀህ? አይባልም ግን እሺ! ……….. ባክሽ አንጀት ነው ታሪኩ። ………… ተረት ነገር ነው የሚመስለው።”

“እየሰራሁ ታወራኛለሃ!!”

ብድግ ብሎ ገላውን አራቆተው።
“እንዴ እዚህ አይደለም የምሰራው።።።” አልኩት

“ቆይ ግን ትልቅ ወንድ ገርዘሽ ታውቂያለሽ?” አለኝ ምንም የተጋለጠ ሳይመስለው ተረጋግቶ ልብሱን ወደሰውነቱ እየመለሰ።

” አዎ። አውቃለሁ። ”

“እኔን የሚያህል?”

” ካንተም የሚበልጡ”

“ይሄን ነገር መቼም እንዲህ እንደቆመ አትገዘግዢውም አይደል?” እፍረት አይታይበትም። ስለቆመው አክሱም እንጂ ስለቆመው ንብረቱ ያወራ አይመስልም። በድጋሚ መሳቅ አምሮኛል። ፊቴን አዙሬ ፈገግታዬን ደበቅኩበት። ጭንቅላቴ ውስጥ ብቅ ያለው ሀሳብ ግን ቆሞ ነበር እንዴ? የሚለው ነበር። በየሱስ ስም!

“ማደንዘዣ እሰጥሃለሁ።”

“እህ! አይደለም ማደንዘዣ ፀሀይ የመሰልሽ ሴት ነክተሽው ሞቼ እንኳን ቢሆን አይቆምም?”

አሁን አለመሳቅ አልችልም ነበር። መጥሪያዬን ተጭኜ እጄን ከማንሳቴ ሲስተር ገባች።

“ኸረ ፍጥነት? በሩ ላይ ነበረች እንዴ? ” በማያገባው የሚገባ ሰው በቸልታ ማለፍ አልችልም እኮ ግን እንዳልሰማ ወደ ሲስተር ዞርኩ

”OR 2 ይዘጋጅልኝ። ማረፊያውን ታሳይሃለች እዛ ቆየኝ።” ካርዱን ለሲስተር አቀበልኳት። እሷ ያልኳትን ሰምታ ወጥታለች። እሱ እንደተቀመጠ በትዝብት ያየኛል።

“ምንድነው?”

“ይሄን ፊትሽን ግን ስሞትልሽ ፀብ ሲኖረኝ ሲኖረኝ እዋስሻለሁ። እንቢ እንዳትዪኝ! ኸረ በኪዳነምህረት!! “

“አቶ ሲሳይ የሚመለከተን ነገር ላይ ትኩረት እናድርግ?“

“you see እያናደድኩሽ እንኳን ፈገግ ብለሽ ነው የምትቆጪኝ። ምክንያቱም ደሞዝሽን የምከፍልሽ እኔ ነኛ! ባትመቺኝ ሌላ አማራጭ እንደምጠቀም ታውቂያለሽ። ስለዚህ ምን ያህል ስድ የሆነ costumer እንኳን ቢገጥምሽ በትህትና ታስተናግጃለሽ። ረዳቶችሽ ወደውሽ እንጂ ደመወዝ ስለምትከፍያቸው ፈርተውሽ እንዲታዘዙሽ አታድርጊ! እንደዛ ሲሆን አብረውሽ ያሉት ምርጫ እስካጡ ድረስ ብቻ ነው ማለት ነው።”

ልለው ያሰብኩት ብዙ ነበረ። ዋጋ ያለው ስላልመሰለኝ ተውኩትና እንዲወጣልኝ ብቻ በሩን አሳየሁት። ተነስቶ እየወጣ በሩን ተደግፎ ቆም አለና

«ያንቺን ስራ ደመወዝ ከፍለሽ እንደምታሰሪያቸው ሳይሆን እነርሱም የስራው አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጊ ያኔ ላንቺ ወይ ለደሞዝ ብለው ሳይሆን የራሳቸው ስራ መሆኑን ስለሚያስቡ ማንም ስራው እንዲበላሽበት አይፈልግም።»

«አቶ ሲሳይ ስድስት አመት ይሄን ሆስፒታል ቀጥ አድርጌ አስተዳርያለሁ። ሰራተኞቼን እንዴት መያዝ እንዳለብኝ አንተ አትነግረኝም!!» እንዴት ያለው ነው? እያናደደኝኮ ነው። ፈገግ ብሎ ከወጣ በኋላ መለስ ብሎ

«አይባልም ግን እሺ! ቤት ውስጥ የተቀጠረ ሰው እንኳን አሁን ቀርቷል ሰራተኛ አይባልም። ሆስተስ፣ አቀናባሪ ምናምን ነው የሚባለው። በሙያቸው የሚረዱሽን ሰዎች ሰራተኞቼ? ኸረ አይባልም!» ብሎኝ በሩን ዘጋው!! ኡፍፍፍፍፍፍፍፍ ምን አይነቱን ነው ዛሬ ደግሞ የጣለብኝ?

★ ★ ★

በሶስት ቀናት ውስጥ የተኛሁባቸው ሰዓታት 7 መሙላታቸውን እንጃ። እቤቴ ሄጄ አላውቅም። ተረኛ ታካሚ እስኪገባ ስጠብቅ እያወራ ወደ ውስጥ ዘለቀ።

“ስንቴ ነው የምትገርዢኝ?”

“ማለት?”

“ቁስሉ ተቦትርፎልሻል። ጨርሺኝ ብዬ ነው አንቺውጋ የመጣሁት።”

“አልገባኝም። እስኪ እዛጋ ሁንልኝ። ምን ሆኖ ነው?” አልኩት

“እኔ አንቺን ማሰብ ማቆም አቃተኝ። እሱም አለመቆም አቃተው። ተነፋፋሁ ሲል ቁስሉ ጣጣጣ…………” የሚያሾፍ ይመስላል። ቁስሉ ግን እንዳለው ቆስሎ ነበር።

“ስነስርዓት ባለው መንገድ እንደአዋቂዎች እናውራ?” አልኩት።ማንም ደንበኛ በዚህ መጠን ነፃነት እንዳወራኝ አላስታውስም።

“እኔ የምለው ማሂ?” አለ ኮስተር እንዳለ

” ዶክተር ማህደር” መለስኩለት

“ኡፍ! ከክብርና ከፍቅር የቱ ይበልጥ ይመስልሻል?”

“ሁለቱም ዋጋ ያላቸው የማይነፃፀሩ ነገሮች ናቸው።”

” ዶክተር ብልሽ ያከበርኩሽ ሊመስል ይችላል። ማሂ ስልሽ ግን ውዴታዬን እየነገርኩሽ ነው። ከክብር ሁሌም ፍቅር ይበልጣል። በክብር ውስጥ ፍቅር ላይኖር ይችላል። በፍቅር ውስጥ ግን ሁሌም ክብር አለ” የሆነ ነገሬን ያወቀ ስለመሰለኝ ተናደድኩ። ለተናገረው ትኩረት የሰጠሁ ባለመምሰል

“ጨርሻለሁ። ተጨማሪ አንድ መድሀኒት አዝልሃለሁ። በትክክል መድሀኒቱን ከወሰድክ በድጋሚ እዚህ መመላለስ አያስፈልግህም።” አልኩት

” OK አልጋ ልትሰጪኝ ማለት ነው? እሱ ጥሩ ሀሳብ ነው። ”

“አቶ ሲሳይ ለጨዋታ ጊዜ የለኝም።”

” ሊኖርሽ ግን ይገባል ማሂ!። ” መልስ ሳይጠብቅ የፃፍኩለትን ወረቀት ተቀብሎኝ ወጣ።

ስንቴ ገረዝኩት (ክፍል ሁለት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...