Tidarfelagi.com

ስለ ዘፈንና ዘፋኞች

በጉብልነቴ ዘመን ፤ እንደዛሬ ዘፈንና ዘፋኝ አልበዛም ነበር። እንኳን ዘፈን መስራት ፣ ዘፈን መስማት ራሱ ብዙ ውጣውረድ ነበረው። ዘፈን ማድመጥ ሲያምረን ከትምርት ቤት ፎርፈን፣ ሻይ ቤት ጎራ ማለት ነበረብን። ያዘዝነው ሻይ ቶሎ አልቆ ፣ አስተናጋጁ እንዳያባርረን ስለምንሰጋ ፣ የብርጭቆውን አፍ እየሳምን፣ እንጎለታለን። እናም ባንድ ብርጭቆ ሻይ ፣ የጊዜው እውቅ ድምፃውያንን ፣የዚነት ሙሃባንና የ(አ) ዳምጠው አየለን ዘፈን ካሴት ሁለት ዙር ሰምተን እንወጣለን።

አብሮ አደጎቼ፣ ማርቆስ ስላፈራቻቸው ዘፋኞች ሲጠየቁ ሙሉቀን መለሰን ፣ኤፍሬም ታምሩንና ፣ጌቴ አንላይን ይጠቅሳሉ። እኔ ደሞ አስቀድሞ ትዝ የሚለኝ ይግረም ንጉሴ ነው።

ይግረም ንጉሴ ሲዘፍን፣ ወፍ ከዛፍ ላይ ያረግፋል። (ባንድ እጁ ማይክ ፣ ባንድ እጁ ወንጭፍ ይዞ ነበር የሚዘፍን😉)

ቆንጆ ድምፅ ቢኖረውም ፣አዲሳባ ሂዶ ዘፈን ለማስቀረፅ የሚያግዘው አቅምም ሆነ ዘመድ አልነበረውም። የሆነ ጊዜ ላይ፤ ከባልንጀሮቹ አንዱ በክራር እያጀበው ፣ባሮጌ ቴፕ ተቀረፀ። ቀስበቀስ ካሴቱ ተባዝቶ ፣እንደ አድባር ንፍሮ በየማእዘኑ ተበተነ።

ርግጥ ነው፤ የይገረም ካሴት ቤት ውስጥ ስለተቀዳ የድምጥ ጥራት አልነበረውም። አንጀት በሚበላ የፍቅር ዘፈን ማህል፣የጎረቤት ህፃናት የሚሻምሾ ጭፈራ ሲለማመዱ ፣እንዲሁም ለፋሲካ ተገዝቶ ፣ጉዋሮ የታሰረ በግ ፣የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰማ ፣ተደርቦ ተቀርፅዋል።

ይባስ ብሎ ፣ካሴቱ አንድ ደቂቃ ተጫውቶ ቀጥ ይላል። አዳማጩ ትግስት ካለው ፣ካሴቱን አውጥቶ ቴፑን እንደ ወንፊት መታ መታ አድርጎ ይመልሰዋል። ካሴቱ ትንሽ አንጎራጉሮ ሲጢጢጥ..ቀጥ!!

ከጥቂት ጊዝያት በሁዋላ፣የኛ ሰፈር፣ ሽማግሌዎች፣ በልጃቸው ወይም በገረዳቸው ተማርርው ሲራገሙ እንዲህ ማለት ጀመሩ፤” አንች ሴት፤ ቆመሽ ቅሪ እንደ ይግረም ካሴት!!”🙄

(2)

አስቻለው አየለ”የዘገሊላ ለት”የሚለውን የይሁኔ በላይ ዝነኛ ዘፈን ዜማ የደረሰ ባለሙያ ነው። አንድ ቀን፣ ዘመድ ወዳጅ ተሰብስቦ ፣ ክፍሉ ተጫጭሶ ፣ እፀ -ሀሴት ተጎርሶ፣ ስናወራ አስቻለው የሆነ ዜማ ብልጭ ብሎለት ተንደርድሮ ኪቦርዱ ላይ ተጣደ። ከዜማው ጋር፤
“ልውጣ ብል በግሮቼ፤ ብሄድ በፈረ-ስ
ፍቅርሽ እንደዳገት…”

የሚል ጅምር ግጥም መጣለት። አስቹ የዜማ እንጂ የግጥም ባለሙያ ስላልሆነ ፣ ዳገቱን የሚጨርስለት ሰው ፍለጋ ሲያማትር ፀጋየ ደቦጭን አየው፤
“ፀግሽየ! ንስማ ይቺን ግጥም ጨርስልኝ”

ፀጋየ ፣ባማርኛ የዘፈን ግጥም ውስጥ ካሉ አንፀባራቂ ኮከቦች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ፣የዚያን ቀን ግጥም የመግጠም ሙድ ላይ አልነበረም። ከይሁኔ በላይ ጋር ሞቅ ያለ ጭውውት ይዘዋል። አስቻለው ግን አለቀቀውም።

“ንስማ ፣አንድ ሀረግ ብቻ ብትጨምርባትኮ ወርቅ የሆነች ዘፈን ይወጣት ነበር፤”እያለ መጎትጎቱን ቀጠለ።
ፀጋየ ፤ጉትጎታው ሲበዛበት ለመገላገል ያህል፤

“ልውጣ ብል በግሮቼ፤ ወይም በፈረ ስ
ፍቅርሽ እንደ ዳገት …ያስጨርሳል ፈስ
ብለህ ሙላው”
አለና ወደ ጨዋታው ተመለሰ።

(3)

የሆነ ጊዜ ላይ ዘፋኞች ባንድ ጀንበር መክበር ጀምረው ነበር። አንዲት የጥንት አልቃሽ፤
“የመከራ ጊዜ ፤ጥቂት ነው ወዳጁ፤
ደስታማ ሲሆን ፤ ይጨቀያል ደጁ” እንዳለችው ፣የዘፋኞችን በረከትና ደስታ ለመቀራመት የሚሽቀዳደሙ ወዳጆች መፍላት ጀመሩ። “እገሌ የተባለው ዘፋኝ ወላጅ አባት እኔ ነኝ “የሚሉ ሼባዎች በየሚድያው መቀላወጥ አበዙ።

አንድ ማለዳ ላይ፣ ድምፃዊ ጌራወርቅ ነቃ ጥበብ ሰው ይፈልግሃል ተብሎ ከቤቱ ወጣ። ወድያው ሽማግሌ ዘሎ፣ተጠመጠበትና” ልጄ፣ እንኳን ደስ አለህ፤ የጠፋሁት አባትህ ተገኝቻለሁ፤ አቶ ነቃ ጥበብ ማለት እኔ ነኝ”ብሎ ትከሻውን ተንተርሶ ማልቀስ ጀመረ።
ጌራ ” ሰውየ ተሳስተሃል። አሁን ስታስጠራኝ እኔ ካባቴጋ ቁርስ እየበላሁ ነበር” ብሎ በትህትና ፣ሁለት ሜትር ያህል ገፈተረው።

ሰውየው ባይበሉባው እንባውን እያበሰ እንዲህ አለ፤
“እንግዲህ ምን አረጋለሁ፤ ደሞ ፍቅረ አዲስ ነቃጥበብ ጋ ሂጄ እድሌን ልሞክር እንጂ”

(የሚቀጥል)

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...