Tidarfelagi.com

ስለ ቡሔ(ቡሄ!)

“መጣና ባመቱ
አረ እንደምን ሰነበቱ
ክፈትልኝ በሩን የጌታዬን
ሆያ-ሆዬ-ሆ…”

ቡሄ! ወይንም ደብረ ታቦር በመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓቢይ (ዋና) በዓላት አንዱ ነው።

የዚህ በዓል መሠረት የክርስቲያን እምነት ሲሆን፣ ደብረ ታቦር በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው።

የማቴዎስ ወንገል ምዕራፍ ፲፯፦ ቁጥር ፩ እስከ ፭ ” ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።”

ዓቢይ መሠረቱ ይሄ ሲሆን፣ በአገራችን የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት ‘ቡሄ’ የሚለውን ስያሜ አገኘች። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡

በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ፡፡ ታዲያ ያንን ማስታወሻ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው፡፡

የቡሄ ዜማዎች

በዋዜማው የሠፈር ልጆች በየቤቱ እየዞሩ ሆያ ሆዬ! አሲዮ ቤሌማ እያሉ ይጨፍራሉ።

ቡሄ በሉ፣ ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ
ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ

ክፈትልን በሩን
የጌታዬን

እዚያ ማዶ ነጭ ሻሽ
እዚህ ማዶ ጥቁር ሻሽ
የእኔማ ጌታ ነጭ ለባሽ።

የወንዜው ነብር የወንዜው ነብር
የኛማ ጌታ ሊሰጡን ነበር።

ሆይ ሾህዬ ሎሚታ
ልምጣ ወይ ወደማታ።

ለብሩ ነወይ ነወይ ሽጉዱ
በአባትህ ጊዜ ሰንጋ ነው ልምዱ

================

ቡሄ በሉ ! ሆ!
ቡሄ በሉ ! ሆ!
ያዳም ልጅ ሁሉ`! ሆ!
የኛማ ጌታ ፣ የአለም ፈጣሪ
የሰላም አምላክ፣ ትሁት መካሪ

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና

ያዕቆብ ዮሃንስ ሆ! እንዲሁም ጴጥሮስ
አምላክን አዩት ሆ! ሙሴ ኤልያስ
አባቱም አለ ሆ! ልጄን ስሙት
ቃሌ ነውና ሆ! የወለለድኩት

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና።

================
ይሄ የንጋት ወጋገን ሲፈናጠቅ በጠዋት ውርጭ የሚዘመር ሲሆን በከባድ ድምጽና በጅራፍ ጩኸት የሚታጀብ፣ ስራዬ ተብሎ በገደላገደል ስር እንዲያስተጋባ ተደርጎ ብዛት ባላቸው ህጻናት በከፍተኛ ድምጽ የሚዘመር ነው። ሙሉ ዜማው ብዙ ቢሆንም በጥቂቱ እንዲህ ይላል

ቡሄ ና! ቡሄ
ቡሄ ና! ቡሄ
አበባ ማለት ያደርሳል ካመት ( ጅራፍ ና ጥንጅት ድምጽ)
ኦሆ!
ቡሄ ቡሄ ና!
ቡሄ ቡሄ ና!

ቡሄ ና! ቡሄ!( የጥንጅትና የጅራፍ ድምጽ )
ቡሄ ና! ቡሄ!

ለአባ ወራ

መጣና መጣና ደጅ ልንጥና
መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣
ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን
ክፈት በለዉ ተነሳ ያንን አንበሳ፣
መጣሁኝ በዝና ተዉ ስጠኝ ምዘዝና
የኔማ ጌታ የገደለበት
ስፍራዉ ጎድጉዶ ዉሃ ሞላበት
እንኳን ሰዉና ወፍ አይዞርበት
ያሞራ ባልቴት ዉሃ ትቅዳበት።
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ
ከዚህ ብመዘዉ ጎንደር አበራ፣
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ስንዴ
ገና ሳልበላዉ አበጠ ክንዴ።
ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
እግንባሩ ላይ አለዉ ምልክት፣
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት
ሆያ ሆዪ፣
ሆያ ሆዪ
ወይ የኔ ጌታ
ዋርካ ነህ ዋርካ
ቢጠለሉብህ የማታስነካ

ለእማ ወራ

የኔማ እመቤት፣ እሜት እሜት
ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት
የኔ እማ እመቤት የፈተለችዉ
የሸረሪት ድር አስመሰለችዉ
ሸማኔ ጠፍት ማርያም ሰራችዉ
ለዝያች ለማርያም እዘኑላት
አመት ከመንፈቅ ወሰደባት
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ።
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታዉ ይጣራል ገመገም ዞሮ
የኔማ እመቤት የጋገረችዉ
የንብ እንጀራ አስመሰለችዉ።

በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ ይሰጧቸውና እየገመጡ ጅራፋቸውን ሲያጮሁ ያመሻሉ። የቡሄ ዕለት ለእያንዳንዱ የቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ልጅ አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ በልጆቹ ልክ ይሰጣል። በቆሎ ተማሪዎች ዘንድ ደግሞ ደብረ ታቦር ‘የተማሪዎች በዓል’ ነው። ተማሪዎቹ ቀደም ብለው “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ እህሉንም፣ ብቅሉንም፣ ጌሾውንም ይለምኑና ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምዕመናን ሁሉ ይጋብዛሉ።

buhe4

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...