Tidarfelagi.com

ስለችጋር

 • ችጋር ምንድን ነው? ሰፊ ቦታንና ብዙ ሕዝብን የሚሸፍን፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣ ምንም የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ እንስሳት (ሰውንም ጨምሮ) ዕለት በዕለት የራሳቸውን አካል እስኪያልቅ ድረስ ‹‹እየበሉ›› በመጨረሻም የሚሞቱበት ሁኔታ ነው፤ ረሀብ አካል ሲዳከም አካልን ለመገንባት የሚደረግ ጥሪ ነው፡፡
 • ችጋር የሚያጠቃው ማንን ነው? ትልቁና ዋናው የችጋር እንቆቅልሽ የዚህ ጥያቄ መልስ ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ ችጋር የሚያጠቃው ከገበያ ጋር የማይገናኙትን ምግብ አምራቾችን ገበሬዎችን፣ በተለይም እያመረቱ ከእጅ ወዳፍ ብቻ የሚኖሩትን ነው፤ እነዚህ ገበሬዎች የገጠሩ ሕዝብ፣ ማለትም የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጨረሻ ደሀዎች ናቸው፤ ኑሮአቸው ሁልጊዜም በችጋር አፋፍ ላይ ነው፡፡
 • ችጋር ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ነው? ከላይ እንደተባለው በችጋር ላይ የሚወድቁት ገበሬዎች ከገበያ ጋር እምብዛም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፤ ይህም እምብዛም ጥሬ ገንዘብ የላቸውም ማለት ነው፤ ስለዚህ በገበያ ላይ እህል ቢኖርም የመግዛት አቅም የላቸውም፤ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ ነው፤ ምርታቸው መቶ በመቶ በተፈጥሮ ችሮታ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ስለዚህም ተፈጥሮ በትንሹ እንኳን ፊቱን ካዞረ ምርቱ ያንሳል ወይም ጭራሹኑ ይጠፋል፡፡
 • ተፈጥሮ ፊቱን የሚያዞረው እንዴት ነው? ብዙ መንገዶች አሉ፤የእርሻ ምርት በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የተመሠረተ ነው፤ መሬት (አፈር)፣ ውሀ፣ የዓየር ጠባይና ጉልበት፣ ተፈጥሮ በነዚህ ላይ ፊቱን ማዞሩ የሚገለጥባቸው ዋና ዋናዎቹ፡—-
  • ዝናብ ወይ ይበዛል ወይ ያንሳል፤
  • የዝናቡ ወቅት ይቀድማል፤ ወይም ይዘገያል፤
  • ምርቱን ውርጭ ይመታዋል፤
  • ምርቱን ተምች ይመታዋል፤
  • ምርቱን በሽታ ይበላዋል፤
  • ምርቱን ከባድ ጎርፍ ወይም ከባድ በረዶ ያጠቃዋል፤   ሌላም፣ ሌላም፣
 • ተፈጥሮ በአንድ ምክንያት ፊቱን ሲያዞር ለወትሮው በችጋር አፋፍ ላይ የነበሩት ደሀ ገበሬዎቸው ወደችጋሩ ገደል መግባት ይጀምራሉ፤
 • ችጋር ሕዝብን በጅምላ የሚጨፈጭፍበት ጊዜ ከስድስት እስከስምንት ወራት ይፈጃል፤ የተፈጥሮ ችግር መኖሩ ከታወቀ ጀምሮ ከስድስት አስከስምንት ወሮች ሰዎች አካላቸውን ‹‹እየበሉ›› ይቆያሉ፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከሰተ የተባለው ድርቅ ሰዎችን በችጋር መረፍረፍ የሚጀምረው በሚያዝያና በመጋቢት ነው፤ ገበሬዎቹ ከአሁን ጀምሮ እስከመጋቢት ምንም ሰፊና ትልቅ ዘላቂ እርዳታ ካላገኙ በመጋቢትና በሚያዝያ ሰው እንደቅጠል የሚረግፍበት ጊዜ ይሆናል፤
 • ልብ በሉ የመጀመሪያው የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ወይ የተዘራው ጠፍቶአል፤ ወይ ቀንሶአል፤ ወይ ተበላሽቶል፤ ስለዚህም ገና በክረምት ወራት አዝመራ እንደማይኖር ይታወቃል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስከመጋቢትና ሚያዝያ ቢያንስ ስምንት ወራት አሉ፤ በዚህ ጊዜ ሰዎች ወደችጋሩ ገደል እንዳይገቡ የሚያግደው፡-
  ሀ) እያንዳንዱ ሰው ወይም ቤተሰብ ለክፉ ቀን ለመጠባበቂያ የሚሆን እህል በጎተራ ለምን አያስቀምጥም?
  ለ) ለክፉ ቀን ጥሬ ገንዘብ በባንከ ለማን አያስቀምጥም?
  ሐ) አገዛዙ የእርሻ ምርት የሚቀንስ ወይም የሚጠፋ መሆኑ ከታወቀ ጀምሮ ተጠቂ ለሚሆነው ሕዝብ በቂ ምግብ ለምን አያዘጋጅም? ሕዝቡ ራሱ ለችጋር አደጋ እንዳይጋለጥ በየወረዳው ‹‹የእህል ባንክ›› ለምን አያቋቁምም?
  መ) ከእጅ ወደአፍ የማያልፍ ምርት የሚያመርቱ (ሁሌም ለችጋር የሚጋለጡት) ገበሬዎች ለምን ግብርና ሌሎችም መዋጮዎች እንዲከፍሉ ይገደዳሉ? እንዲያውም በአንጻሩ አገዛዙ እነዚህ ለአደጋ የተጋለጡ ገበሬዎች ማኅበራዊና መዋዕለ ንዋያዊ አቅማቸው አቅማቸው እንዲዳብርና እንዲበረታ የማያደርገው ለምንድን ነው? ደሀነታቸውንና ደካማነታቸውን የሚፈልገው ለምንድን ነው?
  ሌሎች፣ ሌሎች ጥያቄዎችም ……
 • የመጨረሻውና ዋናው ነጥብ ማናቸውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ከችጋር ጋር በቀጥታ የተያያዘ አለመሆኑ ነው፤ ከአደጋው በፊት ለማኅበረሰቡ የኑሮና የአስተዳደር ግንኙነት የተገነባው ሕጋዊ የነጻነትና የልማት ሥርዓት መኖር ወይም አለመኖር በአንድ በኩል፣ አደጋውን ተከትሎ እያንዳንዱ ግለሰብ በተናጠል፣ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ያደረጉትን ወይም ሊያደርጉት የሚገባውን አብረን ስንመለከተው በተፈጥሮ አደጋውና በችጋር መሀከል ያለው ረጅም የጊዜ ርቀት ችጋርን የአገዛዝ ውላጅ ያደርገዋል፡፡
 • ስለዚህም ለልማትም ሆነ የተፈጥሮ አደጋን ለመቋቋም ግለሰቡ በሕጋዊ ሥርዓት ስር በሙሉ ነጻነት የማይኖር ከሆነ ከችጋር የሚወጣበት መንገድ አያገኝም፡፡
 • ላችንም በየቀኑ የሚያጋጥመን ረሀብና ለብዙ ወራት ቆይቶ ሥጋን ጨርሶና አጥንትን ፍቆ ለሞት የሚዳርገው ችጋር አንድ አይደሉም፤
 • ድርቅ የሚባለው የተፈጥሮ አደጋና በሰው ልጆች ቸልተኛነት የሚከሰተው ችጋር አንድ አይደሉም፤ ሁለቱን አንድ ለማድረግ የሚሞከረው ኃላፊነትን ለመሸሽ ነው፤

ችጋርና የእውቀት ችጋር

በፈረንጆች ባህል እውቀት ሥልጣን ነው፤ እንዲያውም እውቀት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ባህል እውቀት ሥልጣን የለውም፤ እንዲያውም ሥልጣን እውቀት ይመስለናል፡፡

በ1951 ዓ.ም. በትግራይ ችጋርን በዓይኔ አይቻለሁ፤ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፤ በአካሌ ቀምሼዋለሁ፤ ጠኔ ይዞኝ ተደግፌ ወደቤቴ ገብቻለሁ፡፡
በመቀሌ ያየኋት አንዲት የመቀሌ ወጣት እናት ከነሕጻንዋ በአእምሮዬ ተቀርጸውና ተቆራኝተውኝ በሕልሜም በእውኔም እየወተወቱኝ ስለችጋር እንዳጠና አስገደዱኝ፡፡ ችጋርን እያገለበጥሁ ከሰባት ዓመታት በላይ አጠናሁ፤ የጥናቴ ውጤት RURAL VULNERABILITY TO FAMINE IN ETHIOPIA: 1958-1977 በሚል ርእስ በህንድ አገር፣ በኒው ዴልሂ ከተማ ታትሞ በ1977 ዓ.ም. (በአአ በ1984) ወጣ፤ በአሜሪካ የተማርሁበት ክላርክ ዩኒቨርሲቲ ለጥናቱ ድጎማ የሚሆን የ$30,000 ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በእኔ በኩል አበርክቶአል፤ ለእኔ የተረፈኝ አንድ መቶ መጻሕፍት ብቻ ነበር፡፡ እአአ ከ1984 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መጽሐፉ ይሸጣል፤ እኔ ሳልጠየቅ አንድ INTERMEDIATE TECHNOLOGY Publications (9 King Street, London WC2E 8HW,UK), የሚባል የእንግሊዝ ኩባንያ እአአ ከ1986 ጀምሮ በተደጋጋሚ እያሳተመ ይቸበችበዋል፤ ለእኔ አንድ ሣንቲም አልደረሰኝም! በዚህ የችጋር ምክንያት ሌሎች የደረሱብኝን ነገሮች መግለጹ አይደለም፤ ጥቁር ከመሆን፣ ኢትዮጵያዊ ከመሆን፣ … የተነሣ የተሰነዘሩ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚያም በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስል በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ አውራጃዎች በጣም ዝርዝር የሆነ ጥናት በሁለት መቶ ሰማንያ አምስት መንደሮች ጥናት አካሂጄ ውጤቱ እአአ በ1991 SUFFERING UNDER GOD’S ENVIRONMENT: A Vertical Study of the Predicament of Peasants in North-Central Ethiopia, (Published by AFRICAN MOUNTAINS ASSOCIATION AND GEOGRAPHICA BERNENSIA, Marceline, Missour, USA, 1991) ታተመ፡፡
***************************************************************************************
ዛሬ በቴሌቪዥን ስለድርቅ፣ ስለችጋር የሚያወሩና በተለያየ ቦታ የሚጽፉ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መጽሐፎች ሲሆን ሁለቱንም፣ አለዚያ አንዱን ያለነበቡ ከእግር ጥፍራቸው እስከራስ ጸጉራቸው በእፍረት ይከናነቡ፤ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ ማኅበራዊ ሁኔታ በእውቀት፣ ማለትም በተጣራ እውቀት እየዳበረ ከትውልድ ወደትውልድ እንዳይተላለፍ የሚያደርገው ይህ አስመሳይነትና የመንፈስ ውርደትና የአእምሮ ስንፍና ነው፤ እውቀት የማኅበረሰብ ሞተር ሆኖ ወደፊት የሚያራምደው ከቀደመው ትውልድ የተረከቡትን በሚገባ አጥንተውና አዳብረው ለሚቀጥለው ትውልድ ሲያስረክቡ ነው፤ ወይም የተረከቡት የማይረባ መሆኑን አስመስክረው ሲጥሉትና በሌላ ሲተኩት ነው፡፡
ሰሞኑን የማየውና የምሰማው ያሳፍረኛል!

በዚህም ምክንያት ከትውልድ ወደትውልድ እውቀት ሆኖ የሚተላለፈው ከሥልጣን ጋር የተያያዘው ብቻ ነው፤ ሥልጣን
የእህል ምርት እጥረት
የአህል ምርት እጥረት የሚከሰተው
ድርቅ የተፈጥሮ ቀውስ፣ ችጋር በጭቆና መኖር
ችጋር ማንን የጠቃል
ሰሞኑን ብዙ ጸሐፊዎች ስለችጋር ያወራሉ (አብዛኛዎቹ የሚሉት ረሀብ ነው)፤ እንደሚመስለኝ እነሱ መጻፍ ከመጀመራቸው በፊት ስለችጋር ማንም ያሰበ፣ ማንም የጻፈ አይመስላቸውም፤ ስለዚህም በነሱ ቤት የሚጀምሩት ከዜሮ ነው፤ ስለዚህም በረሀብና በችጋር መሀከል ያላውን ልዩነት አያውቁትም፤ ስለዚህም በድርቅና በችጋር መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁትም፤ ስለዚህም በችጋሮች መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁም፤ ሳያውቁ ለማሳወቅ መሞከር ከምን ይመጣል?

Ethiopian academician and peace activist who has been actively engaged in a peaceful movement to bring justice, equality and peace for all the people in Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...