Tidarfelagi.com

ሳንሱራም!

ሳንሱራሞችን አትከልክሏቸው፣ ብትከለክሏቸውም አይከለኩልም የሚል ያልተከተበ ህግ አለ መሰለኝ።ሰዉ ሳንሱራም ነው። ያንተ ሃሳብ በገዛ ሞዱ ልክክ ብሎ ካልገጠመለት፣ ይጎመዝዘዋል። ሊያጣጥለው ላይ ታች ይወርዳል። አይዞህ ብቻህን አይደለህም፤የብዙዎቻችን ችግር ነው።

የገዛ ሃሳብን እያሽሞኖሞኑ፣ የገዛ ልጅ ነው ብለው ከነንፍጡ የሚወዱ ሰዎች የሌሎች ለየት ያለ ሃሳብ ይጎፈንናቸዋል።
«ባክህ ጠሽ ነው» ብለህ ጀምረህ… በጓሮ በር ወደ ስድብ፣ ሲያድግ ወደ ዱላ አድራሻ ታደርሰዋለህ።
«የሰው ልጅ፣ ባይወልዱትም ልጅ ነው» የሚሉ ጥቂት ናቸው። ለብዙ ሰው የሰው ልጅ፣ሁሌም የሰው ልጅ ነው።
አንባገነን መንግስታት የሚወለዱት ይህቺን መሰል የአስተሳሰብ ኩርባ ላይ ነው። የእኔ ብቻ ልክ ብሎ ያደገ፣ ስልጣን ብትሰጠው ልክ ያስገባሃል እንጂ « ልክ ነህ» ብሎ ሊያደምጥህ አይዘጋጅም።

አንዳንዴ ፕሮግረሲቭ በሚመስሉህ ሰዎች መሃል ክንፍ አውጥቶ ሲበር ታገኘዋለህ።ብዙዎቻችን የያዝናቸው ሃሳቦች ከትናንሽ «እንዲህ መሰለኞች»፣ «ተጭኖ ካሳደገን አካባቢና አስተዳደግ» ወዘተ የመነጩ መሆኑን እንረሳዋለን። እንዴት እዚህ እንደደረስን ዘንግተን የደረስንበት አመለካከት ትልቅ ስነተፈጥሯዊ ሀቅ አድርገን ጉሮሯችን እስኪነቃ መጮህ ነው።
በቅርብ አንዷ «አዳም ረታ የዓለማችን አንደኛ ደራሲ ነው» አለች። መጀመሪያ ሳቅኩ። ከዛ ተሟገትኳት። ያን ቀን የዘረጋችው ለንቦጭ እስከዛሬ አልሰበሰበችውም 🙂 የሚመለከተው አካል ሰብስቦ ወደ ቦታው እንዲመልሰው እማፀናለሁ ሃሃሃ

ጩኸቴ ሃቅ፣ ጩኸትህ ያካባቢ ብክለት ይመስለኛል። ሳንሱሬን ይዤ መጣለሁ። ልክ አይደለህም እላለሁ። ልክ እንዳልሆንኩ ትነግረኛለህ። ፋራ ከሆንን በዛችው ተጣልተን እንቀራለን። ወደ ልቦናችን ቶሎ ከተመለስን «ይመችሽ» ተባብለን በእንግሊዝ በር እንወጣለን።

የጀመርነውን የሳንሱር መንገድ ግን፣በየቀያችን ሰፋ አድርገን እንጠርጋለን። ዘርዓያቆብ በአንዲት ግልገል መፅሐፍ ተወስኖ የቀረው በሳንሱር ነው። በዓሉ ግርማን የበላው ሳንሱር ነው። እልፍ ወጣት ያለቀበት የዛ ትውልድ ቀይ እና ነጭ ሽብራችን ሳንሱር ነው።ዛሬ ትውልዱን «ፀረ ልማታዊ አተነፋፈስ መተንፈስ ክልክል ነው»የሚለው መንግስት በሳንሱር ማህፀን ተፀንሶ የተወለደ ሳንሱራም መንግስት ነው!
ሳንሱር በህግ ተከልክሏል ቢሉህ አትመን።ህግ የማይከላው ሳንሱር ነው፣ በዙር የሚቀጣን። ህዝብ እና መንግስት እንኳን የሚጣላው በሳንሱ ነው። ህዝብ የራሱን ሳንሱር ይዞ ይመጣል።መንግስትም የራሱን። የኔን ፈፅም ይባባሉና፣ ሳንሱራቸውን ጥለው ራሳቸው ይጣላሉ። መንግስት ባለብረት አይደል? ጊዜው እስኪያልፍበት፣ የተቃወሙትን እየጣለ ይቀጥላል! 

ይሄን ፅሁፍ ብዙ ምሳሌ እየጠራሁ ላረዝመው ነበር። ግን እንኳን ሌላ ሰው ራሳችንም በላያችን ላይ ሳንሱራም ነን። «ምን ይሉኝ ይሆን?» ብሎ ከሚጀምረው፣ እስከ «እንደ ጎረቤቴ ልሁን» ብሎ እስከሚፍጨረጨረው… ግለ ሂሳም ነው። «ትንሽ አታፍርም» እስከ ሚለው፣ «እንዲህ አይደረግም» የሚለው የሳንሱር ፀጉር ቤት ባለመቀሳም ነው።
አዳሜ ሳንሱራም ነው።
የሰውን ልጅ አጉልተው ከሚገልፁ ባህሪያት አንዱ ሳንሱራምነቱ ነው!
ሳንሱራም 🙂

===============

ሳንሱራም 2

ምናልባት እንቆቅልሽ ላይ ብቻ ይሆናል፣ «እንቆቅልህ» ስትለው «ምን አውቅልህ» ባይ ያለው። በተረፈ «እኔ አውቅልህ!» ባዩ ከምድር አሸዋ ይበዛል።
ሳንሱር በራሱ አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ቦታዎች አንዱ ህግ ነው። አመፀኛ ባህሪ ያለው ሰው እልፍ ነው።ህግ ቀንዱን መቶት ያስጎነብሰዋል። ያ ባይሆን፣ ቆንጆ ሚስት አግብተህ በሰላም አትኖር ነበር። ልጅህ በደህንነት ትምህርት ቤት ደርሳ አትመጣም ነበር ። ለዚህ መልካም ሆነልኝ በል።

ሳንሱር በምድራዊ ህግ ብቻ አይወሰንም። መንፈሳዊው ህይወትም ሳንሱር ነው መሰረቱ። የአድርግ በር እና የአታድርግ አጥር ናቸው ቤት አድርገው የሰሩት ። አስርቱ ትእዛዛት ምንድናቸው? አስር ሳንሱሮች አይደሉም? አትግደል የሚል ሰዋዊና «መንፈሳዊ» ህግ ባይኖር ኑሯችን ያዳኝ ታዳኝ አይሆንም? 

የሳንሱራሞች አንዱ ተግባር ውክልና ሳይሰጣቸው መቀበል ነው።ዛሬ እንትን ብሔር ይገንጠል ብሎ፣ ጆሮህ እስኪገነጠል የሚጮህብ ዲስኩራም በገዛ ብሔሩ ላይ የሳንሱር መቀስ ያነሳ ነው። «አብረን እንኑር» የሚሉ ሌሎች አመለካከቶች አይታዩኝም ብሎ በመቀሱ ቆርጦ የጣለ እኔ አውቅልህ ባይ ልብ አውላቂ ነው!
ለብሔሩ ውክልናውን ይወስዳል።
ማልኮም X «I knew that no one would kill you quicker than a Muslim if he felt that’s what Allah wanted him to do» ሲል ምን ማለቱ ነው? የአላህን ስም የሚጠራ አደገኛ ሳንሱራም በሽ ነው ማለቱ ነው። ተወካይ ነኝ ብሎ መመድመድ የሳንሱራም ባህሪ ነው።
ባህሉ አይፈቅድም እያለ ሊከርክምህ ደፋ ቀና የሚለው የማህበረሰቡ አካል ወይ ተወካይ አድርጎ ራሱን የሾመው ነው።የትም ሂድ፣ ሳንሱር ያልነገሰበት ሰርጥ አታገኝም።
ህዝብ ብትሆን ሳንሱራም፣ብሔር ብትሆን ሳንሱራም፣ ግለሰብ ብትሆን ሳንሱራም፣ ሀገር ብትሆን ሳንሱራም ነህ። ሱፐር ሳንሱራም ፍጡር ነው ሰው። እመን እንጂ አትፍራ።

የሳንሱር አለንጋን በደንብ ከሚቀምሷት መሃል ልጆች ዋነኞቹ ናቸው። ወላጅ በልጁ ዘመን ላይ ተፈናጦ መኖር የሚፈልግ ያልፎ ሂያጅ ዘመን ጀሌ ነው። ሳሙኤል ጆንሰን «ራስ ሴላስ፣የኢትዮጵያዊው መስፍን ታሪክ»ባለው መፅሐፍ ያለው ይህንን ነው።
«አባት ዓለሙን ለመተው ዝግጁ ሳይሆን ልጁ ውስጥ ገብቼ ልደሰት ይላል፤ባንድ ጊዜ ውስጥ ለሁለት ትውልድ ስፍራ የለም»

ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ ሲባሉ፣ በለጋ አንደበታቸው «ዶክተር፣ፖይለት፣መሃንዲስ» ቢሉ አትስማ።አትመን። የሚያወሩት ልጆቹ አይደሉም። ወላጃቸው ነው የሚያወራህ። ፖይለት የመሆን ከፍ እና ዝቁን የማወቅ የህይወት ልምድ የላቸው። ልጆቹን በሚፈለገው ልክ ከርክሞ ለገበያ የሚያወጣ ወላጅ ነው።
ወላጅ በልጆቹ ውስጥ የሚፈልገውን ማፅደቅ ብቻ ሳይሆን፣ የማይፈልገውን መንቀል ተግባሩ ነው።
ብዙዎቻችን በልጅነት መስካችን ውስጥ፣ ወላጆቻችን የሳንሱር ማጭዳቸውን ይዘው ገብተው መድምደው የፈጠሩን ነን።
ስታድግ ከምትወርሳቸው ውድ እቃዎች መሃል አንዱ፣ የወላጆችህ ማጭድ ነው። ማጭዳም ትውልድ ይቀጥላል… ኢንሻ አላህ!
ሳንሱራም ሁላ 🙂

 

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • Kassahailu6@gmail.com'
    ጀማሉዲን ሚፍታ፡፡ commented on December 27, 2017 Reply

    Good.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...