Tidarfelagi.com

‹‹ሲያመኝ ነው የከረመው››

ከሁለት አመታት በፊት ኤርትራ ስሄድ ብዙዎች የለየለት አምባገነን የሚሉትን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በታማኝ የሚደግፉ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት የድጋፍ ምክንያት አንድ ነበር።
‹‹ዙሪያውን እና ከበታቹ ያሉት ናቸው እንጂ እሱ እኮ ጥሩ ሰው ነው…አይዘርፍም…አያጠፋም…ለኤርትራ ታማኝ ነው›› የሚል ነበር።
እንደ ዘፈን አዝማች ይደጋግሙት ነበር።
እንደዚያ ባሉኝ ቁጥር አምባገነን የሚሰራው ከእንዲህ ያለው ከንቱ ውዳሴ እና ጭፍኝ ታማኝነት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። እንዲህ ባሉኝ ቁጥር ፣ ሰውየውና መንግስቱ ለሚሰሩት ጥፋት፣ ለሚያደርሱት ጉዳት ሰውየውን ተጠያቂ ላለማድረግ አይናቸውን ጭፍን፣ ጆሯቸውን ድፍን፣ መንገዳቸውን ቅይር እንደሚያደርጉ ይገባኝ ነበር።
ሳይቆይ እኛም ላይ ደረሰ።
በዚያው ሰሞን በጠቅላይ ሚኒስትራችን ‹‹መግደል መሸነፍ ነው›› ዲስኩርና እርምጃ አለመውሰድ ሁናቴ በመናደዴ ‹‹አብይ አህመድ የሹም ዶሮ አይደሉም። ሲያበጁ ይወደሳሉ፣ ሲያጠፉ ይወቀሳሉ›› በማለቴ የአድባር ዛፍ የነቀነቅኩ፣ ቅዱስ ያጠለሸሁ ይመስል ብዙ ሰዎች ወረዱብኝ።
ሲያጠፋ በጊዜ አጥፍተሃል የማይባል መሪ ወዴት እንደሚሄድ ስለገባኝ ነበር የስድብ ወርጅብኙን ችዬ ደስ ሲለኝ አበጀህ፣ ሲከፍኝ አጠፋህ ማለቴን የቀጠልኩት።

ከፌስቡክ በራቅኩባቸው ባለፉት ጥቂት ወራት ነገሮችን ረጋ ብሎ ለማብላላት፣ ከጫጫታው ራቅ ብሎ ራሴን ለማዳመጥ እድል አግኝቼ ነበር።
ብዙ ነገሮች ሲያቆሰሉኝ፣ ሆድ ሆዴን ሲበሉኝ፣ ብዙ ነገሮች ሲያንገበግቡኝ ቢከርሙም ስሜቴን ሳላጋገራ ላለመፃፍ ወስኜ ርቄ ቆየሁ። ይሄን ያደረግሁት ለሃገሬ ሰላም ውለታ ልዋል ብዬ ነው በማለት ልመፃደቅበት አልሻም።
ግን ደግሞ እንደ አንድ ሃገርዋን እንደምታፈቅር ሴት መናገሬ ከዝምታዬ ካልተሸለ ያንን መምረጤ ነበር።
ለራሴ እና ለስሜቴ ጊዜ ሰጥቼ ለመመለስ ነበር።
ባለፉት ወራት ሰለሃገሬ በብዙ ታምሜያለሁ።
ስለኢትዮጵያ ጉዳይ በብዙ ተብሰልሰያለሁ። አሁን ወደ አውድማው ተመልሻለሁና ወደ ወግና ልቦለዴ ዘልዬ ከመግባቴ በፊት ህመሜ አሟችሁ ከነበር፣ ጭንቀቄ ጨንቋችሁ ከነበር- የእኔንም ባጭሩ- ሳላንዛዛ ልንገራችሁና ወደ መደበኛው ፅሁፌ እንሂድ ብዬ ነው።
ከጣማችሁ ማንበብ ቀጥሉ።
አሞኝ ነው የከረምኩት….
1ኛ ህመሜ – ‹‹ግጭት›› ወይስ ‹‹ፍጅት››?
መንግስትና በጣቱ የሚያዛቸው ሚዲያዎች ባለፉት ወራት በሃገሪቱ እየሆነ ያለውን ነገር ‹‹በሁለትና ከዚያ በላይ ወገኖች መሃከል እንደተፈጠረ ግጭት›› ሲያወሩት ሲበልቱት አያለሁ።
ሁለት በእኩል የተዘጋጁ ወገኖች እንዳስነሱት ጠብና ጥፋት ሲያወሩት ሰምቻለሁ።
ይህ ያመኛል።
የተደራጀ እና የተሰናዳ ቡድን ወረቀትና ካርታ ይዞ በጎሳ-በሃይማኖት-በግል በቀል በመረጣቸው ሰዎች ላይ ያደረሰውን የታቀደና የታለመ ጥቃት እና ፍጅት ግጭት ብሎ መሸፋፈኑ፣ በውሸት መሰየሙ ከሆነው ዘግናኝ ነገር እኩል ያማል። ያሳፍራል።
2ኛ ህመሜ- ‹‹አሁን በአይኔ መጣሽ››
የጥቃት ምልክቶች ብቻ ሳይሆኑ ዘግናኝ ናሙናዎች በየቦታው ብቅ እያሉ መቶዎችን ሲጨርሱ፣ ሚሊዮኖቹን ሲያፈናቅሉ በትእግስት ሰበብ ሲመለከት የከረመው መንግስት፣ ስንጮህ ተረጋጉ፣ ስናለቅስ ዝም በሉ ሲለን የነበረው አመራር በድንገት ‹‹አጥፊዎቹን ማደን› የጀመረው ትእግስቱ ተሟጦ ሳይሆን ያ ህዝብን ሲያሸብር፣ ያ ስንቶችን ሲያተራምስና ሲፈጅ የነበረው ቡድን በአይኑ-በስልጣኑ መምጣቱን በመረዳቱ መሆኑ ያሳዝነኛል።
3ኛ ህመም- ‹‹አልቀየምህም እንዳሻህ ተናገር››
በተደጋጋሚ አንድ ህዝብን ነጥሎ በይፋ የሚያንቋሽሽ፣ ‹‹ሰራንላቸው›› እያለ በአደባባይ የሚደነፋ፣ የራሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንን የማያስታግስ፣ ተው የማይል፣ ከስፍራው ማንሳቱ ቢቀር ለይስሙላ እንኳን ‹‹ይቅርታ ጠይቅ›› ለማለት ግድ የማይሰጠው መንግስት እያስተዳደረን መሆኑ ያስገርመኛል- ያመኛል።
ስጀምር እንዳልኳችሁ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ‹‹እሱ አይደለም እኮ ዙሪያውን ያሉት ናቸው የሚዘርፉት…ከበታቸሁ ያሉት ናቸው ህዝብ የሚያሰቃዩት ›› እያሉ መሪውን ከደሙ ንፁህ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች እኛም ጋር ተፈጥረዋል።
‹‹ምንም ይሁን ምን ከአብይ ጎን ነኝ…እሱ አይደለም እኮ ከታች ያሉ ሰዎች ናቸው የሚዘርፉት….እሱ አይደለም እኮ ዙሪያው ያሉት ናቸው ይሄን የሚያቀናብሩት ›› የሚሉ ሰዎች በዝተዋል።
ሃገሬን እወዳለሁ።
ህዝቤን አፈቅራለሁ።
መሪዬን አመራሩ እስካሳመነኝ፣ መንግስቱን እስካገለገለኝ ድረስ እደግፋለሁ።
ነገር ግን ዙሪያውን ለማየት አንገቱን የማያዞር መሪን በጭፍን አልደግፍም።
ህመሜን አድምጦ የበታቾቹን -ሃይ የማይል- የማያስተካክል መሪን ‹‹እሱ አይደለም እኮ›› ብዬ ከደሙ ንፁህ አላደርግም።
ምድር ቁና ብትሆንም ‹‹ምንጊዜም ከጎንህ ነኝ›› ብዬ በሰወርዋራ መንገዱ አልከተለውም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...