Tidarfelagi.com

‹‹ሲስተርሊ- ብራዘርሊ››

ከዶ/ር መረራ ኢንትሮዳክሽን ቱ አፍሪካን ፖሊቲካል ሲስተምስ ክላስ ስንወጣ ‹‹ ዛሬ ተሳክቶልኝ ኤፊን ላስተዋውቅሽ ነው›› አለኝ ክብሮም።

ክብሮም፣ በእሱ ቤት ‹‹ንፁህ›› ጓደኛዬ ነው።
(በነገራችን ላይ…ንፁህ ጓደኛ ሲባል ያስቀኛል። ወንድና ሴት ‹‹እሱ እኮ ንፁህ ጓደኛዬ ነው…እሷ እኮ ንፁህ ጓደኛዬ ናት›› የሚባባሉት ወንድና ሴት ሆነው ለፍቅርና ለድሪያ ስላልተፈላለጉ፣ ለስጋ ፍላጎታቸው እጅ ስላልሰጡ፣ ለ‹እንስሳዊ› ስሜታቸው ባሪያ ስላልሆኑ ልዬ ፍጡር እንደሆኑ እንዲታወቅላቸው ስለሚውተረተሩ ይመስለኛል። የጉብዝና አክሊል ድፉልን ለማለት ሲያሽቋልጡ ይመስለኛል። አለ አይደል….‹‹ እዩንማ…እሷ ባለሽንቁር፣ እኔ ባለቃጭል ብንሆንም መደራረግ አንፈልግም…በሌላ ነገር አንፈላለግም….ግንኙነታችን ንጹህና ቅዱስ ነው….ልዩ ፍጡሮች አይደለንም? እንደነ ቀነነኒሳ ወርቅ ሜዳሊያ አይገባንም አይነት ነገር…)

እና ክብሮም በእሱ ቤት ንፁህ ጓደኛው ነኝ። ሰፊ ዳሌ፣ ትላልቅ ጡቶች ቢኖሩኝም፣ የወር አበባ ባይም ከወንድ ጓደኞቹ ለይቶ የማያየኝ ጓደኛው።

በእኔ የቀቢፀ ተስፋ ምስኪን ቤት ግን የወደፊት ባልና ሚስት ነን። በእኔ ቤት ግን ኬቢ የምመካበት ባሌ፣ የምሳሳላቸው ልጆቼ አባት ነው። በህቡእ እወደዋለሁ። ኪቢዬ ኦክስጂኔ! ሳልነግረው አፈቅረዋለሁ።

‹‹በመጨረሻ ከኤፍሬም ጋር ልታስተዋውቀኝ ነው…?›› አልኩና መለስኩለት ።
‹‹እህ! ድሬ ሁለት አመት ውጣው ነው እንጂ ድሮ ነበር ማስተዋውቃችሁ። ትወጂዋለሽ….›› አለኝ ዘወትር በክፍሎች መሃከል ወደምንቀመጥባት ለእኛ የተሰራች የምትመስለኝ የድንጋይ ወንበር ላይ ቀድሞኝ ሄዶ እየተቀመጠ።

‹‹ትወጅዋለሽ›› አባባሉ ሌላውን ነገር ካለበት ሁኔታ ይለይ ነበር…የሆነ አፅንኦት…የሆነ ትኩረት ነበረው።

ቁጭ ካልን በኋላ ትናንሽ አይኖቹን በትላልቅ አይኖቼ እያየሁ ‹‹ በአካል አንገናኝ እንጂ በዚህ ሁሉ አመት ወሬ ማውቀው ማውቀው ነው ሚመስለኝ….ለነገሩ ያንተ ቤስት ፍሬንድ ከሆነ ምክንያት አለው….ላልውደው አልችልም›› አልኩት።

‹‹አሃሃ….ለነገሩ ልክ ነሽ…ኤፊ ከግምት በላይ አሪፍ ልጅ ነው…ትወጅዋለሽ…..››

ሶስት አረፍተነገር ሳንመላለስ ሁለት ጊዜ ‹‹ትወጅዋለሽ›› ፣ ያውም በ‹‹ እርግጠኛ ነኝ…አብራችሁ ትሆናላችሁ›› ስልት ማለቱ በእሱ ቤት ንፁህ ጓደኛ የመሆናችን አንዱ ማረጋገጫ ነው። አዲስ መረጃ ባይሆንም ልቤ እንደጎማ ተነፈሰች። ግን ወሬ አላቆምኩም።

‹‹ምነው ትወጅዋለሽ ትወጅዋለሽ አበዛህ? ልታጣብሰን አስበሃል እንዴ?›› አልኩና ፊቱን ለስሜት ለውጥ በሚመረምር አኳሃን አበክሬ ፈተሽኩ። ሲደነግጥ ወይ ሲያፍር፣ ወይ የደበቀው ነገር ሲታወቅበት እንደሚሆነው ቀይ ፊቱ አልደፈረሰም። ሲከፋ ወይ ቅር ሲሰኝ እንደሚሆነው አይኖቹ ይበልጥ አልጠበቡም።

ያልተለወጠ ፊቱን እያየሁ መልሱን ሰማሁ።
‹‹እና ታዲያስ…ኤፊን አግኝተሽ ነው?›› አለኝ።

ምንም ተስፋ የለኝም።

፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥፥
የዚያኑ እለት ከሰአት ፤ በወሬ ከገነባሁት በአካል ከማላውቀው ኤፍሬም ጋር ተዋወቅን፡:፡ ገና ለገና ኬቢን ስለምወደው…. ኤፍሬምን የመሰለ ልጅ በደብዛዛው ገልጬ፣ አገኘሁት ብዬ ማለፍ ፍትህ ማጓደል ነውና ዘርዝሬ ልንገራችሁ።

ኤፍሬም ፣ ‹‹እስቲ አለሁ የሚል ወንድ ያንበርክከኝ›› ብላ በትእቢት ተወጥራ የመጣችን ሴት ባንዴ የሚያርበደብድ መልካና ቁመና አለው።

እመኑኝ፤ የማያምር ነገር የለውም።

አባቴ ይሙት፣ ጆሮዎቹ ሳይቀሩ ያምራሉ።
የእግሮቹ ጣቶች እንኳን ያምራሉ ( ድሬ ለምዶበት ነው መሰለኝ በአዲስ አበባ ብርድ ቄንጠኛ ነጠላ ጫማ አደርጎ ነው የመጣው) ፤ ቁርጭምጭሚቱ እንኳን ያምራል (ከቁምጣ ረዘም፣ ከመደበኛ ሱሪ አጠር ያለ ‹‹ሚዲ›› ቱታ ነው የለበሰው) ።

ሰውነቱ ለሚበላው የሚጨነቅ፣ መንቀሳቀስ የሚወድ መሆኑን ይነግረኛል። ግን ደግሞ ሌት ተቀን ብረት እያነሳ በአንድ ደረት ላይ ሰላሳ ሶስት ቦታ ፈርጣማ ጡት አውጥቶ የመጠጥ ቤት ቦዲ ጋርድ ከሚመስል ሰው ጋር (በጣም የምጠላው ሰውነት…አቦ ቦርጭ ሁላ ይሻለኛል) የማይመሳሰል አይነት ነው።

አለባበሱ ዘመነኛ፣ ወንዳወንድነቱ ግን የድሮ ነው። አለ አይደል…ስኪኒ ሱሪ አድርጎ መጥቶ ልክ ግሩም ኤርምያስ የአምባሳደርን ሱት ለብሶ ሲመጣ እንደሚሰራው ነው የሚሰራው…ሴት የሚያቅበጠብጥ ወንዳወንድነቱ ስኪኒ ከሚለብሱ ወንዶች የማይገኝ ህልም ነው።

በዚያ ላይ ንፅህናው ያስገርመኛል….ሁሌም ልክ ከሻወር ሲወጣ ያገኛችሁት የሚመስል ንፅህና አለው…አባቴ ይሙት በልጅነቱ ንፍጥ ምናምን ተጠርጎለት ያደገ ሁሉ አይመስለም…ይህንኑ ልብሱን ለብሶ…ሽር ብትን ብሎ ከእናቱ ማህፀን ‹‹ወክ›› አድርጎ የወጣ እንጂ እንደሌሎቻችን በምጥ ተደናብሮ፣ አምርሮ እያለቀሰ…በምናምን ተሸፍኖ የተወለደ አይመስልም።

ሲያወራ የረጋ፣ ግን ደግሞ ተጫዋችም ነው። ጋግርታምም አይደል፣ ቀለብላባም አይባል….

ብቻ በሁሉ ነገሩ ምትሀታዊ በሆነ መልኩ በሁለት ሊያስጠሉ በሚችሉ ፅንፍ ማንነቶች መሃከል አማካይ ነጥብ ላይ በምቾት ተቀምጦ፣ እንደኔ ያለችውን ሴት ለማሳሳት ተሰርቶ የተዘጋጀ የምርጥ ወንድ ሰርቶ ማሳያ ነገር ሆነብኝ።

እመኑኘ፣ ልጁ ትንሽ ፊት ቢሰጡት መነኩሴን አለማዊ የሚያደርግ፣ ጭምትን የሚያሳብድ ያልተለመደ አይነት መስህብ አለው።

እንዲህ ያለን ወንድ፣ ያውም በገዛ ጓደኛው ‹‹አብራችሁ ሁኑ›› የሳምንታት ግፊት እየተገፉ እንዴት ብሎ መቋቋም ይቻላለል? እንዴትስ ብለው ለእንዲህ አይነቱ ሰው በሴት- ያውም በፍቅር እጦት በተጎሳቆለች የሴት ልብ- ላይረቱልት ይቻላል?

ህእ….ልወደው ነው እንዴ?
(ክፍል ሁለት- ነገ ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...