Tidarfelagi.com

ሲስተርሊ ብራዘርሊ – (ክፍል ሶስት)

እንዲህ ስድ መሆኔን፣ ኬቢ ላይ እንዲህ መባለግ መቻሌን ማመን አቃተኝ። ግን ይሄ ግልብ መልስ ከልክ በላይ አንድዶት፣ ይሄንን ድብብቆሽ ቶሎ የሚያፈርስና ‹‹እወድሻለሁ›› የሚያስብለኝ፣ ለአመታት የጠበቅኩትን ልጅ በደቂቃዎች የሚሸልመኝ ስለመሰለኝ እንደዚያ አልኩ።

ልቡ በተሰበረ ሰው አኳሃን አየኝ።
እመኑኝ፤ አግኝቼዋለሁ።

በድንገት ቀና አለና
‹‹ምእራፍዬ፣ በጣም አዝናለሁ…ይሄ ሁሉ የኔ ጥፋት ነው…አንቺ ምንም አላረግሽም›› አለኝ።

አላልኳችሁም? ኑዛዜው ተጀመረ….!
‹‹ምንድነው ጥፋትህ?›› አልኩት ቀስ ብዬ አይን አይኑን እያየሁ።

‹‹የማፈቅራትን ልጅ በድድብናዬ ለሌላ አሳልፌ መስጠቴ። ጅልነቴ። ላንቺ ያለኝን ፍቅር ለማወቅ ይህን ሁሉ ዘመን መፍጀቴ። ከሁሉ በላይ ግን አንቺን እንዲህ ማሰቃየቴ›› ሊለኝ ነው ብዬ ሳስብ…፡

‹‹እኔ ነኝ ገፋፍቼ እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የከተትኩሽ….ለማንኛውም…አሁን እውነቱን ሳውቅ ነው በድፍረት ልንገርሽ ብዬ የመጣሁት››

ያው ነው። እኔ ቀጥታ የሚለኝን ነገር አሰብኩ እሱ ግን ዙሪያ ጥምጥሙን ጀመረ።

ታግሼ ማስጨረስ አለብኝ።
‹‹ምንድነው እውነቱ?›› አልኩኝ እንደመሽኮርመም እየሰራኝ።
‹‹እሱ ኢት ኢዝ ኖት ኢምፖርታንት!››
‹‹ማለት…››
‹‹በቃ እሱን እንተወው…ዋናው ነገር አንቺ ከኤፊ ጋር መሆን የለብሽም››
‹‹እኮ ለምን?››
‹‹በቃ አይሆንም አልኩሽ››
‹‹ምንድነው በቃ አይሆንም አልኩሽ ማለት…ድንገት ምን ተፈጠረ?›› በዙሪያ ጥምጠሙ ትእግስቴ እያለቀ ጠየቅኩ።

በረጅሙ ተነፈሰ። የደፈረሰ ፊቱ ይበልጥ እየደፈረሰ ‹‹በቃ….አንቺ ከእሱ ጋር መሆነን የለብሽም›› አለ።
‹‹ኬብ!›› አልኩት በንዴት ጮክ ብዬ
‹‹እ››
‹‹ቀንተህ ነው አይደል?››
ፊቱ ላይ ከፍተኛ ግራ መጋባት፣ መወናበድ አየሁ።
‹‹ም…..ን?›› አለኝ እጅግ በደነገጠ ሰው ሁኔታ።
‹‹ኢትስ ኦኬ…ንገረኝ…..››
‹‹ምንድነው ምነግርሽ?››
‹‹እውነቱን…››
‹‹ምንድነው እውነት የመሰለሽ?››
‹‹ቀንተህ ነው ወይ…..››
‹‹በማ…በማን ነው ምቀናው?››
‹‹በኤፊ….ከኔ ጋር ስለሆነ ….››
‹‹ምእራፍ አትዘባርቂ!››
‹‹ምን ማለት ነው አትዘባርቂ..?››
‹‹እንደሱ አይደለማ!››
‹‹እንዴት ነው ታዲያ?››
‹‹ምክንያቱ ምን ያደርግልሻል? በቃ እሱ ላንቺ አይሆንም ካልኩ አታምኚኝም?››
‹‹ትላንት ያለሱ ሰው አልተፈጠረም ያልከውን ሰው ዛሬ ከመሬት ተነስተህ ላንቺ አይሆንም ስትለኝ ለምንድነው ማምንህ? ይልቅ ዋናውን አውነት ንገረኝ….››
‹‹ከመሬት ተነስቼ አይደለም!››
‹‹እና ከምን ተነሳህ….›
‹‹እሱን ዛሬ ላወራሽ አልፈልግም››

ነገሩ ሁሉ ሊማሊሞ ዳገት ሆነብኝ። ተዳከምኩ። ተናደድኩም።
‹‹በቃ ልትነገረኝ ካልፈለግህ ተነስና ሂድ!›› አልኩት በመሰላቸት።
‹‹አልሄድም…ህጻን አትሁኚ…››
‹‹ማነው ህጻኑ? እኔ? ማትሄድ ከሆነ እውነቱን ንገረኝ›…እኔ የምጠረጥረው፣ የማውቀው ነገር አለ። ከፈራህ ይሄው ልጀምርልህ….ምእራፍዬ…በል››
‹‹ምን? ምንድነው ምጠረጥሪው?››
‹‹ዝም ብለህ የምልህን በል….››
‹‹ሆሆ…ምን ሆነሻል?››
‹‹ምእራፍዬ በል››
ፊቱ ላይ የንዴት ሳቅ ተስሎ ዝም ብሎ አየኝ።
‹‹በላ››
‹‹ምን?››
‹‹የምልህን ድገም….››
‹‹በናትሽ….››
‹‹አለዛ ሂድ….››
‹‹ወይ ጉድ….ምን አይነት ጨዋታ ነው? እሺ….ምን ልበል?..››
‹‹ምእራፍዬ….››
‹‹ምእራፍዬ…..››
‹‹እኔ ከኤፊ ጋር እንድሆኚ የማልፈልገው….››

ዝም አለ።
‹‹ኬቢ…ድገምልኝ….እኔ ከኤፊ ጋር እንድትሆኚ የማልፈልገው በል››
እያቅማማ ‹‹እኔ…ከኤፊ ጋር እንድትሆኚ የማልፈልገው›› አለ
የሚቀጥለውን አረፍተ ነገር ከአፌ አውጥቼ ድገመው ከማስባሌ በፊት በረጅሙ ተነፈስኩ። በጥልቀት አየሁት። ነገሮች ሊቀየሩ ነው። ሕይወቴ ሊቀየር ነው። በአዲስ የፍቅር ፀሃይ ፀዳል ልደምቅ ነው።

አይኔን ጨፍኜ ታላቁን አረፍተነገር ከአፌ አወጣሁ።

‹‹ራሴ ስለማፈቅርሽ ነው….››

አይኖቼ እንደተጨፈኑ ይሄ ሕይወቴን የሚቀይር አረፍተነገር በምወደው ልጅ አንደበት እስኪወጣ ድረስ ልቤ አታሞ እየመታች፣ መላ ሰውነቴ ውሃም እሳትም እየሆነ ጠበቅኩ።
ሰከንዶች አልፈዋል።

ፍፁም ፀጥታ።

አይኖቼን ከፈትኩ።

ፍጹም በድንጋጤ እና በሃዘን የደረቀ የኬብ ፊት ጠበቀኝ። ይሄን ፊቱን አላውቀውም።

ሁሉ ነገር እንዳበቃለት፣ አይሳሳቱት አይነት ስህተት መሳሳቴ ገባኝ።

ስንት ደቂቃ በሚጎረብጥ ዝምታ እንዳሳለፍን አላውቅም ግን መጀመሪያ የተናገረው እሱ ነበር።

‹‹እህህህህም…ምእራፍዬ…ኤፍሬም ካንቺ ጋር ከጀመረ በኋላ…ከአንድ ሁለት ሴቶች ጋር ሲቃበጥ ስላየሁት ነው….ማለቴ….እኔው ራሴ ገፋፍቼ …አስግድጄ ከእሱ ጋር አድርጌሽ እንዲህ አይነት ነገር ሲሰራሸ ፀፀት ተሰምቶኝ ነው›› አለ።

ሰምቼዋለሁ ግን መልስ የመስጠት ፍላጎትም አቅምም አልነበረኝም።
በኤፍሬም ብልግና ልቤ ተሰብሮ አይደለም። እንኳን ከአንድ ሁለት ከሃያ ሁለት ሴት ጋር ሲዳራ ቢውልና ቢያድር ግድ የለኝም።ምክንያቱም ልብ የሚሰበረው ልብን በሰጡት ሰው ብቻ ነው። ብዙ ስብራት የሚመጣው አብዝተው በሚያፈቅሩት ሰው ነው። እንደ ኤፍሬም አይነቱማ አልፎ ሂያጅ ነው። እኔ በኤፍሬም እንደተጠቀምኩበት ቢጠቀምብኝም ምን ይገርማል? እኔ ኬቢን በሚመኝ አፌ በሽንገላ ከሳምኩት እሱ ደግሞ በዚያው አፉ ቢዋሸኝ ፍትህ ተዛብቷል? አይመስለኝም

እምባ ባዘሉ አይኖቼ አየዋለሁ።
‹‹ምእራፍዬ…አንቺ እኮ ለእኔ….ከእህትም በላይ ነሽ…..የምወዳት እህቴ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሲያደርግ ዝም ማለት አልቻልኩም…ማለት….››

የምወዳት እህቴ። እህህህ።
ሳላስበው አቋረጥኩት።
‹‹በፊት…በፊት ለእኔ እንዲዚህ አይነት ስሜት እንደማይሰማህ አውቅ ነበር…ከኤፊ ጋር ከሆንን ጊዜ ጀምሮ ግን የቀናህ መስሎኝ ነበር….ማለት…ልክ እንደኔ ….ሳታውቀው የምታፈቅረኝ……››

የዝምታ ተራው የእሱ ሆነ። በሃዘን ያየኛል።

ቀጠልኩ።

‹‹ግን እንደዛ አስበኸኝ አታውቅም አይደል…ይሄን ሁሉ አመት አንዲትም ጊዜ?›› አልኩት።

መልሱን ማወቅ የማልፈልገውን ጥያቄ ለምን ጠየቅኩ? ወሽመጤ ተቆርጦ እንዲቆርጥልኝ? ላያዳግም ፍቅሩ እንዲወጣልኝ?
አቀረቀረና ፣ ሳግ በሚመስል በታፈነ ድምጹ
‹‹እኔ..እኔ እንደ እህቴ ነው ማይሽ….በዚያ ላይ ደግሞ….››አለኝ።:
በዚያ ላይ ደግሞ ነው ያለው?
‹‹በዚያ ላይ ደግሞ ምን?› አልኩት
‹‹ሳምሪን…ሳምሪን እንደምወዳት የምታውቂ መስሎኝ…..›› እንዳቀረቀረ።
አረ ተው ኬቢ። የሞተ ሰው ይደበደባል? የደከመን ገድሎ ፉከራው ምንድነው አለች ያቺ ጂጂ። ቀን ቢጥለኝ በወደቅኩበት በካልቾ ያጣድፈኝ?

ሳምሪን አውቃታለሁ። የእኔና ኬቢ የማስተርስ ክላስ ውስጥ ናት። እንኳን እንደሚወዳት በስርአቱ አይቷት እንደሚያውቅ እንኳን አላውቅም። እኔ የማውቀው ቆንጆ ሴት እንደሚወድ ነበር። እኔ የማውቀው ሸንቃጣ ሴት እንደምታቅበጠብጠው ነው። ቁንጅና ስለማይጎድለኝ ምንም ያህል ጊዜ ይፍጅ አንድ ቀን አይኑ ውስጥ እንደምገባ አስብ ነበር።ልክ እንደሚወደው ሸንቃጣ ለመሆን ገመድም እራትም እዘል ነበር። ምስኪን ምእራፍ።

ሳምሪን አሰብኳት። ያቺ ሁለመናዋ ከስብ የተሰራ የስብ ክምር…የሰው ጮማ። ከእኔ በምን በልጣ የማፈቅረው ልጅ ልብ ገባች? እንዴት መግቢያ ፈተናውን አልፋ ራሷን በልቡ ከንቲባነት አወጀች?

ቀና ብዬ ላየው አልቻልኩም።
የሃፍረቴ መጠን በኪሎ ቢመዘን አራት ግብዲያ የጭነት መርከቦች ችለው አይጭኑትም።
እዚያው ከተቀመጥንበት ሳያየኝ መ…….ጭ ብዬ ወደ ማርስ መሄድ ተመኘሁ። በቅርብ ጊዜ ሳይንቲስቶች ሰው በደንበኛው ሊኖርበት ይችላል ሲሉ ሰምቻለሁ። ግን ሚሊዮን ሰው ቢኖርበት ምን ዋጋ አለው። ኬቢ አይኖርም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...