Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አምስት)

«እኔ ደስ የሚለኝ ጓደኛሞች ብንሆን ነው።» አልኩት እቤቱ ይዞኝ የሄደ ቀን
«እረፊ! እኔ አንዴ ልብስሽን አውልቄ ጭንቅላቴ ውስጥ ስዬሻለሁ። ጓደኛሞች እንሁን ብልሽ ውሸቴን ነው። ገና ሳይሽ የቀሚስሽን ሶስት ትንንሽዬ ቁልፎች ፣ ቀጥሎ ዚፑን …….. ወደታች ባወልቀው ወይ ወደላይ የቱ ይፈጥናል? አስቤ ጨርሻለሁ!» የገረመኝ ክፍት አፍነቱ አይደለም። እሱን እየለመድኩት ማፈር ትቻለሁ፣ በዛ ላይ ሌላ ሰው ሲያወራው የሚያሳፍረኝን ነገር እሱ ሲያወራው አለው የሆነ ልከኛ ወሬ የሚያስመስለው ድምፀት። በትክክል ቀሚሴ ከጀርባው የዚፑ መጨረሻ ማጅራቴ ጋር ትንንሽዬ ሶስት ቁልፎች መኖራቸው ነው። ከላይ ደርቤ የነበረውን ኮት ካወለቅኩት 5 ደቂቃ አይልፍም ነበር። ገርሞኝ አፍጥጬ ሳየው። <ነግሬሻለሁኮ> አይነት ፊቱን እና ትከሻውን ሰበቀ።

ቤቱ <እንደማንኛውም ፊልሞች ላይ እንደምናያቸው የሀብታም ፎቆች> ከሚባሉት በይዘትም በስፋትም በጥራትም በሶስት ክፍል ቤት እናትና አባቴን ጨምሮ ለስምንት ላደግኩት እኔ (በዝህችም ጥበቷ ክረምት ላይ የአክስት ልጅ ፣የአጎት ልጅ ፣ የክርስትና ልጅ ፣ የአበልጅ ………… የልጅ ብዛት ቤቷን እንደጉንዳን ይወራታል።) አፌን ከፍቼ የምፈዝበት አይነት ነው። አልተገረምኩም። እንደዛ ዓይነት ቤት እንዳለው ነግሮኛል። የገረመኝ እሱም ያልነገረኝ ሁለት የቤቱ ክፍሎች ናቸው። አንደኛው የአንድ ትልቅ ትምህርት ቤት ላይብረሪ የሚያክለው ሰፊው የቤቱ ውስጥ ላይብረሪ ነው። መሃከሉ ላይ ሰፋ ያለ ኮምፒውተሮችን የተሸከመ ጠረጴዛ በአራት ምቹ ወንበሮች ተከቦ ተንጣሏል። አትርገጡኝ የሚለውን የመሬቱን ምንጣፍ ጫማውን አውልቆ ሲገባ አውልቄ ተከተልኩት። የሆነ የተቀደሰ ቦታ የሚገባ ነው የሚመስለው። ከምን ጀምሬ የቱን እንደምነካ ግራ ገባኝ። በቋንቋ ፣ በይዘት፣ በፀሃፊው ስም ……… በስርዓት ተደራጅተው ነው የተቀመጡት። እስካሁን ያላየሁበትን መጀነን ፊቱ ላይ አገኘሁት።

«ምን ያህሉን አንብበሃቸዋል?»
«ቢያንስ 35%! አማርኛዎቹ በቁጥር ነው የቀሩኝ።» አማርኛዎቹጋ ሄጄ ያነበብኳቸውን ለመቁጠር ሞከርኩ። ያው እንደማንኛውም ማንበብ እንደሚችል ኢትዮጵያዊ <ፍቅር እስከመቃብር> እና <ዴርቶጋዳ> ን ሁለት ብዬ ከሀምሳ የማይበልጡ መፅሃፍትን በዓይኔ ቆጠርኩ። እንግሊዘኛውን ያው ተውኩት።
ሌላኛው ክፍል የወንበሩ ቁጥር ከማነሱ ውጪ በሲኒማ ቤት ቅርፅ የተሰራው ፊልም ማሳያ ክፍል ነው።
«ዶክመንተሪ ፊልሞች እወዳለሁ። ማየት ከፈለግሽ መርጬ ልጋብዝሽ?»

«በኢቲቪ ከታዩት <የጀግናው ሰራዊታችን ፍዳ ዶክመንተሪ፣ የታላቁ ኢህአዲግ ወደር የለሽ ትዕግስት፣ ህገመንግስቱን ለመናድ የታጠቁት ሀይሎች ሴራ …..> ምናምን ከሚሉት ውጪ ዶክመንተሪ ማየቴንም እንጃ። ወይም አይቼ ሊሆን ይችላል። ዶክመንተሪ ይሁን ዶክመንቴሽን ወይም ጥናታዊ ፅሁፍ ልዩነታቸው ምን እንደሆነ ስለማላውቅ እኔእንጃ!» ፈገግ ብቻ ነው ያለው። ብዙ ሰዎች እነሱ በብዙ የሚያውቁትን ነገር የማያውቅ ሰው አለማወቁን ሲነግራቸው የሚስቁትን <ከእኔ በላይ ላሳር> ዓይነት ሳቅ አልሳቀም። በአንደኛው ጥግ ለዓይን እሩቅ ሆነው ከኔ ቁመት በጣም በላይ ከተቆለሉት የሸክላ ሲዲዎች ውስጥ አንዱን እያነሳ
«ከቆዩት ውስጥ ልጋብዝሽ! » ብሎ «night and fog» የሚለውን መረጠ። ማጫወቻው ላይ አድርጎ ሲዲውን የምትጫነዋን ቀጭን አናቷ ድርብ ብረት ሲዲው ላይ ለቆት መብራቱን አጠፋፍቶ እጄን ይዞኝ ከፊት ለፊት ካሉት ወንበሮች መደዳ አስቀመጠኝ። በሹክሹክታ
«የሚጠጣ ምን ትፈልጊያለሽ? መብላት የምትፈልጊውስ ነገር?»
«ፈንድሻ ቢኖር፣ ከዛ ደግሞ ኮካ!» ያልኩት ለጨዋታ ነበር። በስልኩ መልእክት ላከ። አስር ደቂቃ ሳይሆን ቅድም ጓዳ ያየኋት ሴት ያዘዝኩትን ይዛ መጣች።
** ** **

የዛን እለት ………. መጀመሪያ ያየሁት እለት ……… ጤንነት እንደጎደለው ሰው ያየኝ ቀን ላግባሽ ያለኝ እለት…….. እንደእኔ ሀሳብ ጥዬው በሄድኩ፣ እንደእኔ እምነት <ልክ ካልሆነ ሰው> ጋር ተጨማሪ ደቂቃ ባላባከንኩ ፣ እንደእኔ ልምድ ከአፉ የሚወጡት ቃላት አርባ ክንድ ከእርሱ ባራቁኝ ፣ እንደ እኔ አስተዳደግ ይሄ ሰው የብዙ የህይወት መርሆቼ ፉርሸት ነበር። ተጎለትኩ አላልኳችሁም? ለሰዓታት ስለተለያዩ የማህበረሰባችን ምሰሶ አስተሳሰቦች እና እምነቶች ስናነሳ እና ስንጥል ለሰዓታት ተጎለትኩ።

«አልተሳሳትኩም አየሽ! መልክ ብቻ አይደለሽም ታስቢያለሽ!» አለኝ በመሃል
«ደሞ ይሄ ምን ማለት ነው?»
«ቆንጆ ሴት ሳይ ከራሴ ጋር አስይዛለሁ። እወራረዳለሁ። ይህችኛዋ መልክ ብቻ ናት፣ ይህችኛዋ ግድ የለህም ከመልኳ ጀርባ አሪፍ ጭንቅላት አለ፣ ውይይይ ይቺኛዋ ደግሞ የራሷ ሀሳብ የላትም የሰዎችን ጭንቅላት ተውሳ ነው የምታስበው ……… ዓይነት ውርርድ! አንዳንዱ እምነትሽን ብትጠይቂ የሚናድብሽ ስለሚመስልሽ በፍርሃት ያለምክንያታዊነት ሙጭጭ ከማለትሽ ውጪ ታሰላስያለሽ!»
«የሴት ቁንጅና ላንተ በምንድነው የሚለካው?»
«ቁንጅናውን ለምንድነው የምፈልገው? የሚለው ነዋ የሚወስነው? የውስጥ ውበት ምናምን ብዬ እንድዋሽሽ አትጠብቂ! የፊዚካል ውበት አድናቂ ነኝ። አልጋ ላይ ይዣት ለመውደቅ ከምጣደፍባት ሴት ሀሳቧ መንፈሷ አይነት ዝባዝንኬ ትዝ አይለኝም። ችግሩ ከተኛኋት በኋላ የማወራው ስለሚጠፋኝ ቶሎ እንድትለየኝ እፈልጋለሁ። ምናልባት ግን በሌላ ጊዜም ላገኛት እፈልግ ይሆናል። ከወዳጄ ጋር ተማክረን (ወዳጄ ያለው ታች ቤቱን መሆኑን ለማሳየት በእጁ ወደታች ጠቆመኝ) እሷ ትሻለናለች ተባብለን ላገኛት እችላለሁ። የምታሰላስል፣ የምትጠይቅ ሴት ግን ደስ ትለኛለች። ከእራት እስከአልጋ ሳትሰለቸኝ ጊዜ ሰጣታለሁ። አብሮ እስከመኖርም አይከፋኝም። »
የሆነ ……… እየጠሉ የሚወዱት፣ እየፈሩ የሚደፍሩት፣ እንደሚፋጅ እያወቁ የሚሞክሩት ፣ መሸሽ እየፈለጉ የሚቀርቡት ፣ እየረገሙ የሚመርቁት ፣ በአንዴ ልክም ስህተትም የሚሆን ፣ ሲኦልም ገነትም ዓይነት ስሜት ያለው፣ ህመምም እርካታም ዓይነት ስሜት ያለው ……… በቃ በየትኛውም ጎራ የማያቅፉት አይነት ሰው ነበር። የዛን ቀን እቤቴ ከሸኘኝ በኋላ
«ደውዪልኝ!» ብሎ ስልኩን ሰጥቶኝ ሄደ። እኔው ራሴ ያላወቅኩት እብደት ውስጤ መኖሩን ያወቅኩት <ላግባሽ> ያለኝን ደግሜ ከነአመክንዮዎቹ ሳስብ ራሴን ሳገኘው ነው። የሆነ ቀን <ለምንድነው የምደውልለት?> የሚለውን ሳላስብበት ደወልኩለት። ስልኩን እንዳነሳ እኔ መሆኔን ሲያውቅ
« ከሰው ጋር ነኝ በኃላ ልደውልልሽ?» አለኝ። በስልኩ ውስጥ በሹክሹክታ የምታወራ ሴት ድምፅ ሰማሁ።
«እሺ ይቅርታ!» ብዬው ስልኩን ዘጋሁት። ከዛ በራሴ ተናደድኩ። መደወል አልነበረብኝም!! የሆነ ክብሬን ዝቅ ያደረግኩ አይነት ስሜት ተሰማኝ። <ምን አስቤ ነው የደወልኩለት?> ራሴን በወቀሳ ስቀጣ ቆይቼ ከሰዓታት በኋላ ደወለ።
«ከሰው ጋር ነበርኩ።» አለኝ ስልኩን እንዳነሳው
«አወቅኩኝ።» አልኩኝ
«ደብሮሽ ባልሆነ?» ብሎ ድክም ብሎ ሳቀ። ጭራሽ ደበረኝ። ዝም አልኩ። «ኦህህህ አግቢኝ ያልኩሽን አስበሽበታል ማለት ነው። (በእርግጠኛነት ነው የሚያወራው) አሰብሽው እንጂኮ ታዲያ ለእኔ አልነገርሽኝም። ከማንም ጋር ብሆን በእኔ የመናደድ መብት የለሽም» ወሬ ውስጥ ሳቅ ይሰማል? እንደሱ ነው የሰማሁት። «ነገ እራት ልጋብዝሽ?» አለ
«ነገ? » ብዬ ላለመሄድ የምሰጠውን ሰበብ ሳስብ ሳቁ አቋረጠኝ
«እሺ ቅድም ምን ልትዪኝ ነበር የደወልሽው?»
«እኔ እንጃ? ላዋራህ? እኔ እንጃ ለምን እንደደወልኩ!» አሁንም ሳቅ ባጀበው የወሬ ለዛው።
«ነገ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ መጥቼ ፒክ አደርግሻለሁ። እሺ ካልሽ ማለት ነው! ከሴት ጋር ነበርኩ። አብሬያት ሆኜ ሌላ ሴት ላላወራ ቃል ገብቼላታለሁ። ቃሌን ደግሞ የምጠብቅ ሰው ነኝ።»
«አሁን እኔን ስታወራ ቃልህን እያፈረስክ አይደለም?»
«አይደለም! ፊዚካሊ አብረን ስንሆን ነው ውላችን …… ይቅርብሽ ዲቴሉ አትወጂውም። አይጠቅምሽምም! ካንቺምጋ ብሆን ለሚኖሩን ህጎች ቃሌን እጠብቃለሁ። የማልጠብቀውን ቃል አልገባልሽም። እራት እንብላ?»
«እሺ» አልኩት። ምንም አስቤ አይደለም። እራት ከእርሱ ጋር ለመብላት ካለመፈለጌ መፈለጌ ስላየለ ብቻ እሺ አልኩት።
ድጋሚ <ላግባሽ> የሚለውን ነገር ለተወሰኑ ቀናት አላነሳቸውም። በትዳር ዙሪያ ያሉንን ሀሳቦች ግን ማውራት አላቆምንም። ለምሳሌ የሆነኛው ቀን
«ቆይ ሁለት ሰዎች ተጋብተው ወይም ሳይጋቡ ለመኖር ዋነኛው መስፈርት ምንድነው?»
«ፍቅር ዋነኛው ነው። ነገር ግን ፍቅርን የሚያጠነክሩት ……… መከባበር፣ አንዱ የአንዱን ስሜትና ሃሳብ ለመረዳት የሚሄድበት ርቀት፣ መደጋገፍ ……. ብዙ ነገሮች አሉ።»
ፍቅር የሚባል ነገር ስላለመኖሩ ረዥም ማብራሪያ ከሰጠኝ በኋላ
«ይሁንልሽ ፍቅር የምትዪው ስሜት አለ እንበል እና መገለጫው ምንድነው? ሚስተር አፍቃሪ እንዳፈቀረሽ በምን ታውቂያለሽ? አበባ ይዞልሽ የሚመጣ? በ24 ሰዓት 26 ጊዜ የሚደውል? ስለፍቅሩ ስድስት ልብ ወለድ መፅሃፍ የሚወጣው ዲስኩር የሚዘበዝብ? የሚያቅፍሽ? የሚስምሽ? ራቁትሽን ስትሆኚ የማታፍሪው? በየሰርግ ውልደት ግብዣ ላይ ይዞሽ በኩራት የሚዞር? ምን አለ ከዚህ ሌላ? ከዚህ የተለየ የፍቅር ማሳያ ነው የምትዪው ካለ እ?»
ለደቂቃዎች የእውነት ከነዚህ በተጨማሪ አንድ ሰው ፍቅሩን የሚገልፅበት ነገር ያለ እንደሆነ አሰብኩ። ከአፌ የወጣው ግን ሌላ ጥያቄ ነበር።
«አንተ ግን በ42 ዓመት ዘመንህ ፍቅር ይዞህ ያውቃል? ወይም እሺ እንዴት ላስቀምጠው? የጓደኝነት ስሜት መጠቃቀም ሲደመር የወሲብ ስሜት መጠቃቀም ሲደመር ወይ ሳይደመር የቁስ መጠቃቀም ያልከውን የተቃራኒ ፆታ ትስስር ዓይነት ኖሮህ ያውቃል?»
ፊቱ ድንገት እንደመዳመን ዓይነት ሆነ ። «ማናት? መቼ? እንዴት ? ለምን የሚል ጥያቄ አስከትለሽ እንዳትጠይቂኝ። አዎ ኖሮኝ ያውቃል።» አለኝ በደፈናው። ለማውራት አፌን ሳሟሽ «እስከመቼውም የማልነግርሽ ድሮ አለኝ። አትልፊ። ማውራት አልፈልግም!»
የማይተነበይ አይነት ሰው ነው። ሲያወራ ካለመሰልቸቱ እና በእውቀት ላይ ከተመሰረቱት ምክንያታዊ ጨዋታዎቹ በተጨማሪ መኪና አቁሞ ዝናብ ላይ ቆሞ አፉን ከፍቶ ዝናብ እየተደበደበ የዝናብ ጠብታ የሚጠጣ ንቅል ነው። ልክ እንደልከኛ ነገር «ይህቺ ሁለተኛ ሚስቴ ነበረች።» ብሎ እራት እየበላን በአጠገባችን ከሌላ ወንድ ጋር እራት ለመብላት የምትገባን ሴት የሚያስተዋውቀኝ ልክ ያልሆነ ሰው ነው። <እገሌ የፃፈው ገፀባህሪ በፍፁም እንዲህ ሊያደርግ አይችልም። ደራሲው ገፀባህሪውን በደንብ አልተረዳውም።> ብሎ የሚሟገት ንክ ነው። ባጠቃላይ በእኔ ዓለም፣ በእኔ እምነት ፣ በእኔ ባህል፣ በእኔ ልምድ ፣ በእኔ አስተዳደግ አይደለም ባል ብለው ሊመርጡት ለአንድ ቀን እንግዳ አድርገው ሊመርጡት ጤንነቱ የሚያጠራጥር ዓይነት ሰውኮ ነው። እንደሚፋጅ እያወቅኩ ካልነካሁት ብዬ የነካሁት እሳት
«ቤቴን ላሳይሽ?» ሲለኝ እንቢ ለማለት ወይም ለመሽኮርመም ሀሳቡም አልመጣልኝም። ወደእርሱ ዓለም እየተሳብኩ እንደሆነ ያኔ ገባኝ። እሱ ሲያደርገው ወይም ሲያወራው እብደት ወይም ብልግና ሲመስለኝ የነበረው ነገር እኔ ውስጥም ያለ ግን ልኖረው ያልደፈርኩት ልክነት መሆኑ የገባኝ ዶክመንተሪ ፊልሙን አይተን ከጨረስን በኋላ መብራቱን ሲያበራው ሞቆት ይሁን እኔን መፈታተን ፈልጎ የለበሰውን ሸሚዝ አውልቆ ከላይ ፈርጣማ ሰውነቱን ሳየው ልነካው መመኘቴን መደበቅ አቅቶት ሳላዘው እጄ ሲዘረጋ ነው………

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ስድስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...