Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አራት)

ለመጀመሪያ ጊዜ በተያየን በአስረኛው ደቂቃ ነው <ላግባሽ> ያለኝ። የሶስተኛ ታናሼን ሰርግ ልታደም አንደኛው የከተማችን ሆቴል ነበርኩ። የምሳ ቡፌ ከተነሳ በኋላ ማንም ሳያየኝ ከአዳራሹ ውልቅ ብዬ እዛው ህንፃ ላይ ያለ ሬስቶራንት ውስጥ ገባሁ። ቢያድለኝኮ የአክስቶቼን ውግምት የሆነ ዓይን መሸሼ ነበር። ገና ወንበር ስቤ ከመቀመጤ ከየት መጣች ሳልላት አንዷ አክስቴ
«ምነውሳ ያን ከመሰለ ፌሽታ ተነጥለሽ እዚህ ብቻሽን?»
«ቡና መጠጣት ፈልጌ ነው! አንቺስ?»
«እኔማ ስልክ ላወራ ወጥቼ ስትዘልቂ አይቼሽ ነው። በይ እኔ ልመለስ እናቴ!» ብላ ፊቷን አዙራ ስትሄድ በግልግል ልተነፍስ የጀመርኩትን ትንፋሽ መለስ ብላ ስቅታ አደረገችብኝ። «እንግዲህ ሚጡዬ ታናናሾችሽን ሁሉ ድረን ጨረስን። ለሴት ልጅኮ ተፈጥሮም ገደብ ይጥላል! እንደው ምርጫው ይቅርብሽና ከአንዱ ሰብሰብ በይ ለእናትሽ ስትዪ……….ላንቺምኮ ዓለም ነው» (የሆነ ያዘነችልን ታስመስለዋለች። <ላንቺ ብዬ ነው> የሚሏት ዓይነት ቅብ)
«የሚመረጥ አምጥታችሁ ያማረጣችሁኝኮ ነው የምትመስሉት በእርግጠኝነት ስታወሩ። ካላገባሽ እያልሽ በገባች በወጣች ቁጥር በነገር ስትነድፊያት ልጅሽ መጨረሻዋ የሆነው አምስት ማቲ ታቅፋ ተመልሳ ያንቺ ጉያ መታከክ አይደል? ድንቄም ዓለም! ይሄንን ነው ዓለም የምትሉኝ?» ከጀርባዬ ፍቅፍቅ ብሎ የሚስቅ ሰው ድምፅ ስሰማ ነው ሬስቶራንቱ ውስጥ ያለው ገሚሱ ተጠቃሚ ሊሰማኝ በሚችል ድምፅ እየጮህኩ እንደሆነ የታወቀኝ። እሱ ነበር!
ለወትሮ ምንም ቢሉ መልስ አልነበረኝም። ምክር፣ ወቀሳ፣ ሽርደዳ ……… <እፈልግሻለሁ> ብለው እቤታቸው ጠርተውኝ ሁላ ሲግቱኝ ዝም ነበር መልሴ። <ለትልቅ ሰው መልስ አይሰጥም> ፣ <ቢሰድቡሽም ፣ ቢገርፉሽም፣ ጭንቅላትሽ ውስጥ ተደፍድፎ ቀስ በቀስ የሚሸርፍሽን መርዝ በቃላት ቢያቀብሉሽም አዋቂዎች ላንቺ ብለው ነው…….> ተብዬ ነዋ ያደግኩት። ለአክስቴ ሌላ የምትለጥፍልኝ ስም ሰጠኋት። ደንግጣ የጎስት በመሰለ ሽውታ ሽውውው ብላ ወጣች። ሳቁን ሳያቋርጥ አጠገቤ ያለውን ወንበር ስቦ ተቀመጠ።
«ሚጡ ብለውሽ ደግሞ ካላገባሽ ሄዶላቸው ነው?»
«ሁሉንም እየሰማህ ነበር ማለት ነው?»
«እንደዛ ነገር። ሴትየዋንኮ ቆሌዋን ነው ያበነንሽባት። ለሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት በህልሟ ሁሉ ነው የምትመጪባት። እና አንቺ ያላገባሽው ሴትየዋ እንዳሉት ስታማርጪ ነው? ለትዳር ያለሽ ምልከታ ስለሚለይ ነው? ማግባት ስለማትፈልጊ ነው?»
«ዝም ብሎ ትዳር ውስጥ ይገባል እንዴ? በእርግጠኝነት አምነህ ህይወትህን የምታጋራው ሰው በህይወትህ ካልተከሰተ እድሜ ስለሄደ፣ ታናናሾቼ ስላገቡ፣ ቆማ ቀረች ላለመባል …….. ያገኘሁትን አፍሼ አገባለሁ? ቆይ ትክክለኛው ሰው ካልተገኘ ሳያገቡምኮ መኖር ይቻላል። » የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ስጨርስ ለማላውቀው ሰውዬ ማወቅ የሌለበትን እየዘበዘብኩ እንደሆነ ገብቶኛል።

«ሳያገቡ መኖር ይቻላል!! የቻሉ ሴቶችም ይኖራሉ። አንቺ ትችያለሽ ወይ ነው ጥያቄው? መቻልና አማራጭ በማጣት ሁኔታን መቀበል የተለያየ ነገር ነው። ትዳርን ልመሰርት የምመኘው ትክክለኛ ሰው በህይወቴ ካልተከሰተ ትዳር እንዲኖረኝ አልፈልግም የሚል አቋም ኖሮሽ ሳታገቢ ስትኖሪ በውሳኔሽ ደስተኛ ነው የምትሆኚው። ባልየው ቢመጣ ደስ ይልሻል ቢቀርም ግን በውሳኔሽ አትፀፀቺም።< ያ የባለፈው ሰውዬ እኮ ትንሽም ቢሆን ይጠጋጋ ነበር ምንአለ እሱን ባገባሁት?> አትዪም። እንደቅድሟ ዓይነት ሴትዮ መጥተው ሲወርፉሽ እንደቅድሙ አትጨሺም። የቤተሰብ ወይ የማህበረሰብ expectation ግድ አይሰጥሽም። ምርጫ አጥተሽ ሲሆን መጀመሪያ ነገር ውሳኔሽን አታምኚውም። ሰርግ ባየሽ ቁጥር የምትቆዝሚ ፣ አዳራሽ ለቀሽ ወጥተሽ ሬስቶራንት ውስጥ የምትደበቂ፣ ደስታ የራቀሽ ሰው ነው የምትሆኚው።»

የተናገረው እውነት ከመሆኑ በላይ ትንተናው ለወሬ የሚጋብዝ ስለነበር አልጎረበጠኝም። ይልቅስ እንደአብሮ አደግ ወዳጃማቾች ጨዋታ መቀባበል ጀመርን።
«እሱ ልክ ነህ ግን ምርጫ ስታጣም ያለህበትን ሁኔታ ተቀብሎ መኖር ሽንፈት አይደለም እንደውም ብርታት ነው። መንነህ ገዳም ካልገባህ ወይም የተለየ ባህልና እምነት ያለው ማህበረሰብ ያለበት ቦታ ካልተሰደድክ በቀር ግን እንዴት ነው <የማንም expectation ግድ አይሰጠኝም> የሚባለው። ልክ የሆነ አካሌ የጎደለ ያህል እኮ ነው ባል የሚባለው ፍጡር ስለጎደለ ከምድር በረከት የጎደልኩ የሚያስመስሉት! በግልፅ <እስኪ ተጠመቂ> ፣ <ለአምላክ የሚሳነው የለም በንፁህ ልብ ፁሚ ፀልዪ> ይሉኛል። ዞር ስትልላቸው <ይህቺን የመሰለች ልጅ ቆማ መቅረቷ ነው ምፅ!! > ይባባሉብሃል።»
«እንዴ ቆይ ግን ምን ያህል ብታረጂ ነው?»
«34»
«ያነሳሽበትን ስንደምረው ገፍተሻል!»
«ባክህ ሳልኖርበትም ቀንሼበትም አያዋጣኝም!»
« ላግባሽ!» ጥያቄ አይደለም። ኮስተር ያለ፣ እርግጠኝነት ያለበት እንደጥቆማ አይነት ነገር……… ልክ የሆነ ባለሙያ <እንዲህ ብታደርግ ይጠቅምሃል!> ብሎ እንደሚሰጠው አይነት ምክር አዘል ጥቆማ!
«ጭራሽ?»
«የእውነቴን ነው! መቼም በ34 ዓመት የሰው ልጅ ተጠንቶ የሚታወቅ ፍጡር አለመሆኑን አልደረስኩበትም አትይኝም እና ሳንጠናና ሳንፈታተን አትዪኝም! አልጋ ላይ እንዴት ነሽ?»
«አንተ? ጤናም የለህ እንዴ?» ከማፈሬ የተነሳ የሰማው ሰው እንዳይኖር ዞር ዞር አልኩኝ። እሱ ምንም ወጣ ያለ ነገር እንዳላወራ ሁላ ቀጠለ።
« ኦህ ለካ ስም አልተለዋወጥንም። አዲስ እባላለሁ ፣ በሚቀጥለው ሳምንት 42 ይሆነኛል። አልጋ ላይ ጎበዝ ነኝ! ከፈለግሽ አሁኑኑ ወጥተን ላሳይሽ እችላለሁ። (ኮስተር ብሎ ነው የሚያወራው እንደልክ) ፣ ስራዬን ማወቅ ከፈለግሽ ዝርዝሩን ወደፊት አስረዳሻለሁ በጠቅላላው ነጋዴ ነኝ። ይሄ ችርቻሮ ነጋዴ ነገር አይደለሁም። ሀብታም ነኝ፣ በቁስ የምትደሰቺ ዓይነት ሰው ከሆንሽ አብረኸኝ ሾፒንግ ውጣ አትበይኝ እንጂ የተዘባነነ ኑሮ አኖርሻለሁ። እ እ እ ምን ቀረ ምን ቀረ? የትምህርት ደረጃዬን ማወቅ ከፈለግሽ ደረጃ የለኝም! ከዘጠኝ ነው የተውኩት……….በተለያየ ምክንያት ከሀገር ስለምወጣ ቋንቋ ተምሬያለሁ። ሁለቴ አግብቼ ነው የፈታሁት። ሀይማኖት የለኝም! ዋና ዋናው ይኼ መሰለኝ። ማወቅ የምትፈልጊውን እነግርሻለሁ።»
የሚያወራው ከልቡ መሆኑን አልተጠራጠርኩም። ጤንነቱን እንጂ። አፌን ከፍቼ ነው በከፊል ድንጋጤ በከፊል ግርምት በብዙ ግራ መጋባት የማየው። ከእኔ መልስ እየጠበቀ መሆኑ ሲገባኝ ሳቄ መጣ
«ምን? እንደስራ ሲቪ ስለራሴ እንድነግርህ አይደለም አይደል እየጠበቅህ ያለኸው?»
«ትዳርን ምን ለየው? እንተዋወቅ እንጠናና የምትሉት ከዚህ የተለየ የሚያሳውቃችሁ ነገር አለ? ያው ሳታገቢ የምትኖሪውን ህይወት ከማራዘም ውጪ! ያውኮ ነው ይሄን ይሄን ያሟላ ብለሽ ልክ እንደ ስራ ቀጣሪ መስፈርት ታስቀምጫለሽ የሚመጣው ሰውዬ መስፈርትሽን ካለፈ ባል ሆኖ ይቀጠራል። ቆይ እስኪ አንቺ አጋሬ ነው ብለሽ እየጠበቅሽው ያለሽው ሰውዬ ምን አይነት ነው?»
«definitely እንዳንተ ዓይነት አይደለም። ጉረኛ፣ ሲያወራ ግልብ፣ ሁለት አግብቶ የፈታ …….. የለበትም!!»
ከት ብሎ እየተንፈራፈረ ሳቀ።
«ቅድም ስላላገባሽ እንደጎደሎ በመቆጠርሽ ይህን ማህበረሰብ ስትወቅጪው ነበር። ራስሽው ግን አግብቶ መፍታትን የሆነ ተላላፊ በሽታ ይመስል ግፍግፍ እያደረገሽ እንደጉድለት አየሽብኝ ሃሃሃሃሃሃ»
«ይሄና ያ ይለያያል። በ42 ዓመት ሁለቴ አግብቶ መፍታት ቀይ መብራት ነው።»
«ልዩነቱ ኩነኔውን ተቀባይ ቦታ መሆንና ኮናኝ ቦታ መቆም ነው። እንቁላል የሰረቀ ሌባ እገሌ በሬ ሰረቀ ቢሉት <እና ለቀቃችሁት?> ይላል። ለራሳችን ይገባናል ብለን የምናምነው ምህረት ለሌላ ሰው ሲሆን ምህረት ለእርሱ በደል ውድ ናት ብለን እናስባለን። አየሽ ልዩነቱ የቆምንበት ቦታ ብቻ ነው።» የእውነት የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። የሆነ ቁስሉ ላይ ጨው የነሰነስኩ መሰለኝ።
«በጣም ይቅርታ ………» ብዬ ከመቀጠሌ በፊት እየተርገፈገፈ ስቆ
«ኸረ እኔ እውነታውን ነው እንጂ የነገርኩሽ ከፍቶኝ አይደለም። ፈልጌ ነው የፈታኋቸው። ስለፈታኋቸውም ደስተኛ ነኝ።» ብሎ የሆነ ልክ የሆነውን ዓለሜን ልክ ባልሆነው ዓለሙ ቀላቀለብኝ። በውስጤ ተነስቼ ደህና ሁን ብዬው መሄድ አስባለሁ ግን ተጎለትኩ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አምስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...