Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሃያ ሁለት)

(የመጨረሻው ክፍል)

«ዶክተር ራሴን ሀኪም ቤት ካገኘሁት አልድንም ይብስብኛል እመነኝ! ትንሽ ቀን አይተኸኝ ከባሰብኝ ቃል እገባልሃለሁ ራሴው ሄዳለሁ» አልኩት። ከህክምና ጣቢያ ህክምናዬን መከታተል እንዳለብኝ ሲነግረኝ
እቤቱ ይዞኝ ሄደ። በዚህ ጊዜ እንዳለፈው ለማላውቀው ጊዜ ያህል ጨለማና ፍርሃቴ ውስጥ አልነከርም!! አስፈሪው ደቂቃ ትንሽ ነው። ያቃተኝ እንቅልፍ ሲወስደኝ የምቃዠውን ቅዠት ነው። የእናቴ ሬሳ ሆኖ ይጀምራል። በእጄ እንደታቀፍኳት ማዕረግ ትሆንብኛለች። ወይም ሚስቴን! በሌላኛው ቀን ደግሞ ልክ የአባቷን ሞት ስትሰማ እጄ ላይ እንደወደቀችው ስትወድቅ እጀምራለሁ። እንደታቀፍኳት ወይ ማዕረግን ወይ እናቴን ትሆንብኛለች። ለቀናት መተኛት ፈራሁ። ዶክተር መድሃኒት አዘዘልኝ። ለሳምንታት እሱጋ ቆየሁ። አሁንም ግን እሱ የሚለውን ፋይል ለመክፈት ዝግጁ አልነበርኩም! እቤቴ ለመመለስ ዝግጁ ስሆን ተመለስኩ። ከተመለስኩ በኃላ የአባቷን ለቅሶ አብሬያት ስላልነበርኩ ታኮርፈለች ብዬ ስጠብቅ ጭራሽ የእኔ ደህንነት አሳስቧት ደህና መሆኔን ትጠይቀኛለች። ትታኝ እንድትሄድ እፈልጋለሁ። ግን ደግሞ ራሷ ጠልታኝ እንድትሄድ እንጂ በእኔ ምክንያት ከሆነችው መሆን ሲደመር ከአባቷ ሀዘን ጋር ሌላ የከባድ ሀዘኗ ሰበብ መሆን አልፈልግም! ያን የማላደርገው ራሴን ላለመጉዳት ይሁን እሷን አላውቅም። ምናልባትም እናቴ እንዳስታቀፈችኝ አይነት ፀፀት ድጋሚ ላለመሸከም ፈርቼም ይሆናል።

ተናግሬ በማላውቃት ለቤተሰቦቿ በምትልከው ገንዘብ ተናገርኳት። የማትደራደርበት ዋልታዋ ስለሆነ ከጠላችኝ በላይ የምትጠላበት ምክንያት ያቀበልኳት ነበር የመሰለኝ። ትጥላኝ ትውደደኝ አላውቅም ግን ትታኝ አልሄደችም። ከሆነ ጊዜ በኋላ ማታ ላይ እራት ልበላ ተቀምጬ ምስቅል እንዳለች ወደሳሎን ገባች። የእናቷን ቤት መወረስ ስትነግረኝ ደነገጥኩ። አላወቅኩም ነበር! ስለእውነት ትኩረት ሰጥቼም ብሩ መከፈል ማቆም አለማቆሙን አላስተዋልኩም! ከእኔ ቃል እና ከእናቷ የእኔን ቃል እንደምታከብር ልገምት አልችልም ነበር። እያለቀሰች ትታኝ ስትገባ ተከትያት መሄድ ፈለግኩ። ለቀናት ሸሸኋት። ይሄ የመጨረሻዋ ይሆናል ብዬ ጥላኝ እንድትሄድ ስጠብቃት የሆነ ቀን ጠዋት ትታኝ እንደማትሄድ ቁርጥ አድርጋ ነገረችኝ። ዓመቱን ጠብቃ ብሯን ተካፍላ እንደምትሄድ ነገረችኝ። ንግግሩም ሀሳቡም የእሷን ስለማይመስል ግራ ገባኝ። ከፈለግክ አንተ ፍታኝ ብላኛለችኮ እንድትሄድ እፈልግ የለ? ለምንድነው በቃ እንፋታ ማለት ያቃተኝ? ለራሴኮ ደጋግሜ እነግረዋለሁ። እሷን አጊንተህ ራስህን ከምታጣ እና እሷን አጥተህ ራስህን ከምታተርፍ የቱ ይበልጥብሃል? ሁለቱንም በራሴ መወሰን አቃተኝ እሷንም ማጣት ፈራሁ ራሴንም ማጣት ፈራሁ። እሷ እንድትወስንልኝ ፈለግኩ። ራሷን ይዛልኝ እንድትሄድ!! ያገባኋትን ቀን ረገምኩ! አብረን ያሳለፍናቸውን ዓመታት ረገምኩ። የሆነ ቀን ያለወትሮዬ እሷን ሳላገባ በፊት አልፎ አልፎ የምሄድበት ባር ሄጄ ስጠጣ ድሮ እንጎዳጎድ የነበረች ኤክስ ተንጎዳጓጄን አገኘኋት። ድንገት የመጣልኝ ሀሳብ ከሷ ጋር ወደቤት መሄድ! ሊፈጠር የሚችለውን አሰላሁ። እንዴት ሴት ይዘህብኝ መጣህ ብላ በተደፈርኩ ትቀውጠዋለች ፣ ምንም ሳይመስላት ታልፋለች ፣ ትቀናለች ፣ ትከሰኛለች ……….. ምንም ሳትል ተነስታ ጥላኝ ትሄዳለች። አንዱ ይሆናል ወይም የቱም አይሆንም ብዬ ሄድኩ። ብቅም አላለችም!! ምንም ዓይነት ከሴት ጋር የመነካካት ፍላጎቱ ስላልነበረኝ ትንሽ እንደተጫወትን ተኛን። በነገታው ከሰዓት ማታ የተፈጠረውን እንዳወቀች የእርሷ ባልሆነ ስርዓት የለሽ ንግግር ነገረችኝ።

እዚህጋ ጥላቻዋ በደንብ ይታይ ነበር። የመከፋት ሳይሆን ከእኔ ከዚህ የተለየ እንደማትጠብቅ ዓይነት ንቀት ያለበት ነበር አነጋገሯ። እንድትጠላኝ አይደል ስፈልግ የነበረው? ደስታ ግን አልተሰማኝም! የዛን ቀን የእረፍቱ ቀን ቢሆንም ዶክተርጋ ደወልኩ። በምልልሳችን መሃል።

«አዲስ! የጥንካሬዬ መሰረት ናቸው የምትላቸውን መርሆችህን ማጣት መጀመርህን እያስተዋልክ ነው? እሷ ከህይወትህ እንድትወጣልህ መፈለግህ አንድ ነገር ነው። ከእርሷ እና ከራሴ ራሴን መረጥኩ አልክ እንጂ እሷንም ራስህንም እያጣህ ነው። ስሜትህን ለመካድ ወይም ለመሸሽ ስትል በጤነኛ ጭንቅላትህ የማታደርጋቸውን ነገሮች እያደረግክ ነው። አልመረጥክም አዲስ!» አለኝ።

ስለእርሷ መሄድ ወይም መቅረት እዚህና እዛ የሚረግጠውን ውል የለሽ ሀሳብ እና ስሜቴን ለማደብዘዝ ስራ እና መፅሃፎቼ ውስጥ አብዝቼ ጠለቅኩ። አብራኝ አትበላም። ላይብረሪም አትመጣም። ከክፍሏ አትወጣም!! አንድ እሁድ ልጆቼ ጋር በሄድኩበት እዛው መጣች። ልጆቼ እሷን ሲያዩ እየተንደረደሩ እናታችን መጣች ብለው ተጠመጠሙባት። በእነርሱ ፊት የተኳረፈ መምሰል ስላልፈለግኩ ጉንጯን ሳምኳት። የሳምኳትን ቦታ በእጇ ዳብሳ ፍዝዝ ብላ ቆመች። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሳምኳት ነገር። ከልጆቹጋ እየተጫወትኩ ትኩረቴን ከሷ ላይ ማንሳት አቃተኝ። ፍዝዝ ብላ እያየችኝ አይኗ እንባ አቀረረ። ደረስ መለስ የሚለው ፍርሃቴ ተመለሰ። ልጆቹን ማጫወት ትቼ እሷን ማባበል አማረኝ። አሁንም ድረስ አልጠላችኝም። ይሄን ሁሉ አድርጌያትም አልጠላችኝም! የዛን ቀን ተጨማሪ በደል ላልበድላት ለራሴ ቃል ገባሁ! መቆየት እስከፈለገች ጊዜ ትቆይ መሄድ በፈለገች ቀን ትሂድ! አልኩ። ራሴን ረገምኩላትኮ! ከአሁን በኋላ ላልከፋባት ራሴን አስጠነቀቅኩላት!! ማታ ላይ ሻይ ልትወስድ ከክፍሏ ስትወጣ ያለቀሱ አይኖቿ አባብጠው ደፈራርሰዋል። ሳሎን መኖሬን ስታይ እንዳላያት ፊቷን ደበቀችብኝ ግን አይቻታለሁ።»

እያነበብኩ አንገቴ ላይ የሚርመሰመስ እጁን አንድ እጄን ልኬ ያዝኩት። የመከልከል ሳይሆን የመደረብ። የሰርጉ ቀን አጋጣሚ ላይ ስደርስ መጮህ ቃጣኝ።

«የረሳሁትን ሳቋን ተፍለቀለቀች። አውርቶ ሳይጨርስ ይግባባሉ። መቼ ነበር እንዲህ ደስተኛ የነበረችው? እሩቅ!! የማላስታውሰው ቀን ላይ ነበር እንዲህ ስትፍለቀለቅ ያየኋት ! ይሄን ሳቋን ቀምቻታለሁ። በአንድ በኩል ራሴን ረግማለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ የተፍለቀለቀችለት ሰው እኔ ብሆን ብዬ አስባለሁ። ሰው እንዴት ሁለት ጠርዝ ላይ ያለ ስሜት እኩል ይሰማዋል? በጣም ስቀርባትም የምትፈጀኝ ስርቃትም የምትፈጀኝ ዓይነት ነገር ናት። መሃል ስሆን ደግሞ እሷን የምጎዳት!! ቀስ ብዬ ወጥቼ ወደቤት ሄድኩ። እቤት ሸኝቷት በሩ ላይ ከመኪናው ስትወርድ አቅፎ ሲሰናበታት አየኋቸው። ፍልቅልቅ ፊቷ አልተለያትም። »

«አንተኮ ቆንጆ ሆነሻል ስላልከኝ ነው እንደዛ ደስ ብሎኝ የነበረው! ለማዕረግ ያልካትን ታስታውሳለህ? ለእኔም የወንድ መለኪያዬ ነበርክኮ አድስዬ! ያንተን ሚዛን ተለካክቶ አይኔን የሚሞላ ማንም አልነበረም! (ለምን ዝም ብለሽ አታነቢም? ዓይነት አየኝ) እሺ ከአሁን በኋላ ዝም ብዬ አነባለሁ!» ብዬው ማንበቤን ቀጠልኩ።

«ውስጤ ያለው ብዙ ስሜት ቢሆንም ጎልቶ የሚሰማኝ ንዴቴ ነው። ማን ላይ እንደተናደድኩ አላውቅም! በትክክል በየትኛው ምክንያት እንደተናደድኩም አላውቅም!! ተነስቼ ወጣሁ። ድብልቅ ያለ አወዛጋቢ ስሜት ናጠኝ። ከሷጋ ለመጨረሻ ጊዜ ከሁለት ዓመት ከምናምን በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ካደረግነው ጉድጉድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነች ሴት ጋር መሆን ፈለግኩ። በትክክል ምን ፈልጌ እቤት እንዲሆን እንደፈለግኩ አላውቅም! አብራኝ ያለችው ሴት የሆነ ነገር ያደረገችኝ ይመስል እንግልት የበዛበት ነገር እያደረግኳት እንደሆነ ገብቶኛል ግን አላቆምም። የወጠረኝ ደም ሲበርድ የምፀፀት ነበር የመሰለኝ። በምትኩ የሆነ መገላገል አይነት ስሜት ተሰማኝ። የሚራወጥ ጭንቅላቴ እርግት እንደማለት።

«ቀንተሃል! ተናደሃል! በራስህ በሽቀሃል! ያን ግን እየተወጣኸው ያለኸው ትክክለኛ ቦታ አይደለም! በፊት እንደምታደርገው በመፅሃፎችህ ወይም በስራህ ራስህን ልትሸውደው ሞክረህ ሀሳብህ አልሰበሰብ ብሎሃል! ያን በወሲብ እየተካኸው ነው! የቀኑን ውጥረትህን ትቀንስበታለህ እንጂ ቋሚ መፍትሄ አይሆንህም! አንተ ራስህን ልትረዳው ካልፈለግክ እኔ ምንም ላደርግ አልችልም አዲስ መፍትሄው አንተጋ ነው!! ። ራስህን በጊዜያዊ እፎይታ ልትሸውደው አትሞክር! ውጥረት በተሰማህ ቁጥር ያን እፎይታ ፍለጋ በወሲብ ልትወጣው ትሞክራለህ! ስትደጋግመው ልክ እንደማንኛውም ድራግ ነው። የሚሰጥህ እፎይታ መጠን እየቀነሰ ይመጣና ዜሮ ይሆናል። ይሄኔ ውጥረቱ ብቻ ሳይሆን አንተ ባልሆነው ማነነትህ ብስጭትህና ፀፀት ይጨመሩበታል። ወይ ሌላ የምትተነፍስበት ሱስ ትፈልጋለህ ወይም ወደምትሸሸው ጨለማህ ትመለሳለህ!!» አለኝ ዶክተር የሆነ ቀን በሀኪም ለዛ ሳይሆን በአባት ቁጣ!!
በትክክል ሂደቱን ጠብቆ የተከሰተው ያ ነው። ደጋገምኩት! በደጋገምኩት ቁጥር እርካታን ሳይሆን የባሰ ጭንቀትን እያስታቀፈኝ መጣ!! እዚህጋ እሷንም ዘነጋኋት ራሴንም እንደዛው። ከወራት በኋላ ዶክተርጋ ሄጄ
«አሁን ዝግጁ ነኝ የሆንኩትን ሆኜ መዳን እፈልጋለሁ።» አልኩት። ደስ ብሎት ትከሻዬን እየመታ ተቀመጠ። ማውራት የጀመርኩኝ ቀን አስመለሰኝ ሁላ! የእናቴን አልፌ የመጀመሪያ የማዕረግ ክህደቷን አልፌ ሶስተኛው ጋር ስደርስ ተሰምቶኝ የነበረውን ዲቴል ማውራት ያቅተኛል። በየቀኑ ከመጀመሪያው እጀምራለሁ። በየቀኑ ትንሽ እየገፋሁ አቆማለሁ። በዚህ መሃል ለስራ ከከተማ ወጥቼ ስመለስ ነው መኪናዬ የተገለበጠው። እያሰብኩ እንደነበር አስታውሳለሁ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም! ከፊቴ የሚመጣ መኪና ጡሩንባውን ሲያስጮኸው ነው እንደመባነን አድርጎኝ መሪዬን ያጠመዘዝኩት።»
«ለእኔኮ ግን እስከመጨረሻው ነገርከኝ አይደል? ያ ማለት?» አልኩት ካለፈው ስቃዩ የመዳን ምክንያት ሆኖት ከሆነ በሚል
«እናያለና!» አለኝ
«እሺ ቆይ በቃ? ከዛ በኋላ ያለውስ?» አልኩት ኮንፒውተሩን እያስቀመጥኩት።
«ከዛ በኋላ ያለውን አንቺ የማታውቂው የለም ራስሽ ትፅፊዋለሽ!» አለኝ በእርግጠኝነት
«እህ! ያንተን ስሜት ግን በትክክል ላሰፍረው አልችልም!»
«come on! ካንቺ በላይ የሚያውቀኝ ሰው የለም። በስሜት ደረጃ ከማንም ጋር መቆራኘት የማልፈልግ ሰው ዊልቸር ላይ ተቀምጬ በአካልም የሰው እርዳታ የምፈልግ ጥገኛ መሆኔ ምን እንዲሰማኝ እንደሚያደርገኝ ካንቺ በላይ የሚረዳ ሰው አለ? »
«የሰውን ድጋፍ ማግኘትኮ ሁሉም ሰው በሆነኛው የህይወቱ ጊዜ የሚገጥመው ነው! አንተ ሰዎችን ትረዳ የለ? ሰዎች ሲረዱህ ውድቀት የሚሆንብህ ለምንድነው?»

«በቃ እኔ ነኛ! (ትከሻውን ምን ላድርግ አይነት እየሰበቀ) በሰው ድጋፍ የምንቀሳቀስ ሰው መሆን ሞቴ ነው! ያን ታውቂያለሽ!! ለዘመናት የለፋሁትኮ በስሜትም በአካልም በገንዘብም ማንንም ያልተደገፍኩ ነፃ ለመሆን ነው» አለኝ የእርሱ ባልሆነ ማባበል ድምፅ! አላውቅም ምን እንዳሰብኩ ማጅራቴ ላይ ያለ እጁን ስቤ ሳምኩት። ሲጠብቀው የነበረ እርምጃ ይመስል አስከትሎ ከንፈሬን ሳመኝ። እየሳመኝ ያወራ ጀመር እንደበፊቱ ወሬው ግን የቀን ውሎአችንን አይነት አይደለም። ጆሮዬን ማመን እስኪያቅተኝ አዲስ በፍቅር ቁልምጫ ስም እየጠራኝ ነው። ደንግጬ ለሰከንድ በርግጌያለሁ ሁላ! ረዥም ሰዓት ከተሳሳምን በኋላ አቁሞ እንደመሳቅ ነገር እያለ
«ንግስቴ እንደምታደርጊኝ ካላደረግሽኝኮ እግሬን አላዘውም!» አለኝ አባባሉ ውስጥ <አየሽ ለዚህ እንኳን ያንቺን እርዳታ መጠየቅ ግድ ሲለኝ?> አይነት የመሰበር ድምፀት አለው። ሶፋው ስላልተመቸን ምንጣፉ ላይ ወርደን ማላብ ጀመርን! ከላይ ሆኜ እያየሁት እሱ በሚጠራኝ የፍቅር ቁልምጫ ሁሉ ልጠራው እፈልጋለሁኮ! ግን ከአፌ አይወጣም! አንዴ ቢለኝ ብዬ አምላኬን የለመንኩትን ቃል አለኝ። «ልትገምቺው ከምትችዪው በላይ እወድሻለሁ!» አለኝ። ስሰማው እፈነጥዛለሁ ብዬ ያሰብኩትን ያህል አላስፈነጠዘኝም! ንግስቴ ፣ ፍቅሬ ፣ ልዕልቴ ……….. ያላለኝ የለውም። ለዓመታት ያላለውን ማካካስ የሚመስል ፍቅር ……. ስንጨርስ አጠገብ ላጠገብ ተኝተን ዝም ተባባልን። ከሴክስ ስሜት ውጪ ያ የተስገበገብኩለት ፍቅር ስጨብጠው ምንም አልመስልሽ አለኝ ብዬ እውነቱን ነው የምነግረው ወይስ እንደዚሁ እንቀጥላለን ? በተጎዳው ላይ ጉዳት መጨመር መሰለኝ! ምናልባት ሽባ ስለሆንኩ ነው የጠላችኝ ይለኛል እያልኩ ሳስብ
«ይሰማኛል ብለሽ ያሰብሽውን ስሜት ውስጥሽ አጣሽው?» አለኝ
«ለምን እንደእሱ አልክ?»
«አውቅሻለሁ እኮ! በደንብ።»
«ታዲያ ካወቅክ?» ብዬ እንዴት መጠየቅ እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ
«ፍቅርሽን ከጨረሽ እንደቆየሽ አውቃለሁ። ከዛ ሁሉ በደል በኋላ ያ ስሜት ሊኖር አይችልም!»
«የበደልከኝንኮ ግን ትቼልሃለሁ!»
«አውቃለሁ! ይቅር ስትዪኝ ላለፍኩት መንገድ አዘንሽልኝ። ፍቅርን እና ሀዘኔታን ነው ያልለየሽው!»
«እሺ ካወቅክ ለምን?»
«ምንም እንዳልቀረብሽ እንድታውቂ!! ከተመኘሽው ምንም እንዳይጎድልብሽ!» አለኝ።
መኝታ ቤታችን ገብተን አቅፌው ተኛሁ። ነጋችንን እንዴት እንደምንኖረው እያሰብኩ እንቅልፍ ወሰደኝ። አይኖቼን ስገልጥ አንዳች ሸክም ከላዬ እንደተነሳ ቅልል ብሎኝ ነበር። አይኖቹን እንደጨፈነ ነው። ተገላብጬ ደረቱ ላይ ተጠግቼ ተኛሁ።
«አዲስዬ ! አዲስዬ!» ልቀሰቅሰው ሞከርኩ «ዛሬ እኔ ስራ ቦታ ደርሼ ልምጣ?» አይመልስልኝም። ቀና ብዬ አየሁት! «አታደርገውም አዲስዬ!!» ራስጌውጋ ያለውን መጠቀም ያቆመውን ያኔ ከባድ ህመም ሲሰማው ይወስድ የነበረውን ከባድ ፔንኪለር እቃ አየሁት!! «አታደርገውም! አዲስ አታደርገውም!» እቃው ባዶ ነው! ተነስቼ ይሰማኝ ይመስል ደረቱን እየደበደብኩ ማልቀስ ጀመርኩ።

መጠርጠር አልነበረብኝም ሲሸነፍልኝ? ያቺን ከዲያቢሎስ ጋር ሲማከር የሚያመጣትን ፈገግታ ፈገግ ካለ በኋላ ድንገት ቅይር ስል መጠርጠር አልነበረብኝም? አውቀው አልነበር ክፉ ሲያስብ? ከምንም ተነስቶ እንደዛ ቅይር እንደማይል እንዴት ጠፋኝ? ይሄን አስቦት ነው ማታ የሆነውን ሁሉ የሆነው! መጠርጠር አልነበረብኝም ፍቅሩን ሲያምንልኝ? መጠርጠር አልነበረብኝም በደሉን ሲያምንልኝ?? እስከሞት ራሴን የምወደው ራሴን ነው ሲለኝ መጠርጠር አልነበረብኝም? ሁሌም አፍቃሪ ሰውነቱ በተገለጠ ማግስት መዘዝ ተከትሎት እንደሚመጣ እንዴት ዘነጋሁት? ከመሸነፍ ሞትን እንደሚመርጥ አውቀው አልነበር? ድምፅ የወጣው ለቅሶ ማልቀስ አቃተኝ። እንባዬ ጉንጬ ላይ እየተንዠቀዠቀ አገላብጬ ሳምኩት። እያለቀስኩ ወደሳሎን ሄጄ ፀሃይን ጎረቤታችንን እንድትጠራ ስነግራት
«ምነው እናቴ? ምን ሆንሽ?» ስትለኝ
«አዲስ አዲስ » ብዬ መጨረስ አቃተኝ።
«በጠዋት ስትነሳ ስጫት ብሎ ይሄን ወረቀት ሰጥቶኝ ነበር ትናንት! ምነው አመመው እንዴ?» አለችኝ ወረቀቱን እያቀበለችኝ።
«እባክሽ ይሄ ከንቱ ሞተ ብለሽ እንባሽን አታባክኚ! ሞት መጥፎ ነገር ነው ያለ ማን ነው? ማን ያውቃል ከህይወት የተሻለስ ቢሆን! በህይወቴ አንድ ቁምነገር ሰርቼ ባልፍ ትይኝ አልነበር? መፃፋችንን ጨርሺው። ልጆቼን አደራ! ስወድሽ ኖሬያለሁ!!»
የሆነ ጊዜ ላይ ስለሞት ያወራኝን አስታወስኩት። ከ80 ዓመት በላይ መኖር አልፈልግም ይለኝ ነበር ሁሌ። ምክንያቱም መዝረክረክ ስለማይፈልግ!

«ሞትን እንደመጥፎ ነገር የምናየውኮ ማንም ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ስለማያውቅ ነው! ሰው ሲሞት በህይወት ያለው ሰው የሚቀርበውን ስለሚያጣ ሞትን ክፉ ነገር አድርጎ ያወራዋል። ለምሳሌ አስቢው በህመም ሲሰቃይ ለነበረ ሰው ሲሞት ማልቀስ ልክ ነው? ሰውየውኮ ስቃይ ላይ ነበር? የምናለቅሰው ሰውየው ስለተገላገለ ነው? ለራሳችን ነው ለሰውየው ነው የምናለቅሰው? ደግሞስ ከሞት በኋላ ያለው ምናልባት ከህይወት የተሻለ ሁላ ቢሆንስ?» ብሎኝ ነበር። ጭራሽ ድምፅ አውጥቼ እያለቀስኩ።

«እሺ ይሁንልህ! የተሻለ ይሁንልህ!» ብዬ በቂጤ መሬቱ ላይ ተዘረፈጥኩ!!

……ጨርሰናል!!!! ………

 

2 Comments

  • afrocanart@gmail.com'
    Sisay commented on May 12, 2022 Reply

    Superb, kudos ሜሪ!!

  • afrocanart@gmail.com'
    Sisay commented on May 12, 2022 Reply

    በወደፊት እና ወደኋላ ያተራረክ ጡዘት ልብን ሰቃይና ስሜትን ሰቅዞ ያዢነቱ ከእስከ ዛሬ ያነበበኳቸው ፅሁፎችሽ ‘የበለጠ ነው’ እንድል አድርጎኛል። ጎበዝ ሜሪ!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...