Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ስምንት)

«ታውቂያለሽ የአዕምሮ ክፍላችን እድገት በ25 ዓመታችን እንደሚያበቃ? ከዛም ውስጥ ከ80% በላዩ የሚያድገው እስከ 5 ዓመት አካባቢ ባለው እድሜያችን ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ ከ25 ዓመቱ በፊት በሚያዳብረው ልምድ ፣እውቀት ፣ ባህል ፣ ሀይማኖት ……. Whatever ነው የሚቀረፀው። ልክ አለመሆኑን ቢያውቅ እንኳን ለመቀየር ብዙ ጥረት እና ጊዜ ይወስድበታል። ከዛ በኋላ ባለን እድሜ ምንም ያህል እውቀት እና ልምድ ብናዳብር እንኳን ሳናውቀው በsubconscious የአዕምሮ ክፍላችን አማካኝነት አስቀድመን ወዳዳበርነው ልምድ እና እውቀታችን ስንሳብ እንገኛለን።» አለኝ። አደጋው ከደረሰበት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የህፃናት ማቆያውን ሊጎበኝ መጥተን ነው። ለህፃናቱን እኔ እየተመላለስኩ መጠየቅ አላቆምኩም ነበር እና አባታቸው አደጋ እንደደረሰበት አስቀድመው ያውቃሉ። ከበውት <እግዜአብሔርን አጊንተኸው ነው የተመለስከው?> ዓይነት የህፃን ጥያቄ ሁሉ ሲጠይቁት ሲመልስላቸው ነው የዋለው።

«እንዳለመታደል ሆኖ አብዛኛው ወላጅ ስታድግ ሁሉንም የምትረሳ ይመስለዋል እንጂ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ልጃቸው ውስጥ ልምድ እና ባህሪ ሆኖ የሚቀር አይመስላቸውም። ድሮ እንዲህ ብላችሁኝ ነበር ስትላቸው። <ቂመኛ ነሽ> ነው የምትባለው። 80%ቱ እስከ 5 ዓመት ነው የሚያድገው ነው ያልከው? ሆ! እስከ 5 ዓመትህማ እንኳን የሚናገሩ የሚያደርጉት ትርጉም ሰጥቶህ የምታስታውሰው ሆ!» አልኩኝ ልጆቹ እየቦረቁ ሲጫወቱ እያየኋቸው
«ምናልባት ድርጊቶቹን ትረሻቸው ይሆናል። ስሜቱ ግን አብሮሽ ያድጋል። ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ደስታ፣ በራስ መተማመን፣ ………. በዙሪያሽ የሚከናወኑ ክንውኖች ያሳደሩብሽ ስሜት እሱ አብሮሽ ያድጋል። »

ከህፃናቱጋ ስንመለስ መኪና ውስጥ «መቼ ነው ታዲያ መውጣት በለመደ እግርህ ማለቴ ዊልቸርህ ወደ ስራ የምትመለሰው?» አልኩት። በዊልቸር ሆኖ ማንም ሰው እንዲያየው አይፈልግም ነበር። የእኔን ቤተሰቦች ጨምሮ ከሀኪሞቹ ውጪ ማንም ሰው እንዲጠይቀውም እንዲያገኘውም አይፈልግም። ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከሀኪም ቤት ውጪ በፍላጎቱ የወጣው።
«ለዛ እንኳን ዝግጁ አይደለሁም!!» አባባሉ በቅርብ ዝግጁ ለመሆንም ሀሳቡ ያለው አይመስልም። «አሁንማ ከሞላ ጎደል የወረቀቱን ስራ አውቀሽዋል። በየቀኑ ቦታዎቹ ላይ መገኘት ነውኮ የቀረሽ!»

«አንድ ወረቀት አንብቦ ለመፈረም አስሬ ጠይቄህ መቶ ጊዜ አንብቤ ምኑን ለመድኩት? ደግነቱ ሰዎችህ ገራሚዎች ናቸው። ታውቃለህኣ በስራህ እንደማከብርህ? ያንተ ጉብዝና አንድ ነገር ነው። ስራውን ቀጥ አድርገው የሚይዙ ብዙ አንተዎች ማፍራት ሌላ ሌቭል ነው።»
«<ውጤታማ የቢዝነስ ሰው እርሱ ቢኖርም ባይኖርም ስራው ሳይጓደል የሚቀጥልበትን የቢዝነስ ተቋም መገንባት የቻለ ነው> ይል ነበር አባቴ። እሱ ነው ብዙውን ያስተማረኝ። ምናልባት ለእኔ ሊተውልኝ ስላሰበ ይመስለኛል የለፋብኝ።»
«ኦኬ! እያልከኝ ያለኸው የሀብትህ ምንጩ የአባትህ ውርስ ነው?»
«ነበር ማለት ይቀላል!! እየፃፍን ብናወራው የሚሻል መሰለኝ። ከመፅሃፉ አንዱ ምዕራፍ አባቴ ነው መሆን ያለበት። (በምናቡ እየሳለ እንደሆነ እያስታወቀበት።) መፅሃፉ 6 ምዕራፍ ይኖረዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ እናቴ ሁለተኛው ምዕራፍ ማዕረግ ሶስተኛው ምዕራፍ አባቴ አራተኛው ምዕራፍ እኔ አምስተኛውም አንቺ ስድስተኛው ምዕራፍም አንቺ ።»

«ኦኦ ! ያንተ ባዮግራፊ ውስጥ እኔ ሁለቴ ምን አደርጋለሁ? የእናትህ እና የማዕረግ ምዕራፍ እስካሁን የመጣንበት ታሪክ ነው። የአባትህንም በሚቀጥለው ምዕራፍ አገኘዋለሁ እሺ! ያልገባኝ ሁሉም ምዕራፍ ውስጥ አንተ አለህ አይደል? ለምን ለብቻው ሌላ ምዕራፍ? እህህ ረስተህ ከሆነ ሁለት ሚስቶች ነበሩህ!»
«ሶስቱ ምዕራፎች አያጠያይቁም። ከሶስቱ በኋላ ነው ያለማንም ሰንሰለት አዲስ ብቻውን አዲስ ሆኖ የቆመው። ያ ነው ትክክለኛው እኔ ብዬ የምለው የህይወት ምዕራፍ! ፀዲ እና ሰብሊ የዚህኛው ምዕራፍ አካሎች ናቸው። ምዕራፍ አምስት ካንቺ ጋር የነበረኝ የህይወት ምዕራፍ ነው። እኔ የምፅፈው። ያንቺ ገፅ ካልገባበት ግን ታሪኩ ይጎድላል። ስድስተኛውን ምዕራፍ የራስሽን ገፅ አንቺ ትፅፊዋለሽ ማለት ነው። ድራፍቱን ከጨረስን በኋላ ባለሙያ እናማክራለን። ግልፅ ሆንኩ አሁን?»

«አዎን! በስሜት ረገድ ከፋፍለው ብትባል በየትኛው ምዕራፍ ነበር ደስተኛ የነበርከው?» አልኩት ምዕራፍ አምስት ቢለኝ እየተመኘሁ
«በአንፃራዊ ምዕራፍ አራት። ግን የሰው ልጅ 100% ደስተኛ ነኝ የሚልበት ምዕራፍ ይኖረዋል? የደስታ የምትያቸው ቅፅበቶች ይኖሩ ይሆናል እንጂ!»
«በህይወት ውስጥ ልንደርስበት የምንሮጥበት ስኬት ሁሉ ግቡ ደስተኛ መሆን አይደል?»
«ይሆናል። ለእኔ ግን ደስተኛ ሆኖ መኖር ከሚለው ይልቅ ትርጉም ያለው ህይወት ኖሮ ማለፍ የሚለው ብልጫ ይይዝብኛል። ከግለሰብ ደስታ አንፃር ካየሽው አንዳንድ ሰው ሆዱ ካልጎደለ፣ አልጋው ከሞቀ ፣ ለአናቱ መጠለያ ካለው ደስተኛ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ሊያሳካው የሚያልመው ህልም ይኖረውና እሱጋ ለመድረስ ሲባዝን ባጅቶ ሲሳካለት ደስተኛ ይሆናል። አንዳንዱ ደግሞ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች መኖርን የደስታው ምንጭ አድርጎ ይኖራል። ሁሉም ባሰመሩት የደስታቸው ሰበብ ደስተኞች ናቸው እና ከደስታ አንፃር ካየነው ሁሉም ተሳክቶላቸዋል። ስኬት ውጤቱ ነው ብዬ አላምንም መንገዱ እንጂ። እንደእኔ ያ መንገድ በደስታም ይሁን በሃዘን በመውደቅም ይሁን በመነሳት ትርጉም ያለው ሲሆን ጠዋት የምትነቂበት ምክንያት ከሰጠሽ ስኬት ነው።»
ባያብራራልኝም ምን ማለቱ እንደሆነ አውቃለሁ። 316 ህፃናት የሚያሳድግ ተቋም መመስረት እና ማስተዳደር (ያውም እንደወለዳቸው ልጆች የሚጠነቀቅላቸው እና የጎደላቸውን የሚከታተላቸው ሰው ሆኖ)፣ ባጠቃላይ ለ7293 ሰራተኞች ደሞዝ የሚከፍሉ ድርጅቶች ባለቤት መሆን( ያውም እያንዳንዱ ሰራተኛ የሚያከብረው እና በመልካምነት የሚያወሳው አለቃ ሆኖ )ትርጉም ያለው ህይወት ኖሮ ማለፍ ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?
እቤት ደርሰን ብዙም ሳንቆይ ሁለታችንም ላይብረሪ መሄድ ነበር የፈለግነው። ኮምፒውተሬን ይዤ ምዕራፍ ሶስትን ለመቀጠል ጓግቼ ምንጣፉ ላይ ተዘረፈጥኩ። የሆነኛው ሀሳቤ ውስጥ ይሄን ታሪክ ማወቅ የብዙ ጥያቄዬ መልስ ይመስለኛል። ምዕራፍ አምስትጋ የምንደርስበት ሰዓት እረፍት ነስቶ ያጓጓኛል። የተወሰኑ ገጾች ስለአባቱ ባህሪ እና ከእናቱጋ ስለነበረው ግንኙነት ከፃፍን በኋላ የሚቀጥለው አንቀፅ ላይ ስሜቱ ተቀያየረ።

« አብሬው ስራ ስጀምር መጠነኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ነበር የነበረችው። እየቆየ እየተስፋፋ እና ሌላ ቢዝነሶች ላይ መሰማራት ጀመረ። ቀስ በቀስ ብዙ ሃላፊነቶችን ይጥልብኝ ጀመር እናም ውጤታማ በሆንኩለት ቁጥር በሱስ አቅሏን ላጣች ሰካራም እናቴ ጥሎኝ መሄዱ የሚበላውን ነፍሱን ቀስ በቀስ የሚሽርለት ይመስለኛል። አንድ ቀን እኔና እሱ ባር ቁጭ ብለን ቢራ እየጠጣን <ለምንድነው ጥለሃት የሄድከው?> ብዬ ለዘመናት ልጠይቀው እየፈለግኩ ያልቻልኩበትን ጥያቄ ጠየቅኩት። መልሱ መልስ ያልሆነ ግን ሌላ ጥያቄ የማያስነሳ መልስ ነበር። <ምንም ቢሆን አንተን ለመተው በቂ ምክንያት አይሆንም ነበር።> አለኝ። ያላለኝን ብዙ ነገር ሰማሁለት። <አንተ ላይ ምንም አይነት መጥፎ ስሜት የለኝም! አሁን ትልቅ ሰው ሆኛለሁ። ብዙ ነገሮችን ያኔ በምረዳበት መንገድ አልረዳም! በህይወትህ የምትመርጣቸው ምርጫዎች ትልቅ ሰውም ብትሆን ሁሌ ልክ ላይሆኑ ይችላሉ። ላንተ ልክ ቢሆኑ እንኳን ሌላ ሰው ትጎዳበታለህ!! አሁን ሳስበው አልከፋብህም! ምንም ይሁን ምክንያትህ በጊዜው ላንተ ልክ ነበር።> አልኩት። ትከሻዬን ቸብ ቸብ እያደረገ አባቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እንባ ሲታገለው አየሁት። በእኔ ፊት ላለማልቀስ ትቶኝ ወጣ።

ምክንያቱ በእኔ ምክንያት የሚሰማውን ፀፀት ማጠብ ይሁን ወይም ወንድሜ ለሃላፊነት የማይበቃ እንዝህላል በመሆኑ ሲደመር አብሬው እየሰራሁ ብቃቴን ማስመስከሬ አላውቅም። ለሚስቱ የሚገባትን ድርሻ ከፍሎ በአክስዮን መልክ እና በገንዘብ ለወንድሜም ድርሻውን በገንዘብ ከፍሎ ለእኔ ገንዘብ ሳይሆን የቀረውን ስራውን በሙሉ አስረክቦኝ ነበር የሞተው።» መፃፌን ትቼ ስሜቱን ለማንበብ ቀና ስል ገባው።
«ታሞ ነው የሞተው። ቁጭ ብዬ የሱን ሀዘን እያቦካሁ እየጋገርኩ የምተክዝበት ብዙም ጊዜ አልነበረኝም። ስራው እሱ በህይወት እንደነበረው ሁሉ መቀጠል ነበረበት። ያለእርሱ እንዴት እንደምወጣው የማላውቀውን ሀላፊነት ነበር ያሸከመኝ። ሁለተኛ ፍቅረኛዬም ባትሆን ማዕረግ አጠገቤ ነበረች። በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ አጠገቤ ነበረች። ስራዬ ላይ አባቴን በሚገባ ተክቼ በየእለቱ ፍሬያማ እየሆንኩ መጣሁ። አባቴ በህይወት እያለ ብዙም ቦታ የማልሰጠው የሚስቱ ጥላቻ ይሄኔ በይፉ መታየት ጀመረ። ወንድሜም የእኔ ስራ በገንዘብ ቢተመን የሚያወጣውን እኩሌታ መጠን በጥሬ ገንዘብ ያገኘ ቢሆንም በየእለቱ እንደጥፋተኛ ይከሰኝ ነበር። እርግጥ ገንዘቡን ለመበተን አንድ ዓመትም አልፈጀበትም ነበር። ከእነርሱ ጋር መኖሩ ምቾት ስለነሳኝ የራሴን ቤት ገዝቼ ወጣሁ። የሆነ ቀን ከማዕረግ ጋር እራት እየበላን።

<አሁንማ የማይደረስብህ ሰው ሆንክኮ! በሰልክ። መቼ ነው ታዲያ የራስህ የሆነች ሴት ከጎንህ የምትኖረው? አሁን ሁሉ አለህ! በዛ ላይ ማንም ሴት አይታ ምራቋን የምትውጥልህ ወንድ ሆነሃል። ለምንድነው ፍቅረኛ የማይኖርህ?> አለችኝ። ልነግራት አስቤው አልነበረም። ብቻ ግን ብዙ ጊዜ ይሄን አጀንዳ አንስታ ስትጠይቀኝ ስቄና ቀልጄ እንደማልፈው ማለፍ አቃተኝ።
<የሴትም የፍቅርም መለኪያዬኮ አንቺ ነሽ። ሳልሞክር ቀርቼ መሰለሽ? ካንቺ ጋር አይደራረሱም! አንቺን የምትሆን ሴት ከየት ላምጣ? ካለች ጠቁሚኝና ዛሬ ነገ ሳልል ላግባት!> አልኳት።
<ሳትዋሽ አሁንም ለእኔ ስሜት አለህ?> አለችኝ
<ላንቺ ያለኝ ስሜት መቼም ጎድሎ አያውቅም!> አልኳት። በሰዓቱ አላውቅም ምን እንዳሰበች አላውቅም ምን እንዳሰብኩ። ሳመችኝ። ተያይዘን ቀለጥን። እነዚህ ጊዜያት ቀኖቼ ሰኞና እሁድ አይለዩም። ጠዋት እስፖርት ሰራለሁ ፣ በቀን ውስጥ ከ16 ሰዓት በላይ ስራ ነኝ፣ ማዕረግን አገኛታለሁ። ይኸው ነበር። ቀንህ ደባሪ እና የሚገመት ነው ብላ የተወችኝ ሴት ያው የተለመደ እና ተመሳሳይ ቀን መኖሬን ሳላቆም የእሷ ስሜት ለምን ተቀየረ ብዬ አልጠየቅኩም። <አሁን በስያለሁ> ያለችኝን አመንኩ እና የበሰለችው ማዕረግ የሰከነ ህይወት ትፈልግ ይሆናል ብዬ ለራሴ ነገርኩት። ምንስ ቢሆን ደግሞ ማዕረግ የእኔ ትሁንልኝ እንጂ ምክንያቷ ምንም ቢሆን ሂሳብ ልሰራ? ያንን ሂሳብ መስራት የሚችል ጭንቅላት ከኖረኝማ ምኑን እሷ አዘዘችብኝ? ወድያው አንድ ላይ መኖር ጀመርን።»
«እህህህ?» አልኩኝ። ሳቅ አለ። <ያልተነካ ግልግል ያውቃል > አይነት
«ከሷ ውጪ የማውቀው ሴት የለም። እንደእርሷ የማውቀውም ሰው የለም። ቢያንስ በሰዓቱ የማስበው እንደዛ ነበር። ፍቅረኛዬ ሳትሆንም በየቀኑ በህይወቴ ውስጥ አለች። ያቀፋት ክንድ የእኔ ቢሆን ስመኝ ፣ የያዛት እጅ ጣቶች የእኔ ቢሆኑ ሳልም፣ ስለፍቅረኞቿ ባወራችልኝ ቁጥር እነርሱን በሆንኩ ስል ሳላስበው የእኔ ሆነች። የእኔ መሆኗን ላክብር ወይስ ምክንያት ላስላ? አይሆንም ነበር። ለሁለት ዓመታት ሳንጋባ አብረን ኖርን! የሷ ያልነበረ ነገር አልነበረኝም። እኔ ፣ ገንዘቤ፣ ቤቴ ኢቭን ስራ ቦታ አብራኝ እንድትውል ስለፈለግኩ ከምትሰራበት ቦታ ለቅቃ አብራኝ መስራት ጀምራ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ልንጋባ ሽርጉድ ስንል ነበር የሰርጉ ወረቀት ተበትኖ ባለበት የእንጀራ እናቴ ሽማግሌዎች ይዛ መጥታ እቤት ይቅርታ ጠየቀችኝ። የማላውቀው ደመነፍሴኮ ነግሮኛል በመርዝ የተጠመቀ ይቅርታ መሆኑን። የተደገሰልኝ ሳይገባኝ ይቅርታ ተባብለን ተቃቀፍን። በሽማግሌዎቹ ፊት <ይሄ ይቅርታ አላማረኝም። ይቅርብኝ። ይለፈኝ> ይባል ነበር? ማለት ግን አምሮኝ ነበር። ወዲያው ከማዕረግ ጋር ስለሰርጉ እቅድ ሲወያዩ ያልገባኝ ስሜት ማጅራቴን እያሳከከኝ ነበር።»

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ዘጠኝ)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...