Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ አምስት)

ሲመስለኝ ፍቅርም ይረታል። በቁጣ ፣ በክፋት እና በበቀል ይረታል። ወይም ምናልባት እሱን ከማይመስሉ ባህርያት ጋር ግብ ግብ አይገጥም ይሆናል እና ቦታ ይለቃል። ቀስ በቀስ ቁጣ እና መከፋቴ ፍቅሬን እየሸፈነው መጣ። እዚህ ነጥብ ላይ የማስበው ሁሉ በምን መንገድ እኔን ማጣቱ እንዲቆጨው፣ እንዲፀፀት፣ የእግር እሳት እንዲሆንበት እንደማደርገው ነው። በቀል መሆኑ ነው!! በምትኩ በነገረ ስራው የምነደው እኔ ነኝ። ያቺን ከሱሉልታ ፒያሳ የሚሰማ ሳቅ የምታንባርቀውን ሴት እቤቴ ይዟት ከመጣ በኋላ ለሳምንታት ቃላት አልተቀያየርንም። የተያየነውም ለሆኑ ሰከንዶች ያህል ቢሆን ነው። ምግቤን ክፍሌ አስመጣለሁ። ማንበብ የምፈልጋቸውን መፅሃፍት ክፍሌ ይዤ እገባለሁ። (እሱ ከሰጠኝ ስጦታዎች ሁሉ ሳመሰግነው የምኖረው ከማንበብ ጋር በፍቅር እንድወድቅ ስላደረገኝ ነው።) የሆነ ቀን እሁድ ከሰዓት ቢያንስ በወር አንዴ እንደማደርገው ከህፃናቱጋ ላሳልፍ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከሉ ስሄድ እሱ እዛ ነበር። ከህፃናቱጋ ሜዳ ለሜዳ እየተሯሯጠ ይጫወታል። እኔን ሲያዩ ልጆቹ ሰላም ሊሉኝ ወደ እኔ እሮጡ።

ልክ እንደልክ ነገር፣ ትናንት እንዳደረገው የተለመደ ነገር ፤ በመሀከላችን ምንም ፀብ እንደሌለ ነገር በልጆቹ ፊት እቅፍ ነገር አድርጎ ጉንጬን ሳመኝ። ደንዝዤ ባለሁበት ለማላውቀው ጊዜ ያህል ተገተርኩ። ለመጨረሻ ጊዜ የሳመኝን ፣ጭራሽ የነካኝን ጊዜ ለማሰብ ስባዝን እጆቹ እንኳን ቆዳዬን ከነኩት ያኔ ሆስፒታል የተኛሁ ጊዜ ዓመት አለፈው ……… ጠልቼው አልነበር? እንዴት ነው ከንፈሩ ጉንጬ ላይ ሲያርፍ ልቤ ከደረቴ ካላመለጥኩ እያለች የምትደልቀው? መገተሬን ሲያይ መለስ ብሎ አሁንም እንደልክ ነገር ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ
«ልጆቹ እያዩን ነው። ለእነሱ የባልና የሚስት ምሳሌያቸው ፣ የእናት እና የአባት ተስፋቸው ነው። ጨቅላ ጭንቅላታቸው ገና ከጅምሩ በፍቅር ተስፋ እንዲቆርጥ ምክንያት አንሁናቸው!» አለኝ።
ጭንቅላቴ በከንቱነቴ ብስጭት ጦዞ <መጀመሪያስ ምን አስቤ ነው? ምን ዓይነቷ የማልረባ ነኝ በአንድ ጉንጭ መሳም በበደሉ ፈርጥሞ የደደረ ልቤ የሚቀልጥብኝ?> እያለ ያስባል። ከአፌ ማውጣት የቻልኩት ቃል ግን
«እሺ» የሚል ብቻ ነው። ከሰዓቱን በፍቅር እፍ እንዳለ ባል እና ሚስት ስንተውን ከልጆቹ ጋር አሳለፍን።
«እናንተ ለምን የራሳችሁ ልጅ የላችሁም?» አለው አንዱ ተለቅ ያለ ልጅ በልፊያቸው መሃል
«እናንተስ? ይሄ ሁሉ ልጅ የማን ነው? የኛ ልጆች አይደላችሁ?» ብሎ ባኮረፈ አነጋገር ተነጫነጨ።
ልጁ የተከፋበት መስሎት በማባበል አይነት እግሮቹን እያቀፈው
«እኛማኮ ልጆቻችሁ ነን! ሌላ ልጆች ካላችሁ ብዬ ነው! እ? የኛ አባት አይደለህምኮ አይደለም ግን » ብሎ ቀና ብሎ በልምምጥ አየው።
አዲስ ልጁን አንስቶ ተሸክሞት በማላውቀው አዲስ አነጋገር ሲብራራለት እኔ አፌን ከፍቼ እሰማለሁ። ከጨዋታ የተዘናጉትም ህፃናት ገብቷቸው ይሁን አፉ ጣፍጧቸው ይሰሙታል።
«ስለጠየቅከኝ አልከፋኝም እሺ። አንተ ህፃን ልጅ ነህ! ጭንቅላትህ ውስጥ የሚመጣውን ጥያቄ በሙሉ የመጠየቅ መብት አለህ! አዋቂዎች ደግሞ ያንን የመመለስ ግዴታ አለብን! ጥያቄህ ራሳችሁ የወለዳችሁት ልጆች የሏችሁም ወይ? አይደል? እንደሱ ከሆነ የለንም! እናንተ ብቻ ናችሁ ልጆቻችን! (ፈገግ ብሎ በፍቅር ዓይነት እኔን እያየ) እናንተ ትበቁናላችሁ ብለን ነው።»
የዛን ቀን ተመልሼ ወደቤት እየሄድኩ ደብዝዞ የነበረው መከፋቴ አገረሸብኝ። መውደድ ስለማይችል አይደለም። በምርጫው ሊጠላኝ ስለፈለገ እንጂ። አዲስን እስከማውቀው ከህፃናቱ ውጪ ለማንም ሰው የተለየ ፍቅር አያሳይም። ግን ደግሞ ለማንም ሰው ጥላቻን አያሳይም። ስሜት አልባ ይሆናል እንጂ። ላመነበት ምክንያት ማንንም ቢሆን ለመርዳት አያመነታም።ያውም ሰው ስለሆነ ብቻ እንጂ በደም ስለሚጋመድ ወይም ነገ ይጠቅመኛል ብሎ ሳያስብ። ሰውን ከረዳበት ለሚያወጣው ገንዘብም አይጨነቅም። ከቤቱ እና ከመኪናው ውጪ ለየቱም ቁስና ገንዘብ ሌሎች ሰዎች በሚጨነቁት ልክ ግድ ሲሰጠው አይቼ አላውቅም። እኔጋ ሲሆን ብቻ ይለያል ………… እኔን ግን ፈልጎ ነው መግፋት የመረጠው፣ ፈልጎ ነው መበደል የፈለገው፣ ፈልጎ ነው ባልገባኝ ጥፋቴ የሚቀጣኝ። ለምን እንዳልወደደኝ ሳስብ ራሴን መውደድ እቀንሳለሁ።
መጀመሪያውኑም ራስን ስለመውደድ እሱ ነው ያስተማረኝ። ከእርሱ በፊት የረባ የፍቅር ግንኙነት ያልነበረኝ ፣ ቤተሰቦቼን ለማስደሰት ከመዳከር ውጪ ለራሴ ምን እንደምፈልግ እንኳን የማላውቅ ነበርኩ። እሱ የወደደኝ የመሰለኝ ጊዜ ነዋ በእርሱ የመወደድ ዋጋ እንዳለኝ ሳውቅ ራሴን መውደድ የጀመርኩት፣ በራሴ መተማመን መገንባት የጀመርኩት። የሚወደድ ማንነት እንዳለኝ ያሳየኝ እሱ የጠላውን ራሴን መውደድ አቃተኝ። ለሆነ ሰው ማውራት እፈልጋለሁ። ከዛ <ያንቺ ጥፋት አይደለምኮ! አንቺ አሁንም ዋጋሽ ያው ነው እሱ ነው ጥፋተኛው። ቀረበት> እንዲሉኝ። አንደኛ እንደዛ የልቤን የማወራው ጓደኛ የለኝም ሁለተኛ ባወራ እንኳን ለማወራለት ሰው ለፍቅር ያልታደልኩ ዋጋ ቢስ መሆኔን ማውራት ጭራሽ የሚያሳንሰኝ ነው የሚመስለኝ። እሱ እንዳጠፋ ለማውቀው ጥፋት እንኳን በጥፋቱ መንገድ ውስጥ የእኔ ትንሽነት እና መዋረድ ደምቆ ይታየኝና በየቀኑ አንሳለሁ።
ከማሳደጊያው ውሏችን በኋላ በመሀከላችን የነበረው ውጥረት የቀነሰ መሰለ። የጤነኛ አብሮ ነዋሪ ሰዎች ሰላምታ እና ሀሳብ መቀባበል ጀመርን። ስለተፈጠረው ነገር ማናችንም አላነሳንም። እንደውም በቋሚነት ህፃናቱን የምንጎበኝበትን ቀን ልክ እንደበፊቱ <ለልጆቹ ሲባል> ተስማማን። አልፎ አልፎ እራት በአንድ ጠረጴዛ መብላት እና <ቀንህ/ሽ እንዴት ነበር?> አይነት ንግግሮች ጀመርን። አልፎ አልፎም ላይብረሪ ውስጥ ስንገናኝ ስላነበብናቸው መፅሃፍት ማውራት። ስለሚሰማኝ ስሜትም ፣ በትክክል ምን እንደምፈልግም ሳላውቅ በእንደዚህ ያለ ስሙ ያለየለት ኑሮ ወራት ተቆጠሩ። እነዚህ ወራቶች ላይ በተወሰነ መልኩ ነገን አርቄ ሳስብ እሱ የሌለበትን ነገ ማሰብ ጀምሬ ነበር። ባይኖርበትም ግን የሆነ ሰው ሆኜ ያለእርሱ ዋጋ ኖሮኝ አሁንም እንዲያይልኝ እፈልጋለሁ። በተዘዋዋሪ ዋጋዬ ትልቅ መሆኑን ለእርሱው ለራሱ prove ለማድረግ መጋጋጤ ያናድደኛል። ግን ዞሮ ዞሮ ምኞቴ ከዛ አያልፍም።
«የሆነ ሰርግ ተጠርቻለሁ። አብረን እንሂድ?» አለኝ ከእነዚህ ቀናቶች በአንዱ
«እንዴ? አንተ ሰርግ ከመቼ ወዲህ? ማን ቢሆን ነው?»
«እንድሪያስ ሊያገባ ነው።»
ለእኛ ሰርግ ሚዜ የሆነው ሪል ስቴቱን በማናጀርነት የሚሰራለት ሰው ነው። በተለያየ ጊዜ ጎበዝ እና ታማኝ እንደሆነ ነግሮኛል። ቢሆንም አዲስን ሰርግ ሲታደም ማሰብ አስደነቀኝ። የተባለውን ሰርግ ልንሄድ ስንወጣ ልክ ከዛ በፊት ቀሚስ ለብሼ አይቶኝ እንደማያውቅ ሁላ አይኖቹን በልጥጦ እያየኝ
«ቆንጅዬ ሆነሻል!!» አለኝ። ወንድ እንደማታውቅ ልጃገረድ ተሽኮረመምኩ። ባልተረዳሁት ምክንያት የዛን ቀን ደስተኛ ሆንኩ። ችግሩ ደስታሽ አይበርክት ተብዬ ተረግሜያለሁ መሰለኝ ሰርጉ ላይ የማስተምርበት ትምህርት ቤት ባለቤት ተገኝቶ ነበር እና ከአዲስ ጋር አስተዋወቅኩት። እኛ የተቀመጥንበት ጠረጴዛ ላይ ተጋርቶን ተቀመጠ። እና በየመሀሉ ስለትምህርት ቤት እና አንዳንድ ነገሮች እናወራ ነበር። ሰውየው ተጫዋች እና ባየው ነገር ቀልድ መፍጠር የሚችል ዓይነት ስለነበር ሲደመር ከነበረኝ የደስታ ሙድ ጋር ስስቅ እንደነበር አስታውሳለሁ። የሰርግ ዝግጅቱ ሊያልቅ አካባቢ አዲስ ተነስቶ ወጣ። ሽንቱን ሊሸና ወይም ስልክ ሊያናግር ነበር የመሰለኝ። በጣም ሲቆይብኝ ግራ ገብቶኝ ደወልኩለት ግን አያነሳም። ወጥቼ ሳይ መኪናው ከቆመበት አልነበረም። ያ ድሮ የምፈራው ዓይነት ፍርሃቴ ሆዴን አንቦጫቦጨው። ግራ እየገባኝ ደግሞም እየፈራሁ ምናልባት ከልጆቻችን አንዳቸው የሆነ ነገር ሆነው ይሁን ብዬ አስቤ ለአለቃዬም ይሄንኑ ነገርኩት። <በቃ እኔ ላድርስሽ> ብሎኝ እቤቴ ሸኘኝ። እቤቴ ደጅ ላይ አድርሶኝ ከተሰነባበትን በኋላ ቀና ብዬ ሳይ አዲስ በመስኮት እያየኝ አየሁት። ሳቅኩለት። አልመለሰልኝም። እንደገባሁ እሱ ወዳለበት ክፍል ሄጄ
«ሁሉ ነገር ሰላም ነው? ጥለኸኝ ስትመጣ እኮ መጥፎ ነገር የተፈጠረ መስሎኝ።» አልመለሰልኝም! «ሰርጉ ደብሮህ ነው?»
«ከሰውየው ጋርኮ ፊትለፊቴ ልብሳችሁን ልትጋፈፉ ትንሽ ነበር የቀራችሁ።» ሲለኝ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ። ቀንቶ ነው ብዬ አስቤ ደግሞ ለእኔ ስሜት ከሌለው ምን ያስቀናዋል? ወይስ ለማንም ሰው ግምት ግድ የሌለው ሰውዬ ሰዎች ለሚያስቡት ግድ ብሎት?
«ቀንተህ አይደለምኣ? እርግጥ አለቃዬ አማላይ ነው ግን በሌላ ነገር የማስበው ሰው አይደለም!» አልኩት። መቀለዴም ነበር።
«ምን ያስቀናኛል? ሳትሳቀቂ እንደፈለገሽ እንድትሆኚ ነው ትቼሽ የመጣሁትኮ » ብሎኝ ኮስተር ብሎ ቁልፉን አንስቶ እየወጣ «እንደዛሬ ደስተኛ ሆነሽ አይቼሽ የማውቅበት ቀን ትዝ አይለኝም። ካስደሰተሽ why not? ደግሞ አብረን አንድ ጣሪያ ስር ኖርን እንጂ ከወረቀት ባለፈ ምንምኮ አይደለንም!» ብሎኝ ልነግረው አፌን መክፈቴን ከቁብ ሳይቆጥረው በቆምኩበት ጥሎኝ ወጣ።
«ደስተኛ ያደረግከኝኮ አንተ ነህ!» ልለው ነበር።

ባስከፋኝ ቁጥር ህመሙ እየቀነሰ መጥቶ ይሆን እኔ እየለመድኩት አላውቅም ብቻ ከቀን ወደቀን ህመሙ ቀንሷል። የዛን ቀን ለለሊት የቀረበ ሰዓት ከሴት ጋር መጣ። ይህችኛዋ ሳቋ ብቻ አይደለም የሚሰማው አልጋው ሁሉ ሲሸበር ይሰማኛል። ሆነ ብሎ እኔ እንድሰማው እሷን ማስጮህ ፈልጎ ካልሆነ በቀር እሱኮ እንዲህ ድብድብ ቀረሽ ልፍያ አይላፋም ነበር! እሷስ ብትሆን ምንድነው ይሄን ያህል ፆሜን አለማደሬን ጎረቤት ካልሰማልኝ ማለት? ከፍቶኛል ግን አላለቀስኩም። ራሴን ጠልቼዋለሁ ግን በዛው ልክ እሱንም ጠልቼዋለሁ። ማነሴ ተሰምቶኛል ግን እሱም አንሶብኛል። አንድ የሆነ ነገሬ ከውስጤ ክፍል ብሎ የወደቀ ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ደሞ የማይበቃቸው ነገርስ?

ከዚህ ቀን በኋላ ያለው ኑሯችን ህፃን ያቦካው ሊጥ ነው። ወይ ተጋግሮ ለእራት አይበቃ ወይ አልቀጠነ ወይ አልወፈረ እጅ ላይ የሚጣበቅ ሊጥ……. መላ ቅጥ የሌለው። እናወራለንም አናወራምም ለማለት የቸገረ። ምንም እንደማይመስለኝ ላሳየው እንፈራገጣለሁ። ምኑም እንዳልሆንኩ ያሳየኛል። ማንም ግን እጅ ላለመስጠት እልህ ዓይነት እንፋታ የሚል የለም። መቆናጠሩን ለመድኩት። እዚህ ወቅት ላይ ነገዬን ያለእርሱ በደንብ ማሰብ ጀመርኩ። የሆነኛው ቀን ላይ ስንፋታ ምን ያህል ሀብት እንደምካፈለው ሳሰላ ራሴን ያገኘሁት ቀን በእርግጠኛነት እንደጠላሁት አወቅኩ። እራሴም የማላውቃት ሌላ ሴት ሆንኩ። ከዛ በኋላ ሀሳቤ ሁሉ ከእርሱ ከተለየሁ በኋላ ስለሚኖረኝ ህይወት ሆነ። ትቶ መውጣት የሚለውን ሀሳብ ላላነሳ ከርችሜ ጠረቀምኩት። እንዲህ ልቤ ተሰብሮ፣ እንዲህ ተዋርጄማ ባዶ እጄን ትቼው አልሄድም። ማንም ጉዴንና ውርደቴን ሳያውቅ የተከበረው አዲስ ሚስት እየተባልኩ ያቺን ቀን እጠብቃለሁ። ያኔ ባለብዙ ሚሊየን ሀብት ባለቤት ነኝ። ለእናቴ እንደገና ቤት እገዛላታለሁ። የእህቴን ልጅ አስተምራለሁ። ከዚህ በኋላ የማፈቅርበት ልብ ኖሮኝ ትዳር ስጠኝ ብዬ አልለምንም ግን አምላክ ካልጨከነብኝ አንድ ልጅ ቢሰጠኝ በቃኝ! ሳመነዥክ የምከርመው ሀሳብ እንዲህ ያለውን ብቻ ሆነ። ያ ቀን ሩቅ ሲመስለኝ <ምናለ ወይ በገደልከኝ ወይ በገደልከው?> እላለሁ።
ሴት ማምጣቱን ለመድኩት። ተኝቼ ዙር እቆጥራለሁ። <የዛሬዋ ደግሞ ለቅሶና እንጉርጉሮ ለይታ አታውቅም? እንዴት ያለው አጯጯህ ነው የምትጮኸው?> <የዛሬዋ ደግሞ በአንድ ለሊት ስንት ዙር ነው የምትሄደው እንዴ?> ፣ <የዛሬዋ ደግሞ ምን ብታክል ነው ክፍሉ አብሯት የሚንቀጠቀጠው?> እያልኩ ብዙ ዛሬዎችን ከቆጠርኩ በኋላ ……… ስራ ስሄድ ከውጪ ሲታይ እንዳማረው ዘናጭ ቤቴ ያማርኩ መስዬ ሴሚስተሮች ዘልቄ ……. ለቤተሰቦቼ ብዙ ውሸትን ሳጠግብ ከርሜ ……. ብዙ እሁዶችን እንደሚፋቀሩ ባልና ሚስት ለህፃናቱ ስተውን ባጅቼ ……… ህፃን ያቦካው ዓይነት ኑሮዬን ሳጨማልቅ ሰንብቼ ……..ስሜት አልባ ከሆንኩ በኋላ …….. ለምናፍቀው ቀን አንድ ዓመት ብቻ ከቀረኝ በኋላ አንድ ከሰዓት ስልኬ ጠራ
«ባለቤትሽ መኪናው ተገልብጦ አደጋ ደርሶበታል። ቶሎ ድረሽ!» የሚል። ሆስፒታል ደርሼ በህይወት መኖሩን እስካረጋግጥ ድረስ እንኳን የማስበውን ላውቅ ጭርሱኑ እያሰብኩም እንደነበር እንጃ ……… እንደዛ የጠላሁት ሰው እንዳይሞት መባባቴ ገረመኝ። ለአንድ ወር ሀገር ውስጥ ህክምና ካደረገ በኋላ ከሀገር ውጪ ለህክምና ሄደን ነበር። ሁሉም ተመሳሳይ ውጤት ቢነግሩትም አምኖ ለመቀበል ከበደው። ዶክተርና ሀኪምቤት ቢቀያይርም ውጤቱ ያው ነው።
«በጊዜ እና በፊዚዮቴራፒ እርዳታ እጅህና ሌላው ሰውነትህ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው ይመለሳል። እግሮችህ ግን መራመድ አይችሉም።»

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ስድስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...