Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ አራት)

«ታዲያ ቢያንስ ልታሳውቂኝ አይገባም ነበር? እኔ ምን አግብቶኝ ነው የአባትሽን ቁማር ቅሌት የምሸፍነው? ከዛሬ በኋላ ከገንዘቤ ላይ በዚህ ሰበብ ቤሳቤስቲን እንዲነሳ አልፈልግም።» አለኝ
የብዙ ሰዎች ባህሪ መሰለኝ። እየተገፋን እና በፍቅር የወደቅንለት ሰው በማይገባን መልኩ ክፋትና ጥላቻ እያሳየን ያየነውን መመዝበር አምነን ልባችንን ከመሰበር እንደመጠበቅ ይልቅ እዛው እንቆያለን። ምክንያቱም ከሰውየው እውነተኛ የሚታይ ባህሪ ይልቅ ሰውየው ነው ብለን በልባችን የሳልነውን ምስል እናምናለን። ከዛም አንዴም አይደለም ሁለቴም አይደለም። እየደጋገመ በማይገባን መንገድ ክፉውን እሱነቱን ያሳየንና ልባችንም ተሰብሮ ፣ ሞራላችንም ደቆ፣ ከክብራችንም አንሰን ፣ በፍቅር ልባችን ውስጥ የተሳለውንም ምስል በአውሬ ተክተን ………… ያኔ እናምናለን። በዜሮ አማራጭ እና በሚያነክስ ልብ እንለያያለን።

«በየወሩ የሚቆረጠው ብዙ ብር ስላልሆነ ነበር ያልነገርኩህ። ድሮም ቢሆን ከ50 ሺህ ብር በታች የሆነ ገንዘብ እንዳሳውቅህም ግድ ሰጥቶህ አያውቅም፤ ጠይቀኸኝም አታውቅም ነበርኮ! እውነት ለማውራት ብሩ የሚከፈልበት ምክንያትም አሳፍሮኝ ነበር ያልነገርኩህ።»
«እሱ ድሮ ነዋ! ድሮ አልሽውኮ እራስሽም! ራሴ ላይ ለውጥ አድርጌያለሁ አልኩሽ አይደል? ይኸኛው አዲስ ግድ ይለዋል። አንቺን እንጂ ቤተሰብሽን የማኖር ግዴታ የለብኝም።»

«ምን አድርጌህ ነው ግን ቆይ እንደዚህ የጠላኸኝ? ለምንድነው ክፉ እንደሆንክ ልታሳየኝ የምትፈልገው? ምንድነው ሀጥያቴ? ልወቀው በደሌንና እንድተውህ አይደል የምትፈልገው እተውሃለሁ። ምክንያትህን ብቻ ንገረኝ! እንዳምን ላደረግከኝ ማንነትህ በፍቅር ከመውደቅ ውጪ ምንድነው የበደልኩት? ጠልተኸኝም፣ ገፍተኸኝም ደግሞ <ምን በድዬ ነው?> እያልኩ እራሴን ስጠይቅ እንድኖርም ፈርደህብኝ አላሳዝንህም?» አልኩት ላለማልቀስ ከራሴ ጋር ግብ ግብ እየፈጠርኩ
« አንቺ ነው ብለሽ ጭንቅላትሽ ውስጥ ስለሳልሽው ሰው ተጠያቂ አይደለሁም። ራሴን ስለመሆን እንጂ ሰዎች የሚስሉትን ምስሌን ስለመሆን ግድ የለኝም።» ብሎኝ ጭራሽ ስለጠየቅኩትም የሆነ ያጠፋሁ ነገር አስመስሎት ያነብ የነበረውን መፅሃፍ የመወርወር ያህል ጠረጴዛው ላይ ጥሎት እየተበሳጨብኝ ወጣ!

ሲጀምር ፍቅሩን ፣ገላውን፣ ትንፋሹን ፣ እቅፉን …….. ራሱን ነበር የከለከለኝ እንጂ በንግግር የሚያስከፋኝን ወይም የሚጎዳኝን ነገር ተናግሮ አያውቅም ነበር። ሳይናገር ግን እንድፈራው ያደርገኝ ነበር። ራሱን ከኔ በማራቅ ፍቅርን ስለከለከለኝ ተስፋ ቆርጬበት ጥዬው የምሄድ ነበር የመሰለው ይመስለኛል። በዚህኛው ጊዜ <ይወደኛል! ያሳለፈው የሆነ መራራ ህይወት ፍቅርን እንዲፈራ አድርጎት ነው!! ምን ያህል እንደማፈቅረው ሲያውቅ ይመለስልኛል።> የሚል ሰበብ ነበር ለራሴ የምሰጠው። እየገፋኝ እና እንደሌለሁ እየቆጠረኝ እንኳን ስር ስሩ ከማለት ውጪ የሱን ልብ ልረታበት የምችልበት ምንም መላ ላመጣ ባልችልም በሆነኛው ተዓምር ብቻ የፍቅሬ ልክ እንዲገባው ተስፋ አደረግኩ። አልገባውም ወይም እንዲገባው አልፈለገም! ይሄኛው መንገድ እንዳልሰራ ሲያውቅ ንግግራችንንም በጥላቻ ይለውስብኝ ያዘ። ምን ያህል እንድተወው እንደፈለገ ቢገባኝም እዚህኛው ነጥብ ላይ ሰበቤ ብዙ ነው። <ይወደኛል> የሚለውን <ሊያየኝ አይፈልግም> በሚለው ተክቼዋለሁ።

የዋሁ ልቤ በልቤ የተሸከምኩትን ፣ በፍቅሩ የታመምኩለትን ፣ እኔ ራሴን ስስትበት ፓኒክ ያደረገውን፣ በልግስናው ከማንም የማላወዳድረውን ፣ ለታይታ የማይኖረውን ፣ ያ < እንባሽን ከማይ ሳምንት ፀሃይን ባላይ> የሚለኝን ፣ እንደእኔ ዓይነት ባል የታደለች ሴት የለችም ብዬ የምጎርርበትን ፣ ከነግራ ማጋባቱ የማብድለትን ………… ያን አዲስ ምስሉን ከልቤ ሳይሸረሽረው፤ ክፋቱ በዝቶ መልካም ትዝታዎቼን ሳያጠፋብኝ ፤ እንዳፈቀርኩት ማቄን ጨርቄን ሳልል እብስ ብዬ መጥፋት ያምረዋል። ሌላኛው ልቤ ደግሞ ከጭንቅላቴ ጋር ይማከር እና ከዛስ? ይለኛል።

ከዛስ? በዚህ እድሜዬ እናቴ ቤት ልገባ? ምን ቤት አላት? ቤት ገዛሁልሽ ብያት ከቀበሌ ቤቷ አስወጥቻታለሁ። ሟች ባሏ ያስያዘባትን ቤት እዳ እከፍልልሻለሁ ብያት ከዚህ በኋላ ልከፍልላት አልችልም። ትቼው የነበረውን ማስተማር እቤት እየዋልኩኝ ስብሰከሰክ ከመዋል ብዬ ድጋሚ የጀመርኩት ቢሆንም ደመወዜ እንኳን የቤቱን እዳ ሊከፍል ቤት እንኳን ብንከራይ የቤት ኪራይ አይሸፍንም! ምንስ ብዬ ነው አሁን የምነግራት? ከቤቷ ወጥታ የት ትኖራለች? የአባዬ የጡረታ ብር አይደለም የቤት ኪራይ ሊከፍልላት ብቻዋን እንኳን ብትሆን የቀለብ አይችላትም እንኳን የታናሼ እና የልጇ ሆድ ተጨምሮ። ታናሽ እህቴንስ ምንድነው የምላት? በቃ ከዛሬ በኋላ ልጅሽን የምታደርጊውን አድርጊው ልረዳሽ አልችልም ነው የምላት? አንዳንዴ ምናልባት እንደመጀመሪያ ሚስቱ ጥዬው ብሄድም ባዶ እጄን አይሰደኝም ብዬ አስብ እና ከእርሷ ጋር በሰላም ተከባብረው እንደተለያዩ ሳስበው እጣዬ እንደሁለተኛ ሚስቱ አጨብጭቦ በባዶ እጅ መቅረት ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ። (ሰብለ ፍታኝ ስትለው ትነዳው ከነበረ መኪና ውጪ ምንም ሳይሰጣት ነው የፈታት።) እኔ ደግሞ እሱጋ ያለኝን ቦታ እንኳን ለይቼ አላውቀውም። ይጠላኛል? ይወደኛል? እንደምንስ ይሆን የሚያየኝ?
ከዛ በኋላ የተኳኋነው እብደት ነው። የአዋቂም የጤናም ያልሆነ እብደት……………. አልኳችሁ አይደል?
ይሄን ሁሉ ሀሳብ ደምሬ ቀንሼ እና አባዝቼ ደግሞ እልህ ይይዘኛል። በየቀኑ በቃላት ሊገፋኝ በጣረ ቁጥር ፍቅሬ ከክምሩ ትንሽ በትንሽ እየተናደ …….. ንዴት እና ቁጣ በምትኩ ትንሽ በትንሽ እየተቆለሉ ………. ንዴት እና ፍቅሬ እኩል መጠን ላይ ሲደርሱ ጥላቻ እና እልህ ተወለዱ። አንድ ብለው መሰረታቸውን አኖሩ ……… እፈራው ነበር። ለካንስ እፈራው የነበረው ስለማፈቅረው ነበር። የምፈራው የነበረው እንዳላጣው ስለምንሰፈሰፍ ነበር። ልክ ፍቅሬ መጉደል ሲጀምር የምፈራው ነገር እኩል እየቀነሰ መጣ።

ሁለት ወር የሰውየውን ብር መክፈል ሲያቅተኝ ሰውዬው ለእማዬ ማስጠንቀቂያ ላከ። ከዚህ በላይ መሸሽ የምችለው ሀቅ ስላልነበረ እማዬንም ሁሉንም ሰብስቤ እውነቱን ነገርኳቸው። ሁሉንም ጥቃቅን ነገር ባላወራቸውም አዲስ ደስተኛ ስላልሆነ እንዳልከፍል እንደከለከለኝ ነገርኳቸው። በወንድሞቼ ዓይን ስወርድ ታየኝ። እማዬ ግን ገባት። እንደውም ለብቻዬ ጠርታ ደህና መሆኔን ጠየቀችኝ። ከወንድሞቼጋ ተጋግዘን ልናኖራት ቤት ተከራየንላት። እቃዎቿን ስትሸጥ አይኗን ማየት ስለከበደኝ አላገዝኳትም። መከፋቴን፣ ማፈሬን ፣ ማነሴን የምነግረው ሰው ስላልነበረኝ መኝታ ቤቴን ዘግቼ ተንሰቀሰቅኩ። ቤቷን የለቀቀች ቀን ግን የሆነችውን መሆን ሳየው ቤቷን ለማጣቷ ሰበቡ አባቴ ቢሆንም ላተርፍላት ባለመቻሌ ራሴን ጠላሁት። <ልጄ ዓለሜን እንዳሳየሽኝ ድመቂ > ብላ የመረቀችኝ እናቴ ዓለሜ ያለችውን ቤቷን ራሴ የቀማኋት መሰለኝ። ከታናሽ እህቴ ጋር እና ከልጇ ጋር አንድ መኝታ ቤት ያለው ኮንዶሚንየም ነበር የተከራየንላት። በህይወቴ የተመኘሁት አንድ ነገር ለቤተሰቦቼ ኩራት መሆን ነበር። በቃ ሌላ ምኞትም ህልምም አልነበረኝም። እስከማስታውሰው ለራሴ በሆንኩት ብዬ አጥብቄ የተመኘሁት የለኝም።

«እንዲህ ያለው ቅሌትስ በዘርም አይድረስ! በመምሻ እድሜዋ አሳይቶ ነሳት!» እያሉ ጎረቤቶቿ ከንፈራቸውን መጠጡላት።
ላፍነው የማልችለው አይነት መከፋት ከፋኝ። መኖር የምመኝለት ዓላማ ጠፋኝ። ለቤተሰቤ መሆን አልቻልኩበትም: ወይም መፅናኛዬ የምለው ልጅ እና የራሴ ቤተሰብ የለኝ: ወይም በፍቅሩ እካሳለሁ የምለው ባል የለኝ : ወይም ገና ወጣት ነኝ ነገ የተሻለ ነው የምለው ጊዜ የለኝ : ልደበቅበት የምለው ሙያ እና ህልም የለኝ…… ምንድነው የምኖርበት ዓላማ??
«አምላኬ ሆይ ለምን አሳይተህ ነሳኸኝ? እሺ እኔን ከሆነ መቅጣት የፈለግከው እኔን አትቀጣኝም? ለምን እናቴን? ለምን በስተእርጅና እሷ ትከፋ? ምንድነው ያደረግኩህ ?? ለምንድነው አንድም በህይወቴ የሰመረ መንገድ የሌለኝ??» እግዚዘብሄርን ማማረር ያዝኩ። እናቴን የተከራየችው ቤት አስገብቻት የመጣሁ ቀን …. አዲስ ቀድሞኝ እቤት ገብቶ ነበር። … መፍራቴ ትቶኝ የለ??
“በነገርህ ላይ! ምንም እንደማይመስልህ አውቃለሁ ግን እንደው ለጠቅላላ መረጃ እንዲጠቅምህ እናቴ ቤቷን አጥታለች። .. ዛሬ ኮንዶሚንየም ቤት አስገብቻት መጣሁ።” አልኩት። ዝም አለ። ህመሜን እንዴትም ላጋባበት እንደማልችል ባውቅም መከፋቴ ደረቴ ላይ ተነባብሮ ካልወጣሁ ብሎ እያነቀኝ ስለነበር ዝም ማለት አቃተኝ።

“የ48 ዓመት ባሏን እና ጏደኛዋን ባጣች በወራት ውስጥ ቤቷን አጥታ : እቃዋን ሸጣ: በስተርጅናዋ መከፋት ሲሰብራት ብታያት ጥሩ ነበር። ምንም አይመስልህ እንደው ታውቀው ነበር።” እያወራው ያለሁትኮ ከእናቴ ገንዘቡን ስላስበለጠ እንዲሰማው ላስፀፅተው ነበር። መከፋቱም ፀፀቱም በእኔው ብሶ እንባዬ ወሬዬንም አደፈራረሰው እና እየሮጥኩ መኝታ ቤቴ ገባሁ። ህቅ ህቅ ብዬ ተንሰቀሰቅኩ። …. ለቀናት እየሸሸኝ መሰለኝ ወይም አስጠልቼው እንዳንገጣጠም በተቻለው መጠን ጣረ። የሆነ ቀን ጠዋት ተገጣጠምን። አላውቅም ምን እንዳስቆጣኝ ብቻ ግን ውስጤ ያለው እልህ እና ቁጣ ነው።
” ጥላኝ ትሄዳለች ብለህ አትድከም! ስምንት ዓመት እስኪሆን መታገስ አያቅተኝም። በውላችን መሰረት ግን አንተ ፍቺ ከፈለግክ ይስማማኛል።” አልኩት ልክ እንደእሱ እኔም ለእርሱ ምንም ስሜት እንደሌለኝ ማሳየት ነበርኮ የምፈልገው ግን ድምፄ ልምምጥ እንጂ ቆራጥ ውሳኔዬ እንዳልሆነ አሳበቀብኝ።
ከ8 ዓመት በፊት ፍቺውን የፈለገው እሱ ከሆነ ንብረቱን እኩል የማካፈል ግዴታ አለበት። … በልቤ ‘እሺ’ ቢለኝ የሚለውን ሳስብ ገና ደስ እንደማይለኝ ገባኝ። እሺ ብሎ ቢፈታኝ ገንዘቡ እሱን ማጣቴን ይክሰዋል? አላውቅም! እሺ አሁንስ እሱ አለኝ ነው የሚባለው?? ምን እንደምፈልግ ሁሉ ግራ ገባኝ። ሁለቱም ትርጉሙ ያማልኮ …. አንቺ በህይወቴ ውስጥ ከምትኖሪ ግማሽ ልፋቴን ውሰጂና ውጪልኝ መባል ወይም ግማሽ ልፋቴን ከምሰጥሽማ እንዲሁ ጥዕም አልባ ቀን ብኖር ይሻለኛል መባል…… ሁለቱም ያማል። … ሁለቱንም በቃሉ አልመለሰልኝም።….. ከጊዜ በኃላ ግን በተግባር ምርጫው ሁለተኛው እንደሆነ አሳየኝ።

ሳምንት ሳምንትን ሲወልድ የጠላሁት ሁሉ መሰለኝ። … ንግግራችን እየቀነሰ መጣ። የሆነ ቀን ምሽት ግን በቁሜ ተኩሶ ልቤን የመታኝ ያህል ተሰማኝ። … አምሽቶ ከሴት ጋር መጣ!! አንድ ቤት ከማደራችን ውጪኮ የእኔ እንዳልሆነ አውቃለሁ! የዛን ቀን ግን ሲገባኝ …. ይመለሳል የሚል ተስፋዬ አልሞተም ነበር። የትኛው ይበልጥ እንዳመመኝ አላውቅም!! እዛው እቤቱ አስቀምጦኝ ሴት ይዞ መጥቶ ክብር የማይገባኝ ምንም እንደሆንኩ የነገረኝ ወይም ለዘለአለም እንደሄደ ማወቄ!! መኝታ ቤት ሆኜ የፀሃይን ያልሆነ የሴት ሳቅ ሰምቼ መኝታቤቴን ከፍቼ ብቅ አልኩ። ወደእርሱ ክፍል ደረጃውን እየወጡ ነበር። … ተከትያቸው ወጥቼ ልጅቷን ‘ሚስት እንዳለው ታውቂያለሽ?’ ልላት አስቤ ነበር። ወይም ከእርሱ ጋር ‘ምን እያደረግክ ነው?’ ብዬ ልጣላ…. ወድያው ጭንቅላቴ ውስጥ የመጣው ብዙ ነበር። … ይበልጥ ራሴን ማዋረድ መሰለኝ። መኝታ ቤቴን ዘግቼው እንኳን የሷ ሳቅ ይሰማኛል። … ሆነ ብሎ እንድሰማ እስኪመስለኝ የመኝታ ቤቱን በር አልዘጋውም። …. ከእነሱ እንዳላየኃቸው እንዳልሰማኃቸው መስዬ መኝታ ቤት ውስጥ ተደበቅኩ ከራሴ ግን የት ልሽሽ??
አዲስ የፈለገውን እና ያመነበትን ነገር የሚያደርግ ሰው ነው። ነገር ግን የሚኖራቸው መርሆች ያሉት ሰው ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወሲብ ላይ ያለው መርህ ነው።
“በፍቅር ካላመንክ: ልጅ ካልፈለግህ: ወሲብን በፈለግከው ጊዜ ማግኘት ትችላለህ ለምን ትዳርን ትደጋግማለህ? ያውም የዓመት ገደብ እያበጀህ “ብዬው ከመጋባታችን በፊት
“እኔ ሴሰኛ አይነት ሰው አይደለሁም!! በየሄድኩበት ባየኃት ሴት ሁሉ ደሜ አይሞቅም። ከተለያየ ሴት ጋር መባዘን አይመቸኝም። ከተመቸችኝ ሴት ጋር ባደርገው ነው ደስ የሚለኝ። ከወሲብ በተጨማሪ ማሰብ የምትችል አብሬያት ብኖር ደስ የምትለኝ ሴት ስትገጥመኝ በሳምንት ሁለቴ ከቤቷ እየጠራሁ ላሽኮረምማት አልፈልግም። አብሬያት መኖር ደስ ይለኛል እስክንሰለቻች… ይሄን ስልሽ ለሴክስ ብዬ ብቻ ሴት ቀርቤ አላውቅም እያልኩሽ አይደለም። ግን ለሴክስ ብቻ አብሬያት እንዳለሁም እያወቅኩ ቢሆን እሷ ከህይወቴ ካልወጣች ከሌላ ሴት ጋር አልሆንም ያ መርሄ ነው።” ብሎኝ ነበር።
ቅናት ቆዳዬን ቆጠቆጠኝ። … የሳመኝ ከንፈር የሆነችዋን ሴት እንደሚስማት ማሰብ : ከኔ ጋር የሰራቸውን ፍቅሮች ከሆነችዋ ጋር ሊሰራው እንደሆነ ማሰብ …. ያውም እዚሁ አንድ ደረጃ ወጥቶ አናቴ ላይ…. የማይታክተኝን ለቅሶዬን ተንሰቀሰቅኩት። … አልወጣልሽ አለኝ። … … በዛ ምሽት እናቴጋ ሄድኩ። ስታየኝ ደነገጠች። ‘ባሌ እቤቴ ሴት ይዞ መጣብኝ!’ ብዬ ልነግራት አፈርኩ። ‘ተጣላን!’ ብቻ ብያት መንሰቅሰቅ ጀመርኩ።

“ባልና ሚስት ይጋጫል… እኔና አባትሽ ..” ብላ የግጭት አፈታት ብልሃት ስትመክረኝ አደረች። በነገታው እሁድ ነበር። ከእናቴጋ ቤተክርስትያን ሄጄ ከሰዓት አካባቢ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ሳየው ፍቅሬ ቁጣን አልፎ ጥላቻን … ጥላቻን አልፎ በቀልጋ መድረሱ ገባኝ…. መናደዴን እንዲያውቅም አልፈለግኩም። ድምፄ ልናገርበት በፈለግኩት ትክክለኛ ድምፀት ታዘዘልኝ….
“ቢያንስ ስትዳራ መኝታቤትህን ዝጋው ቢበዛ ደግሞ ማታ 5 ሰዓት ላይ ለመንደር የሚሰማ ሳቅ እንደማይሳቅ የምታውቅ ኩል ሴት የምትውልበት ዋል።” ብዬው ለፀሃይ ሲመሽ እራቴን መኝታ ቤት እንድታመጣልኝ እንደምፈልግ ነግሬያት መኝታ ቤት ገባሁ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ አምስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...