Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ ሶስት)

«ሁሉም ሰውኮ አንድ የሆነ ስስ የሆነበት ጎን አለው። ሰዎች ስስ ጎንህን ማወቃቸው ሁሌም መጥፎ ነገር አይደለም። በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ድክመትህን ለመጥፎ ቀን አንተን ለመጣያ ጥይት አድርገው ሊጠቀሙበት ያስቀምጡታል። ለማን ምን ልንገር የሚለው ይመስለኛል እንጂ የሚወስነው ………..» ከአፌ ነጥቆኝ ቀጠለ
«ሁሉም ድክመትሽን የነገርሽው ሰው ድክመትሽን በነገርሽው ሰዓት ይረዳኛል ያልሽው፣ ወዳጄ ያልሽው፣ ያዝንልኛል ያልሽው፣ የኔ ነው ያልሽው…….. ሰው ነው የሚሆነው። አብዛኞቻችን ስንወዳጅ እንለያየን ወይም እንጣላለን ብለን አስበን አይደለም እና ቁስልሽን ቀምሞ አንቺኑ የሚጥልበት ጥይት እንደሚያደርገው የምትረጂው በሆነ ነገር ሳትስማሙ ስትቀሩ እና ስትለያዩ ነው። አየሽ እኔ ደግሞ ትዳርን ጨምሮ ምንም አይነት በሰዎች መሃል ያለ መስተጋብር አንድ ቀን እንደሚፎርሽ አውቃለሁ። ያ ማለት ሳትለያዪም ሚስቴ ያልሻት ሴት ድክመትን ያወቀችው ቀን የተጠቃች ሲመስላት መጀመሪያ የምትመዘው ያንን ስስ ጎንሽን ነው። በዛ ላይ ሰው ምፅ ሲልልሽ እንደሚቀፈው በዚህ ምድር ቀፋፊ ነገር አለ?» አለኝ። የጀመርነውን ባዮግራፊ መፃፍ በመሃል አቁመን ነው ይሄን የምናወራው። ቡና ጠጥተን መጻፍችንን ቀጠልን።

«< ምፅ ! ያላደለው ልጅ! ኖራውም ሞታም ጦስ ሆነችበት። የእናቱን እሬሳ አቅፎ ሲያለቅስ ሰይጣን አጊንቶት ነው!> ይላሉ ሲያዩኝ። የተያዘው አንደበቴ ብቻ ሳይሆን ጆሮዬም የተደፈነ ይመስላቸዋል። የእናቴን ሬሳ ካገኘሁበት ቀን በኋላ ማውራት አቃተኝ። አጋንንት ለክፎት ነው ብለው የአባቴ እህት እና እንጀራ እናቴ በየፀበሉ ይዘውኝ ዞሩ። ዲዳ የሆንኩበትን ምክንያት በየፀበሉ፣ በየመንገዱ <ምን ሆኖ ነው?> ላላቸው ሁሉ ሲያብራሩ አብሬያቸው መሆኔን ይዘነጉታል። እንደገና መሽተት የጀመረው የሬሳዋ ሽታ አፍንጫዬን ያፍነኛል ፣ የተገታተረ ደረቅ ሰውነቷ እጄን ይሻክረኛል፣ ትንፋሽ ያጥረኝና እሰቃያለሁ። <እናቱ ሞታ እሬሳዋን ……..> ማብራራታቸውን ይቀጥላሉ። የሚሰማቸው ሰው <ምፅ ምስኪን!> ይላቸዋል። ምፅ የሚል ሀዘኔታ ሰውነቴን ያሳክከኝ ጀመር። አንድ ዓመት! አንድ ዓመት ሙሉ መናገር አልቻልኩም። የተፀበልኩት ፀበል፣ መስዋእት የቀረበለት አዋቂ፣ ፈዋሽ የተባለ ፀላይ…… ማናቸውም አላዳኑኝም። ማናቸውም ያልገባቸው ካለመናገሬ በላይ መዳን የምፈልገው ጭንቅላቴ ውስጥ ተስሎ ካለው ምስሏ ነበር። በእያንዳንዱ ቀን መስማትም እያቆምኩ እየመሰለኝ ጠዋት ስነሳ ድምፅ መስማቴን እፈትሻለሁ።

በአመቱ አባቴ በጥቆማ አንድ ዶክተር ጋር ወሰደኝ። የተፈጠረውን ነገር ከአባቴ ከሰማ በኋላ የሚፈጠር ነገር መሆኑን አብራራልን። አንደኛው psychogenic mutism ከሚባሉት ውስጥ ነው። ልጆች በተለያየ trauma ውስጥ ሲያልፉ ይከሰታል። ገና አፉን እንደሚፈታ ህፃን ሀ ሁ ብዬ ድምፅ ማውጣት መማር ጀመርኩ። ለወራት ህክምና ስከታተል ቆይቼ ለመጀመሪያ ቀን ቃላት ሰካክቼ ያወራሁ ቀን በቃላት መተንፈስ የፈለግኩት የነበረው።
« ጥያት ባልሄድ ኖሮ አትሞትም ነበር።» የሚለውን ነበር።

አስተካክዬ መናገር የጀመርኩ ቀን መቃብሯ ላይ ሄጄ ስለእሷ ማለት የፈለግኩትን ሁሉ በቃሌ እያልኩኝ አለቀስኩላት። ለሰዓታት አለቀስኩ። የሆነ ነገር ቀለለኝ። የሬሳዋ ሽታ ከአፍንጫዬ ላይ የጠፋ መሰለኝ። እንደማንኛውም ልጅ ማንኛውም ዓይነት የልጅ ህይወት ለመቀጠል ትምህርቴን ካቆምኩበት ቀጥዬ መማር ጀመርኩ።
«እንረፍና እንቀጥል?» ዝም አለ። ዊልቸሩን እየገፋሁ ወደሳሎን መጣን። የሚጨንቅ ዝምታ ዝም አለ። እየደጋገምኩ <ደህና ነህኣ?> እለዋለሁ። ማለት የምፈልገው ብዙ ነበር። ያዘንኩለት ሳልመስል ማዘኔን እንዴት ነው የምነግረው? ይሄን ሁሉ ትናንቱን አውቄ ቢሆን ኖሮ የሆነውን ሁሉ መካኋናችንን ያስቀርልን ነበር? የተወኝን ፣ የገፋኝን፣ የጠላኝን ያስቀርልን ነበር?
«የዛን ቀን እንደምወድህ ባልነግርህ ኖሮ ነገሮች ይቀየሩ ነበር? ያለፉትን መጥፎ ነገሮች ያስቀሩልን ነበር?» አልኩት
«አላውቅም! ማንም ሰው ያለምንም ምላሽ እና ጥበቃ ለዘለዓለሙ አይወድም! (አይወድም የሚለውን በእጁ የትምህርተ ጥቅስ ምልክት ሰርቶ ነው የገለፀው) የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ቀን ትነግሪኝ ነበር። ምላሹንም ትጠብቂ ነበር።»
«እና የዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መንስኤ እኔ እንደምወድህ መንገሬ ነው?»
«አይደለም። ባትነግሪኝም አውቀው ነበር።»
« እና እሺ ምንድንነበር? ምላሹን ስጠኝኮ አላልኩህም ነበር። ያለምንም ጥበቃኮ ወድጄህ ነበር።» አልኩኝ ድምፄ ሁላ ያኔ ወደነበረው ስሜቴ ሄዶ
«የምታስቢው ዓይነት ሰው ሳልሆንልሽ ስቀር ደግሞ የመጥላትን ጥግ ጠልተሽኝም ነበር።»
«ያንን ነበር prove ማድረግ የፈለግከው? ምንም ዓይነት ሰው ብትሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አፈቅርህ እንደነበር?»
«አይደለም!»
«እኮ እሺ ምንድነው?»
«በቃ አንቺ የሌለሽበትን ህይወት መኖር ነበር የፈለግኩት! አንቺ ወደህይወቴ ሳትመጪ በፈቀድኩት መንገድ የማዝዘው ሀሳብና ስሜቴን መልሼ መቆጣጠር ብቻ ነበር የፈለግኩት!» ጮኸብኝ። መጀመሪያ ደነገጥኩ ከዛ ግን ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ። ብዙ ልጠይቀው ፈለግኩ ግን ያ ድሮ እፈራው የነበረውን ዓይነት ፍርሃት ፈራሁት። ዝም አልኩ።
…………….

የዛኔ! ሌላ ሰው ሆኖ ከተመለሰ በኋላ
«ምርጫውን ላንቺ ሰጥሻለሁ! ምንድነው ሆነሽ መኖር የምትፈልጊው? የራሴን ፍላጎት ደግሞ እነግርሻለሁ። አንድ መኝታ ቤት መተኛትም ምንም አይነት ስሜታዊ መነካካት አልፈልግም። ከዛ በተረፈ አብሮ መውጣት መግባቱ አይጎረብጠኝም። የግድ ካልተዋሰብን አብሬህ መኖር አልፈልግም ካልሽ እሱም ምርጫው ያንቺ ነው።» ካለኝ በኋላ
የተኳኋነው እብደት ነው። የአዋቂም የጤናም ያልሆነ እብደት…………….
ምርጫው ያንቺ ነው እንዳለኝ መረጥኩ። አዲሱ አዲስ እስኪበርድለት መታገስ፣ እንደፈለገው ሆኖ የድሮው አዲስ እንዲመለስልኝ ተስፋ ሳልቆርጥ ልጠብቀው ወሰንኩ። አልተመለሰም!! እቤት ሲመጣ እንደእህቱ ነገር ፣ እንደ ጎረቤቱ ነገር፣ እንደ ቤት ደባሉ ነገር ….. አለመቅረብም አለመራቅም የሆነ አኳኋን መሆኑን ቀጠለ። ከህይወቱ ሹልክ ብዬ እንድወጣለት ግን በራሴ እንድወጣለት እንጂ እሱ ውጪ እንደማይለኝ አውቄያለሁ። ብዙ እንደእነዚህ ያሉ የተጃጃሉ ውላቸው ያልለየ ቀኖች ካሳለፍን በኋላ የሆነ ቀን ማታ ላይብረሪ ቁጭ ብለን እያነበብን
«እኔ የምልሽ? በየወሩ ለአቶ ጌትነት የሚል አካውንት ብር የሚላከው ለማንነው? ማነው ሰውየው?» አለኝ። አባቴ ቤቱን በቁማር አስይዞት እንደነበር እና እሱን እየከፈልኩ እንደሆነ አስረዳሁት።
«ታዲያ ቢያንስ ልታሳውቂኝ አይገባም ነበር? እኔ ምን አግብቶኝ ነው የአባትሽን ቁማር ቅሌት የምሸፍነው? ከዛሬ በኋላ ከገንዘቤ ላይ በዚህ ሰበብ ቤሳቤስቲን እንዲነሳ አልፈልግም።» አለኝ
የዛን ቀን ያቺን ሰዓት ለመጀመርያ ጊዜ እልህና ፍቅሬ ፣ ፍቅርና የጥላቻ ዘር ውስጤ ተሳከረ

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ አራት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...