Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሀያ)

እና ሰዓት ብላችሁ ከመነጫነጫችሁ በፊት ይቅርታ ብያለሁ!! ሜሪ ፈለቀ ከማይታይ ፊርማጋ )
«ትናንትህ ላይ በበደሉህ ሰዎች ነው ዓለምን በሙሉ እየዳኘህ ያለኸውኮ! በዙሪያህ ያሉ ሰዎች በሙሉ እንደእነሱ ናቸው ማለት አይደለም! በተቃራኒው የሆኑ ሰዎች አሉ። አንተ ያደረግከው ለማንም ምንም እድል አለመስጠትን ነው።» ከምሳ በኋላ ፀሃይ ቡና አፍልታ ሳሎን ቡናችንን እየጠጣን ነው ስላለፉት ውሳኔዎቹ የጀመርነውን የሀሳብ ልውውጥ የቀጠልነው።

«ካለፈው ውድቀትሽ ወይም ስህተትሽ መማር ማለት ታዲያ ምንድነው? ትናንቴን አልደግምም ማለት አይደል? ያለፈውን ስህተትሽን አለመድገም አይደል? ያለፈው ስህተቴ አለልክ ሰዎችን ማመኔ ፣ ያለገደብ ራሴን እስኪያሳጣኝ ከሰው ጋር መቆራኘቴ አይደል? ያንን ነው ያስወገድኩት!! የሰዎችን ስሜት ለውጥ፣ ክፋት ወይም ቅንነት ልትቆጣጠሪ አትችዪም። ልትቆጣጠሪ የምትችዪው የራስሽን ስሜት እና ራስሽን ብቻ ነው። ሰዎች ለምን እንደእኔ አልተሰማቸውም ማለት አትችዪም። በጠበቅሻቸው ልክ ሳይገኙልሽ ሲቀሩ እንዴት ማለት አትችዪም! ምክንያቱም እንዳንቺ ጥበቃ ሳይሆን እንደራሳቸው ስሜት እና እውቀት ነው ህይወታቸውን የሚመሩት። እነሱን መቀየር አትችዪም! አንቺ ስለእነሱ ያለሽን መጠበቅ እና ቅርበት ግን መወሰን ትችያለሽ!! ከማንኛውም የሰው ፍጡር ምንም ባለመጠበቅ ውስጥ እና ባለመተሳሰር ውስጥ ራሴን አትርፊያለሁ።»

«በፍፁም ከማንም ምንም አልጠብቅም ወይም በምንም ማንንም አልደገፍም አልያም ከማንም ጋር በስሜት አልቆራኝም ማለት አትችልም። ያንተም ህይወት ከዛ እጅግ የራቀ ነው። ለምሳሌ ከልጆችህ ጋር ያለህን ቁርኝት እየው! ለእነርሱ የምትሆነውን መሆን ለማንምና ለምንም ስትሆን አይቼህ አላውቅም! ሌላ ምሳሌ እንጥቀስ ቢያንስ በትንሹ ከሰራተኞችህ ጥንቅቅ ያለ ስራ ትጠብቃለህ! አንተ ባትኖር እነርሱ እንደማይኖሩት ሁላ እነርሱ ባይኖሩም ያንተ ቢዝነስ የለም!»

«የሆነ ጊዜ ነግሬሻለሁ መሰለኝ። በህይወት ውስጥ ለደስተኛነት ከመኖር ትርጉም ያለው ህይወት መኖር እንደመረጥኩ። ከዛ የጨለማ ውድቀት በኋላ ስነሳ ባለፈው አንቺ እንዳልሽው ደስተኛ ህይወት ለመኖር ዳከርኩ። እኔ ባለፍኩበት ዓይነት መንገድ ላለፈ ሰው ደስታ ከፍርሃት ጋር የተለወሰ ነው። እዛ የዝቅታ ወለል ላይ ደርሰሽ ካላየሽው ምን እንደምል ብዙም ላይገባሽ ይችላል። የሆኑ የሆኑ ጠርዞች አሉ ፍራሃትሽ የሚፈጥረውን ሀሳብሽን እና እውነታውን መለየት የሚያስቸግርሽ ጠርዝ። እሱ ጠርዝ ላይ መቆም አለብሽ ትግል አይጠቅምሽም። ምክንያቱም ያቺን ጠርዝ ካለፍሽ አለቀ። አዲሱን አዲስ መስራት ስጀምር ማን መሆን እንደምፈልግ እና ምን ዓይነት ህይወት መምራት እንዳለብኝ የራሴን የህይወት መመሪያና መርህ መቅረፅ ነበረብኝ። የማንንም ህይወት መኮረጅ አያዋጣኝም ነበር ምክንያቱም ማንም እኔ ያለፍኩበትን መንገድ አላለፈም። ለውጡ ይሄ ነው ያለማንም እርዳታ ሲሆን ራስሽን የሰራሽው ምርጫ አለሽ ምንና ማን መሆን እንደምትፈልጊ። እናም ደስታን ውስጤ ስፈልገው ከፍርሃቴ ጋር የተለወሰ ነበር እና በምትኩ የምኖርለት እና ትርጉም የሚሰጠኝ ዓላማ ላይ ራሴን ቢዚ ማድረግን ተማርኩ። ስለዚህ ልጆቼን እና ስራን እንደ ዓላማ ነው የምወስዳቸው።»

«በዚህ መጠን ትኩረት እና ጊዜ ለምትሰጠው ዓላማ ታዲያ ምንም ዓይነት የስሜት ቁርኝት የለኝም ማለት ትችላለህ?»
«ራሴን አያሳጣኝ እንጂ ትኩረቴን የማሳርፍበት ዓይነት ቁርኝት አይጎረብጠኝም። ጥያቄው የሚመጣው እኔን ጥያቄ ውስጥ ካስገባ ነው። ከራሴ እና ከምንም ወይም ከማንም መምረጥ ካለብኝ ራሴን ነው የምመርጠው። እውነቱንስ እናውራ ከተባለ ማንስ ራሱን አይደል የሚመርጠው?»
«እንዴ በፍፁም ራስህን የምትሰጥለት ሰው አለ። ኤጭ በምን ላስረዳህ ፍቅርን ታጣጥልብኛለህ እንጂ (ይሁን ቀጥዪ ዓይነት በእጁ እና በጭንቅላቱ ንቅናቄ ምልክት አሳየኝ።) እሺ! አይደለም ፍላጎትህንና ስሜትህን ነፍስህን ብትሰጠው worth የሚያደርግ የፍቅር ልክ አለ» ስለው ከት ብሎ ሳቀ
«መቼም ፍቅር እስከመቃብርን ወይም ሮምዮ እና ጁሌትን አትጠቅሺልኝም! ለስሜት ትስስር ብለሽ ሞትን ከመረጥሽ ቂል ነሽ ነው የምልሽ!! እኔና አንቺ እውነቱን አይደል የምናወራው? እስከሞት ልወድ የምችለው ራሴን ብቻ ነው!!» ብሎኝ ዊልቸሩን አንቀሳቀሰ። ስሜቱ ጥሩ ስላልነበር ለሁለት ቀን መጻፋችንን አቁመን ነበር።

«ለምን ዛሬ ቦታ አንቀይርም? እዚሁ እንፃፍ ወይም ውጪ!» አልኩት
«ውጪ አሪፍ!» አለኝ። ለፀሃይ ሳሩ ላይ ፍራሽ እንድታነጥፍ ነግሬያት ኮምፒውተሬን ላመጣ ወደ ላይብረሪ ሄድኩ። ፍራሹ የተነጠፈበት ዛፍ ስር የጥላው ቅዝቃዜ እና የቅጠሉ ቀዝቃዛ አየር እያጫወተን እሱ ትራስ ደራርቦ ተጋድሞ እኔ ቁጭ ብዬ መፃፍ ቀጠልን።
«ምዕራፍ አምስት!» ብሎ ሊቀጥል ሲል ሳላውቀው ጮህኩ።
«እንዴ? አራትን በአንድ ገፅ ልታልፈው አትችልም! ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉኮ! ከዛ ሁሉ ድቅድቅ ጨለማ በኃላ አዲስን በቃ ሰራሁት ብለህ አንባቢን ልታሳምን አትችልም። ኸረ ደግሞ ፀዲን እና ሰብለን እዚህ ምዕራፍ ውስጥ ልናነባቸው አይገባም? ከቤተሰብህ ጋር እና ከማዕረግ ጋር የነበረህ ታሪክስ እንደዛው በእንጥልጥል ይዘጋል? »
«ኸረ ቆይ እሺ (ከት ብሎ እየሳቀ) የት ሄድኩብሽ አለሁ አይደል?» ብሎ ቀጠለ።
«ለተወሰነ ጊዜ የመረጥኩት መንገድ ራሴን በስራ ቢዚ ማድረግ ነበር። ጎን ለጎን ሙያዊ ድጋፍ ያስፈልገኝ ስለነበር ሳይካትሪስት ጋር ክትትል ማድረግ ነበረብኝ። በትክክል የሚጠቅመኝን ህክምና የሚያደርግልኝ ሳይካትሪስት ማግኘት እጅግ ከባዱ ነበር። አንዳንዶቹ ዝም ብሎ መስማት ይመስላቸዋል መሰለኝ ሙያው ማስታወሻ እና እስክሪብቶ ይዘው ያስለፈልፉኛል። አንዳንዶቹ የሚሰጡሽ ምክር ደግሞ ራሳቸው ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል። የብዙ ሳይካትሪስት ቢሮ እና ፊት ከጎበኘሁ በኋላ በትክክል ሙያውን የሚያውቅ ፣ ለእኔ የሚያስፈልገኝ ህክምና የቱ እንደሆነ የገባው ዶክተር አገኘሁ። ከጊዜ ወደጊዜ ለውጡን የምገነዘበው ዓይነት ነበር። ከህክምናው ጎን ለጎን ራሴን በማንበብ ጠመድኩ። ንባብ ስልሽ እገሌ የሚባለው ደራሲ እንዲህ ብሎ ፅፏል ወይም እንትን መፅሃፍ ላይ ያለው ገፀባህሪ ምናምን እያሉ ጥቅስ ለማጣቀስ የሚረዳ ማንበብ ሳይሆን ልኖረው የምችለው እና ከራሴ ጋር የማዋህደው እውቀት ፍለጋ ነበር የማነበው። ለምሳሌ ሰዎች ያነባሉ። አንድን ርዕስ ነጥለን ብንወስድ ስለይቅርታ እልፍ ጥቅስ ይጠቅሱልሻል። የማይኖሩትን ህይወት ሊመክሩሽ ይችላሉ። ነገር ግን በህይወታቸው ለመጎዳት ምክንያት የሆናቸውን ሰውጋ ይቅርታ ማድረግ ዳገት ይሆንባቸዋል። ያውቁታል እንጂ እውቀታቸው የእነርሱ አካል አይደለም ወይም አይኖሩትም። ከእውቀቴ ከስሜቴ ከህክምናዬ እና ካለፈው ልምዴ ጨምቄ የመኖሪያ መተዳደሪያዬን ፃፍኩ። በየቀኑ ያን ለመኖር ራሴን አሰለጠንኩ። አዲሱ አዲስ የዚህ ውጤት ነው። አለቀ!!» ብሎ ትንፋሽ ሰበሰበ። የምፅፈውን ገታ አድርጌ
«የተነበበ ሁሉ እኮ ግን አይኖርማ?»
«ያስማማናል። የትኛው እውቀት ብትኖሪው እንደሚበጅሽ የምታውቂው አንቺ ብቻ ነሽ!! የምርጫ ጉዳይ ነው።» አለኝና እንደገና ቀጠለ።
«ስለእነፀዲ ስለእውነት ምን መፃፍ እንዳለበት እንጃ!! ፀዲን መፅሃፍ መደብር ነው ያገኘኋት። እውነተኛ ሀቀኛ ግን የምትፈልገውን ጠንቅቃ የምታውቅ ብልህ ነበረች።በዛ ላይ ታነባለች። ለተወሰነ ጊዜ አብረን ካሳለፍን በኋላ ተጋባን። በጊዜ ብዛት የምትቀይረኝ ይመስላት ስለነበር ብዙ ታገሰችኝ። በተለይ ለልጅ የነበራት ፍቅር ግን በእኔ የምትቀይረው ዓይነት አልነበረም እና መለያየት መረጠች። አሁንም ቢሆን ጓደኛሞች ነን። አብረንም ሳለን ጓደኝነታችን ያመዝን ነበር። ከዚህ የተለየ ይሄ ነው የሚባል የተለየ ዓመታት አልነበረም። ሰብሊ ትለያለች በግልፅ ከስምንት ዓመት በኋላ ስለምትካፈለው ንብረት ብላ እንደምታገባኝ ነግራኝ ነው የተጋባነው። ቀጥተኛነቷን እወደዋለሁ። ጭንቅላቷ ያስባል። በባህል ወግ ሀይማኖት ተፅዕኖ ያልሳሳ ራሷን የሆነ ማንነት ነው ያላት። አልጋ ላይ ጎበዝ ናት! እውነት ለማውራት ለማቴሪያል ያላት ጥማት ትንሽ ከመጭነቁ ውጪ የማትሰለች ዓይነት ነበረች። እየቆየች ከእኔጋር ፍቅር እንደያዛት ነገረችኝ። ምላሹን እንደማታገኝ ስታውቅ ሂሳብ ሰራች። በዛ ላይ ዓለምን እየዞሩ ማየት ህልሟ ነበር። እኔ ደግሞ በተቃራኒው መብላት እና መጠጣት እንኳን እቤቴ የሚያስደስተኝ ሰው ነበርኩ። ሰለቸኋት! እንደሷ የመዞር አባዜ ካለበት አንድ ሀብታም ጋር ተጣብሳ ፈታችኝ።» ትንሽ እንደማሰብ ብሎ
«ስለማዕረግ እስከአሁንም ምንም መረጃ የለኝም። እውነት ለማውራት ማወቅም አልፈልግም። እንጀራ እናቴም ብትሆን ከዘመናት በኋላ ቢሮዬ አፈላልጋኝ እስከመጣችበት ቀን ድረስ የማውቀው ነገር አልነበረም። ይቅርታ ልትጠይቀኝ ነበር የመጣችው (በፌዝ ሳቅ አለ) አንተ ላይ ላደረስኩት በደል እግዜያብሄር ቀጥቶኛል። ልጄ እንኳን ይሙት ይኑር አላውቅም! አለችኝ»
«እና ምን አልካት? ይቅር ብዬሻለሁ አላልካትምኣ?» ያልኩት አስቤው አልነበረም። ከት ብሎ ሳቀብኝ
« የምታምኚው አምላክ ይቅር በሉ ይል የለ? አየሽ ቅድም ያልኩሽን? የምናውቀውን ሁሉ አንኖርም እናወራዋለን እንጂ እኔን ለበደለችኝ በደል አንቺ ስላመመሽ ይቅር መባል እንደሌለባት አሰብሽ።» አለኝ ሳቁን እየቀጠለ
«እግዜር ራሱ ይቅር የሚላት አይመስለኝም። ይልቅ ንገረኝ።»
«አላልኳትም። በተቃራኒው ውስጤን በጥሩ እምነት ሞልቼዋለሁ ብዬ ያመንኩትን የተጠራጠርኩት የዛን ቀን ነው። ያቺ ስትራመድ ሞገሷ መንገዱን የሚቀድላት የምትመስል ሴትዮ የእርሷ ያልሆነ ሰውነት እና አለባበስ አጅቧት ቢሮዬ ሳያት የማላውቀው ጭካኔ ነው የተሰማኝ። ዘበኞች ጠርቼ እንዲያስወጡልኝ ሳደርግ እያለቀሰች እንኳን ልቤ ምንም ርህራሄ አልተሰማውም። ለቀናት ስላየኋት ብቻ ስሜቴ ተረበሸ። ያለችበት ሁኔታ እንዳለችው ስቃይ ከሆነ ነፍሴ ደስታን መቃረም ስለሻተች እንዲያጣሩልኝ አደረግኩ። የማይሆን ባል አግብታ ቤቷን እና ንብሯቷን አሽጧት እንደእናቴ ሰካራም ሆና ከንቱ ህይወት እንደምትኖር ሰማሁ። ከዛ በኋላ ያየኋት ባለፈው እቤቴ ስትመጣ ነው። አደጋ እንደደረሰብኝ ስታውቅ ጮቤ እንደረገጠች አልጠራጠርም። ወይም ሽባ ስሆን የሚራራ ልብ ይኖረኝ ከሆነ ልታረጋግጥ ይሆናል። አላውቅም! ማወቅም አልፈልግም! ሳያት ሲኦል ነው ትዝ የሚለኝ!» አለኝ እየዘገነነው።
የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ሰው ብንን ብሎ። « የሆነ ቀን ቁጭ ብዬ ቴሌቭዥን ሳይ ሉሲን አየኋት። (ሳቅ ብሎ) ተዋናይ ሆና! በቲቪ ባየኋት በወራት ውስጥ ታዋቂ ሾው ላይ ኢንተርቪው ስትሰጥ ያልሆነ ነገር ተናግራ ህዝበ ኢትዮጵያ በስድብ ሲቀባበላት ከረመ። ባጋጣሚ ወሬውን ሰምቼ ፕሮፋይሎቿን ሳጣራ እያለቀሰች ህዝቡን ይቅርታ የጠየቀችበት ቪዲዮ አየሁ። የኛ ህዝብ የሚገመት ስድቡን እና ዘለፋውን ጨመረላት። ላገኛት ፈለግኩ ምናልባት ልጅ ስለነበረች ወይም አሁን አወዳደቋ ተሰምቶኝ፤ እድል ሰጥቻት ለምን ያንን እንዳደረገች መስማት ፈለግኩ። አገኘኋት! ያለችኝን አመንኩ። እሷ የእናቴ እና የእናቷ መጠቀሚያ ብቻ ነበረች። በሰዓቱ አባቷ ታሞ ብዙ ብር ያስፈልጋቸው ነበር። ያን እኔም አውቅ ነበር። አባቷን ለማዳን የሚጠበቅባት ያቺን ድራማ መስራት እንደነበር እና የቀረውን ተንኮል እና ማስረጃ እነርሱ እንደሚጨርሱት አሳመኗት። ያን በማድረጓ ለተወሰነ ዓመትም ቢሆን ለአባቷ እድሜ ቀጥላለታለች። የሚገርመው <አንተን ጎድቼ ባይሆን አባቴን ያተረፍኩት እመርጥ ነበር። ምንም አማራጭ በሌለበት ግን አባቴን በመምረጤ አልተፀፀትኩም! ለደረሰብህ ነገር ግን ይቅርታ!> ነበር ያለችኝ። (ፈገግ አባባሉ ስለሆነች የሚወዳት ልጅ የሚያወራ እንጂ መቀመቅ ስላስወረወረችው ልጅ የሚያወራ አይመስልም ነበር።)»
«ልገምት በህይወቷ ውስጥ የሆነ መልካም ነገር አድርገሃል?» አልኩት ከፈገግታው እየገመትኩ
«በጣም ዲፕረስድ ሆና ነበር። ከሀገር ወጥታ የምትማርበትን መንገድ አመቻችቼላት እንግሊዝ ነው ያለችው።» አለኝ
«ግራ የሆንክ ሰው ነህኮ!» አልኩት
«አውቃለሁ!! አትወጂውም ግን አንድ ሀሳብ አለኝ! ምዕራፍ አምስትን እኔ ልፃፈው! አንቺ ከፃፍሽው አስቢው በየመሃሉ የመልስ ምት ልትሰጪኝ ነው። ከፈለግሽ እኔ ልፃፈውና እያነበብሽ ማውራት እንችላለን!! ከዛ ደግሞ ስላንቺ ላንቺው መተረክ ደስ አይልም። ነፃነቴን አጊንቼ እራሴ ልፃፈው እና አንብቢው።» ልደርስበት የጓጓሁበትን ምዕራፍ ለመፃፍ ስለተከለከልኩ ከፋኝ ግን ደግሞ ነፃነት ያለውን አመንኩለት እና ቅር እያለኝም ቢሆን ተስማማሁ። ኮንፒውተሬን ዘግቼ ዝም ተባብለን ፍራሹ ላይ ጋደም እንዳልን ከንፋሱ ጋር ማውራት ያዝን
(የምላችሁ ሰው ሆኖ ሀሳቡ የማይሳካለት እኔ ብቻ አይደለሁም። 🤣🤪🤣🤪 እና ምን ለማለት ነው ልጨርስ እና ልፖስተው ካልኩ ለሊት ይሆንባችሁና ልትገሉኝ ነው። ውሎዬን እንዴት እንዴት አድርጌ እንደፃፍኩኝ ብታውቁልኝ!! እና አልጨረስኩማ ማነህ እናሲዝ ያልከኝ ልጅ በቃ አምኛለሁ በስንቷ ነበር ያስያዝነው? ሳስበው ጭንቅላቴ ውስጥኮ ሁለት አንቀፅ ነበር ስፅፈው ይሄ ሁሉ ከየት አባቱ እንደሚመጣ 😂🤣😂🤣)
ሰዓት ምናምን ብላችሁ እንዳትነጫነጩ ጌታን አኮርፋችኋለሁ። ከአቅሜ በላይ ባይሆን አላሳልፍባችሁም ታውቃላችሁ!!

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሀያ አንድ)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...