Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስር)

«የእናቱን ለቀናት የቆየ የሚሸት ሬሳ ታቅፎ ከጎሮሮው የማይወጣ ጩኸት ጮኸ። ድምፁ ከጉሮሮው እንደማይወጣ ቢያውቅም በሆነ ተዓምር የሆነ ሰው እንዲደርስለት ተመኘ። በማይሰማ ድምፅ ሊደርስለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ስላወቀ አይኞቹን ጨፍኖ <አምላኬ ሆይ እባክህ ድረስልኝ? እባክህ ድረስልኝ? እባክህ? ……… > እያለ በልቡ የፀለየውን ባይሰማው እንኳን እንባውን አይቶ እንዲራራለት እራሱ እግዚአብሔር ቢያጠራቅመው ለአንድ ክረምት የሚበቃውን እንባ አነባ። እግዚአብሔር ግን ለልቡም ፀሎት ለዓይኑም እንባ መልሱ ዝም ነበር! ዝም!! » የመጨረሻዎቹ ቃላት ላይ ድምፁ እየቀነሰ፣ እየሻከረ መጣ። ከመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር በኋላ አልፃፍኩም። ጣቶቼ አደጋ ከደረሰባቸው የእርሱ ጣቶች በላይ ተንቀጠቀጡ።
«ስንት ዓመቱ ነበር?» አልኩት ቀና ብዬ
«አስራ ሁለት» አለኝ። ስሜቱ መረበሹ በግልፅ እያስታወቀበት አስተካክሎ መግፋት የለመደውን ዊልቸር እየገፋ ላይብረሪ ውስጥ ወዲህ ወዲያ እያለ። የህይወት መርሆቹ እና የሚያስብበት ጥግ፣ ሀሳብን የሚገልፅበት መንገድ ሁሌም ሲያስገርመኝ <አንተኮ መፅሃፍ መፃፍ ነበረብህ!> እለዋለው። ሁሌም መልሱ ተመሳሳይ ነበር። <መስራት ሲደክመኝ ወይ ማቆም ስወስን …… በደንብ ጊዜ ሲኖረኝ እፅፋለሁ። አንድ መፅሃፍ ይኖረኛል። እሱም የራሴ ባዮግራፊ ነው የሚሆነው።>

ከቀናት በፊት ከተለመደው የፊዚዮቴራፒ ህክምናው እየተመለስን ድንገት የሆነ መገለጥ እንደበራለት ሰው።
«አሁን ጊዜው አይመስልሽም?» አለኝ። ቀጠል አድርጎ ግራ በመጋባት ለጥያቄ የተሰናዳ አፌን ከመክፈቴ በፊት « መፅሃፌን ለመፃፍ?»
«ጣቶችህ አሁንም ቢሆን ይቀራቸዋል። ዶክተሯን አልሰማሃትም? 100 ፐርሰንት እስኪሆን ጫና እንዳታበዛበት ብላሃለችኮ!»
«አውቃለሁ! እኔ እየነገርኩሽ አንቺ ትፅፊልኛለሽ ብዬ ነበር ተስፋ ያደረግኩት!!»
«መቼ እንጀምር?»
ሚስጥር ማወቅ ነው ያጓጓኝ። እንጂ ከእርሱ ትናንትጋ ራሴው ተላትሜ አዙሪት እንደሚሆንብኝ አላሰብኩም። ሚስጥር ማወቅ የሆነ የመለኮታዊነት ዓለም ተቋዳሽ የመሆንን ስሜት ስለሚፈጥር ይመስለኛል ደስ የሚለው። ስለሆነሰው ከአምላክ ውጪ ማንም ሰው አያውቀውም ብለን የምናስበውን ማወቅ …………

ያቺ ባለፈው የመጣችው ሴት ማንናት? ያቺ ድሮዬ ውስጥ ነበረች ያላት ሴት ምን አይነት ነበረች? በቃ ስለእርሱ ማወቅ። እሱ ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ ይለኛል እንጂ ድሮ ቢቀብሩት እንኳን አራሙቻውን በጣጥሶ ዛሬን የማነቅ ጉልበት እንዳለው አውቃለሁ። አንዳንድ ድሮ ይብሱኑ ክስተቱ ከሆነበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ ላይ ይበረታል።
«አንቺ ብትሆኚ ታሪክሽን ከምንድነው የምትጀምሪው?»
«ከጡዘት! በህይወቴ ውስጥ ወሳኙ ነው ከምለው ምእራፍ! ከዛ ታሪኩን ወደፊትና ወደኋላ አጫውተዋለሁ። ሲጀመር ግን አንባቢን ሰቅዞ ከሚይዝ ቦታ ነው የምጀምረው።»
«ዝግጁ ስሆን እነግርሻለሁ።» ካለኝ ከቀናት በኋላ ነው ላይብረሪው ውስጥ የተከሰትነው። የምለው ጨነቀኝ። ያለፈውን ለማወቅ ከመጓጓቴ በላይ ገና ሳልጀምረው ልቤ ቀዘቀዘ።
«ለምን አሁን?» አልኩት ጭንቅላቴ ያሰበውን አፌ ሳያስፈቅደኝ
«ለምን አሁን ምን?»
«ለምን አሁን እንዳውቅ ፈለግክ? እንደዛ ላውቅህ ስቧችር ድሮዬ ውስጥ አትፈልጊኝ ብለኸኝ እኔን ግን በድሮህ እየቀጣኸኝ እንደዛ ስለምንህ ዝም ብለህ…….. ዛሬ ለምን?»
በረዥሙ ተነፈሰ እና እየመሰለው ምንም እንዳልመሰለው ሲሆን የሚያመጣትን ፈገግታ ፈገግ ብሎ
«መፃፉን ብትቀጥዪ ታውቂው የለ?»
«እሺ በቃ ወይ ደስ ከሚለው ህይወቱ እንጀምር?» አልኩት።
«ኦኬ! ደስ ከሚለው? ደስ ከሚለው ሆኖ አሁንም ጡዘት ያለበት? » እንደማሰብ ብሎ
« ሰውነቱ ከመቀዝቀዙ የተነሳ ለሰዓታት የተኛበት አንሶላ እንኳን ሳይሞቅ ድጋሚ ተመልሳ በሩን ከፍታ ገባች። እንደቅድሙ በሩን አላባበለችውም። ሆነ ብላ በሩን አስጩኻው ገብታ <ምንድነው ያደረግኩህ? ንገረኝ ምንድነው ጥፋቴ?> (ከዚህ በኋላ ያለውንም አልፃፍኩትም። አቁሜ ግን ቀና ማለት አቅቶኝ እየሰማሁት ነው።) <እንፋታ!> ሲላት ራሱን ሰማው»
ከተቀመጥኩበት ዘልዬ ተነሳሁ። «ይሄ ነው ደስ የሚለው ዘመኑ? ……. እሺ በቃ እኔ ለመፃፍ ዝግጁ አይደለሁም።!» ብዬ ከላይብረሪ ወጣሁ። ማልቀስ ካቆምኩ እጅግ ሰንብቼ ነበር። ማልቀስ አማረኝ።
እሱ የደስታው ጡዘት ብሎ የጀመረበት ታሪካችን የእኔ የመድቀቅ ጡዘት ነበርኮ! በቃ አለም ሁላ ከእርሱ ጋር በአሻጥር ትሰራ ይመስል ቀስ በቀስ የመኖር ማገሮቼ የምላቸው ሲመዘዙ ዓቅም አጥቼ ከማየት ውጪ ምርጫ አጥቼ ተምዘግዝጌ የወደቅኩበት ጡዘት ……
የዛን እለት … እንፋታ ካለኝ በኃላ … ፀዲጋ የሄድኩ እለት …
«እንዴት ቻልሽው? እንዴት ረሳሽው?» አልኳት ፀዲን
« የማትክጂው ሀቅ <ሰዎች ከአጋራቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው የስሜት መጠቃቀም ሲጎድል ለዛ ሰው ያላቸው ስሜት ይጎድላል > የሚለው ነገሩ ልክ ነው። (ሳቅ አለች እዚህጋ የድሮውን በማስታወስ ዓይነት) የሆነ ጊዜ ላይ የተከራከርሽውን ፍልስፍናውን ሁሉ በራስሽ ላይ prove ስታደርጊለት ራስሽን ታገኚዋለሽ። ያለምንም ምላሽ ማፍቀር ይደክማል። የሆነ ቀን ራስሽን ሲደክምሽ ታገኚዋለሽ። ከፍ ሲልም በተጎዳሽው ልክ ስትጠዪው ራስሽን ታገኚዋለሽ።!»
«ይቅርታ አድርጊልኝና the most romantic የምትዪውን ቅፅበት ንገሪኝ? እባክሽ እንደድፍረት አትውሰጂብኝ በቃ ጭንቅ ብሎኝ ነው»
«ኸረ ችግር የለውም በናትሽ ይገባኛል!» ብላ እጄን ስትይዘኝ እንባዬን እንዴት ቁም ልበለው? ደንግጣ አቀፈችኝ። ከሳጌ ጋር እየተናነቅኩኝ አስሬ «ይቅርታ!» እላታለሁ።
«ወይኔ ፀደይ! አዲስ ምንድነው ያደረግከው?» አለች የሆነ ጣሪያው ላይ ሆኖ የሚሰማት ትንሽዬ አምላክ ይመስል። አባብላኝ ስታበቃ።
«የመጨረሻ የምንለያይ ቀን (እሩቅ የተጓዘ ፈገግታ ፈገግ አለች) <ለነበረን የሚታወሱ ትዝታዎች በጣም ነው የማመሰግነው። ለምትወልጃቸው ልጆች የምትገርሚ እናት እንደምትሆኚ አውቃለሁ! ካስፈለግኩሽ የልጅ ልጆች ወልደሽም ቢሆን አስታውሰሽ ከደወልሽልኝ የምችለውን አለሁ። ከእኔ ጋር ላሳለፍሽው ምርጥ ጊዜ እስካሁን ሰጥቼሽ ለማላውቀው ስጦታዎች ምትክ እና ለወደፊት ህይወትሽ መጀመሪያ ይሆንሻል።> ብሎ ንብረቱ ቢሰላ የሚያወጣውን እኩሌታ ገንዘብ የሰጠኝ።» ዝም ስትል ቀጣዩን እየጠበቅኩ እንደሆነ ገብቷት እንደመባነን ዓይነት« that was the most romantic day I ever had with him» ብላ ጨረሰችው።
«አላውቅም! ውላችሁን ስላፈረስሽ ንብረቱን ያልተካፈልሽ ነበር የመሰለኝ!»
«አዲስ ጥሩ ነገር ሰራሁ ብሎ አይነግርሽም! ራስሽ ካልደረስሽበት በቀር! ጥሩ ስለሆነ እንድትወጂው አይፈልግም ራሱን ስለሆነ እንድትቀበዪው ነው የሚፈልገው። ሲመስለኝ ለማንም ሰው ደስታ ሀላፊነት መውሰድ አይፈልግም። ችግሩ ደስታው አይደለም። ቀጥሎ ለሚመጣው ሀዘን ራሱን ተወቃሽ ማድረግ ስለማይፈልግ ይመስለኛል። ለደስታው ሰበብ የሆንኩትን ሰው የሆነ ቀን ለሀዘኑ ሀላፊ ነኝ ብሎ ስለሚያምን ይመስለኛል።»
«ደስተኛ ነሽ?» የሚለው ጥያቄ ከአፌ ከወጣ በኋላ ስላለፈው ይሁን ስለአሁኑ ህይወቷ የጠየቅኳት ራሴው ግራ ገባኝ።
«ውይ በጣም! ከአዲስ ጋር ያሳለፍኩትን ግዜ እወደዋለሁ። እንደሰው ብዙ ያደግኩበት እና የተማርኩበት ጊዜዬ ነው። ስላገባሁትም! ስለፈታሁትም! በሁለቱም ውሳኔዬ ደስተና ነኝ!! አሁን ደግሞ እንደምታዪው {ብላ ከባል እና ሁለት ልጆቿ ጋር የተነሳችውን ፎቶ አሳየችኝ} በጣም! ባሌን እወደዋለሁ! አዲስ በሰጠኝ ስጦታ ነው የራሳችንን ቢዝነስ ጀምረን የምንኖረው። {ሳቅ ብላ } ህይወት ደስ ይላል። »
ስታወራኝ አዲስ እሷ ውስጥ ምን እንደሳበው ለማወቅ አልተቸገርኩም። ሽራፊ አዲስ ውስጧ አለ። የቀለለ ስሜት እንዲሰማኝ ልታስቀኝ ስትሞክር ቆይታ ወደቤቴ ተመለስኩ።

«የአዲስ ሚስቶች ማህበር ነገርማ መመስረት አለብን! ብታዪ አሁን እኔና ሰብሊ በጣም ጓደኛሞች ነን። የሆነ ቀን አብረን ሻይ መጠጣት እንችላለን!» ብላ እንደቀልድ ያወራችውን አሰብኩት። ከእነርሱ ጋር ሻይ መጠጣት አልነበረም ፍላጎቴ! ፍቅር በዚህ ልክ ያቃቂላል? የሚስቶቹን ታሪክ እየሰማሁ ከራሴ ጋር በማነፃፀር መፍታት ያልቻልኩትን እዚህም እዛም የተበታተነ አመክንዮ አጋጭቼ ራሴን ለማፅናናት ነው። እቤት እንደተመለስኩ የጣልኩትን ሰውነቴን ሰብስቤ አፋፍሼ በቁሟ ያለች ሴት ለመምሰል ተጣጥቤ ለባበስኩ።

አራቱን ዓመት አብረን ስንኖር ምን ብለብስ እንደምደምቅለት አስቤው አላውቅም። ልብሴን አይቶ አያውቅም! ሁሌም እኔን ነው የሚያየው የነበረው። አሁን ግን እኔን ማየት አቁሟል። የልብስ ምርጫውንም አላውቅም! አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል ቆይቼ የሆነ ቀሚስ ለበስኩ። እራት ላይ ተቀብቼ የማላውቀውን ቀይ ሊፒስቲክ ተቀብቼ ተገኘሁ። ለወጉ እልሉን ፊቴ አስቀምጠዋለሁ እንጂ ከሁለት ጉርሻ በላይ ማላመጥ ካቃተኝ ሰንብቻለሁ።
«ደህና ዋልክ?»
«ደህና! ቀንሽ እንዴት ነበር?» ቀና እንኳን ብሎ አላየኝም። እንዲያየኝ ስለፈለግኩ ብቻ
«ዛሬ ፀዲን አገኘኋት!» አልኩት። ባለመገረም ቀና ብሎ አይቶኝ ዓይኖቹ ለውጦቼን በአንድ አሰሳ ካዳረሱት በኋላ ተመልሶ ወደ እህሉ እያጎነበሰ
«ጥሩ ጊዜ አሳለፋችሁ?» አለኝ።
«እ!» አልኩኝ ልቤ ዝቅ እያለብኝ። በልቶ ሲጨርስ ተነስቶ ወደላይብረሪው ሄደ። ወደመኝታ ቤቴ ገብቼ ጉልበቴን አቅፌ ለሰዓታት አለቀስኩ! ሰው ለምን አልወደደኝም ተብሎ ይለቀሳል? ቂልነት እየመሰለኝም ማልቀሴን አላቆምም!! በየቀኑ የማልበላውን እራት ለመብላት የማያየውን መዘነጥ እየዘነጥኩ እቀርባለሁ። የተለመደውን እይታ ገርቦኝ የራሱን እራት በልቶ ወደላይብረሪው ከዛም ወደአንዱ እኔ የሌለሁበት ክፍል ይሄዳል። ለቀናት ለሳምንታት…… የሆነኛው ቀን ወንድሜ በጠዋት ሲበር እቤቴ መጣ። ያየኝ ሰው ሁሉ <ምነው ደህና አይደለሽም?> የሚለኝን አይነት የሰውነት መቀነስ ሾቄ፣ በትክክል ማሰብ ስላቃተኝ ትምህርት ቤት መሄዱን ትቼ፣ ሰኞ እና ቅዳሜ ተምታተውብኝ፣ ጥቅምትና ሀምሌ ተሳክረውብኝ ፣ ቀንና ማታው ተምታቶብኝ ……….. “ ምነው እህቴ ደህና ነሽ ግን?» የሚል ሰላምታ አልነበረም ከአፉ የወጣው።
«እንዴት በቤተሰቦችሽ ትጨክኛለሽ? ጎዳና ቢወጡ ኩራትሽ የሚሆን ነው የሚመስልሽ?» በሚል ወቀሳ ነው የተቀበለኝ። የራሴ ችግር ያለብኝ አይመስላቸውም፣ የራሴ መከፋት ያለብኝ እንደሆነ አያውቁም፣ እኔ በቃ የሆነ የተንጣለለ ቤት ውስጥ የምኖር የኤቲኤም ማሽን ብቻ ነኝ ለእነሱ ሲቸግራቸው እንጂ ቸግሮኝ ይሆን ትዝ የማልላቸው፣ ሲከፋቸው እንጂ ከፍቶኝ ይሆን የማልታወሳቸው፣ ልደርስላቸው እንጂ ግዴታ ያለብኝ ሊደርሱልኝ እሩቃቸው ነኝ። አባቴ ድሮ የተወውን ቁማር በስተእርጅና አዲስ ካፈራቸው ወዳጆቹጋ ሲቆምር ቤቱን አስበልቶ ነው ልክ የእኔ ጥፋት ይመስል በየተራ እየመጡ የሚያስጨንቁኝ።
«ምናገባኝ! ገዝቼ የሰጠሁትን ቤት አላወጣሁበትም ብሎ አይደል በማይረባ ገንዘብ ያስያዘው? እንዴ ቆይ እሺ በምን እዳዬ ነው የቁማር ብር የመክፈል ግዴታ እንዳለብኝ የምታስቡት?»
«ምንም ቢሆንኮ ቤተሰቦችሽ ናቸው።» ያለበት አባባል። ውስጡ ምንአይነቷ ክፉ ነሽ የሚል ቅላፄ ነበረው። ትቼ ነበርኮ! የማልችለውን ለመቻል መጋጋጥ አቁሜ ነበር። ያኔ ያጎበዘኝ አዲስ ነበር። አሁን ግን ግራ ገባኝ የምርም ዝም ብላቸው እንዴት ይኖራሉ? በዛ ላይ ታናሽ እህቴ ስራም ሳይኖራት ለልጁ ወተት እንኳን ከማይገዛ ወንድ ወልዳ እቤት እነሱጋ ናት። በየወሩ ለቀለብ የምቆርጥላቸው ከአዲስ ጋር ተነጋግረን በጋራ ከምንጠቀመው አካውንት ነው። ጭራሽ አባቴ ሲቆምር ቤቱን አሲዞ ስለተበላ 400 ሺህ ብር ካልሰጠኸኝ ብዬ ልጠይቀው? አይሆንም!! ያውም አሁን!!
«አሁን ምንም ማድረግ አልችልም! የዛን ያህል ብር ከየትም ላመጣ አልችልም!» አልኩት። የሆነ እኔጋ ያስቀመጠውን ብር የከለከልኩት እንጂ እርዳታዬን የፈለገ አይመስልም አበሰጫጨቱ። ጥሎ ከቤቴ ወጣ!! የዛን ቀን እራት ሳልቀርብ ተውኩት። አቅም አነሰኝ። የራሴን ስቃይ እየዛቅኩ ስባዝን፣ የቤተሰቤን ሁኔታ እያሰላሰልኩ ስተክን በሬ ተንኳኳ! ከሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደመኝታ ቤታችን መጣ! ሁሉም ነገር ረጭ አለብኝ!! እረሳሁት! ድካሜን እረሳሁት! ስቃዬን እረሳሁት! ቤተሰቦቼን እረሳኋቸው! እሱ ስጎድልበት ሊፈልገኝ መጣኣ!!
«ደህና ነሽ? እራት ላይ ቀረሽ?» አለኝ በሩ ላይ እንደቆመ። ልለው የምፈልገው ብዙ ነው ጭንቅላቴ ውስጥ የሚራወጠው። <ግድ ይሰጥሃል? ብቀርብም ባልቀርብም ጠረጴዛውን ከከበቡት ወንበሮች ለይተህ አታየኝም ብዬ እኮ ነው የቀረሁት፣ ዓለም ካንተ ጋር አብራ ዞራብኝ ነው፣ ምግብ አልወርድ ብሎኝ ነው> ብዙ ልለው አስባለሁ። አንዲት ቃል ከአፌ ከወጣች ለቅሶዬ እንደሚቀድመኝ ስላወቅኩ ዝም አልኩ። ዋጥ!!
«ፀሃይ ዛሬ አሞሽ እንደዋለ ነገረችን፣ እህልም እየበላሽ እንዳልሆነ፤ ሀኪም ቤት ልውሰድሽ?» <ህመሜኮ አንተ ነህ ሀኪም ምን ይፈይድልኛል? > ማለት እፈልጋለሁ። ከአፌ የሚወጣ ቃል ግን የለም። አጠገቤ ደርሶ አልጋው ላይ ሲቀመጥ ማሰቢያዬ ተንገዳገደ። እጁን ግንባሬ ላይ አድርጎ «ታተኩሻለሽኮ! ሀኪም ቤት እንሂድ?» ደግሞ ተነስቶ አንደኛውን መስኮት እየከፈተ «ቤቱኮ ታፍኗል! ንፋስ ገብቶበት ያውቃል?»
ፊቴን አዞርኩ። ትራሴ ውስጥ ሸፈንኩት። ትንፋሽና ሳጌን ውጬ መዋጥ የማልችለውን እንባዬን ፈቀድኩለት። ለተወሰነ ደቂቃ እንደቆመ ይሰማኛል። ከዛ ቀስ ብሎ በሩን ዘግቶት ወጣ!! እኔም በነፃነት እሪታዬን አስነካሁት። በሚቀጥለው ቀን እራት ስላልሄድኩ ይመጣል ብዬ ጠበቅኩት። ሲመጣ እንደትናንቱ ዝም አልልም! እንዲህ እለዋለው! እንዲያ እለዋለሁ ! እያልኩ ጠበቅኩት! አልመጣም! ከቀናት በኋላ እጅግ በጣም በጠዋት ቀሰቀሰኝ።
«ሰዎች ሊያናግሩሽ መጥተዋል!» እንዲህ ሲጨነቅ አይቼው አላውቅም!! ቁምሳጥኔን ከፍቶ የምደርበው ልብስ እንደመፈለግ አደረገው።
«ማነው በዚህ ጠዋት የሚፈልገኝ?» በደመነፍስ ሲሊፐሬን አጥልቄ ያቀበለኝን ጋውን ለብሼ ወደሳሎን እየሄድኩ የመጡትን ሰዎች ሳያቸው ሳይነግሩኝ በፊት ገባኝ!! አባቴ!! እናቴ እንደትናንት ደውላ አባትሽ ደምግፊቱ ተነስቶበታል ሲነጋ መጥተሽ እዪው ብላኝ ነበር። እሱን ዞሬ አየሁት! መልሼ እነሱን አየሁ! እግሬ መቆም አቃተው! ዘሎ እጆቹን ከስሬ ሲያነጥፋቸው፣ እጁ ላይ ራሴን ስጥል፣ አይኔ ከመከደኑ በፊት ከጉሮሮው የማይወጣ ጩኸት እያማጠ ሊጮህ ሲታገል አየዋለሁ። ስቃይ ያለበት ፊት

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስራ አንድ)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...