Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አንድ)

«ሞቼ ቢሆን ኖሮ ደስ ይልሽ ነበር አይደል?» አለኝ በወጉ ማሽከርከር ያልለመደውን ዊልቸር እየገፋ ወደሳሎን ብቅ እንዳለ። ፊቱ ምሬት ወይ ጥላቻ በቅጡ ያልለየሁት ስሜት ይተራመስበታል። ዝም ያልኩት መመላለሱ ልቤን ስለሚያደክመኝ ነበር። በጎማው እየተንቀራፈፈ አጠገቤ ደርሶ « ንገሪኛ ደስ ይልሽ ነበር አይደል?»
«አይከፋኝም ነበር።» መለስኩለት። እግዚአብሔር ይሁን ሰይጣን አደጋውን ያደረሱበት አንዳቸው ምርጫ ሰጥተውኝ ቢሆን ኖሮ እንኳን የቱን እንደምመርጥ እንጃ! (ሰዎች በህይወታቸው የሆነ የከፋ ነገር ሲገጥማቸው <እግዜር ሊያስተምረው ነው!> ይሉን የለ? ያው ራሳቸው ሰዎች ደግሞ የክፉ ነገር ምንጭ ሰይጣን ነውም ይሉናል። ነገሩ ለእኔ ጭንቅላት የተሳከረ ነገር ስላለው ነው ከሁለቱ አንዳቸው ቢሆኑ ያልኩት!! አስቡት የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነው አምላክ ፣ ለሰው ልጅ በምርጫው እንዲኖር ነፃነትን የሰጠው የነፃነት አምላክ ሊያስተምር ሲፈልግ በክፉ ሲቀጣ? አንዳንዴ ፈጣሪ በክፉ አይፈትንም ብዬ ሳስብ ለራሴ የምሰጠው ማመሳከሪያ የመፅሃፍ ቅዱሱ እዮብ ነው። ፈጣሪ ጥበቃውን እንደእዮብ ያነሳብህና ለክፉ አባት አሳልፎ ይሰጥሃል እንጂ ራሱ አምላክ ክፉውን አያዘንብም! ከዛ ግን ሞትና የሲኦል መኖር ይሄን እሳቤዬን ከአፈር ያደባይብኛል። ብቻ ማናቸውም ይሁኑ የዛን ቀን እየነዳ የነበረውን ጣዖቱ የነበረ መኪና ከገደል ፈጥፍጠውልኛል። እግዜር ይስጣቸው!!_)

«እግዜሩ እንድትበቀዪኝ እድሉን እየሰጠሽ ይሆናልኮ! ለምን ደግ እየሆንሽ የተሰጠሽን እድል ታባክኛለሽ?» አለ የሰራሁለትን ምግብ ላጎርሰው እጄን ስዘረጋ! ከፍቅሬ ጥልቀት አይደለም የማጎርሰው። በአደጋው ምክንያት እጁ እንደፈለገው ስለማይታዘዝለት እንጂ።
«ከዛስ? በእኔ ክፉት ክፉትህን ልታቀል? በእኔ ሀጢያት በደልህን ልትሰርዝ? በእኔ በቀል ሀጢያትህን ልታወራርድ? በፍፁም ያን ደስታማ አልሰጥህም!!»
በቀል ዓይን ላጠፋ ዓይን ማጥፋት ፣ የገደለን መግደል …………… ባጠቃላይ በቀል ለክፋት ክፋትን መመለስ ነው ያለ ማን ነው? ለሰራው ስራ የስራውን መኸርማ መሰብሰብ የተፈጥሮ ህግም አይደል? ያጭዳል!! ምኗ እንከፍ ብሆን ነው <ወይ በገደልከኝ ወይ በገደልከው> ብዬ ስማፀን የከረምኩበትን ሰው እንዳይሞት እንዳይድን አድርጎ እጄ ላይ ሲያስቀምጠው በክፋት የምበቀለው?
ገብቶታል። ጤነኛ ሆኖ ሰራተኛ ያበሰለውን ምግብ የምንበላ ሰዎች ራሴ የሚበላውን ጓዳ ገብቼ ሳበስልለት በደሉን እንደማላቀልለት ገብቶታል። እልህ የሚይዘው ከእኔ ይሁን ከራሱ እንጃ ርሃብ አንጀቱን ካልፋቀው በቀር እሺ ብሎ አይበላም። አይጠይቅምም!! ከሆስፒታል እቤት የገባ ሰሞን <ነርስ ይቀጠርልኝ> ሲል <እኔ ሚስትህ እያለሁ እንዴት ገበናህን ባዳ ያያል?> ብዬው አልጋው ላይ ሲፀዳዳ እሱንም አልጋውንም ሳፀዳ በቀላሉ ይቅር እንደማልለው ገብቶታል። ከሀዘኔታ ልብ ወይም ከፍቅር ፅዋ ከፈለቀ ደግነት እንደማልንከባከበው ያውቃል። ግን ደግሞ በደሉን በበደሌ አላለቀልቅለትም። እሱም ያ ገብቶታል።

ሞቶ ቢሆንና እንደወጉ ነጠላዬን አዘቅዝቄ ከሬሳው ጋር ወደ ቀብር እየሄድኩ ምንድን ነበር የምለው? ሰው ምን ይለኛል ብዬ ደረቴን እደቃ ነበር? ወይስ <ተመስገን ገላገልከኝ> እያልኩ በፈገግታ ከአፈሩ ጋር የሰባት ዓመት ትዳራችንን ወደ ጉድጓዱ መልሼ እመለስ ነበር? የቱ የበለጠ ደስ ይላል? ሞቱ? ወይስ ስንክልክሉ የወጣ አካላቱን እና ከተሰበሩት አጥንቶቹ እኩል እንክትክት ያለ ትህምክቱን፣ ትእቢቱን፣ ሞራሉን ፣ አምላክ ነኝ ባይ ልቡን ………. ታቅፎ ……….. እንኳን እኔ ላይ ራሱ ላይ እንኳን የማዘዝ አቅም የሌለው ከንቱ ሆኖ ማየቱ? የቱ የበለጠ ደስ ይላል? ወይስ ከነጭራሹ ደስታ አለው? ካለመዋሸት አለው! የሆነ ደስ የሚል ስሜት አለው። አንዳንዴ በ7 ዓመት የዲያቢሎስ ሚስትነት ዘመኔ በደነደነ ክፉ ልቤ ውስጥ የተረፈው ሚጢጥዬ የርህራሄ ጭላንጭል ተስፋ ብቅ ይልና ደስታዬን ይበርዝብኛል።

ደስታዬን መደበቅ ግን አልችልም። በጠዋት ተነስቼ እንዲፀዳዳ እያገዝኩት ፈገግታዬ ያመልጠኛል። ጥርሱን እየቦረሽኩለት፣ ፀጉሩን እያበጠርኩለት፣ ልብሱን እየቀየርኩለት፣ የሚንቀጠቀጡ እጆቹ አስተካክለው ስልኩን መያዝ ስለማይችሉ ስልኩ ሲጠራ ሲንፈራገጥ ሳየው አንስቼ እያቀበልኩት ሁላ ከንፈሬን እንደተከደነ ማስቀረት ያቅተኛል። የሚወደውን ምግብ በዜማ እያፏጨሁ አበስልለታለሁ፤ሲዝረከረክ በሶፍት እያፀዳሁ አጎርሰዋለሁ፤ በጤነኛ ዘመኑ ሰራተኛዋ የማታጓድለውን የምሳ ሰዓት ቡና ከነጭሱ እሱ እንደሚወደው ራሴ አፈላለታለሁ፤ ፈገግታዬ በየቀኑ ከማፈነዳው ፈንድሻ ጋር ይፈካል። የየቀን ምኞቱ እዛው አልጋው ላይ እንድረሳው ወይ ትቼው እንድሄድ ወይም በእንክብካቤ ፈንታ ባንገላታው እንደሆነ አውቃለሁ።

በጤነኛ ዘመኑ ከሚያገኘው እንክብካቤ አንዳች አላጎልበትም እንደውም እንደ ሰሞንኛ ሙሽራ አቀበጥኩት እንጂ! አሁንም ፈጣሪ ይሁን ሰይጣን ሲቀጡት አጓጉል አድርገውት እንጂ በጤነኛ ዘመኑ በየቀኑ ማታ አጅበውት የሚመጡትን ለዛዛ ሴቶች ሁላ አመጣለት ነበር። የሚታገዝ ቢሆን እኔ መኝታ ቤት የሚሰማኝን ሴቶቹን የሚያስጮሃቸውን ልፋቱን እያገዝኩት አስከውነው ነበር። አለመታደሉ እንኳን ለጉድጉድ ለመሽናቱም በድጋፍ ሆነበት።
«እሺ ምን ብሰጥሽ ትተይኛለሽ? ከውላችን በተጨማሪ ባንክ ያለኝን ገንዘብ ልስጥሽ ተይኝ!» አለኝ ምግቡን አብልቼው እንደጨረስኩ።
ውላችን ያለው ስንጋባ ያስፈረመኝን ነው። ከኔ በፊት እንዳገባቸው ሁለት ሚስቶቹ እኔንም 8 ዓመት አብሬው ከኖርኩ የንብረቱ ተካፋይ እንደምሆን ፣ ከዛ ቀድሜ መለያየት ካማረኝ ቤሳቤስቲን እንደማላገኝ አስፈርሞኛል። እንደቀደሙት ሚስቶቹ ጨርቄን ማቄን ሳልል በአንዱ ቀን ብን እንደምል እርግጠኛ ነበር።

«ወይ አለመታደልህ! እንዲህ ተይዘህም ገንዘብህ ሁሉን ነገር የመግዛት አቅም እንዳለው ነው የምታስበው?»
«እሺ ምንድነው የምትፈልጊው?»
«ለጊዜው ምንም! ፍቅሬን መንከባከብ!» አልኩት ፈገግ ብዬ ጉንጩን እየዳበስኩት። ጥሎኝ ሊሄድ ተውተረተረ። የሚንቀጠቀጡ እጆቹ አስተካክለው የዊልቸሩን መንቀሳቀሻ ስላልተጫኑለት ስልኩ ሲጮህ እንደሚወራጨው ተወራጨ። ፈገግታዬን መደበቅ እያቃተኝ ረዳሁት!!

ዛሬ ላይ እንዴት ተገኘሁ? ይህችኛዋን እኔ አድርጎ እሱ በሰይጣናዊ እጁ አቡክቶ ሳያበለሻሸኝ በፊት እግዚአብሔር የሰራት እኔ ምን አይነት ነበርኩ?

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት (ክፍል ሁለት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...