Tidarfelagi.com

ሰርፕራይዝ

(ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ)

ትናንትና የልደት በአሌን በማስመልከት ከወዳጆቼ አንዱ ወይም አንዲቱ ሰርፕራይዝ ያደርገኛል/ታረገኛለች ብየ ብጠብቅ ብጠብቅ ወፍ የለም። ግን ተስፋ አልቆረጥኩም። ባካባቢየ ወደሚገኝ አንድ ያበሻ ሬስቶራንት ሂጄ ተቀመጥሁ። ያዘዝኩት ሰላጣ እስኪመጣ ፌስ ቡኬን ለኮስኩ። አንዱ በቀጥታ ካዲሳባ online ላይ ጠመደኝ።

“ስንት አመትህ ሆነህ ማለት ነው በውቄ?”

“ሰላሳ ሰባት!”

” ትክክለኛ እድሜህን የማትናገረው ትንሽ በዛ ብለው ግብር እንዳይጥሉብህ ፈርተህ ነው?”

“ትክክለኛው እድሜየን ስንት ገምተኸው ነው?” አልሁት።

” እንጃ ! ብቻ ፎቶህን ሳየው ያልማዝ ኢዮቤልዩ ሊከበርለት የሚገባ ፊት ነው ያለህ”

“ስነስርአት!” አልኩ በንዴት ጦፌ።

” ራስህ ስነስርአት!! ቀለም በወፍ ላባ እያጣቀስክ ግጥም የፃፍህ ሼባ ሰላሳ ሰባት ነኝ ስትል ትንሽ ሼም ነገር አይቆነጥጥህም? ?”

Blocked

ከጀርባየ የተቀመጡ ሁለት ተስተናጋጆች ወሬውንና ምግቡን ጎንለጎን ሲያስኬዱት ሰማሁ።

” ብላ እንጂ!” ይላል አንደኛው

“ዘጋኝ ባክህ! እኔ ፍቅር ሲይዘኝ ካንድ ክትፎ በላይ መብላት አልቺልም”

ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ዘፈን ተጀመረ። አየ !! ዘፈን ሚሊኒየም አዳራሽ ቀረ!!

የመዝፈኛይቱ መድረክ በጣም ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ዘፋኙ በእናቱ የሽንኩርት መክተፍያ ላይ ቆሞ የሚዘፍን ይመስላል።

ከዘፋኙ ጀርባ ኪቦርድ ተጨዋቹ አቀርቅሯል። የሙዚቃ ተጫዋች ሳይሆን የመንደር ልብስ ሰፊ ነው የሚመስለው።

ከጎኑ የግእዙን አስር ቁጥር የሚመስል ሰውየ ባለ እጄታ ሳንዱቅ የመሰለ ግብዳ ጊታር ተሸክሞ ቁሟል። ከጊታሩ የሚመነጭ ድምፅ አልሰማሁም። የሆነ ባልደረባው ” ሽንቴን ሸንቼ እስክመጣ ይህንን ጊታር ይዘህልኝ ቆይ” ብሎት የሄደ ነው የሚመስለው። በመድረኩና በተመጋቢው ማሃል መለስተኛ ዙ ሃያዘጠኝ የሚመስል ድምፅ ማጉያ ተጠምዷል። የዘፋኙን ድምፅ ብቻ ሳይሆን ሀሳቡን ሳያጎላው አይቀርም።

በሩ አጠገብ ጠብደል አፍሮ አሜሪካዊ እልፍኝ አስከልካይ ተከምሯል። ሰውነቱ ግዙፍ ሲሆን ዘለግ ያለ ፂም አለው። ካንገት በታች ነፃ ትግል ታጋይ -ካንገት በላይ አቡነ አረጋይ- ነው ማለት ይቻላል: : የሚረብሽ ተስተናጋጅ ፍለጋ አይኑ በየማእዘኑ ይንከራተታል። ብዙ አልቆየም። አንድ stress የተጫወተበት አጭር ሰካራም ወደመድረኩ መጥቶ “ካሽ ስላልያዝኩ ነው! በክሬዲት ካርድ ብሸልምህ ይደብርሃል?” እያለ ዘፋኙን መበጥበጥ ጀመረ።

አስከልካዩ በኮሌታው አንጠልጥሎ ይዞት ወጣ። ሳየው የመኪና ቁልፍ እንጂ ሰው ከነ ጭንቀቱ ያንጠለጠለ አይመስልም። ከብዙ ዘመን የቅምቀማ ልምዴ እንደተረዳሁት ከረጅም ቀምቃሚዎች ይልቅ አጫጭር ቀምቃሚዎች ፈጥነው ይሰክራሉ። ምክንያቱም አልኮል ረጅም ሰው ጭንቅላት ላይ ለመድረስ ብዙ ርቀት መራመድ አለበት።

ሂሳብ ከፍየ እጄን ታጥቤ ልወጣ ሽንትቤት ገባሁ። ከጀርባየ ሁለት ሰዎች ጎንለጎን ቆመው ይሸናሉ።

አንደኛው አርፎ በመሽናት ፋንታ በድንበርተኛው ሸኚ ላይ አስተያየት አይሉት ጥያቄ ሰነዘረ።

“ፍሬንድ በመጥረቢያ ነው እንዴ የተገረዝከው?”

ድንገት ስልኬ ጠራ። አደይ ናት። አደይ የዛሬ አራት አመት አብራኝ መጥታ ጥገኝነት የጠየቀች ባለንጀራየ ናት።

“Birthday boy የት ነው ያለኸው?” አለቺኝ

ያለሁበትን ተናገርኩ።

“እንዳትወጣ ጠብቀኝ”

እንሆ በመጨረሻ!!!

ይሄን ላልማዝ ኢዮቤልዩ የታጨ ፊቴን ለሰርፕራይዝ አሰናድቼ ጠበቅሁ። ምንም ማድረግ አይቻልም። እድሌ ነው። ወንዶች ይታገሉህ ሴቶች ያገልግሉህ ተብየ የተፈጠርኩ ነኝ።

ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ አደይ መጣች

ትንሽ ስናወጋ ቆየና ከቦርሳዋ የሆነ ጥቅል አወጣች ። I knew it ይላል ፈረንጂ!!😉

ምን የመሰለ I phone 7 ከፊቴ ቦገግ አለ።

“እንዴው ቆይ ምን አሳሰበሽ ” ብየ ልጠመጠምባት ስል ቀደመቺኝ።

“ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ይህን ስልክ ለታናሽ ወንድሜ ትሰጥልኛለህ”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • zerihuntemesgenmekiso@gmail.com'
    ዘሪሁን commented on August 10, 2017 Reply

    አንደኛ!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...