Tidarfelagi.com

ራስ ወሌ ቡጡል

ራስ ወሌ ቡጡል
( ከደረስጌ እስከ አድዋ)
እንግዲህ ስለ ወሌ ቡጡል ጥቂት ብናወራ ምን ይለናል። ድስ ይለናል ላሉ ቀጠልን…

ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነው። እናቱ የውብዳር ይባላሉ። አባቱ ሰኔ 22/ 1845 ራስ አሊ ከቴዎድሮስ ጋር ባደረጉት የአይሻል ጦርነት ቆስለው ሞተዋል። ከአባቱ ሞት በኋላ እናቱ አንድ አለቃ በማግባታቸው፣ መርሶ ወደ ተባለ አጎቱ ዘንድ ሄደ። በዚያም ደስተኛ ባለመሆኑ፣ ደጃች ውቤ ወደተባሉት ሌላው አጎቱ ዘንድ ሄደ። ደጃች ውቤ ደረስጌ ላይ በቴውድሮስ ሲሸነፉ እስረኛ ሆኖ ተወሰደ። እንግዲህ ይህ እስር ነው ለእሱ እና ለእህቱ ጣይቱ ቡጥል ከሚኒሊክ ጋር የመተዋወቅ ሰበብ የሆነው።

ራስ ወሌ እጁን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጦርነት ያፍታታው በደረስጌ ጦርነት ነበር። ምኒሊክ የሸዋ ንጉስ በነበሩ ሰዓት የየጁ ግዛት የተሰጠው ሲሆን፣ ምኒሊክ ከነገሱ በኋላ ራስ ተብሎ ላስታ እና በጌምድር ተጨምሮለታል። የየጁ ገዢ ሆኖ በመሾሙ አስር የአካባቢው ደጃዝማቾች ተባብረው ወሌ ለመውጋት ይስማማሉ። ጦርነታቸውም በወልድያ ውስጥ ጃርሳ በተባለ ቦታ ይከናወናል። ድል የወሌ ሆነች። በዚህም ምክንያት የሚከተለው ግጥም ተገጠመለት፤
“ አስር ደጃዝማች የጠመቀውን
የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን”

የራስ ወሌ የጦርነት ጀብዱ እስከ አድዋ የዘለቀ ነው። በአድዋ ጦርነት ወቅት ራስ ወሌ የተሰለፉበት ቦታ እና ያስከተሉት የወታደር መጠን በቡዙ ታሪክ ፀሐፊዎች ዘንድ አከራካሪ ቢሆንም በአድዋ ውጤት ላይ ትልቅ አስተዋፆ ነበራቸው መሆኑ አሌ አይባልም። በርግጥ ከአድዋ በፊት ራስ ወሌ ከአድዋ በፊት እንደ ራስ ሚካኤል፣ እንደ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ እንደ ዋግሹም ብሩ…. እና ሌሎችም ከኢጣሊያን(በተለይም ከባራቴሪ) ጋር በሚስጥር ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ ሚኒሊክ ቢያውቁባቸው የሚኖረውን ውጤት በመስጋት ብዙም ሳይገፉበት አቋርጠውታል።

ራስ ወሌ በአድዋ ጦርነት ላይ ከ ስድስት ሺ እስከ ሰባት ሺ እንዳሉት ይገመታል። ከላይን ነካ እንዳረግነው የወሌን ጦር ቁጥር ከፍም ዝቅም የሚያደርጉት ሰዎች አሉ።ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ ኮንቲ ሮሲኒ፣ ዋይልድ…ስለወሌ አሰላለፍ የተለያየ ነገር ያወራሉ። ከነዚህ አንዱ ካፑቺ ሲሆን አምስት ሺ ነበሩ ይላል( በርግጥ ካፑቺ እራሱ ለጣሊያኖች ሚስጥር ሲያቀብል ታስሮ የነበረ በመሆኑ ልናምነው እንቸገራለን)

በአድዋ ወቅት ኢትዮጵዯውዯን ለጣሊያን የተሳሳቱ መረጃዎችን ይሰጡ ነበር። ከመረጃዎቹ አንዱ፣ ራስ ወሌ ሞቷል፣ ምኒሊክ ታሟል የሚል ነበር። ነገር ግን በጦርነቱ ትልቅ ሚና ከነበራቸው መሪዎች ውስጥ ሊጠቀስ ችሏል።
….. እኔ ምለው? በመጨረሻ የራስ ወሌ አዝማሪ የነበረውን የበላቸውን የተገጠመውን ግጥም ተገባብዘን ለምን አንሰነባበትም? ያዙ…

“…. የባህር ማዶ ሰው ረጅም ገፋፋ
እገዛለሁ በሎ በየወንዙ ጠፋ
በግራ ቀኝ ጅብ ፉርኖ እየሾገጡ
ከመሃል ሜዳው ላይ ፈስ እያንዛረጡ
አይ ጣሊያን ሞኙ
እንዲህ ብሎ ነው ወይ አበሻን ሲመኙ!”

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • Soliyana commented on November 14, 2022 Reply

    I like it but please can you write moral and generally short note….

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...