Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል አሥር)

የገዛ ሚስትህ በአደባባይ አብረሃት እየሄድክ ጡቶቿን የከለላቸውን ጨርቆች ገፋ ሳምልኝ ብትልህ ብልግና ይሆንብሃል። በሷ ድርጊት አንተ ትሸማቀቃለህ። መኝታ ቤታችሁ ውስጥ ራቁቷን ሆና ያንኑ ነገር ብትልህ ለቦታው የሚገባ ቅድስና አድርገህ ልትቆጥረው ትችላለህ። ምናልባትም ከዛ በላይ ‘ስድ’ ብትሆንልህ ያምርሃል።

በመንፈሳዊው ዓለም የመጀመሪያው ለሰው ልጆች የተሰጠ የተፃፈ ህግ አስርቱ ትዕዛዛት ናቸው። አትግደል የሚል ህግ ፅፎ ሰጥቷቸዋል። ጠላት በተነሳባቸው ጊዜ ግን አሳልፌ ሰጥቻችኋለሁና ዝመቱባቸው ብሎ እልፎች ያስገድላል።

በምድረኛው ህግም መግደል ወንጀል ነው ይልሃል። አንዳንድ ወንጀሎች ግን በዛው ህግ በሞት ያስቀጣሉ። እናም ፍትህ ነው ይልሃል። በተመሳሳይ በቀል ሀጢያት ነው ይሉሃል። የበደለህን ሰው አስጠፍንገህ ወህኒ ማስወርወር ግን በቀል ሳይሆን ፍትህ ነው ትባላለህ። ምናልባት አንተም ከዛ በላይ የምታደርገው ላይኖር ይችል ይሆናል እኮ!

አየህ በዚህኛው አለም ስትኖር ሀጢያት ወይ ፅድቅ፣ ልክ ወይ ስህተት፣ መልካም ወይም ክፉ፣ ብልግና ወይ ጨዋነት… … እነዚህ አንዱ ከሌላኛው ተቃራኒ ዋልታ የሚገኝ መቼም የማይስማሙ ሊመስል ይችላል። አይደለም! እንደውም አንዱ በአንደኛው የሚተካካበት ቦታ አለ። በመሃከላቸው የተሰመረ የሚመስልህን ቀይ መስመር ስታልፍ ከአንደኛው ክልል ወደሌላኛው አልተሻገርክም። ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ…… ምናልባትም ሌላ ተጨማሪ ገቢር ትርጉማቸውን ያፋልሰዋል።

የሆነውን ለመረዳት(ለመዳኘት አላልኩም) ከነዚህ ሁለት ተቃራኒ ፅንፍ ከሚመስሉ ሀሳቦች መሃከል በሀሳባችን በምናሰምረው መሃል መስመር ላይ እንቁም! ወደየትኛውም እቅፍ ተጠግተን አንሙቅ።
እናማ የሆነው እንዲህ ነው…………

አንድ
የውብ ዳር አባቴን እና እናቴን ለያይታ አባቴን ያገባችው ስላፈቀረችው አልነበረም። ለበቀል እንጂ! የውብዳርና እማዬ ከልጅነት ጀምሮ ጓደኛሞች ነበሩ። የውብዳር ወንድም ያፈቀራትን እናቴን ማግባት የነፍስም የስጋም ፍፃሜያዊ ትልሙ ነበር። እና እናቴ ከአባቴ ጋር ፍቅር ስትጀምር ለምናልባቱ ያስቀመጡት የባይሆን ጭላንጭል የሌላቸው ስጋና ነፍሱ አድመው በዚህ ዓለም ዓለመኖርን መረጡ። የውብዳር ለብቸኛ ታላቅ ወንድሟ መርዝ ጠጥቶ መሞት ተጠያቂዋ ጓደኛዋ መሆኗን ብታምንም በራሷ እጅ ፍትህን ካላደረገች በቀር በየትኛውም ህግ እንደማትዳኝ ታውቃለች። (እዚህጋ የእማዬን ሚና በትክክል አላውቅም። ‘ከዳችው’ የሚለውን የየውብዳርን ቃል ወይም ‘ምንም አልነበረንም’ የሚለውን የእማዬን ቃል የትኛውን እንደማምን አላውቅም።) የሆነው ሆነና እናትና አባቴ ሲጋቡ የእናቴ ሚዜዋ የውብዳር ነበረች። በዓል ሆኖ እኛ ቤት ያልመጣችበት ቀን የለም።(እናቴ ስራ የሆነችባቸውን በዓላት የእመቤትነት ስርዓቱን የምትከውነው እሷ ነበረች።) እኔ ወይ አባዬ ታመን እማዬ ከሌለች እያደረች የምታስተዳድረን እሷ ነበረች። ልደቴ ሲከበር የሚያጓጓኝ የእርሷ ስጦታ ነበር። በቤታችን የፎቶ አልበም ውስጥ እሷ የሌለችበት ፎቶ ውስን እንደሆነው ሁሉ በኑሯችን ውስጥም እሷ የሌለችበት ገፅ ውስን ነበር።

ዘጠኝ ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ አባትና እናቴ ሲሳሳሙ ወይ ሲላፍ ደርሼባቸው በሀፍረት ጉንጫቸው ቀልቶ አስደንግጫቸው ይሆናል እንጂ ተጣልተው ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፌ ነቅቼ ያውም እናቴ አባቴን በጥፊ ስትለው አይቼ በመጮሄ አስደንግጫቸው አላውቅም። በሰዓቱ የፀቡ መንስኤ እማዬ ፓንት መኝታ ቤት ማግኘቷ መሆኑን ብሰማም አባዬ ከየውብዳር ጋር መማገጡን እሱ ከሰጠኝ ደብዳቤዎች ነው የተረዳሁት። (በደብዳቤው ላይ ጠጥቶ እንደነበር እና ስህተት እንደሆነ ፅፎ ይቅርታ ይለምናታል። የውብዳር ፓንቷን መኝታ ቤት ጥላ መሄዷ ያሰበችበት ተንኮል ነበረ።) ከዚህ በኋላ በብዙ ላብና እድሜ የከመሩትን ጡብ በአንድ ቀን እንደማፍረስ ሁሉ ቤታችን የፈረሰው ተምዘግዝጎ ነበር። እማዬ የበለጠ የጎዳት ከሌላ ሴት ጋር መተኛቱ አይደለም። ከምትወዳት ጓደኛዋ ጋር መተኛቱ እንጂ…… የየውዳር በቀል የገባት ሲቆይ ነው።

እዚህ ተረክ ውስጥ ማናቸውም ጥሩ አይደሉም። ማናቸውም ክፉ አይደሉም። እንደማንኛውም ሰው ባበዙት ይጠሩበታል። ቤታችን በየእለቱ ጭቅጭቅ ሆነ። እማዬ አባቴን ጥላ ከእኔጋ ማደር ጀመረች። በነዚህ ሁሉ ጊዜያት የይቅርታ ደብዳቤ ፅፎላታል። ብዙም ሳይቆይ የውብዳር ማርገዟ ታወቀ። እናቴ ከልጁና ከእሷ እንዲመርጥ ነገረችው። ይሄን ከሰማች በኋላ እማዬ አንድ ቀን ከስራ ውጪ ሌላ ቦታ አደረች። ከሌላ ሰው ጋር… … አባቴ አወቀ። …… የአባቴ በደል ወይስ የራሷ ፀፀት አላውቅም ብዙ ሳይቆይ በአዕምሮ መታወክ ስራዋን አጣች። እህቷ ፀበል ይዛት ትኳትን ጀመር። አባቴ መምረጥ ነበረበት። እብድ ሚስቱን ወይም በፍቅርህ ሞትኩ የምትለውን የውብዳርን፤ በደሏን በራሱ በደል አጣፍቶ ይቅር ማለት እና ከእናቴ ጋር መኖር (ይሄ ያልተወለደች ልጁን ችላ ማለትን ያካትታል።) ወይም አዲስ ህይወት መጀመር።

አየህ ክልል ብሎ ፍልስፍና እንደሌለ? ያበደች ሚስቱን ትቶ ገና ተወልዳ ያላያትን ልጁን መምረጥ ልክ አይደለም። ለፍቅሩና ለሚስቱ አድልቶ በእነርሱ በደል ምንም የማታውቀውን ልጁን ቤተሰብ መንሳትም ልክ አይሆንም። ግድ ሲሆን ግን ከሁለት ስህተት አንዱን ስህተት መምረጥ ልክ ይሆናላ!

ትልቅ የሚባል ስኬት ፣ ፍፁም የሚባል ፍቅር ፣ ግዙፍ የሚባል እምነት ፣ የማይረታ የሚባል አንድነት…… ለመውደቅ ‘ትልቅ ምክንያት’ ሊያንገዳግደው ግድ አይደለም። ብዙ ትንሽ ምክንያቶች ከስሩ መንግለው ይደፉታል።

ሁለት
ቤተሰቦቼ በራሳቸው ጡዘት ሲጦዙ ዕጣ ፈንታዬ ምን እንደሚሆን አርቀው ያላሰቡልኝ እኔ እነርሱ በበሉት የተበላሸ ምግብ እኔ ስቀዝን ኖርኩ። እነርሱ በበሉት የተበላሸ ፍሬ የእኔ ጥርስ በለዘ። እናቴ በከፊል ጤነኛ በሆነ ጭንቅላቷ በከፊል በእህቷ ጭንቅላት ከአባቴ ጋር ላለመኖር ወሰነች። አባቴ የውብዳርን አገባ። ከአባቴ እና ከእንጀራ እናቴጋ ሁለት ዓመት ኖርኩ። ያጣሁት እናቴን ብቻ አልነበረም። አባቴም በዝምታና በድባቴ የተከበበ እኔ ከማውቀው ሳቅና ፍቅር ከሞላው አባቴ የተለየ ሌላ ሰው ሆነ። አብዛኛውን ምሽት አምሽቶ ጠጥቶ ስለሚገባ አላገኘውም። የቤቱ አዛዥ ሚስቱ ናት! እሱ ደግሞ ለሚሆነው ሁሉ መልሱ ዝምታ ነው። አክስቴ ስትወስደኝ ሚስቱ ምን ያህል እንደምትከፋብኝ ስለሚያውቅ አባቴ አልተቃወመም።

እዚህጋ ስህተትም ልክም ፅድቅም ሀጢያትም… … መልካምነትም ክፋትም… … ሁሉም ቦታ የላቸውም። ምክንያቱም ለእነዚህ ሁሉ ክስተቶች አንዲት ጥሬ ዘር ያላበረከትኩ እኔ ጎተራ ሙሉ መራራ ፍሬ ሳጭድ በየትኛው ሚዛን ተዳኝቶ ከአንዳቸው ይመደባል?

“ብትጠይኝ አልፈርድብሽም። በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የተጎዳሽው አንቺ ነሽ።” አለኝ አባቴ ከዘመናት በኋላ ዛሬ ላይ

“ስለእውነት እንደክህደትህ ብጠላህ ደስ ይለኛል። ከቤትህ አውጥተህ እንደጣልከው ቆሻሻ ስለረሳኸኝ አስከፍልህ ነበር። እድሜ ለእናቴ በል በሷ ልብ ውስጥ ስላነገሰችው ማንነትህ ስል እንደማንኛውም በህይወቴ ትርጉም እንደሌለው ሰው ቆጥሬሃለሁ።”

“ምንም ብልሽ ላንቺ በቂ የሚሆን ምክንያት ልሰጥሽ አልችልም። ግን አልከዳሁሽም። አንድም ቀን ረስቼሽም አላውቅም። አንቺንም ሆነ እናትሽን እንዳላያችሁ አክስትሽ በህግ አስከልክላኛለች። አንቺን ከእናትሽ መንጠቁ ደግሞ
እናትሽን እንደመግደል ነበር።”

አያችሁ…… ትልቅ ምክንያት አያስፈልግም። አባት ልጁን ለመተው እንኳን ቢሆን ትንንሽ ብዙ ምክንያቶች ሀያል ጉልበት አላቸው። እናቴን በማጣቱ መጎዳቱ፣ ሌላኛዋንም ልጁን እንደእኔ የተመሳቀለ ህይወት እንዳይኖራት ለመከላከል፣ የአክስቴ ሀይለኛነት፣ የእኔ እማዬጋ ለመኖር መፈለግ፣ የእንጀራ እናቴ ክፋት……… አንዳቸው ለብቻቸው ምንም የማይሆኑ ሲደማመሩ በኔና በሱ መሀከል ያለውን ትስስር መበጠስ የቻሉ ምክንያቶች ናቸው። አሁን ደግሞ ሚስቱን ሊፈታት ነው። ምክንያቱ ልጁ ስላገባች ከየውዳር ጋር የሚያኖር ምክንያት እንደሌለው ስለሚያስብ።

“ይቅርታ ልጄ! አሁን ይቅርታዬ ያለፍሽበትን ነገር እንደማይሽር አውቃለሁ። አስቤሽ ሁሌም እንደምታመም ግን እወቂ።”

“አሁን ዋናው ነገር የእማዬ ደስታ ነው። በቀራት ጊዜ ደስተኛ እንድትሆንልኝ እፈልጋለሁ።” አልኩት አንድ ቀን መጥቶ ይጠይቀኛል ብዬ የጠበቅኳቸው ቀናት እንዳልነበሩ፣ ከእኔና ከእናቴ የውዳርንና እህቴን በመምረጡ በእህቴ እንዳልቀናሁ፣ እነርሱን ትቶ ከእኛጋር እንዲኖር ልለምነው አስቤ እንደማላውቅ…………

ሶስት
ፍትህ ፍርዱ ልክ እንዳልሆነ እያወቀ ትዝታ 25 ዓመት ሲፈረድባት እጅ ሰጥቶ መቀመጥን መረጠ። ምክንያቱ ደግሞ የነበረው ምርጫ ማሸነፍ ወይ መሸነፍ አልነበረም። ይሄ ቀሽም የአንደኛ ደረጃ መምህር ያዘጋጀው ዓይነት ምርጫ ቀላል በሆነለት ነበር። ሁለት የማይመረጡ ምርጫዎች ነበሩት። ትዝታን ማዳን ወይ ቤተሰቡን ማዳን!! ትዝታን መርጦ ከሚወዳቸው አንዳችንን ማጣት ለእርሱ በምንም ስሌት ልክ አይሆንም። የሚወዳቸውን መርጦ ትዝታን መክዳትም በሂሳብም በሳይንስም ልክ አይሆንም። አየህ ድንበር ብሎ ፈሊጥ እንደሌለ? ግድ ሲሆን ከሁለት ስህተት አንዱን ስህተት መምረጥ ልክ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ቆይ ቆይ…… እንዲህ ቀላልና ምክንያታዊ ውሳኔ አልነበረም። ሁላችንንም ዋጋ ያስከፈ እንጂ……

እንደውም ትዝታን ማዳን የሚለው ምርጫ አይደለም። ትዝታ መዳን አትፈልግም። ደፍሯታል ወይም አታሏታል…… ልጅን ያህል ነገር ወልዳለች። ለምን ለዚህ ሰው ትከላከልለታለች? የልጇ አባት አጎቷ መሆኑን ፍትህ ሲጠይቃት ድንጋጤዋ እውነቱን ቢያሳብቅባትም ካደች።

“በቅቶኛል። ራሁ ይህቺ ልጅ ምንም መስዋዕትነት የሚገባት አይደለችም።” አለኝ ፍትህ።

“ፍትህ ለእርሷ ብለህ ነው ወይስ ለሙያህ? ለእውነት? ለፍትህ?”

“የሆነ ሰው አርፌ ካልተቀመጥኩ አንቺን፣ ካስዬን ወይ እማዬን እንደሚያስከፍለኝ አስጠንቅቆኛል። ማስፈራሪያ ብቻ አይደለም።” አለኝ በሰጋ ልብ። እሱ ይሄን ከማለቱ ከአንድ ሰዓት በፊት የማላውቀው ሰው ሆስፒታሉ መግቢያ ጋር አስቁሞኝ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ለእኔም ሰጥቶኛል።

 

ራሴው ማበዴ ነው (የመጨረሻ ክፍል)

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...