Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ስምንት)

በሰላሳ አንድ ዓመቴ ማንም ወንድ ነክቷት የማታውቅ ድንግል ሴት መሆን የሚያኮራ ነገር ይሁን የሚያሳፍር አላውቅም። (‘ድንግል’ የሚለውን ቃል እጠላዋለሁ። ቃሉን እንጂ ነገርየውን አይደለም። በእርግጥ ነገርየውንም ልውደደው ልጥላው እርግጠኛ አይደለሁም። ቃሉ ግን የሆነ አፍ ላይ ሲባል ራሱ ድንግል፣ ደናግል፣ ድንጉላ……… ድንዝና አለበት።) እውነታው እግሮቼ መሃል ካለ ነገር ድፍንነት ወይ ጠባብነት በላይ ዓይኖቼን የማያስነቅሉ የኔን ትኩረት የሚሹ አሳሳቢ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች የከበቡኝ ሴት ሆኜ በመኖሬ ትርጉሙም ጣዕሙም አይገባኝም። ድንገት እንኳን በሀሳቤ ሽው ካለ የማልም የነበረው አቅፎኝ የሚያድር የሆነ የማላውቀው ፈርጣማ ወንድ ሰውነት ነው። ማቀፍ ብቻ!! ሌላውን ‘ፓኬጅ’ አላስበውም። እኔ እና እማዬ ብቻችን መኖር የጀመርን ዓመት እማዬ ሲነሳባት ለሊቶቹ ይረዝሙብኛል። ምን እንደምፈራ አላውቅም ግን ስለምፈራ ዓይኔን አልከድንም። ጨለማው፣ ኮሽታው፣ ፀጥታው…… ሁሉም ያስፈራኛል። እጅግ ጥልቅ ፍርሃት እፈራለሁ። ድፍረት የፍርሃት ተቃራኒ አይደለም። የፍርሃት ሌላ ተቃራኒ ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱም ድፍረት አለመፍራት አይደለማ። ይልቁንስ ድፍረት ፍርሃትን መጋፈጥ ነው። ድፍረት ፍርሃት እንዳያስቆምህ እየተንቀጠቀጥክም ሆነ እየዳህክ በፍርሃትህ ጫካ ውስጥ ሰንጥቀህ ማለፍ ነው።

እማዬ እና አባቴ ከተለያዩ በኋላ ከታላቅ እህቷ (ከአክስቴ) ጋር ነበር የምንኖረው። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቴን ጨርሼ ውጤት እየጠበቅኩ በነበረበት ክረምት አክስቴ ትኖር የነበረበትን ትልቅነቱ እና ፀጥታው የሚያስፈራ ቤቷንና ቢያንስ በዓመት ሶስቴ እብደቷ የሚነሳባት እህቷን (እናቴን) አስተዳድሪ ብላኝ አውስትራሊያ ከሄዱ ከእኔ እድሜ በላይ ያስቆጠሩ ቤተሰቦቻቸውን ተቀላቀለች። ከእርሷ በቀር ሀገር ውስጥ የቀረ የቅርብ ዘመድ ያልነበራት እናቴ ብዙም ሳትቆይ የበረራ ቁጥሯን መቁጠር ጀመረች። እንኳን እሷን ላረጋጋት እኔ ከርሷ ብሼ እጅና እግሬ እየተንቀጠቀጠ አለቅሳለሁ። መድሃኒቷን በስቃይ ወስዳ ስታንቀላፋልኝ። እያንዳንዱ የቆዳዬ ነጠብጣብ ቀዳዳ ፍርሃትን እየማገ ወደሰውነቴ ሲነዛው እየተሰማኝ ተስፋ ላለመቁረጥ እና ላለመውደቅ እታገላለሁ። ለፍርሃት እጅ ላለመስጠት!! ያ ነው ድፍረት ማለት። መታገል!! በነዚህ ጊዜያት ነበር በእቅፉ የሚከልለኝ ሰውነት የምመኘው!! ሰውነቱን እንጂ ሰውየውን አልሜ አላውቅም። ሰፊ ትከሻ፣ ሰፊ ደረት፣ ፈርጣማ ጡንቻ፣ ረዥም ቁመት…… ለውበት ሳይሆን ከፍርሃቴ ለመከለያ፤ ለስሜት ሳይሆን ለመደበቂያ፤ ለመፈንጠዣ ሳይሆን ለመወሸቂያ… …ከአንገቱ በላይ ባይኖረውም አልያም ምንም ቢመስልም አስቤው አላውቅም።

“ራሁ? እየሰማሽኝ እኮ አይደለም። ምን ሆነሻል? ከቅድም ጀምሮ ላጫውትሽ እሞክራለሁ። ከእኔ ጋር አይደለሽም።”

“ይቅርታ ፍትህ ትንሽ ራሴን አሞኛል።”

“ምን ላድርግልሽ? ሀኪም ቤት ልውሰድሽ? (እጁን ግንባሬ ላይ አድርጎ ማተኮሴን ያረጋግጣል። በጭንቅላቴ ንቅናቄ መሄድ ያለመፈለጌን ነገርኩት።) እሺ በቃ ነገ ይደርሳል ነገ አወራሻለሁ።እረፍት አድርጊ!” ብሎኝ ተነሳ። ምን አስቤ እንደሆነ እንኳን ለመረዳት ከራሴ ተማክሬ ያላደረግኩትን ድርጊት ተስፈንጥሬ እጁን ይዤ አሰቆምኩት። ቀጥዬ ለምን እንዳስቆምኩት የምሰጠው ምክንያት አልነበረኝም።

“ወዬ? ምን ላድርግልሽ? እንዲህ አድርግልኝ በይኝ። እ ራሁ? (ተመልሶ ተቀምጦ ይዞ ያስቀረውን እጄን እያሻሸ ፣ዓይን ዓይኔን እያየ እና ሁሉም የስሜት ህዋሳቶቼ በሚገባቸው ድምፅ ተንሾካሾከ።) ልታወሪልኝ የምትፈልጊው ነገር አለ? እ? እሺ እንዳድርልሽ ትፈልጊያለሽ?”

“አይይይ አልፈልግም።” አልኩት። አጠገቤ እንዲሆን እኮ እፈልጋለሁ። ሲነካኝ ግን እበረግጋለሁ። እጆቼን ሲያሻሽ ፣ ቅድም እንዳደረገው አንገቴ ስር ሲስመኝ ፣ ዓይኖቼን በሚለማመጡ ዓይኖቹ ሲያያቸው…… መሸሽ እፈልጋለሁ። እንዲህ ሲያደርግ የሚሰማኝን ስሜት ስለምጠላው አይደለም። ስለምወደው እንጂ። ነገር ግን ደስ የሚለኝ አዲስ ስሜት ያስፈራኛል። ሁሌም ቢሆን ያልተለማመድነው አዲስ ነገር፣ አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ ስሜት……… ብቻ አዲስ ልምድ መጠኑ ቢለያይም ፍርሃት ያጅበዋል። ምክንያቱ ደግሞ ውጤቱ ከግምት ያለፈ ማረጋገጫ የለውም። ለዚህ ይመስለኛል የብዙ ሰዎች ኑሮ የተለመደ እና የተደጋገመ የሚሆነው። ከአዲስ ነገር ጋር አብሮ ብልጭ የሚለውን ፍርሃት መጋፈጥ የቻሉ ጥቂት ደፋሮች ለአለማችን አዳዲስ ሀሳቦች እና ፈጠራዎች አበርክተዋል።

“እሺ እኛ ቤት እንሂድ? ከካስዬ ጋር ስትጫወቺ ይለቅሻል። እንሂድ?”

“አይ… … ስለትዝታ የደረስኩበት ነገር አለኝ አላልክም ነበር? እሱን እንድትነግረኝ ነው።” የሚል ምክንያት ነበር የመጣልኝ

“ስለትዝታ ልትጠይቂኝ ነው እጅሽ የሚያልብሽ?( ያላበው መዳፌን በእጁ እየጠረገ ያደርቃል። ይሄኔ እኮ ድምፅ ከጆሮ ውጪ በሌላ የስሜት ህዋስ እንዴት ይተረጎማል? ብሎ የሚጠይቅ አላዋቂ አይጠፋም። አሁን ፍትህ እያወራ ያለበት ባለጣዕም ድምፅ ቀላል ይጣፍጣል?) ስለትዝታ ልትጠይቂኝ ነው ዓይንሽ የሚሸሸኝ? (ይሄን ያለበት ድምፅስ ቀላል የሚያውድ መዓዛ አለው?) ስለትዝታ ልትጠይቂኝ ነው ጉንጭሽ የቀላው? (ይሄኛው ቀለማት አሉት። ዓይን የሚይዝ የቀለም ስብጥር) ስለትዝታ ልትጠይቂኝ ነው ቃላት ለማውጣት ያማጥሽው?( ይሄኛው እንደሚያባብል የውሃ ዳር ንፋስ በቆዳዬ ላይ ሽውውውው እያለ ይዳብሰኛል።)” ጭራሽ የማወራው ጠፋብኝ። በዛው ድምፅ ቀጠለ

“ስለስራ ስታወሪ ዓይኖችሽ ዓይኖቼን ያሳድዳሉ ፣ አንገትሽን ቀና አድርገሽ የምትናገሪው ተፅፎ የተሰጠሽ አይነት ‘articulated’ ነው፣ በጥያቄሽ ብዛት እኔን ያልበኛል። …… ንገሪኝ ምን ልትዪኝ ነበር እጄን የያዝሽኝ?” (ይሄንን ድምፅ ጥፍሬ እና ፀጉሮቼ እንኳን ላይሰሙት አይችሉም።)

“ምንም!! ምንም የምልህ ነገር ኖሮኝ አይደለም። …… በቃ እንድትቆይ ብቻ ፈልጌ ነው።”

“እሺ (ያልከለለውን ፀጉሬን ወደኋላ እያደረገ) እሺ እንድቆይልሽ እስከምትፈልጊው ጊዜ ሙሉ የእድሜዬን ቁጥርም ቢሆን እቆይልሻለሁ። ምን እያደረግኩልሽ እንድቆይ ነው የምትፈልጊው?”

“አላውቅም!! ፍትህ የተሰማኝን ስለነገርኩህ እንዳፍር እያደረግከኝ ነው።” ስለው ፈገግ ማለቱን ሳላየው በምን አወቅኩ? ምራቄን እየደጋገምኩ በሚያስተጋባ ጉሮሮዬ የምውጠው ምን ሆኜ ነው? አፍንጫዬ ሳይቀር የሚያልበኝስ?

“እሺ!!” ብሎኝ እጄን ለቀቀኝ። ከሶፋው ላይ ትንሽዬዋን ትራስ አንስቶ እኔ ከተቀመጥኩበት በተቃራኒ ጥግ ተቀመጠ።ትራሷን ጭኑ ላይ ካስቀመጠ በኋላ በእጁ እየመታ ጠቆመኝ። ጀርባዬን ሰጥቼው እግሬን ሰቅዬ እሱን ተንተርሼ ተጋደምኩ።

“ፊትሽን አትከልዪኝ። ወደዚህ ዙሪና ከፈለግሽ ዓይንሽን ጨፍኚ።” አለኝ ቀጠለና። እንዳለኝ አደረግኩ። ዓይኔን ግን አልጨፈንኩም። ፀጉሬን በጣቱ እያበጠረ ለደቂቃዎች ካለምንም የቃላት ልውውጥ ከቆየን በኋላ።

“እንቅልፍሽ ከመጣ መተኛት ትችያለሽ።” አለኝ

“ከዛስ? አንተስ?”

“ያላደለው ጨለማ ላይ አፍጥጦ ያድር የለ? አንቺን የመሰለ ውበት ላይ አፍጥጦ ማደር ተገኝቶ ነው? ውብ’ኮ ነሽ ካስዬ ይሙት! (እጄን የማስቀምጥበት አጥቼ አቅበዘበዝኩት።) እፍረትሽ መጣ?” ብሎኝ ሳቅ ሲል በጨረፍታ አየሁት።

” አንዳንድ ነገር ሳጣራ ነበር። ምን ያህል እንደሚጠቅመኝ ባላውቅም አንዳንድ መረጃዎች ……”

“እስኪ ንገረኝ።”

“የሟች ታሪክ ትዝታ ካለችው የራቀ ነው። ሟች የሰውየው ፍቅረኛ አልነበረችም። ከዚያ ቀን በፊትም ተያይተው አያውቁም። የምትማርበት ትምህርት ቤት ጓደኞቿ የሞተች ዕለት መጥቶ ከትምህርት ቤቷ ወሰዳት ያሉትን ሰው አገኘሁት።”

“እና?” ከተጋደምኩበት ቀና ብዬ ለመልሱ አቆበቆብኩ። ፈገግ አለ። ‘ስለስራ ሲሆንማ እንዲህ ነው የምትሆኚው’ የሚል ትዝብት ያለበት ዓይነት ፈገግታ።

“ወንጀሉን መሸፈኛ ስራው ትዳር ፈላጊ አገናኝ ነው። ዋነኛ ስራው ተማሪ ህፃናትና ወጣት ሴቶችን ለከተማችን ዋልጌ ሀብታም ሽማግሌዎች ማቅረብ ነው። ‘ሀብታም የሆነ ባል ፈልጋለሁ ስላለችኝ ነው ያገናኘኋት።’ ባይ ነው። ትዝታ ለመጀመሪያ ጊዜ እቤታቸው የመጣችን ሴት ‘ልጄን በጥፊ ስለመታቻት’ በሚል ቀሽም ምክንያት ትገድላታለች ብሎ ማመን ይከብዳል። ካልሆነስ ማንን እየተከላከለች ነው? ሰውየውን? እሱስ ቢሆን ከዚያን ቀን በፊት አይቷት የማያውቃትን ሴት ለመግደል ምን በቂ ምክንያት ይኖረዋል?”

“አንድ የሆነ ነገር ግን አለ። ልጅ አለሽ ወይ ብላ የጠየቀችኝ ቀን በደንብ አስተውለሃታል? አነጋገሯ ለልጇ ብላ እየከፈለች ያለችው መስዋዕትነት እንደሆነ ነገር ነው።”

“ሌላው ነገር… …ማንም የሚያውቀው ሰው ክፉ ስለማያወራለት አጎቷ አንድ ትኩረቴን የሳበ መረጃ ሰማሁ። የትዝታ ፍቅረኛ ፣ የልጇ አባት ትዝታ እርጉዝ በነበረችበት ወቅት እቤታቸው ድረስ መጥቶ አጎትየውን ደብድቦት ሄደ። ከዚያ ቀን በኋላ ልጁን አየሁት የሚል ሰው የለም። ትዝታም ምንም ልትነግረኝ ፈቃደኛ አይደለችም። አጎትየው በሁለቱ ግንኙነት ደስተኛ ካልነበረ ጥቃት ሊያደርስ የሚገባው እሱ ሆኖ የተገላቢጦሽ እንዴት ሆነ?”

“እሱን እያሰብኩ ነበር። ጎብዘኻል ግን ደስ ብሎኛል።” አልኩት ለጊዜውም ቢሆን ያ የሚያሽኮረምመኝ ፍትህ ተዘንግቶኝ ዓይን ዓይኑን እያየሁ።

“በልብሽ ደምቄ ለመፃፍ የሚያስከፍለኝ ጉብዝናን ከሆነ እተጋለሁዋ ምን አማራጭ አለኝ?” አለኝ እሽኩርምሚቴን በሚያመጣው ድምፁ። ተመልሼ እንደመጀመሪያው እላዩ ላይ ተጋደምኩ እና ዓይኔን ጨፈንኩ። ፀጉሬን በጣቶቹ እያበጠረ መነሻም ማረፊያም የሌለው ወሬ እያወራኝ ለምን ያህል ደቂቃ እንደቆየ አላውቅም። እንቅልፍ ወስዶኝ የነቃሁት ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ነው። የሶፋውን መደገፊያ ተደግፎ በተቀመጠበት እንቅልፍ ወስዶታል። ጣቶቹ ከፀጉሬ መሃል አልወጡም። በሁለት የሶፋ ትራስ እግሬን ሸፍኖ ከብርድ ከልሎልኛል። ሆስፒታል ለማደር አስቦ ስለነበር የወጣው ቱታ ሱሪና ጃኬት ነበር የለበሰው። ጃኬቱን አውልቆት እጄን አልብሶኝ በ‘ፓክ አውት’ ነበር። ቀሰቀስኩት።

” ፍትህ ተነስ በስርዓቱ ተኛ አንገትህን ያምሃል። ተነስ እኔ መኝታ ቤት ተኛ። እኔ እማዬ ክፍል እተኛለሁ።” ይሄን የሚለው በምክንያትና በእውቀት ካላመንኩ የሚለው ጭንቅላቴ ነው። ልቤ ግን ከአጠገቡ መራቅን አልፈለገም።

“ከአንቺጋ እንድተኛ ካልፈቀድሽልኝ እዚሁ ሶፋ ላይ የምለብሰው ስጪኝና እተኛለሁ።” አለኝ አይኑን እንኳን አስተካክሎ ሳይገልጥ። ግራ ገባኝ ምን እንደምለው። ያንን እሱም ያወቀ መሰለኝ

“አብረን ተኝተን ነበር እኮ! አልጋ ላይ ሲሆን ምኑ ይለያል? ራሁ ስወድሽ አታወሳስቢው።”

“እሺ!” እያልኩት ወደመኝታዬ ገባሁ። ተከትሎኝ ገብቶ ጫማውን ብቻ አውልቆ ቀድሞኝ አልጋ ልብሶቹ ውስጥ ገብቶ በጀርባው ተኛ። አይኑን ጨፍኖ እጁን ለማቀፍ ዘረጋልኝ። አለማወሳሰብ ይሔ መሆኑን እየገመትኩ እቅፉ ውስጥ ገባሁ። በሁለቱም እጆቹ ደረቱ ላይ አጣብቆ አቅፎኝ ተኛ።… … አፌን እየሞላ እና ጉሮሮዬ ውስጥ የገደል ማሚቶ እየሰራ የሚያልፈውን ምራቄን እየዋጥኩ፤ ድው ድውታው ለእርሱ የሚሰማውን ልቤን ለመቆጣጠር እየታገልኩ የሚቀጥለውን እንቅስቃሴ ጠበቅኩ።… … ጠበቅኩ። …… ጠበቅኩ። …ተኝቷል። …… እንቅልፍ ወስዶታል። ካለፍርሃት ተኛሁ።

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ዘጠኝ )

One Comment

  • ሲፈን ማሞ commented on December 11, 2017 Reply

    የትዝታ ነገር ውስብስብነቱ መሳጭ አድርጎታል !

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...