Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል አምስት)

“ራሔል ከዚህ በላይ እናትሽን እቤት ልታቆያቸው የምትችዪ አይመስለኝም። አደገኛ ነው የሚሆነው።”

“ዶክተር በፍፁም ሆስፒታል እንደማልተዋት ቃል ገብቼላታለሁ። አይሆንም!! ታውቅ የለ ምን ያህል እንደምትጠላ?”

“ራሔል እስቲ ተቀመጪ።” አለኝ ወንበሩን እያሳየኝ። በእማዬ ምክንያት ከማውቀው ልምድ በዶክተሮች አባባል ‘እስኪ አረፍ በይ፣ እስኪ ተቀመጪ፣ ለመረጋጋት ሞክሪ፣ የቅርብ ዘመድ ነሽ ወይ?…… ’ ዓይነት ንግግሮች ‘ ለሚከተለው አሳዛኝ ዜና ተዘጋጂ።’ የሚል አንድምታ ነው ያዘለው። ቅርፍፍፍፍፍ እያልኩ ተቀመጥኩ።

” አየሽ ራሔል በህይወት አንዳንዴ ትክክለኛው ውሳኔ ከባዱ ውሳኔ ይሆናል። አሁን እናትሽ ከፍተኛ የህክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል። እእ… … (እንዲህ እ…እ ሲጀምር የሚነግረኝ ነገር ጨንቆታል።) እ ራሔል ታውቂያለሽ እናትሽ ከአዕምሮ መታወኩ በላይ ካንሰሩ ጎድቷቸዋል። ብዙ ጊዜ የላቸውም።…… ” ምን እያለ እንደሆነ ገብቶኛል። ግን ደግሞ አልገባኝም። ብዙ ምክር አክሎበት እናቴ ከግማሽ ዓመት ያለፈ ጊዜ እንደሌላት ነገረኝ። በህይወት እያለች እንዳትሰቃይ ላደርግላት የምችለው ብቸኛ ነገር አባቴ እንዲያያት ማግባባት መሆኑንም አከለልኝ። …… አልጠየቅኩም። አልመለስኩም። ቢሮውን ለቅቄ ወጣሁ። ፍትህ ውጪ እየጠበቀኝ ነበር። ከትናንት ጀምሮ እዚሁ ነበረ።

“ፍትህ ምንም ነገር እንዳትጠይቀኝ።” ብዬው ነበር።

“ምንም ልጠይቅሽ አላሰብኩም።” ነበር መልሱ። እስከአሁንም ስለምንም አልጠየቀኝም። ወደ ስራው እንዲመለስ ደጋግሜ ወትውቼዋለሁ። አልሰማኝም እንጂ። ከዶክተሩ ቢሮ እንደወጣሁ ፍትህ ወደነበረበት ሄጄ ወንበር ላይ ዘፍ አልኩ። አጠገቤ ያለው ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳይመቻች አቀፈኝ። ጥሩ ዜና እንዳልሰማሁ ገብቶታል።

“እማዬ መሞቻዋ ደርሷል ተዘጋጂ አለኝ።” ስለው ደንግጦ ለቀቀኝ። “ከስድስት ወር ያለፈ ጊዜ የላትም።”

“እሺ። እሺ በቃ! እሺ።” የሚለኝ ከኔ በባሰ ግራ ተጋብቶ የሚለው ጠፍቶት መሆኑ ገብቶኛል። “እሺ በቃ ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን። አንድ መንገድ አናጣም።” ይለኛል።

“አሰቃየሁሽ አይደል?” አለችኝ እማዬ ገና ወደ ክፍሏ ስገባ። ሁሌም ቢሆን መጥፎ ነገር ካደረገች በኋላ ልክ ከቅዥቱ እንደባነነ ሰው ፍፁም ጤነኛ ጭንቅላት ይኖራታል።

“አንቺ ተሰቃየሽብኝ እማ።” እያልኳት ለአፍታ ሞት ለሷ ግልግል መሆኑ በጭንቅላቴ ሽው አለኝ። እንደዛ በማሰቤ ራሴን ተፀየፍኩት። ግን እንዳትሞት የምፈልገው ለሷ ነው ለራሴ? ዘመኗን ከመድሃኒት፣ ከቴራፒዎችና ከቅዥት ጋር በስቃይ እየኖረች ያለች እናቴ እንዳትሞት የምፈልገው ለሷ ስል ነው ለራሴ?

“እማ ፍትህ ይባላል። አንድ ላይ ነው የምንሰራው። ትናንት ሆስፒታል ያደረሰሽ……”

“አስታውሳለሁ። አውቄዋለሁ ልጄ…” አለችኝ ከግርጌዋ ቆሞ ወደነበረው ፍትህ እያየች። “መልካም ልጅ ነህ። በክፉ ሰዓት ባላውቅህ ደስ ይለኝ ነበር።” እያለችው። ወደ ክፍሉ አንድ ሰው ገባ። ድርብብ ያለ ጎልማሳ፤ ልብወለዶች ላይ ያለ ደግ አባት የሚመስል፤ ፀጉሩ እና ፂሙ ሽበት ጣል ጣል ያደረገበት፤ ቁመቱ ረዥም፤ ቀላ ያለ ፤በለስላሳ ፂም የተሸፈነ ጉንጭ ያለው፤ ደልደል ያለ…… ሰውዬ

“ካስዬ መጣህ?” አለ ፍትህ ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ ቀጠለና “ራሔል እሷ ናት። እሳቸው እናቷ ናቸው።” አለው።

“እንዴት ነሽ ልጄ?” ብሎ ሳብ አድርጎ በግዙፍ ሰውነቱ ውስጥ ወሸቀኝ። ፀጉሬን ደጋግሞ እየሳመ ወደ ሰውነቱ አጣብቆ አቀፈኝ።ልል የነበረው ‘ፍትህ የማላውቀውን ሰው እንዴት ይጠራብኛል? ነበር። ደረቱ ላይ በእጆቹ ተከብቤ ላስብ የቻልኩት ግን ‘ይሄን ፍቅር የት ነው የማውቀው?’ የሚለውን ብቻ ነው። ጀርባዬን አይዞሽ እንደማለት፣ አለሁልሽ እንደማለት አሸት አሸት አድርጎ ወደ እማዬ ሄደ። ወንበሩን ሳብ አድርጎ አጠገቧ እየተቀመጠ

“ሽማግሌ ነኝ አንቺን አንቱ አልልሽም። እንዴት ነሽ? እጅሽን ደግሞ እንዲህ አታድርጊው (የጉሉኮሱ መርፌ የተደረገላትን እጇን አንስቶ አስተካክሎ እያስቀመጠላት።) ያብጥብሽና ያምሻል።…………” አኳኋኑ ትናንት አብሯት የነበረ፣ ሲያስታምማት የከረመ ፣ የምታውቀው፣ የቅርብ ወዳጇ ዓይነት እንጂ ዛሬ የሚያውቃት አይመስልም።

“አባቴ ነው።” አለ ፍትህ

ለወትሮው አዲስ ፊት የሚያስደነብራት እማዬ እንኳን እንደምታውቀው ሰው ሁሉ የሚጠይቃትን ጥያቄ ደስ እያላት ትመልስለታለች። እጇን፣ ፀጉሯን የለበሰችውን ጋቢ እያስተካከለ ነው የሚያወራው። “ምግብ መውሰድ ትችያለሽ? ምግብ ከወሰድሽ ስንት ሰዓት ሆነሽ? ምን ባመጣልሽ ደስ ብሎሽ ትቀምሻለሽ? ……… ”

(አንዳንድ ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም? ሰውየውን ገና እንዳያችሁት ላትወዱት አትችሉም። አንዳንድ ሰው ደግሞ አለላችሁ ገና እንዳያችሁት አትወዱትም። ጥሩ እያደረገላችሁ እንኳን ይከብዳችኋል።ሰውየውን የከበበው ቫይብ ነው!! ወይ ይስባችኋል አልያም ይገፈትራችኋል።)

ፍትህን ሆስፒታል ከእማዬ ጋር እንዲቆይ እና እኔ አርፌ እንድመለስ የነገረን በማስፈቀድ ዓይነት አይደለም። ትዕዛዝም አይደለም። ብቻ ‘እንቢ’ የሚሉት ዓይነት አጠያየቅ አይደለም። የገረመኝ ግን የእማዬ ከፍትህ ጋር ለመቆየት በደስታ መስማማት ነው።

“ወዴት ነው የምንሄደው?” አልኩኝ በመኪናው እቤት ሊያደርሰኝ ተስማምተን መንገድ ከጀመርን በኋላ

“ወደቤት ነዋ!”

“መንገድ ስተዋል በዚህጋ ነው ቤቴ።”

“ውይይ ………አንቱ ብለሽ አግተለተልሽኝ እኮ።(ዝግንን እያለው) የምንሄደው እኛ ቤት ነው። አሁን እቤትሽ ባደርስሽም አታርፊም። ብትፈልጊም ትናንት የተፈጠረውን ረስተሽ ምንም እንዳልተፈጠረ ልትተኚ አትችዪም።”

“ኸረ እንደውም የማላውቀው አዲስ ቤት እንቅልፍ እሺ አይለኝም። እዛው እቤቴ ይሻለኛል።” ያልኩት ከምሬ ነው። በእርግጥ ቤቴም ብሄድ ሰውነቴን ባሳርፍ እንጂ እንቅልፍ እንደማይወስደኝ አውቃለሁ።

“እስቲ ግድ የለሽም። እንድረስና መተኛት ካቃተሽ ራሴው ቤትሽ አደርስሻለሁ።” ብሎኝ መንዳቱን ቀጠለ።

ክፉ እና ደግ እንዳለየች ህፃን ልጁ እጄን ይዞ እየመራኝ ሳሎን አስገባኝ። ጎኑ ስር ሲያቅፈኝ፣ አንዴ ግንባሬን ሌላ ጊዜ ፀጉሬን ሲስመኝ ፣ እጄን ሲይዘኝ… …… ለእሱ ብዙ ዘመን ሲያደርገው እንደኖረ ሁሉ የተለመደ አይነት ነው። እኔ ያልለመድኩት ነገር ስለመሆኑ ማወቁን እንጃ! ማወቅ መፈለጉንም እንጃ!! እቤቱ እንደገባሁ መብላት መፈለጌን አልጠየቀኝም።ለሰራተኛቸው ምግብ እንድታቀርብ እና ለእንቅልፍ እንደሚረዳኝ ነግሮኝ ወተትም አፍልታ እንድታመጣ አዘዛት። መታጠብ እፈልግ እንደሆነ አይደለም የጠየቀኝ። ውሃው ሙቅ ወይስ ቀዝቃዛ ቢሆን እንደምመርጥ እንጂ። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ለዘመናት አብረን የኖርን አይነት እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ከታጠብኩ በኋላ እንድለብስ የፍትህን ቢጃማ ሱሪና ቲሸርት መታጠቢያ ቤቱ መስቀያ ላይ ሲሰቅል ይደብረኝ እንደሆነ አልጠየቀኝም። ቢሰፋኝም የሱሪውን ወገብ በማሰሪያው አጥብቤ እንድለብሰው ነገረኝ እንጂ። ምግቡን በእጄ አላስነካኝም። እያጎረሰኝ መብላት ጀመርኩ። እየሆነ ያለው ሁሉ ግራ ገባኝ።

“ለምንድነው እንዲህ ጥሩ የሆንክልኝ? ወይስ ለሁሉም ሰው እንዲህ ነህ?” አልኩት

“ለማንም ሰው ቢሆን አዎን ጥሩ ለመሆን ነው የምሞክረው። ላንቺ ግን በተለየ ጥሩ ለመሆን እየሞከርኩ ነው።”

“ለምን? ለምን በተለየ?”
አልኩት የዘረጋልኝን ጉርሻ ከመጉረሴ በፊት

“ምክንያቱም ልጄ ይወድሻል። አንቺ ትወጂዋለሽ ወይስ አትወጂውም ሌላ ነገር ነው። ይህን የማደርገውም push ላደርግሽ አይደለም።”

“ማን? ፍትህ? መውደድ ማለት? በፍቅር እያልከኝ አይደለምኣ?”

“ነው። እንደዛ እያልኩሽ ነው። ወተቱን ማጊበትና ይህቺን ጉረሺ።” ያጎረሰኝን አላምጬ ሳበቃ

“እስከማውቀው ድረስ ፍትህ እንደኔ አይነት ሴት ምርጫው አይደለችም። ደግሞ ይቅርታ አድርግልኝና በሴት ረገድ ልጅህ መረን ነው። በጣም ይቅርታ ግን!”

“አውቃለሁ። ስለልጄ የማላውቀው ነገር የለም። ፍትህ እናቱን ያጣው በ13 ዓመቱ ነው። እኔ ለስራ ሌላ ሀገር በሄድኩ ማታ እቤት ገብተው በዘረፉን ወንበዴዎች በሽጉጥ ነው የተገደለችው። (እስከአሁን ያላየሁበትን መከፋት ፊቱ ላይ አየሁ።) ስትመታና ስትወድቅ ስትሞትም ፍትህ እዛው ነበር። እያያት!! ለብዙ አመታት የእናቱ ሞት ሀዘን የተጫነው ምስኪን ልጅ ነበር። ተንከባክቤ አሳደግኩት ፤ ደስተኛ ያደርገዋል ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ አደረግኩ ፤ የእናቱ መጉደል ፍፃሜውን እንዳያበላሽ ስለፈራሁ አቀበጥኩት። ነገር ግን ቆይቶ ሲገባኝ ልጄን ለድርጊቶቹ ሀላፊነት የማይወስድ ግድ የለሽ አደርጌ ነው ያሳደግኩት፤ መጎዳቱን ፍራቻ ሲያጠፋ እንኳን አምርሬ አልቆጣውም ነበር። ምንም ጎድሎበት አያውቅም።ያለው ሁሉ በጥረቱ ያገኘው አልነበረም እናም ዋጋ የሚያስከፍለው ምንም ነገር አይፈልግም። ጥሩ ትምህርት ቤት አስተምሬዋለሁ። አስጠኚ ቀጥሬ እንዲጎብዝ ጥሬያለሁ። ዩንቨርስቲ ገብቶ ተመርቆ ቢወጣም ስራ መስራት አይፈልግም። እኔን ላለማስከፋት ነው ስራ የሚሰራው። ከዛ ይልቅ ከሴትና ከመጠጥ ጋር ውሎ አዳሩ ቢሆን ደስተኛ ነው። ስለእውነት አሁንም ቢሆን ጨክኜ አምርሬ ልቆጣው ያሳሳኛል። ቁጭ አድርጌ እመክረዋለሁ። እናንተጋ መስራት ከጀመረ ቀን ጀምሮ ስለአንቺ ሳያወራልኝ አድሮ አያውቅም። ቆንጆ መሆንሽን፣ ደረቅ መሆንሽን፣ በስራሽ ጉብዝናሽን፣ ስቀሽ እንደማታውቂ…… ። ላለፋት ሁለት ሳምንት ግን ፍትህ ሌላ ሰው ነበር። በጊዜ ወደቤቱ ይገባና ሲጨቀጭቀኝ ያመሻል። ‘ምን ሆና ይሆን? አትወደኝም እኮ ቁምነገር የሌለው ዱርዬ ነው የምመስላት፣ ካስዬ ቆይ እሺ እንድታዋራኝ ከዚህ በላይ ምን ላድርግ?’ ሲለኝ ይመሻል። ትናንት ደውሎ የተፈጠረውን ነገረኝ። ልጄ በህይወቱ ስለምንም እንደዚህ ግድ ሰጥቶት አያውቅም።” የሚያወራልኝን እየሰማሁ የቀረበውን ምግብ በጉርሻ አገባድጄዋለሁ።

“በቃኝ በናትህ ብዙ በላሁ።”

“አንድ የመጨረሻ ይህቺን!”

የፍትህ መኝታ ቤት እንዳርፍ ተሰናዳልኝ። ድምፁ ዝግ ያለ ተመሳጮች ለተመስጦ የሚጠቀሙበትን የሚመስል የኮሪያ ክላሲካል ሙዚቃ ተከፍቶ ክፍሉ የሆነ የሚያባብል ድባብ አለው።
“በቃ ትንሽ አረፍ በይና እናትሽጋ እንሄዳለን። የምትፈልጊው ነገር አለ?”

“የለም። በጣም ነው የማመሰግነው።” አልኩት አልጋው ጫፍ ላይ እየተቀመጥኩ።

“እንደሱ ስትዪኝ ይከፋኛል። እቤቴ እኮ አስገባሁሽ ፤ በእጆቼ አጎረስኩሽ …… ከዚህ በላይ ቅርበት ምንድነው? እንደአባትሽ እይኝ።…… ” ይሄን ሲለኝ ከየት መጣ ያላልኩት የእንባዬ ጥርቅም በሳግ ታጅቦ ተንዠቀዠቀ።… … አጠገቤ መጥቶ በእጆቹ አጀብ ደረቱ ላይ አኖረኝ። አላባበለኝም። እንዳለቅስ ፈቀደልኝ።

“ንገሪኝ!” አለኝ ሲበርድልኝ ጠብቆ

“ምኑን?”

“ይሄ የዛሬ ወይ የትናንት ሀዘን የፈነቀለው ለቅሶ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ንገሪኝ ሁሉንም!!”

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ስድስት)

One Comment

  • ROBEL.TILAYE@GMAIL.COM'
    Robel commented on August 19, 2017 Reply

    Seriously have no words Fascinating!!!!!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...