Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (የመጨረሻ ክፍል)

[አልነገርኩትም። የማላውቀው ሰው የሆስፒታሉ መግቢያ በርጋ ጠብቆኝ የትዝታን ጉዳይ ማነፍነፍ ካላቆምኩ ከምወዳቸው ሰዎች አንዳቸውን እንደማጣ እንዳስጠነቀቀኝ አልነገርኩትም። ብዙ ነገር አልነገርኩትም። እንዲያውም ምንም አልነገርኩትም። እማዬ ከዚህ በኋላ ህክምና የሚፈይድላት ነገር ስለሌለ ወደቤቷ ወስደናት ዓይን ዓይኗን እያየሁ የምትሞትበትን ቀን መጠበቅ ትኩስ ቁስል ላይ ሚጥሚጣ እንደመበተን እየለበለበኝ እንደሆነ አልነገርኩትም። እቅፉ ውስጥ ሆኜ እዬዬ ብዬ ማልቀስ እንደምፈልግም። ከሰሞኑ አባቴን ሆስፒታል በማድረስ ሰበብ አዘውትረው ሲመጡ እህቴና ባሏን ማየት ልቤን በደም ፈንታ ቅናት እንደሚያስረጨው አልነገርኩትም። በእኔና በእርሱ መሃል ምንም ነገር እንደሌለ የሚሆነው መሆን እየከፋኝ አልቅሺ አልቅሺ እንደሚለኝ አልነገርኩትም። በዚህ ሁሉ ማጥ ውስጥ አቅፎኝ ያደረ ቀን የማግኩት ጠረኑን እርሱ አጠገቤ ሳይኖር እንኳን ካለበት ንፋሱ እያንጓለለ ለአፍንጫዬ እንደሚያቀብለው አልነገርኩትም። አጠገቤ ሆኖ ስለስራ እያወራኝ ልነካው እንደምፈልግ፣ ልስመው እንደምጎመዥ፣ እርሱ የኔ ቢሆንና በፈለግኩት ቁልምጫ ልጠራው እንደምመኝ… … አልነገርኩትም።]

“ማንናቸው?” አለኝ ዓይኔን ተከትሎ መኪና ውስጥ ያሉትን እህቴንና ባሏን እያያቸው

“እህምም…… እህቴ ናት! ባሏ ነው። አባቴን ወደቤት ሊያደርሱት እየጠበቁት ነው።” አልኩት አንገቴን ሰብሬ

“ታዲያ ምን?” አለኝ ዓይኔን እየፈለገ

“ምን?”

“ለምንድነው ስታያቸው በነበረው እይታ የምታያቸው? ምንድነው እሱ?”

“ኸረ ምንም አይደለም። በቃ ከእህቴ ጋር ስለማንነጋገር ነው።”

“አይደለም ራሁ። እያየሁሽ እኮ ነው። ቆይ ምንባደርግ ነው የተሰማሽን ልትነግሪኝ የምታምኚኝ? የበለጠ የቀረብኩሽ በመሰለኝ ቁጥር ለአካልሽ እንጂ ለልብሽ አልቀርብሽም። አብሬሽ ውዬ ባድር ቅርበቴ አይሰማሽም።…”

“ፍቅረኛዬ ነበረ። እህቴ ያገባችው ሰው…” ወቀሳውን እንዲያቆምልኝ ይሆን ለልቤ መቅረቡን እንዲያውቅልኝ አላውቅም። ነገርኩት!!

[ ዘጠነኛ ክፍል ስገባ አንድ ወንበር ላይ ከተቀመጥን ጀምሮ ብቸኛ ጓደኛዬ ዓለማየሁ እንደነበረ ግን አልነገርኩትም። የአስረኛ ክፍል ፈተና ተፈትነን ከተማሪዎች ጋር ከከተማ የወጣን ጊዜ ከንፈሬን ሲስመኝ ከርሱ ውጪ ያለውን ዓለም እንደረሳሁ አልነገርኩትም። በመከራ ከተከበበው ኑሮዬ የተረፈኝን ሰዓት ከርሱ ጋር ማሳለፌ በነገ ተስፋ እንዳልቆርጥ መፅናኛዬ ሆኖ በጥሩ ውጤት አብረን ዩንቨርስቲ እንደገባን አልነገርኩትም። ብዙ ጊዜ ‘ድብቅ ነሽ አላውቅሽም’ እያለ ቢነጫነጭም ይተወኛል ብዬ ለአፍታ አስቤ ባለማወቄ ሲተወኝ ከእማዬጋ አብሬ ማበድ ዳድቶኝ እንደነበረም አልነገርኩትም። የባሰው ደግሞ ከዓመታት በኋላ እሱ ዩንቨርስቲ አስተማሪ ሆኖ ተማሪው ከሆነችው እህቴ ጋር በአጋጣሚ ይሁን አስቦበት እስከአሁንም በማይገባኝ ሁናቴ ግንኙነት መጀመራቸውን ሆነ ብሎ ደውሎ የነገረኝ ማታ ራሴን ልስት እንደነበረ አልነገርኩትም። እህቴ ከዩንቨርስቲ በተባረረች በወራት ውስጥ የሰርጋቸው ጥሪ ካርድ ሲደርሰኝ ራሴን ባለመፈለግ ስሜት ውስጥ አዝቅጬው መብሰክሰኬን አልነገርኩትም። ከዓለማየሁ በፊትም በኋላም ሌላ ፍቅር እንደማላውቅም አልነገርኩትም።]

“እና አሁንም ድረስ ትወጂዋለሽ? እየቀናሽ ነው?” አለኝ

“አይይይ ለሱ ምንም ስሜት የለኝም። በሱ አልቀናም።”

“በሷ?” እያለኝ በጣም ተጠጋኝ። ትንፋሹ ጉንጮቼ ላይ እያቃጠለኝ አስቤ የተሰደሩ ቃላት መናገር አልችልም ነበር። በጭንቅላቴ ንቅናቄ ‘አዎን’ አልኩት። አልበቃውም እንድቀጥልለት ይጠብቃል። ምራቄ እያነቀኝ ነው።

“አባቴ ከእኔ እሷን ነበር የመረጠው። ፍቅረኛዬም… …” አላስጨረሰኝም ከንፈሬን በከንፈሩ ከደነው። መሳሙ ቀለምም ነበረው፣ ሽታም ነበረው፣ ጣዕምም ነበረው……

“በሚፈጠሩ ክስተቶች ውስጥ ራስሽን እየከተትሽ አትስፈሪ። ሁኔታዎች ሁሉ አንቺን ሚዛን ላይ አስቀምጠው አይለኩም።” አለኝ ለምን ያህል ደቂቃ እንደሆነ ስሞኝ ሲያበቃ… … ሰምቼዋለሁ? ገብቶኛልስ? መሳሙን እያጣጣምኩ ነበር።

“ተያቸው! እርሻቸው!” አለኝ ወደእነእህቴ እያየ። እያየኋቸው ነበር። የልጅ ስሜት ቢመስልም አዎን ሲስመኝ ማየታቸውን ለማረጋገጥ ነበር የማያቸው። አለ አይደለ እኔም ሰው አለኝ አይነት! አልጎዳችሁኝም አይነት! እንዳዩኝ በማወቄም በከፊል የታባታችሁ አይነት ስሜት……

በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ብዙ ነገር ተቀየረ። እንደውም ሁሉም ነገር!! እማዬ ወደቤት መጣች። ካስዬና አባቴ እቤታችን እየመጡ እናቴን መጠየቅ ጀመሩ። እኔና ፍትህ ቤተሰቦቻችን እስኪያውቁ እንደፍቅረኛሞች ገብተን መውጣት ጀመርን። ፍትህ የትዝታን ጉዳይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሊጠይቅ በተዘጋጀበት ወቅት እጅ ያሰጠው ሁናቴ ተፈጠረ። አባቴ ሞቶ ተገኘ።

ቆይ ቆይ ፍትህ በትዝታ ጉዳይ ተስፋ መቁረጡ እና 25 ዓመት ሲፈረድባት መዋጡ ቀላል አልነበረም። ቤተሰቡን በሙሉ ያስከፈለ መስዋዕትነት እንጂ… …… ካልንበት እንቀጥል። አባቴ ተገደለ! ይቅርታ እንዳደርግለት ሲለማመጠኝ የነበረው አባቴ አንድስ እንኳን በጎ ቃል ሳልነግረው ሞተ። በራሴው ጉዳይ እርሱ አንዲት ጠጠር ባላበረከተበት የነገር ካብ ህይወቱን አጣ!! ለፍትህ ይሄ የመጀመሪያው መሆኑ እና ካላረፈ ሌሎቻችንም ተራ ጠባቂዎች መሆናችን እና ቀጣይዋ እኔ መሆኔ ማስጠንቀቂያ ደረሰው። ይሄኔ ነው እጅ የሰጠው! ከእኔ በላይ ሁሉ የተጎዳ መሰለኝ።

“በፍፁም አንቺን ለምርጫ ማቅረብ አልችልም። አንቺን ማጣት አልችልም።” ይለኛል እየደጋገመ። ለማን እንዳለቀሰ ያልገባኝን ለቅሶ በአባቴ ቀብር ላይ ምርር ብሎ አለቀሰ። ግራ የገባው ስሜት ውስጥ ጠለቅኩ። አንዱ አካሌ ሽባ የሆነ ነገር ይመስለኛል። ከሬሳው ጋር የቀበርኩት ነገር ያለ ይመስል የሆነ ስሜቴ ወደአባቴ መቃብር ይጎትተኛል።

የባሰው ነገር ለእናቴ የፍቅሯን ሞት ማርዳት ነበር። በየቀኑ እየመጣ ሲያያት የከረመውን ሰው በምንም ሰበብ ቀረ ልንላት አንችልም። እንደገና እንደተዋት በምንም ምክንያት ሰንገን ብንነግራት ጤነኛ አትሆንም። መሞቱንም ብታውቅ ጤነኛ አትሆንም። ቢያንስ ግን ከመከዳት ስሜት ፍቅረኛዋ እያፈቀራት መሞቱን ማወቋ ይሻላል በሚል ተስማምተን የተሻለ ሁኔታ ላይ ያለው ካስዬ ነገራት። ዝም አለች። ለሁለት ሰዓታት ዝም አለች። እኔን የምታይበትን መንገድ አልወደድኩትም። ያንቺ ጦስ ነው ፍቅሬን ያሳጣኝ አይነት መልዕክት አለው። ድንገት ከየት ባመጣችው ጉልበት እንደሆነ እንጃ ተስፈንጥራ ተነስታ ቀብሩን እሄዳለሁ ብላ አመሰችን። ካስሽ ይዟት ሄደ። ካስሽ ደግፏት ፍቅሯ አፈር ሲገባ አነባች። አለቃቀሷ ግጥምም ቃልም ሳይኖረው ዜማ አለው። እያየኋት ለአባቴ ይሁን ለእርሷ ብቻ አነባሁ! ስለእውነት የውብዳር እንኳን ስታለቅስ አሳዘነችኝ። በየመሃሉ ለሞቱ ተጠያቂ መሆኔን ልትነግረኝ አንዳንድ ሀረግ ትመዛለች። እህቴ አፈሩ ላይ ተልሞሰሞሰች። ትንፋሽ አጥሮኝ ደረቴ ላይ ሲያፍነኝ ነው ቀብሩ ያበቃው እና ወደቤታችን የተመለስነው።

እቤት ከመግባታችን እማዬ “ይሄ የበረራ ቁጥር… …” ማለት ጀመረች። መሬቷ ያንሳፈፈችኝ አይነት ስሜት ተሰማኝ። ግራቪቲ የከዳኝ! ያልበላሁት ምግብ ወደ ላይ ወደላይ አለኝ። እሪሪሪ ብዬ ማልቀስ እፈልጋለሁ። ግን ጉሮሮዬም ደረቴም የታፈነ ይመስለኛል።

“እኔ አለሁ አንቺ እረፊ!” አለኝ ካስዬ። እንዳለውም ከዚያን ቀን በኋላ ኖረ። ምክንያቱም በሚቀጥሉት ቀናት እናቴ ማነሽ? ማለት ጀመረች። ፍትህንም ስታይ መበርገግ ጀመረች። የሚገርመው ካስዬን በባሏ ስም አንድዬ እያለች መጥራት ጀመረች። ከእርሱ ውጪ ማንንም አታስጠጋም። (ሀኪሟ እሷ እንኳን ሳታውቀው ለካስዬ የሆነ የተለየ ስሜት እንደነበራት እና ሲያማት ከፍቅሯ ጋር እንደተማታባት ሳይኮሎጂ ጠቅሶ መላ ምት መታ።) ፍትህ በኔ ልመናና ጭቅጨቃ ይግባኝ በመጠየቁ ስጋቱ ሊያሳብደው ደርሶ ራቅ ያለ ቦታ አዲስ ቤት ተከራይተን አብረን መኖር ጀመርን።

” 20 ዓመት ሙሉ ያላየሁት አባቴ ለወራት ካጠገቤ ነበረ። ይቅር በይኝ እያለኝ ፣ እንደምጠላው እያሰበ… አልጠላህም ሳልለው፣ ስናፍቅህ ነው የኖርኩት ሳልለው፣ ይቅር ብዬሃለሁ ሳልለው ነው የገደሉት……” እንባዬን ማስቆም ተስኖኝ በመሃከላችን ባለው ርቀት እንዲሰማት ጮክ እያልኩ ለትዝታ ነው የምነግራት። አትመልስልኝም። የአባቴ መሞትም የእኔ እንባም ስሜት የሰጣት አትመስልም።

“እናቴ ልትሞትብኝ ነው። በሰዎችሽ ጦስ አዕምሮዋ ተቃውሶ እኔን ልጇን እንኳን አታውቀኝም። ያ ምን ማለት እንደሆነ ታውቂያለሽ? ማን እንደሆንኩ ሳታውቅ ሳትሰናበተኝ እማዬ ትሞትብኛለች ማለት ነው።” ብዙ የሀሳብ ድሮች ያደሩበት በሚመስል ጠባብ እይታ ታየኛለች እንጂ አትመልስልኝም።

“ፍቅረኛሽን አስገድለውታል። አንቺንም ለማይሆን ህይወት ዳርገውሻል። ሀያ አምስት ዓመት ወህኒ እንድትበሰብሺ አጨብጭበው ሸኝተውሻል።ልጅሽም ነገ እጣዋ ምን እንደሆነ አይታወቅም። እና አሁንም ለእነርሱ ትከራከሪያለሽ! ምንድነው ችግርሽ? አሁን ካለሽበት የባሰ ምን እንዳይመጣ ነው?…… ” ለፍልፌ ሳበቃ

“እወደዋለሁ።” አለችኝ

“ማንን?” የማስበው እውነት ባይሆንና ብንንን ብሎ ቢጠፋ እየተመኘሁ

“ሰለሞንን!”(አጎቷ ነው) ደነዘዝኩ። ከሁለት አንዳችን ጤነኛ ባንሆን ነው። ለተከታዮቹ ደቂቃዎች እሷ ተናጋሪ እኔ በድን ሰሚ ሆንን። ትቻት ስወጣም በድኔን እየጎተትኩ ነበር። ጭንቅላቴ ውስጥ የሀሳብ መዘውር ያለ ይመስለኛል። አንዱ ሀሳብ ሌላውን እያስከተለ በመዘውሩ የሚፈጭ…… ርርርርር የሚል የሞተር ድምፅ ያለው መዘውር።

ሰውየው አስገድዷት አይደለም። ገና ከ12 አመቷ ጀምሮ እያባበለ ያስለመዳት የስድ ጨዋታ ነው። ለምዳዋለች። ልምዱን አልጠላችውም። እንደውም ስታወራኝ እንኳን ከሚወዱት ፍቅረኛ ጋር እንዳሳለፉት ጣፋጭ ጊዜ የፊቷ ፀዳል እየበራ ነው። በመጀመሪያ ፊልሞች ያሳያታል። እያንገላቱ፣ እያሰቃዩና እየገረፉ የሚረኩ ወንዶች ፊልም… … በስቃዩ ውስጥ የተሳመች ያህል በማቃሰት የምታብድ… … እንዲያሰቃያት የምትለምን ሴት ያለችበት ፊልም… … ቀስ በቀስ አለማመዳት። ጤነኛ ሰው ሊወደው የማይችለውን sex torture እንደ ሱስ ለመደችው። ደስ ብሏትና ፈልጋ የምታደርገው ቅውሰት ሆነ። አጎትየውን ከሴት ጋር ስላገኘችው በእልህ ታዲዎስን ፍቅረኛዋ አደረገችው። ሰላማዊው ታዲዎስ አጎቷ የሚነዳትን የእብደት ቁልቁለት ሊያንቆለቁላት አይችልምና ሱስ እንዳባዘተው ወመኔ በሱስ ጥም አዛጋች። ከሁለቱም ጋር ሆነች። በዚህ መሃል የአጎቷን ልጅ አረገዘች። ታዲዎስ የእኔ ልጅ ነው ብሎ ቁምስቅሏን ሲያሳያት ነው እውነቱን የነገረችውና የዘመኑ ቁጥር በአጎቷ በጎ ፈቃደኝነት እንዲወሰን የፈረደችበት። ከዛ የቫንፓየር ወይ የማርስ ፍጡሮች ተረት እንጂ ሰውነት የማይመስል አኗኗር ሰውየው ከወንድሙ ልጅጋር እንደባልና ሚስት ኖሩ።… … የዛን ዕለት ምሽት ሴት ይዞ እቤት መጣ! በቅናት የነደደ አካሏ ያዘዛትን አደረገች። ምንም የማታውቅ ንፁህ ነፍስ ጠፋች።

“ልጄ ከአጎቴ እንደወለድኳት እንድታውቅ አልፈልግም። ሶልም ይሄ ነገሩ ቢታወቅ ስሙ ይጠፋል፣ ይታሰራል። የወንድሙም ስም አብሮ ይነሳል(ባለስልጣን ወንድሙን ማለቷ ነው።) ሶልን እወደዋለሁ። መጥፎ ነገር እንዲደርስበት አልፈልግም።” አለችኝ የሆነ ልክ የሆነ ነገር እንደነገረችኝ ሁሉ ሀፍረት ሳይሰማት። ዘገነነችኝ። በእርግጥ አሳዘነችኝም። የሆነ አይነት በሽታ እንደሚሆን አሰብኩ። የገዛ ሰውነቴ እየሸከከኝ ወጣሁ። ጭንቅላቴ ውስጥ ያለው መዘውር አልቆመም።

የኑሯችን መዘውር የሚዞረው በሚገጥሙን ክስተቶች ግብዓትነት አይደለም እያልኩ አስባለሁ። ይልቅስ በገጠሙን ክስተቶች ላይ በወሰንነው ውሳኔና በዘረጋነው እርምጃ እንጂ…… ኑሯችን የውሳኔያችን ውጤት እንጂ ያጋጠሙን መከራና ፍሰሃ ውጤት አይደለም። ……

“ literally she is sick, serious ህክምና ያስፈልጋታል።” አለኝ ፍትህ ነገሩን ስነግረው እየሰቀጠጠው።

“ከአሁን በኋላ የትዝታ ኬዝ አይደለም። አባቷን በስድ ግፈኞች የተቀማች ልጅ ኬዝ ነው። የራሴ ጉዳይ ነው።” አልኩኝ ከመናገሬ በፊት ያሰብኩት ያልመሰለኝን ንግግር! …………

እስከዛሬ ያላነበባችሁም አንብቡ! ታግ ማድረግ ሳቆም ያቆማችሁም ቀጥሉ!

እና ደግሞ መልካም በዓል!!

4 Comments

 • helinaberhane26@gmail.com'
  Helina berhane commented on December 7, 2017 Reply

  Most fascinating! !

 • Sifenmamo@gmail.com'
  ሲፈን ማሞ commented on December 11, 2017 Reply

  ጉጉትን የሚፈጥርና መሳጭ ብዬዋለሁ !

 • Sifenmamo@gmail.com'
  ሲፈን ማሞ commented on December 11, 2017 Reply

  በእውነት ጉጉትን የሚፈጥርና መሳጭና ስሜትን የሚነካ ነበር !

 • asniwitnes@gmail.com'
  wizme12 commented on November 30, 2019 Reply

  እጅሽ ይባረክ ማለቁን አላመንኩም

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...