Tidarfelagi.com

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ሰባት)

“ይሄ ኬዝ እንዲህ ቀልብሽን የሳበው የትኛው ነጥብ ነው? ግልፅ ማስረጃ ነው የተያዘባት። ራሷም ድርጊቱን መፈፀሟን አምናለች።”

“ፍትህ ሰዎቹን ፈራሃቸው እንዴ?”

“በፍፁም ፈርቼ አይደለም። ከእነሱ ጋር ስለመያያዙም ገና መላምት ነው ያለሽ።”

ከፍትህ ጋር ሻይ እየጠጣን እየተነጋገርን ያለነው ስለትዝታ ነው። ትዝታ የ23 ዓመት ልጅ ናት። የአጎቷን ‘ፍቅረኛ’ በአጎቷ ሽጉጥ አራት ጊዜ ተኩሳ መግደሏን አምናለች። ለፖሊስ እጇን የሰጠችው ራሷ ናት። ለመግደል አበቃኝ ያለችው ምክንያት ለጥፊም የሚጋብዝ አይደለም። አጎት በአዲሳባችን ካሉ ባለሀብት አንዱ ነው። በተጨማሪም የሚንስቴር ወንድም ነው። ትዝታ አባቷ በ7 አመቷ ስለሞተ ያሳደጋት አጎቷ ነው። በ16 አመቷ ከጋብቻ ውጪ የወደቻትን ልጇንም እያሳደገላት ነው።

“ሰውየው ምንም ነገር የማድረግ አቅሙ ያለው ሆኖ ሳለ ጠበቃ እንኳን የቀጠሩላት የእናቷ ዘመዶች ናቸው። አስበው ትዝታ ልጁ ማለት ናት። ሌላው የሟች ጉዳይ ነው። ሟች የናጠጠ ሀብታም ሰውዬ ፍቅረኛ ሆና እናትና አባቷ ግን ከልጃቸው እጅ ስባሪ ሳንቲም ያልተለገሳቸው እና ለእለት ምግብ የሚቸግራቸው ሰዎች መሆናቸው ሲደመር ፍቅረኛ እንዳላትም አለማወቃቸው የሚጎረብጥ ነገር አለው። ትዝታ የሆነን ሰው እየተከላከለች እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።”

“ማንን?”

“እሱን ማወቅ ያንተ ድርሻ ነው። እ? ገብተህበታል?”

“እሺ። ገብቼበታለሁ።” ይበለኝ እንጂ እንዳላመነበት ያስታውቅበታል።

“ፍትህ በህይወትህ ያልተለመደ ዓይነት ስኬት ላይ መድረስ ከፈለግክ ያልተለመደ ዓይነት ድፍረት ሊኖርህ ይገባል። ከተራ መንገድ ለመውጣት ማፈንገጥ አለብህ። ለእኔ ብለህ ብቻ እንድታደርገው አልፈልግም። አንዲት እርምጃ ከመራመድህ በፊት አንተ እንድታምንበት እፈልጋለሁ።” አልኩት።

“እስቲ መጀመሪያ ከትዝታ ጋር የምገናኝበትን መንገድ አመቻቺልኝ።”

“ሌላው ችግር ይሄ ነው። ጉዳዩን ውስብስብ እና አዳጋች የሚያደርገው ትዝታ ምንም አይነት መረጃ አትሰጥህም። መታሰር ነው የምትፈልገው። ጠበቃ እንዲኖራትም አትፈልግም። አንድ ሺህ ጊዜ ብትጠይቃት አንድ ሺህ ጊዜ የምትመልስልህ አንድ ዓይነት መልስ ነው። ለማንኛውም ግን ነገ ቀጠሮ አለኝ እናገኛታለን።”

በዚህ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ ባልሆንኩበት ምክንያት ፍትህ ጥሩ ሰርቶ ማየት እፈልጋለሁ። እንድኮራበት እፈልጋለሁ። አባቱ እንዲኮራበት እፈልጋለሁ። እሱም ራሱ በራሱ እንዲኮራ እፈልጋለሁ።

“ፍትህ አባትህ ዛሬ ደብሮታል። አንተ ወደ ቤት ሂድ። እኔ እማዬጋ ልመለስ።”

“ህምም እናቴጋ ሄዶ ነበር?”

“አዎን” አልኩት ሂሳብ እንዲቀበሉን አስተናጋጅ ለመጥራት እጄን እያነሳሁ። እጄን ለቀም አድርጎ ያዘኝ። ደንግጬ አየዋለሁ።

“ይቅርታ ራሁ አስደነገጥኩሽ። ትንሽ አብረሽኝ ቆዪ?” አለኝ ያያዘውን እጄን አጥብቆ እየያዘው። በጭንቅላቴ እሺ አልኩት። ዓይኖቹን ሳያርገበግብ ስላፈጠጠብኝ ተጨነቅኩ። ዓይኔን ከዓይኑ ብነቅልም እንዳፈጠጠብኝ ይታወቀኛል። ምራቄን ስውጥ ጉሮሮዬ ያስተጋባል። ያልያዘውን እጄን ጣቶች ከጠረጴዛው ስር አፍተለትላለሁ።

“ዓይኖቼን እንድታያቸው የግድ ስለስራ ነው ማውራት ያለብን?” ድምፁ ወፍራም ግን ለስላሳ ዓይነት ሆነ። የሰውነቴ ቆዳ ላይ እንደሆነ ሞገድ ሽው ሲል ይታወቀኛል።

“እያሳፈርከኝ ነው ፍትህ!” አልኩት። ባላየውም ፈገግ ማለቱን አውቄያለሁ። ባይናገርም አንደኛውን እጁን ዘርግቶ የጠየቀኝ ሌላኛውን እጄን መሆኑን ስላወቅኩ አቀበልኩት። እጆቼን ዘርግቶ ጣቶቼን እያያቸው ቀና ይላል።

“ጣቶችሽ ያምራሉ።” ባለኝ ቅፅበት ተራ በተራ ሁለቱንም እጆቼን ጣቶቼጋ ሳማቸው። ሆነ ብሎ ከንፈሮቹን ጣቶቼ ላይ አቆይቶ የተሰማኝን ለማወቅ ዓይኖቼን ይፈልጋል። በርግጌ ተነስቼ ልቆም ትንሽ ነበር የቀረኝ። ‘አገኘሁሽ’ አይነት ፈገግታ ፈገግ አለ።

“ፍትህ ሰው እያየንኮ ነው?”

“እና እኔ ምንአገባኝ? ዓይኑን የሚያሳርፍበት ቆንጆ ጎኑ ባይኖር ነው።” ብሎኝ የእጆቼን መዳፍ ተራ በተራ ሳማቸው። አይኔን ጨፈንኩ ልበል?

“ስለአንቺ የማላውቀውን አንድ ነገር ንገሪኝ?” አለኝ ወደእኔ እየሰገገ ተጠግቶኝ።

“ምንም አታውቅምኮ። ስለምንድነው ማወቅ የፈለግከው?”

“አሁን እኔ ማወቅ ስለሚገባኝ ነገር” ድምፁ ልክ የሆነ ስሜት አይሰጥም። እንኳን ቃላት ሰካክቼ በስርዓቱ ላወራ የማስበውን እንኳን ይበትንብኛል።

“ማለት?”

“አሁን መስማትም ማወቅም የምፈልገው እነዚህን እጆች የሚጨብጣቸው ሰው አለመኖሩን ነው።(እጆቹ እጆቼ ላይ አስማታዊ መርመስመሳቸውን አያቆሙም።) ፤ ፀጉርሽ ውስጥ ጣቶቹን ሰክቶ የአንገትሽን ጠረን የሚምግ፣ ከንፈሮችሽን ጎርሶ በትንፋሽሽ እድሜውን የሚቀጥል፣ (ዓይኖቹ የሚጠራቸው የሰውነት አካሌ ላይ በስድ እይታ ያርፋሉ። እኔን ግን ምን እየነካኝ ነው? የምሰማው ድርጊት እየሆነ ያለ ያህል ይሞቀኛል።) በአይኖችሽ መስለምለም ቀኖቹን የሚያደምቅ፣ የሸሚዞችሽን ቁልፍ ከፍቶ… ”

“እረፍ ፍትህ! እረፍ በቃህ! ማንም የለም!” አስቤ የተናገርኩት አልነበረም። አሁንም የቅድሙን ፈገግታ ደገመልኝ። እጆቼን ስለለቀቀልኝ ተነፈስኩ። ሆስፒታል ሸኝቶኝ ተመለሰ። ካፌ ተቀምጠን ያደረገውን እንዳላደረገ በቅጡ እንኳን ሳይጨብጠኝ ነው የሄደው። ተናደድኩ ልበል? ምን እየሆንኩ ነው? ምን እንዲያደርግ ነበር የፈለግኩት? ምናልባት የሚያደርገው ሁሉ ለብዙ ሌሎች ሴቶች ያደረገው ለእርሱ ምኑም ያልሆነ ይሆን? ምንዓይነቷ ቀሽም ነኝ?

እማዬ አስር ጊዜ “ምን ሆነሻል?” ስትለኝ ራሴን ገስፃለሁ። እየሆንኩ ያለሁት በግሳፄ ማቆም የምችለው ጉዳይ ግን አልሆነም።

“አባትሽ ስለመጣ ተናደሻል?” እማዬ ስትጠይቀኝ በራሴ በሸቅኩ። ምንም የኑሮ ማገር እንዳላፈነገጠብኝ ስለፍትህ በዚህ ጥልቀት ማሰቤ አናደደኝ።

“ኸረ እማዬ… … ለምን እናደዳለሁ? አንቺ ደስ ካለሽ የኔ ደስታ ያ ነው።”

“እንደምትጠዪው አውቃለሁ። አንቺን ደስ ካላለሽ ድጋሚ እንዳይመጣ እነግረዋለሁ።”

“እማዬ አንደኛ አልጠላውም። አልወደውም ማለት እጠላዋለሁ ማለት አይደለም። ከመጥላትና ከመውደድ ፅንፍ መሃል ምንም ስሜት ማጣት አለ። እንደዛ ነው ለሱ ያለኝ ስሜት። ሁለተኛ የአንቺ ፈቃድ ይሁን እንጂ በተመቸው ሰዓት መጥቶ ሊያይሽ ይችላል።”

የአባቴን ጉዳይ በጤነኛ ጭንቅላቷ ስትሆን ደፍራ አታወራኝም። በዚህ ሁሉ ስቃይዋ እሱን ማፍቀሯ እኔን መበደል የሚመስላት ይመስለኛል። ለእኔ አንዳችም የአባት ርህራሄ ያላሳየኝን ሰው ጭንቅላቷ እስኪዛባ ማፍቀሯ እኔ ለእርሷ ያደረግኩትን መልካምነት መደለዝ ይመስላታል መሰለኝ። ስለእውነቱ ሰውየውን አልወደውም። እሷ ስለምታፈቅረው ግን አልናደድባትም። ያንን ደግሞ ያስተማረችኝ ራሷ ናት። ‘ኩታ በየፈርጁ ይለበሳል።’ ትለኛለች። ለእሱ ያላት ፍቅርና ለእኔ ያላት ቦታ የሚጋጭም ፣አንዱ ሲጨምር ሌላው የሚቀንስም ፣ የሚወዳደርም አይደለም። ስለዚህ እኔንና እሱን ለምርጫ አላቀርብላትም። ሁለታችንንም በልቧ መያዝ ትችላለች።

“እማዬ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ? ካልፈለግሽ አለመመለስ ትችያለሽ። ”

“ጠይቂኝ!”

“የእውነትሽን ያደረገሽን ነገር ረስተሽለት ነው? ይቅር ብለሽው ነው?”

“በእርግጥ ይቅር ብዬው ነው። ያ ማለት ያደረገኝን ረስቼው ነው ማለት አይደለም። አየሽ ሚሚሾ በደንብ ስሚኝ ከመስከረም እስከ ነሃሴ በፍቅሩ ከልሎ ፣ በርህራሄው ከብቦሽ፣ በሀዘንሽ አልቅሶ፣ በደስታሽ ፈንጥዞ ፣ በጉያው አሙቆ…… ያከረመሽ ሰው ጳጉሜ 5 ላይ ቢበድልሽ የቱን ትቆጥሪበታለሽ? ብዙ ፍቅሩን ወይስ አንዲት በደሉን? ሰዎች ስሪታችን ሆኖ ከፍቅር ይልቅ በደል በደማችን ቶሎ ይሰርፃል። እኔ የመረጥኩት ብዙ ፍቅሩን ነው። ፍቅሩ በደሉን ይከድንብኛል። ለነፍሴም ሰላም የሚሰጠኝ ያ ነው።” አለችኝ በጣም በተረጋጋ መንፈስ። በልቤ ይዣት መኖር የምፈልገው ይህቺን እናቴን ነው። በብዙ ምክሯና ፍቅሯ በማይነቃነቅ የሞራል አለት ላይ የተከለችኝ እናቴን።

“እሺ!” ከማለት ውጪ እሷ ላለችበት የፍቅር ልእልና መልስ አልነበረኝም።

“ደግሞም ልጄ የተበደልነው ህመም ከበደልነው በላይ የሚጠዘጥዝ እንደሆነ ስለሚሰማን የተደረገብን እንጂ ያደረግነው የሚፈጥረው ቁስል አያመንም እንጂ አባትሽን ከበደለኝ በላይ በድዬዋለሁ። ምናልባትም እኔ ካለፍኩት ስቃይ ያለፈ ተሰቃይቷል።” አለችኝ ቀጥላ። ‘አንቺ በየሆስፒታሉ ስትሰቃዪ እሱ ሚስት አግብቶ ወልዷል። የወለዳትን ልጅ ድሯል። እንዴት ተሰቃየ?’ ልላት ነበር ያሰብኩት። እንደ እማዬ ፍቅርና ቅንነት የሞላበት ሀሳብ ባልታደልም ይሄን ማለት ቅን ሀሳቧን በክፋት የመበረዝ ሀጢያት ስለመሰለኝ ዝምታን መረጥኩ።

በሰዎች የእለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የማይቀየር አንድ ህግ አለ። የሰዎች ድርጊት የሀሳባቸው ልጅ ነው። ልምዳቸው ደግሞ የሀሳባቸው የልጅ ልጅ ነው። ታስባለህ– ታደርጋለህ– ልምድህ ይሆናል። ድርጊትህ ወይም የየዕለት ልምድህ በሀሳብህ ያረገዝከውን አንኳር ይመስላል።

በሚቀጥለው ቀን አባቴ እናቴን ሊያያት ሲመጣ እኔና ፍትህ ትዝታን ልናያት ሄድን።

“እኔ የማንም እርዳታ አያስፈልገኝም። አንቺንም እሱንም አልፈልግም።” አለችኝ ትዝታ ከዛሬ በኋላ ጠበቃዋ ፍትህ መሆኑን ስነግራት። ከብዙ ልመና ቀረሽ ንግግር በኋላ ፍትህ ጠበቃ እንዲሆን በ‘ምንቸገረኝ’ ተስማማች። ትቻቸው ልወጣ ስል

“ጠበቃ ልጅ አለሽ?” አለችኝ።

“የለኝም። ምነው ጠየቅሽኝ? ትዝታ በልጅሽ እያስፈራራሽ ያለ ሰው አለ? ንገሪኝ? ማንም ቢሆን ከህግ አያመልጥም። በእኔ ልትተማመኚብኝ ትችያለሽ እባክሽ ንገሪኝ።” ከዚህ በኋላ ምንም ቃል አልተናገረችም። ትቻቸው ወጥቼ እንኳን የኔ ጭንቅላት ግን በሀሳብ እዚህና እዚያ መርገጡን አላቆመም።

ከዚህ ቀን በኋላ አባቴ በየቀኑ እናቴጋ ይመጣል፣ ፍትህ በትዝታ ጉዳይ አዲስ ነገር ለማግኘት ቀን ሲሯሯጥ ይውላል… … አመሻሹን እማዬጋ መጥቶ አይቶን ወደቤቱ ይሄዳል ወይ ያድራል ፣ ካሳሁን በተመቸው ሰዓት ሁሉ ከእኔና ከእማዬ ጎን ይሆናል… ፤ እኔ የፍትህ ክፍል ማደሬን ትቼ ፍትህ ሆስፒታል የሚያድር ቀን እቤቴ አድራለሁ። ሌላውን ቀን ከእማዬጋር። ……
በአንዱ ቀን አባቴ በትንሽዬ ካርቶን ያለ ነገር ሰጥቶኝ ሄደ። እቤቴ ገብቼ አየሁት። ደብዳቤዎች ናቸው። እማዬጋ የሌሉ እሱ የፃፈላት ደብዳቤዎች። አንብቤያቸው ስጨርስ አንድ ነገር ገባኝ። እማዬጋ ያሉት በሙሉ የፍቅር ደብዳቤዎች ናቸው። እሱጋ ያሉት ግን ቅሬታና በደል የተፃፈባቸው ናቸው። እንደ እማዬ አባባል እሱ አንዲትን በደል መርጧል። እሷ ለዘመናት የፍቅር ደብዳቤዎቹን ስታነብ እሱ ለዘመናት በደሉን እያነበበ ቂም ሲደምር ኖሯል። …… እሷ ከመስከረም እስከ ነሃሴ ላይ ናት። እሱ ግን ጳጉሜ 5 ላይ ነው። በሬ ሲንኳኳ ነው የባነንኩት

“ፍትህ? እማዬ ምን ሆነች?”

“ኸረ ምንም አልሆነችም። አባትሽ እሷጋ ሊያድር ነው። ወደቤት ከመግባቴ በፊት ስለትዝታ አንዳንድ ነገር ላውራሽ ብዬ ነው የመጣሁት።”

“ነገ መድረስ የማይችል ጉዳይ ነው?”

“ወሬው ይደርሳል። ……” ብሎኝ እጆቹን በአንገቴ ስር አሳልፎ ፀጉሬ መሀከል ጣቶቹን ሰክቶ ወደራሱ አስጠጋኝ። አንገቴ ስር ስሞኝ በሹክሹክታ “… ይሄ ግን ለነገ ማደር አይችልም ነበር።” አለኝ።

ራሴው ማበዴ ነው (ክፍል ስምንት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...