Tidarfelagi.com

ረከቦት ጎዳና

ካልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ

አዲሳበባ ድምጻዊት ከተማ ናት ። አዱ ገነት ውስጥ ፤ ከመኪና የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በብዛት፤ በሥራ ላይ የሚውለው ክላክሱ ነው። እንዲያው ሸገር ውስጥ መኪና- ነፊ እንጂ መኪና- ነጂ ያለ አይመስለኝም ። አንድ አሽከርካሪ ቆንጆ እግረኛ ሲመለከት ምሥራቅ አፍሪካን በጥሩንባ ይቀውጠዋል ። ጲጵ -“ ባዛኝቱ ዞረሽ ሹፊኝማ ” ማለቱ ነው። ትንሽ ነድቶ መብራት ሲያቆመው ፤ ጲጵ ” አቦ ዞር በል ልሙትበት!“ ማለቱ ነው። የሚያውቀው ሰው ሲያልፍ ጲጵ – ” አንተ እድሜልክህ በእግርህ ስታካልል፤ እኔ ይሄን የመሰለ መኪና እነዳለሁ “ብሎ መጎረሩ ነው።
ብቻ ምን ልበላችሁ ፤ ሸገር ውስጥ መኪና ማለት፤ በአራት ጎማ የሚሄድ ጅንጀና ቁጣና ጉራ ነው።
እድሜ ለዘመነ- ዩቲውብ ፤ ባዲሳባ ካሴት መሸጫ ሱቆች ከስመዋል። በምትካቸው፤ በራፋቸው ላይ የጢያን ትክል ድንጋይ የሚያክል ድምጽ ማጉያ ገትረው፤ አካባቢውን በዘፈን ድብልቅልቁን የሚያረጉ ቡቲኮች ለምልመዋል ። ባለፈው፤ አንድ ከክፍለሀገር የመጣ ልጅ ፤የሆነ ቡቲክ ውስጥ ገብቶ “ያረጋኝ ወራሽ ሁለተኛ ካሴት ይኖራችኋል ?” ብሎ ሲወዛገብ ሰምቸዋለሁ። አሁን አሁን፤ ካንድ ከሚደንስ እብድ በስተጀርባ ፤ አንድ አዲስ የተከፈተ ቡቲክ ይኖራል።

የዘፈን ነገር ከተነሣ ላይቀር፤ በቃ ማስታወቂያ መሥራት ማለት እቃ አቅፎ መዝፈን ሆኖ ቀረ? ሳሙናው ፤ ጫማው ፤ቢራው ብስኩቱ በጠቅላላው ፤ እንደሠርገኛ በዘፈንና በውዝዋዜ ካልታጀበ አይተዋወቅም። ድሮ ሱፐር ማርኬት ገብቸ፤ ገና የታሸገ ፓስታ ሳይ ምራቄን እውጥ ነበር። አሁን እድሜ ለሠራዊት ፍቅሬ ፤ በስጎ ያበደ ፓስታ ሲሸተኝ ፤ ደንስ ደንስ ነው የሚለኝ። ወይ እምየ ኢትዮጵያ !ኑሮሽ ትካዜ፤ ንግድሽ ውዝዋዜ።

ባለፈው እንደነገርኳችሁ፤ ጊዜየን የማሳልፈው ቲቪ በማየትና እግሬ በመራኝ በመሄድ ነው። በተለይ ቃና ቲቪ ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ስቸክል በመዋሌ፤ የአስተዋዋቂዋ ጋዜጠኛ ዲምፕል እና የዛራ እምብርት ይምታታብኝ ጀምሯል ። ቴለቪዥኔን በጥሞና እንዳልከታተል የሚያደርገኝ የሠፈራችን ማቲዎች የማያባራ ጭፈራ ነው። ልጆቹ ከቡሄ ዋዜማ እስከዛሬ ድረስ ከጭፈራና ከፈለጣ አልፎረሹም። በዚህ አያያዛቸው ከፋሲካ በፊት የሚያቆሙ አይመስሉም። ሲመጡ ብሬን ስመዝ! ሲመጡ ስሸልም!ሲመጡ ስሸልም! ከመንግስት እውቅና አለማግኘቴ እንጂ የሰው ልጅ በጉዲፈቻ እያሳደግሁ ነው ማለት ይቻላል። ያመት በአል አንድ ችግሩ የፈለጣ “ ላይሰንስ ”መስጠቱ ነው።ከጭፈራው በላይ አላስቆም አላስቀምጥ ያለኝ ይሄ የሚያፈነዱት ነገር ነው ። በበራፌ ስንጥቅ ሥር ፊኛና መሰል ነገሮችን ሰደው ባፈነዱ ቁጥር፤ ባለ ስናይፐሩ ምኔ ላይ መታኝ? የሚለውን ለማረጋገጥ ገላየን ሁለቴ እዳብሳለሁ።

ከቤቴ ወጥቸ ወክ ሳደርግ እግረኝነቴ ከባለመኪኖች የተሻለ ነጻነት እንደሰጠኝ ይሰማኛል ። የሰው መኪና ስፖኪዮ ሰበርኩ ብየ ሳልጨነቅ ፤ የጎዳና ተዳዳሪ ገጭተሀል ተብየ በቁጥጥር እታሠራለሁ ብየ ሳአልሰጋ፤ የዲሳባን ወገብ ሁለቴ መዞር እችላለሁ ። በርግጥ ከሃያሁለት እስከ ቦሌ በተዘረጋው የእግረኛ መንገድ ዳር መንግሥት ባመቻቸላቸው ቀላል ኢንዱስትሪ መርሃግብር የታቀፉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሴቶች የጀበና ቡና አፍተው ይሸጣሉ። ኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና የሚባለውን በራሴ ስልጣን ” ረከቦት ጎዳና ”ብየ የሰየምኩት ያለ ምክንያት አይደለም። እና በዚህ ጎዳና ላይ ተራምዶ ፤ አንድ ሁለት ጀበና ሳይሰብር ወደቤቱ መግባት የሚችለው፤ የሠርከስ ባለሙያ ብቻ ነው።

የእግረኝነት ዋና ችግር የሚመስለኝ ፤ ለለከፋ መዳረጉ ነው። ለምሳሌ እንዲህ እንደ ዛሬ የተስተካከለ ቅርጽ ባለቤት ከመሆኔ በፊት ፤እንደ አዲሳበባ ቀላል ባቡር ፊትና ኋላየን መለየት አስቸጋሪ ነበር። አንድ ቀን የሰማያዊ ፓርቲ አባልነት ተመዝግቤ ለመታገል ወደ ካዛንችስ ጽፈት ቤት ወክ ሳደርግ ፤ ስልክ ግንድ ተደግፎ የቆመ ጎረምሳ አይቶኝ“ ኧረ በውቄ ! በዚህ ቁመት ላይ ይሄን የሚያህል ቦርጭ ይደብራል! የስሚንቶ ማቡኪያ ማሽን መሰልህ እኮ ” አለኝ። በጣም ከመናደዴ የተነሣ ለዚህ ህዝብ ነው እንዴ የምታገልለት ብየ ወደ ድራፍት ቤት ሄድኩ ። መንገድ ላይ የሚፎግሩኝን በጠረባ ለማስጣት ቴኳንዶ ለመሰልጠን ወስኘ ነበር። አሰልጣኙ በወር ሁለት ሺህ ብር ጠየቁኝ። በወር ይሄን ያህል ብር መክፈል ከቻልኩ ፤ ለምን እሰለጥናለሁ? የተቀነሰ ፌዴራል በቦዲጋርድነት አልቀጥርም እንዴ?

ትናንት እዚህ ሀያሁለት ማዞርያ ትንሽ ወክ እንዳደረግሁ፤ አንድ ኮሳሳ የመጽሐፍ አዟሪ አስቆመኝና ዙርያ ገባውን ቃኝቶ ፤ወደ ጆሮየ ተጠግቶ “በውቄ የተከለከለው መጽሐፍ ያስፈልጋል ?” አለኝ። ይችን ይወዳል! የምኖረው የተከለከለ ነገር ፍለጋ አይደለም እንዴ ? ሳላቅማማ የጠየቀኝን ሦስት መቶ ብር ከፍየ፤ የመለስ ዜናዊ ፎቶ በያዘ ጋዜጣ የተለበደ መጽሐፍ ተቀበልኩት ። አይ ጎጄ የፍቅሬ ቶሎሳን መጽሀፍ በመሌ መላጣ ጠቅልላ እየቸበቸበች ይሄን ገገማ መንግስት ትሸውደዋለች ! ብየ አዟሪውን እያደነቅሁ ወደማዘወትረው ካፌ ጎራ አልሁ። ካፌው ጭር እስኪል ድረስ ጠብቄ መጽሀፉን ገለጥኩ። ባዟሪው የተሸወደው መንግስት ሳይሆን በውነቱ ሥዩም የተባለ ጭቁን መሆኑን የተገነዘብኩት መጽሐፉ “የመለስ ዜናዊ ህይወት ትግል ”የሚል መሆኑን ሳውቅ ነው። ደሜ ፈልቶ ዞር ዞር ብል መጽሐፍ አዟሪው ስድቤ የማይደርስበት ርቀት ላይ ቆሞ፤ ሌላ ባለተራ ሲሸውድ አየሁት።

መቸም አንዴ ገንዘቤን ከስክሸበታለሁ ብየ ፤ የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ተጥጀ ፤ ገድለ መለስን መጨምጨም ጀመርኩ ። ከመጽሐፉ ውስጥ ያነበብኩት እውነት የሚመስል አንድ ነገር ቢኖር “ አቶ ዜናዊ ባጠቃላይ አስራ ሦስት ልጆች አላቸው ” የሚለውን ብቻ ነበር ። አቶ ዜናዊ ላገራቸው አስራ ሦስት ህዝብ እንዳበረከቱ እንዴት እስከዛሬ ሳላውቅ ቀረሁ? እንዴት ይሄን የመሰለ ቁምነገር አመለጠኝ? እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የሆነ ጊዜ ላይ የሆኑ ጎልማሳ ባለመኪና ያንዱን ጎረምሳ መኪና ከኋላ ከገጩት በኋላ ትራፊክ ሊጠራባቸው ሲል” ልጄ ይቅር በለኝ ፤ ያስራ ሁለት ልጆች አባት ነኝ“ ብለው ተማጸኑት ፡ ፡ ጎረምሳው ግን ሰውየው ካደረሱት የመኪና አደጋ በላይ ለህዝብ ቁጥር አለቅጥ መበራከት ያደረጉት አስተዋጾኦ ስላናደደው “ በዴ የተባለው ዘፈን የተዘፈነው ለርሶዎ ነው እንዴ ” ብሎ መለሰላቸው።
ኣንድ መጽሐፍ አንብቤ ከደበረኝ ወደ ቤቴ ይዠው ለመግባት አልፈቅድም ። ይህንን መጻፍ በካፌው ጠረጴዛ ላይ ጥየው በሞላ ታኪሲ ጋቢና ውስጥ ተንደርድሬ ገባሁ። ግን ምን ዋጋ አለው፤ አስተናጋጁ በሞተር ሳይክል አሳድዶ ደረሰብኝና ” ጠቃሚ መጽሀፍ ረስተሃል“ ብሎ በታክሲው መስኮት አሾልኮ ወረወረልኝ።

ትናንት በ “ጀት ፋም ሆቴል ” በር ሳልፍ የሆነ ነገር ዐየሁ። የሠፈራችን ሰዎች ፤ ከሆቴሉ የሚያካፋውን ዋይ ፋይ ለመጠቀም ከጎረቤት ካፌ በረንዳ ላይ ተኮልኩለዋል ። የካፌው ባለቤት የጎረቤት ኢንተርኔት ማጣመርያ እንዲሆን ስለተፈረደበት የተናደደ ይመስላል ። አንዴ ደብረማርቆስ ውስጥ የሆነ ሰውየ ሻይ ቤት ከፍቶ ነበር። ሌላ ሰውየ ከጎኑ ዳቦ ቤት ከፈተ። ጎረምሶች ከዳቦ ቤቱ ዳቦ ገዝተው ወደ ሻይቤቱ ጎራ ካሉ በኋላ እየነከሩ መብላት ለመዱ ። አንድ ቀን የከተማው ነዋሪ ባለሻይቤቱ ን አግኝቶት “ ሥራ እንዴት ነው? ቢለው “ ምን ሥራ አለ? የሰው ቂጣ ማማጊያ ሆኘ ቀረሁ እንጂ” አለው አሉ። የማርቆሱ ታሪክ ከሀያሁለቱ ካፌ ገጠመኝ ጋር የሚገናኘው በምንድን ነው? ያው ዋይ ፋይ ነው።

ካስር አመት በፊት በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ አላፊ አግዳሚውን የሚሾፍ ፤ ወይም “ተጫወት እንጂ” እየተባባለ ወሬ የሚገባበዝ ተሰተናጋጅ ማየት የተለመደ ነበር። አሁን በረንዳው ላይ የተጎለተ ተስተናጋጅ ሁላ ሞባይሉ ላይ በሙሉ ልቡ ተቸክሎ፤ ከሰማይ ምድሩ ጋር ተቆራርጧል። አይበለው እንጂ የሆነ አልሻባብ፤ በየተስተናጋጁ ኪስ ውስጥ በነፍስወከፍ አንዳንድ ፈንጅ አስቀምጦ ቢሄድ እንኳን ዞር ብሎ የሚያየው አልመሰለኝም።ከተስተናጋጆች ማህል ምኡዝን ሞባይሉ ላይ ተደፍቶ አየሁት። ፊቱ ላይ ያለው ወገግታ በቻት ጅንጀና እንደተጠመደ ያሳብቃል ። ከፊትለፊቱ ቆሜ ፤ እንደ ሰመጠ ሰው እጄን ባውለበልብ ፤ ብጣራ ዞር ብሎ ሊያኝ አልቻለም። ቢቸግረኝ፤ ሰላምታየን ኢንቦክስ አድርጌለት ጉዞየን ቀጠልኩ።

በነገራችን ላይ መስቀል እንዴት አለፈ? የደመራው ምሶሶ ባድማ መታኝ መኪና ተገጭቶ፤ ካራት ኪሎ በተቃራኒ እንዲወድቅ ተደረገ የተባለው እውነት ነውን?። ደመራ ሲነሣ ትዝ የሚለኝ የዛሬ አስር አመት ገደማ በህዝባዊ ተቃውሞ የተጠናቀቀው ታሪካዊ ደመራ ነው ። በጊዜው ደመራውን የለኮሱት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያው ወፍራም ሊቀ- ጳጳስ የሆኑት አቡነ በርኖስ ነበሩ። የዚያን ቀን ትልቅ ዙፋን ላይ ተቀምጠው የደመራውን እሳት ሲሞቁ ካጠገቤ የነበረው አቤ ቶኪቻው አቤ-ዎታዊ ደምፍላቱን መቆጣጠር ተስኖት ” ይሁዳ!“ብሎ ጮከባቸው፡ ፡ አቡኑ“ጌታ ይገስጽህ” ይሉታል ተብሎ ሲጠበቅ ” ኦነግ ተረዳ “ ብለው መለሱለት።ይህን ሲሉ በማህል ጣታቸው ያሳዩት ምልክት ፤ርዳታን የሚወክል እንዳልነበረ የተገነዘብኩት በቅርቡ ነው።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • እንድሪስ ታየ commented on January 6, 2017 Reply

    የበእውቀቱቀልድይመቻል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...