Tidarfelagi.com

ሥግር ልብ ወለድ፤ ሕፅናዊነት (ክፍል 2)

“ነው” ተብሎ ቢደነገግም ባይደነገግም ማንኛውም ልብ ወለድ ሥግር ነው። ማለት የራሱን ጉጥ/ዐይን መርጦ የራሱን ሥግር ይሰራል። የየራሱን አቋምና ልዩነት ይደነግጋል። ልዩነት ሲባል ሂደት ማለት ነው። ስለዚህ አፍ ሥግር ነው ብዬ በንዑስ ርዕስ መጥቀሴ ስለ ነጠላ ዕቅዴ ይናገራል እንጂ ስር ነቀል የሚያደርገው ነገር የለም።

የምናውቃቸው ልብ ወለዶች ሁሉ ሥግር ናቸው። ከአድማስ ባሻገር፥ ፍቅር እስከመቃብር፥ የቴዎድሮስ እንባ ወዘተ። እንዲህ ስል ድፍረት አይደለም።

ማንኛውም ልብ ወለድ ሊነበብና ሃሳብ ሊሰጥበት የተፃፈ ነው። ተወደደም ተጠላም ታዳሚ በተለያየ መልክ ትርጓሜውን ወይም አመለካከቱን ያበጃል። ማንኛውም ልብ ወለድ ሥግር ነው ማለት፤ አንድም በተከፈተ ሂደቱ ነው። ይሄም ሁለት ስያሜዎች ይሰጠናል። ንቁ ስግርና ኢ-ንቁ ስግር።

በማሕሌት የትረካዎች መድብል ውስጥ ያለችው ሰላማዊት የተባለችው ገፀ ባህርይ የስንብት ቀለማት ውስጥ ስትመጣ (ከሃያ አመታት በኋላ) ኢ-ንቁ ሥግር የነበረው አጭር ታሪክ ንቁ ሥግር ይሆናል።

ይሄ ንቁ ሥግር በሌላ ልብ ወለድ እስኪጠለፍ ድረስ (ከሁለት አመታት በኋላ) ኢ-ንቁነት ይረጋና አፍ ልብ ወለድ ውስጥ ሰላማዊት በዚህ ዘመን ስትመጣ አጭሯ ልብ ወለድ ኤልዛቤል ኢ-ንቁ ሥግር ትሆናለች።

ሰላማዊት (ወይም አጭር ታሪኩ ኤልዛቤል) በዱሉዝ ቋንቋ መጀመርያ (territorialize) ካደረገችበት ኤልዛቤል (1980) ወደ ስንብት ቀለማት (2008) ትመጣለች። አመጣጧ (deterritorialize) ማድረግ ወይም ስፍራ መልቀቅ ይባላል። የስንብት ቀለማት ውስጥ (reterritorialize) (ደግማ መስፈር) ካደረገች በኋላ deterritorialize አድርጋ አፍ ውስጥ ትገባለች። (2010)

በተወሰነ የሂስ ባህል ልማድና ቁነና (canonization) ደረጃ የተሰጣቸው ልብ ወለዶች በዚህ አይነት ዘላናዊ (nomadic) ንቅናቄ ተዋረዳቸው እየተናጋ ዘለንገታዊ (horizontal) ስርዓት ውስጥ እየገቡ ለተለያየ ትኩረት ክፍት ይሆናሉ።

በመግዘፉ የገነነ የመሰለው የስንብት ቀለማት ንቁ ሥግር ሆኖ ጭብጡ አናሳ በመሰለው አፍ በተባለው ልብ ወለድ ጥላ ስር ለአዲስ ትኩረት ይጠራ’ል። በዚህ ሂደት ውስጥ ትረካም ብቻ ሳይሆን ትርጉምም ይፋለሳል (ይጠባል ወይንም ይሰፋል)።

ፍቅር እስከ መቃብር፤ መረቅ ልብ ወለድ ውስጥ በሰብለና በዘመዶቿ ይጠራ’ል። ወይም ንቁ ሥግር ይሆናል። በአጭሩ በሂሰኞች አነፃፃሪነት በራሱ የትረካ እድሞ የተገለለው ማንኛውም የኪነት ስራ በአዲስ ትረካ ይሰባል ለሌላ ትርጉም ይናጣል።

***
ትንሽ ስለ ስድራት (Asemblage)

ሕይወት የመያያዝና የመስተጋብር ውጤት ናት። ማንም ፍጡርና ቁስ የመያያዝ ሂደት ውጤት ነው። ስለ ደንብ፣ ስለ ስርዓትና ቀውስ ስለ አጀማመርና አጨራረስ ከማውራታችን በፊት ቀዳሚው ግንኙነታችንን መፈተሽ ነው።

ፍጡራን የሚፈጥሩትና የሚስፋፉት የግንኙነት ስፍራዎች በመለኮስ ነው። ለምሳሌ ብርሃን ከተክሎች ጋር ይገናኝና ፎቶ ሲንቴሲስ ይፈጥራል።

አፍ አንድ የልብ ወለድ መፅሀፍ ቢሆንም ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ‘በሚበሩ’ በሆነ መልክ ግን አጠቃላይ ምስል በሚሰጡን መስመሮች የተሞላ ነው። በአጭሩ፤ የስድራት ውጤት ነው።

መሰደር ማለት መኮልኮል፣ መመደብ፣ በተራ ማስቀመጥ ማለት ነው። ሥግር ሲባልም አፍ የሚባለው ልብ ወለድ ለሌላ ለሰፋ ስድራት ራሱን ሲያጭ ነው። ሲሰደር ወይም በእንግሊዝኛ (assemblage) መሆኑ ነው። ስድራት የተባለው ቃል አሰምብላዥን በጥሩ የሚተረጉመው ይመስለኛል።

አሰምብላዥ ዴሉዝና ጓታሪ 1000 አምባዎች በተባለው መፅሀፋቸው የተገለገሉበት ፅንሰ ሃሳብ ነው። የስድራት ነጠላ ገላዎቹ ብዝሃነት ያላቸውና በተጨማሪም ነፃ የሆኑ ናቸው። እነዚህ ነጠላዎች ከሌሎች ነጠላዎች ውጫዊ ግንኙነት ያላቸው፣ ሌሎቹን ነጠላዎች መለወጥ የሚችሉና በሌሎች መለወጥ የሚችሉ ናቸው።ሙሉው የነጠላዎች ችብታ (እክብ) ነጠላዎችን ሊገታና ሊቆሰቁሳቸውም ይችላል። ስድራት የሌላ ሰፊ ጉዳይ አባል ወይም ነጠላ ሲሆን እሱም በተራው አችቦ የያዛቸው ነጠላዎች በውስጡ አሉ።

እንግዲህ ይህ ሁሉ የምናየው የዓለም እውነታ የስድራቶች ስድራት ነው ማለት እንችላለን። መሰረታዊ ፍቺውም እንዲህ ነው።

“It is the process of arranging, organizing and fitting together. They are complex constellation of objects, bodies, expressions, qualities and territories that come together for varying periods of time to ideally create new ways of functioning. The concept of assemblage applies to all structures, from the behavior patterns of an individual, the organization of institutions, an arrangement of spaces, to the functioning of ecologies”

(Adrian Parker, Deluze Dictionary, 2010)

***

 

ሥግር ልብ ወለድ፤ ሕፅናዊነት (ክፍል 3)

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...