Tidarfelagi.com

ሥልጣኔ የኋልዮሽ

ቀደም ባለው ዘመን ደመቅ ብለው የጠቆሩ የዳር አገር ብሄረሰቦችን በባርነት መፈንገል የተለመደ ነበር። ብዙዎቹ የኦሮሞ የአማራና የትግራይ ጌቶች እልል ያሉ የባርያ ፈንጋይና አሳዳሪ ነበሩ።ተፈንጋዮቹን ለፍንገላ ያጋለጣቸው ከነሠንሠለታቸው ስለተወለዱ አልነበረም። ማስገበር ደንብ በነበረበት በዚያ ዘመን ራሳቸውን የሚመክቱበት ነፍጥ ወይም አደረጃጃት ስላልነበራቸው ነው ። አሸናፊው በተሸናፊው ላይ የፈለገውን ማድረግ መብት ነበረው። ቢሻው ቆራርጦ ላሞራ ይሰጠዋል ፤ቢሻው ወደ መሣርያነት ይለውጠዋል።

ባርያ ማሳደር ያንድ ንጉሥ ወይም ያንድ ብሄረሰብ አመል ሳይሆን ያንድ ዘመን ጸባይ ነበር። በዘመኑ የነበረ ሁሉ ከወረርሽኙ አላመለጠም። ይህን የሚክዱ ከታሪክ ይልቅ ሰመመናቸውን (ፋንታዝያቸውን) የሚያምኑ ናቸው።
(ርግጥ ነው፤ ህግ ባይጫናቸው ባርያ ለመፈንገል ዓይናቸውን የማያሹ ሰዎች ዛሬም አይጠፉም። የዛሬ ሰባት ኣመት፤ ባንዱ ሀሙስ ፤ ባንድ ቤት ምሳ ተጋበዝሁ። ምን የመሰለ ዶሮየን በልቸ የፈረሰኛ ቅሬቴን በስቴኪኒ እያራገፍሁ ልወጣ ስል ሠራተኛዋ ጓዳ ውስጥ ኣይኑ የጠፋ ሽሮ ስትበላ መለከትኳት። ሠራተኛዋ ለባለቤቶችና ለእንግዶች ያዘጋጀችውን ዶሮ ያልበላችው ቬጅተርያን ስለነበረች አልነበረም።ባርነት ጠፍቷል ብለን በተዘናጋንበት ዘመን የምትኖር ባርያ ስለሆነች ነው።)
በቀዳማዊ ኀይለሥላሤ ዘመን መጀመርያ ላይ የባርያ ልጆችን የማስተማር ዘመቻ ተጀምሯል። ይህ የሞራል እድገት የመጣው በውጭ ጫና ነው ወይስ በሌላ ምክንያት የሚለውን ለተጨማሪ ጥናት እናሳድረው። ይሁን እንጂ ከዛሬው ዘበን ጋር ሲወዳደር እንኳ አስደናቂ የሞራል እመርታ መሆኑ አይካድም።
ኡምርቶ ኤኮ የሚባል ጣልያን ያለውን ልዋስና “ አንዳንዴ ሥልጣኔ የኋልዮሽ ሲመርሽ እናየዋለን ”። በዘመናችን ብዙ ብሄረሰቦች ከኦሪታዊው ያኗኗር ዘይቤ ፈቀቅ እንዲሉ አይፈለግም ። በራስን ማስተዳደር ስም የንፍገት ሰለባ ሆነዋል። “ ዘመናዊ ትምርት ከተማሩ የነጻነትን ጣም ያውቃሉ። መብታቸውን ይጠይቃሉ። ሲበደሉ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ላለም ይነዛሉ ” ተብሎ ተሰግቶ ይሆን?
ባለፈው ሁለት አሥርት አመታት ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ፓርክ ሆናለች። ማለቴ ብሄረሰቦችን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ እንደ ብርቅ ወፍ መጎብኘትና ፎቶ ማንሳት ወግ ሆኗል።

በኑሮ የደረስኩበትን አንድ እውነት ላካፍል ። የህዝብ ተወካዮች እንጂ ህዝቦች የራሳቸው ምርጫ የላቸውም። ለምሳሌ ፤ ከሆነ ከብት አርቢ ብሄረሰብ ጀርባ ሁሌም አንድ ጮሌ ያገር ሽማግሌ ይኖራል። ሽማግሌው ከራሱ ብሄር ቋንቋ ባሻገር መጠነኛ አማርኛም ይናገራል ፤አልፎ አልፎ በየቲቪው ብቅ እያለ የተሸመደደ ፖለቲካዊ መነባንብ በኢንተርቪው ስም ይሰጣል። ባለ ረጅም አንቴና ሬድዮ ያዳምጣል ። ክላሽ ያማርጣል። ከገባሮች ጋር ወተት ፤ከጌቶች ጋር ደግሞ ውስኪ ይጠጣል። ሲመቸው ለጥቅሙ ሲል ወክያቸዋለሁ የሚላቸውን ሰዎች ርስት ይሸጣል።
የምናየው ሁሉ የዚያ ውጤት ነው።

በመጨረሻ ይቺን ማለፍያ ፎቶ ለቅቄባችሁ ላምልጥ ።

old_pic_Ethslavery

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በትምርት ካጠመቋቸው የባርያ ልጆች መካከል አንዱን ብላቴና ታሪክ እንዲህ ቀርጾ አስቀርቶታል

 

 

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...