Tidarfelagi.com

ሞት እኩል ይሆናል ሕይወት

ሞት = ህይወት

‘‘የሞት እንቆቅልሽ የሚመስጠን፣ የማይቀር፤ ነገር ግን የማናውቀው ነገር በመሆኑ ነው’’-(አፍሮጋዳ)

የ“አምላክ” ትልቁ ጥበቡ ሞትን መፍጠሩ ነው- ለኔ! እያንዳንዱ ሃይማኖት እግሩን ያቆመው በሞት ላይ ነው። ሞት ባይኖር የሰው ልጅ፣ በአምላክ አማኝ አይሆንም።ሃይማቶች እግር ይከዳቸዋል። …ዘር ካልሞተ/ካልበሰበሰ ፍሬ አይሆንም። በዚህች ሰከንድ በሰውነታችን ውስጥ ህዋሳት እየሞቱ እራሳቸውን ባያድሱ ህልው መሆን አንችልም።
ሞት እንደቡዙዎቻችን እምነት የህይወት ማብቂያ አይደለም። እያንዳንዱ ህያው አካል ውስጥ የተጎነጎነ ሞት አለ። ግልፅ ነው-ሞት የሌለበት ህይወት ህይወት ሊሆን አይችልም! ህይወትን ህይወት ያደረገው ሞት ነው። ስለዚህ ህይወት ሞት ነው። ወይም ሞት ህይወት ነው። ወይም ደግሞ ህይወት፣ ህይወትና ሞት ነው። መወለድ የህይወት አካል እንደሆነው ሞትም የህይወት አካል ነው።

ህይወታችንን እንደምንኖር፣ ሞታችንን እንኖራለን። ሄራክሊተስ የተባለው ፈላስፋ፣ አማልክትን ሟቾች ሰዎችን ግን ሞታቸውን ጭምር የሚኖሩ፣ ህይወታቸውን የሚሞቱ ዘላለማውያን ያደርጋቸዋል… እንዲህ ይላል፤ “ Gods are mortal, humans immortal, living their death, dying their life’’

ከሞት የሚያመልጥ ማንም የለም፤ ለሕያዋን ሁሉ የተሰጠ ስጦታ ነው። ዓለም እስካለች አለ፣ ዓለም ደግሞ ያለ ሞት አትኖርም። ሞት ሲሞት ዓለም ትሞታለች። ዓለም ስትሞት ሞት ይሞታል።

“….አስር ዓመትም፣ መቶ ዓመትም፣ ሺ ዓመትም በሕይወት ብትኖር ከሞት ጋር ክርክር የለህም” (መፅሐፈ ሲራክ 41፣4)

የሞት መልካምነት!
‘‘Death destroys a man, but the idea of death saves him’’ E.M.Forster

መፅሐፉ ሞት በአዳምና ሔዋን ጥፋት በኩል እንደመጣብን ይነግረናል። በልጅነታችን…
“አዳምና ሄዋን ባጠፉት ጥፋት
እኛ ላይ ደረሰ የዘላለም ሞት”
ብለው እያዘመሩ የቄስ አስተማሪዎቻችን አዳምና ሄዋንን አስወቅሰውናል። እኔ ግን አዳምና ሄዋን ካመጡልን መልካም ነገር አንፃር ሊሸለሙ ይገባቸዋል ነው የምለው(እናመሰግናለን እሺ አዳምዬና ሄዋንዬ…ባላችሁበት ይመቻችሁ!) ለእግዜር ይህን የመሰለ ውለታ ውለውለት “ሂዱ ከዚህ” ብሎ ከገነት ማባረሩ ሁሌም ይገርመኛል። ሞት ባይኖር በእግዜር የሚያምን ማን ነው? ሃጢያት ብንሰራ አንሞት!( የሃጢያት ደሞዙ ሞት ነው ይላልና) …የንስሃ ጊዜ ያልፍብናል ብለን አንፈራ ነገር፣ ዘላለም ኗሪ ነን። እና ምን ፈልገን አምላክን እናምናለን። ከሞት በኋላ ያለ ህይወታችንን የተዋበ ለማድረግም አይደል የምናምነው? ሞት ከሌለ ታዲያ የምን ከሞት በኋላ ህይወት አለ፣ ለወዲያኛው ዓለም የተገባልን ቃል፣ ወዲያኛው ዓለም መሄድ የሚባል ነገር ስለሌለ አብሮ ይሞታል። በእርግጥ ግን በእምነቱ ከሄድን፣ ሞትን የፈጠሩት አዳምና ሄዋን ሳይሆኑ ፈጣሪ ነው፤ አዳምና ሄዋን የፈጠረውን ነው ያፀደቁት! እሱ ሞትን እፀበለሱ ውስጥ ጠቅልሎ አስቀመጠው፣ እነሱ በልተው ፈቱት( just if we take the Biblical point of view)

ማንም ይፍጠረው እንዴትም ይፈጠር ሞት አያሌ ጥቅሞች አሉት። አንዱ ከታካች ህይወት መገላገያነቱ ነው። ሰው መኖር ቢደክመው እራሱን ያጠፋል፣ ሞት ባይኖር ምን ያደርጋል? እኔ ግን የምር ሞት ባይኖር እራን በራሴ የምሰቅል ነው የሚመስለኝ… ዉይይ ለካ ሞት የለም… ለመሞት ብለን የተሰቀልንበት ገመድ የአንገት ጌጥ ብቻ ሆኖ ሊያርፍ ነው…. መሞት እየፈለጉ፣ መሞት አለመቻል……. ሲደብር!!!
/ይቀጥላል/
/ስፎግራችሁ ነው አይቀጥልም/
/ ኸረ ስለሞት እኮ ነው የምናወራው፣ ምኑ ተነካና- ከአፍታ ቆይታ በኋላ ይቀጥላል!/

 

************************************************ ክፍል ሁለት  *************************************************

መፅሐፈ ጥበብ 7፣6 “…. የሁሉም ወደዚህ ዓለም አመጣጡ አንዲት ናት፣ የሑሉም መውጣቱ እኩል ናት”

ሌላው የሞት ጥቅም የእርጅና መድሃኒት መሆኑ ነው። ሞት ባይኖር እየጃጁ መኖር እንጂ መሞት አይታሰብም።ህዋሳትህ ደክመው፣ አይኖች ማየት ተስኗቸው፣ ጉልበት ከድቶህ ስትነሳም ስትቀመጥም ጫን ጫን እየተነፈስክ ትኖራታለህ እንጂ፣ ሞትን ብትለምንም አታገኘውም። እና ይህን ከመሰለው ኩነኔ መኛ አይደለምን? ለዚህ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም፣ “ኦቶባዮግራፊ(የህይወቴ ታሪክ)” በተባለ መፅሐፋቸው ያሉትን ጠቅሼ ልለፍ፤
“ ሞት የማይታለፍ እዳ የሆነበት ምክንያት ለካ እርጅናን ለማስወገድ ኖሯል?…… እንጊዲያውስ ሞትን በጣም መጥላት ወይም መፍራት አያስፈልግም። ጥሩ መድሃኒት ነው፤ ያሳርፋል።”(ገፅ 122)
ግልግል ለፈለገውም አለሁ ባይ ነው! ሞት። የሰው ፊት ከማየት ሞትን የመረጠው እንዲህ ይላል፤
“ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም
አፈሩ ድንጋዩ ከሰው ፊት አይከብድም”

እና ከሰው ፊት ይቀለኛል ያለው ሞት ነው ይቅርበት የምትሉት ይሄ ሰውዬ ለይ? ምን አደረጋችሁ እስቲ? ….. እሺ ጠቅላይ ሚኒስትሩስ በምን ምክንት ባለ ራዕይ ሆኑ፣ በመሞታቸው/በሞት ምክንያት አይደለምን?
በስተእርጅናው ለህይወት ጨለምተኛ አመለካከትን የያዘው ጠቢቡ ሰለሞን፣ በመፅሐፈ መክብብ መፅሐፉ በምን እንደሚሻል ባይገልፅም፤ “ ከመልካም ሽቶ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” ይላል።

ሞትን በአሟሟት…!

በብዙ ሰው ዘንድ፣ ከሞቱ አይቀር በአሟሟት ሞትን ማሰፈር ይቻላል ተብሎ ይታመናል። አሟሟቴን አሳምርልኝ ይላል የኛ ሰው። በጀግንነት ኖረው፣ ሞት ላይ ምላሳቸው ሲያወጡ እድሜያቸው አሳልፈው አሟሟታቸው የሚከፋባቸው አሉ። ጀግና የነበረን ሰው. “አይሞቱ አሟሟት ሞተ.. እምጵ!” ሲሉለት እንሰማለን። ይህ ከመሞትም ባለፈ፣ የአሟሟት አይነት እንዳለ ይነግረናል። የፈሪ ሞት፣ የጀግና ሞት፣ ድንገቴ ሞት፣ አስገራሚ ሞት፣ አሰቃቂ ሞት….እንዲህ ነው የማይሉት ሞት አለ፣ አሉ።
ፕሮፍ መስፍን ወ/ማርያም በ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፋቸው፤ “ ሞት የማያመልጡት ግዴታ ቢሆንም በአሟሟት ሊሸነፍ ይችላል” (183) ይላሉ።

ገጣሚው ደግሞ እንዲህ ይላል፤
“አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ
ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ”
የዚህ ደግሞ የተለየ ነው፤ ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ባለ ማየቱ አሟሟቱን አይረቤ ያደርገዋል። ምስኪን የሆነ፣ ምናለ በዚህ በኛ ዘመን ተወልዶ ባየው… ጉች ጉች ያለ ጡት በየመንገዱ እዩኝ እዩኝ እያለ ሲማጠን ኖሮ ቢሆን አሟሟቱን በምን ይወቅስ ነበር? መቼም የዛሬ ጡት ከመታየት ወደ ማየት ተሸጋግሯል አይደል?

ሰዎች በአሟሟታቸው ምክንያት ይጀግናሉ። የጀግና ሞት ይባልላቸዋል። የአፄ ቴዎድሮስን ጀግንነት ከፍታ ከሰጡት ነገሮች አንዱ አሟሟታቸው ነው። ሟች አሟሟቱ የፈሪ ከሆነ ደግሞ ይነቀፋል። ዮፍታሄ ንጉሴ በአፋጀሽኝ ቲያትሩ እነዲህ ይለዋል ፈሪውን ሟች፤
“ ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ላሊበላ
ሲሸሽ የሞተ ሰው ተስካሩ፣ሲሸሽ የሞተ ሰው፣ ተስካሩ አይበላ”
ፍትህ የማያውቅ ሞትም አለ። ፊቱ ሲንጎማለሉበት ዝም ብሎ፣ በሌላ ጊዜ ተልከስክሶ የሚመጣ፣ አልከስክሶ የሚገድል። እንዲህ ይላል ዮፍታሄ በሌላ ግጥሙ፤

“ዋናውስ በሽታ ምንም አልነካቸው
ካገገሙ ኋላ ግርሻ ገደላቸው”

ሞት ፈሩትም ደፈሩት ያው ሞት ነው። የማይቀርን ነገር ከመፍራት ግን በተዛና መንፈስ መቀበሉ የተሻለ ነው።

ሞትን ማወቅ፣ መቀበል!…

“ የሰው ልጅ የመጨረሻው ጥበብ ላይ ደረሰ የሚባለው ሞት መኖሩን ሲያውቅና ሲረዳ ነው” (እኔና ቹ፣ 164)
ምን ማለት ነው? ሞት መኖሩን የማያውቅ ሰው አለ? አዎ! የማያውቁ ሰዎች አሉ። የማያውቁ ከማለት የሚዘነጉ ብንላቸው ይሻላል በእርግጥ። ዘላለም የሚኖሩ ይመስል ሀብት ያጋብሳሉ፣ ይነጥቃሉ። እገድላለሁ ብለው ይፎክራሉ፣ እገድላለሁ ብሎ መሞት እንዳለ ግን ለአፍታም ትዝ አይላቸውም። ህይወት ሞትን ጨምሮ አይመስላቸውም፣ የሌላው እን የነሱ ሟችነት ትዝም አይላቸው።

የሰው ልጆች በሙሉ ሞትን ቢያውቁ እና ቢረዱ ምድር እጅግ የተዋበች ትሆን ነበር። ብዙዎች ግን ሌሎች ይሞታሉ እንጂ እነሱ ዘላለማዊ የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ዘረማንዘራቸው በልቶ የማይጨርሰውን ሀብት ሲያከማቹ፣ ለመቼ የሚል ጥያቄ ለአፍታ አዕምሯቸው ውስጥ አይመጣም።

ሞትን ለማወቅና ለመረዳት የሞት ፍርሀትን ማስወገድ ያስፈልጋል( ሞት ምኑ ያስፈራል መጀመሪያዉንስ ግን?) ሞት ሊፈራ እንደማይገባ ከሰበኩ ፈላስፎች አንዱ የግሪኩ ኢፒኩረስ ነው። ሞት ሊጎዳን እንደማይችል ለማሳየት እቺን አመክንዮ ያስቀምጣል፤
“ For when you are, death is not, and when death is, you are not. Therefore, death can not harm you’’
ይሄው ፈላስፋ(ኢፒኩረስ) የፍልስፍና ዓላማ፣ የደስታ መሰናክል የሆነውን የሞት ፍርሃት በማስወገድ ደስታን እውን ማድረግ እንደሆነ ያምናል። “ በሃይማኖት ምክንያት የተፈጠረብን የሞት ፍርሃት ተረት ነው ሲልም ይናገራል። “Death is no evil’’ ይላችኋል ከፈለጋችሁ።

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በ “ ስልጣን ባህል እና አገዛዝ መፅሐፋቸው” ይህን ይላሉ፤ “ልደት የሞት ዋዜማ ነው፤ ሕይወት የሞት ጥሪ ነው፣ ኑሮ የሕይወት ጻዕር ነው። ሰው መሆን ይህንን እውነት ማወቅ ነው”

ሰው ለምን ሞትን ይፈራል? አንደኛው ምክንያት ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት አለማወቁ ነው። ሁለተኛ ኢፒኩረስ እንዳለው በሃይማቶች ምክንያት የሚፈጠርበት የሞት ፍርሃት አለ፤ ተቃጠልክ፣ ነደድክ፣ ነፈርክ እያሉ ልቡን በፍርሃት ያነዷታል። ለዛ ሲል ከሞት በኋላ ዋስትና ይሆነኛል ብሎ ለሚያስበው አምላክ ይንበረከካል። ግንኙነቱ ከለላ ፍለጋ ይሆናል። ስሙም እምነት ይባላል።
እዚህ ጋር ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ፣
አዳምና ሄዋን እፀ በለሲቷን በመብላታቸው ምክንያት! ሞት መጣባቸው። እሺ ይሁን… ሌሎች እንስሳትስ ምን ስለበሉ ሞት የመጣባቸው?ሞት የመጣው እፀ በለሲቷን በመብላት ከሆነ፣ ያልበሉት ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ነው እፀ በለሲቱን በልተው ነበር? እንደው ለመጠየቅ ያህል ነው….ማነው የተባረከ ጎበዝ እቺን ጥያቄ መልስ የሚያደርግልኝ? የምሬን ነው።

********************************************** ክፍል ሦስት ******************************************

በቅድሚያ ሳንጨርሰቀው ብዙ በመቆየታችን ይቅርታ አርጉለነ
‹‹‹‹‹›››››››››››
“ጭምት ነው ይሉኛል እንዴት አልጨምት
እፊቴ አስቀምጬ፣ እርጅናና ሞት” /ፅላሎት ልብ ወለድ ላይ ያለ አንድ አዝማሪ/

ከዚህ በፊት በነበረው ፅሁፍ መዝጊያ ላይ፣ “አዳምና ሄዋን እፀ በለሲቷን በመብላታቸው ምክንያት! ሞት መጣባቸው። እሺ ይሁን… ሌሎች እንስሳትስ ምን ስለበሉ ነው ሞት የመጣባቸው? ሞት የመጣው እፀ በለሲቷን በመብላት ከሆነ፣ ያልበሉት ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ነው በጊዜው እነ አዳም እና እንስሳቱ አንድ ሆድ ነበር በጋራ የሚጠቀሙት? ብለን ጠይቀን ይሄ ነው የሚባል መልስ የሚመልስልን አላገኘንም። ባይመለስም ጥያቄውን ይዘን እሹሩሩ አንልም። ወደሌላው እንለፍ።
ግን መልስ ይሆነን ዘንድ ከመፅሐፉ ሌላ ክፍል እንጥቀስለት እስቲ፤
መፅሐፈ ሲራክ 42፣ 24 ላይ “ሁሉም አንዱ የሌላው ተቃራኒ በመሆን ሁለት ሁለት ናቸው፣ ምንም ነጠላ አድርጎ የፈጠረው የለም” ይለናል። ይሄ ሞት በአዳም እና በሄዋን ምክንያት መጣ የሚለው ቃል ላይ “ሐሰት” ብሎ የሚመሰክር ቃል ነው። ሁሉንም ሁለት ሁለት አድርጎ ከፈጠረ ፣ለብርሃን ጨለማን፣ ለፍቅር ጥላቻን…ወዘተን ሲፈጥር ህይወትንም ሲፈጥር አብሮ ሞትን ፈጥሯል ማለት ነው። ታዲያ ምንድን ነው፣ “…..ቀጥሎም በሰው ልጆች ላይ ሞት መጣባቸው” እያሉ ማ(መ)ደናገር?

የሞት ክፋት…!

ሞትን በጎ አድርጌ ሳወራ ፍፁም ቅድስና እየሰጠሁት አይደለም። የራሱ ክፋትና ጥፋቶች አሉት።
“ ሞት ሆይ ሰው በምድር ሲኖር በሁሉ ተዘጋጅቶ ሳለ፣ ኀይልም ሳለው፣ ለመብላትም ሆዱ ተከፍቶ ሳለ፣ በሰው ላይ በምትመጣ ጊዜ ስም አጠራርህ እንዴት መራራ ነው!” (መፅሐፈ ሲራክ 41፣1)
የሞት ብቸኛ ክፋቱ ባልተጠበቀ ጊዜ መምጣቱ እና ጣዕሙ ከተለመደው ህይወት መነጠሉ ነው። እገሌ በሚባል ዩንቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቧቻቸው እየተመለሱ ባለበት ወቅት በደረሰ የመኪና አደጋ ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው አለፈ የሚል ዜና ስንሰማ፣ ኑሮን ጠንክረው መጋፈጥ ያልቻሉ ህፃናት ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ያየን ወቅት፣ ዛሬ ነገ ደርሼላት የምንላት እናታችንን በድንገኛ ሞት የተነጠቅን ቀን፣ ዓይናችን ስር ድክ ድክ ሲል ልባችንን በደስታ የሚያዘልላትን የአብራካችን ክፋይ በሞት ፍርግርግ እፊታችንን ተመቶ ሲወድቅ የማየት ዕጣ የተጣለብን ቀን…. ያኔ ሞት ከመራርም መራር ነው። ‘‘ Death is neither pleasure nor painful, is pleasure than life’ ቢልም ሔገስያስ፣ የመራራነቱ ሃይል ምክናያታዊነታችን ላይ ቆሞ በሹፈት ሲጨፍር እናገኛዋለን።

“ ሞት ሆይ፣ ኀይል በሌለው ፈፅሞም ባረጀ፣ ሊያደርገው የሚችል ምንም በሌለው፣የሚያውቀው በሌለው በድሃ ሰው ላይ በምትመጣ ጊዜ ፍርድህ እንዴት መልካም ነው!” ( መፅሐፈ ሲራክ 41፣1-2) ….እንዲህ ዓይነቱ መልካም ጊዜ ያመለጠው የእኛ ሰው ደግሞ እንዲህ ሲል በምሬት ያለቃቅሳል፤
“ምነው አምና በሞትኩ፣ እንዲያ እንዳማረብኝ
ይህ የመንደር ልክፍት ሰርፆ ሳይገባብኝ”
እንግዲህ አሟሟቴን አሳምርልኝ ብቻ ሳይሆን፣ የመሞቻ ጊዜዬን አሳምርልኝ የምትል ፀሎት የፀሎት ሜኑዋችን ላይ ልንጨምር ነው።
/ከአፍታ ቆይታ በኋላ የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል/

 

**********************************************ክፍል አራት (የመጨረሻ ክፍል) ******************************************

 

በዓለም ላይ በልዩ ልዩ ምክንያቶች በቀን 150000 ሰዎች እንደሚሞቱ ይገመታል። ከመሞታቸው ጎን ለጎን ግን መሞታቸውን በእርግጠኝነት መናገር የዘመናት ፈተና እንደሆነ አለ። አንዳንዱ ሞት እንቢ ሞተ ሲሉት ሳጥኑን ከፍቶ ይወጣል። በአዲስ አበባ ደጋግማ ሞታለች ተብላ ደጋግማ የተነሳችውን ሴት ማስታወስ ይቻላል።

በ18ኛው ክ/ዘ የነበሩ ሀኪሞች ሞት ልብ እና ሳንባ ስራቸውን ሲያቆሙ የሚከሰት መሆኑን እርግጠኛ ቢሆኑም፣ አንድ ሰው ሞቷል ብለው በእርግጠኝነት ለመናገር ግን አልቻሉም ነበር። ወዲያ ወደ ጥንታዊ ግሪኮች እና ሮማውያን ስንሄድ ደግሞ ሰውየው መሞቱን ለማረጋረጥ ሶስት ቀን ይጠብቁ እንደነበር እንሰማለን። ቀጠሉና ሮማውያኑ ጣቱን በመቁረጥ ደም መፍሰፍ አለመፍሰሱን ማረጋገጥ ጀመሩ።(ደም ከፈሰሰው አልሞተም!)

እናልዎ ድሮ ድሮ ስንቱ ሳይመርሽ ለአፈር ተዳርጓል መሰልዎ!
Jean brushier-d’ A blaincourt የተባለ የፈረንሳይ ሐኪም 72 ሰዎች በስህተት ሞቱ መባላቸውን እ.አ.አ በ1742 ባጠናው ጥናት አረጋግጧል (End of life communication; page 67) በዚሁ መፅሐፍ ተመሳሳይ ገፅ ላይ carre የተባለ ሰው 46 ስድስት ሰዎች ሞተዋል ከተባለ በኋላ ከቀብራቸው በፊት እንደተነሱ መመዝገቡ ተገልፅዋል። ቀልጣፋ እድሮችን መፍራት ይሄኔ ነው።
‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹‹ ››››››››››››››››››
በዕውቀቱ ስዩም፣ በእንቅልፍ እና ዕድሜ መፅሐፉ እንዲህ ይላል፤
“ሞት ምን ቢወጣጠር ከተኛ ሰው ቁመት አይበልጥም”(ገፅ 98) እንደዚህች አባባል ሞትን በጥፊ አጩሎ-ሞገሱን ገፎ የሚያባርር አገላለፅ አላገኘሁም።

ለአንዳንዱ ከመለያየት ያነሰ አቅም ነው ያለው፣
“አባይን ተሻግሮ፣ አባይ አለ ወይ
ሞትና መለየት አንድ አይደለም ወይ
ሞትና መለየት ምን አንድ አደረገው
ሞት ይሻላል እንጂ፣ ቁርጡ የታወቀው” እንዲል።
በርግጥ ስለሞት ይሄንን ሁሉ የሚያናግር እውቀት አለን ወይ? ሞተን አናውቅ ነገር። ሲሞቱ አየን እንጂ ሞተን አላየን። ታዲያ የማናውቀውን መዘላበድ አይሆንብንም? “ማንም ስለሞት የሚያውቅ የለም። ሳይወለድ ስለ ህይወት፣ በህይወት እያሉ ስለሞት መተንበይ አይቻልም” እንዲል ሌሊሳ በአፍሮጋዳ መፅሐፉ(ገፅ 148)

ከሞት በኋላ ምን አለ?
ሰዉን ስለሞት እዚህ ድረስ የሚያባዝነው፣ የሚያሰግድ የሚያንከራትተው “ከሞት በኋላ…” የሚባል ያልታየ ምናልባትም የማይታይ ጨለማ ክፍል አለ። እውነት ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ማለት ይቻላል? የሰው እድሜ በአንፃሩ ስናየው በጣም አጭር ነው። ቢበዛ ከመቶ ጥቂት አስሮች ነው የሚገፋው። እና ወደ ምድር የመጣሁት ለዚህች አጭር እድሜ ነው ብሎ እንደምን ይመን? ህፃናት ባልጠና እድሜያቸው ይሞታሉ፣ ወጣቶች በአፍላ እድሜያቸው በሞት ይነጠቃሉ። እና እንዴት በዚህ እድሜያቸው መሰናበት የመጨረሻቸው ነው ብሎ ይመን? ሳይወድ በግዱ፣ ከሞት በኋላ ህይወት አለ ለማለት ይገደዳል። አሊያማ ህይወት ከንቱ ሆነ- ጨዋታ!! (አይደለችም እንዴ ድሮስ?) የፈለገ ከንቱ ጨዋታ ብትሆንም ቅሉ፣ ብዙዎች ናት ብለው ማመን አይፈልጉም (አይደለችም መባሏ፣ ከከንቱነት ያስቀራት ይመስል) በእድሜው መጨራሻ ከንቱነትን መዝፈን የጀመረው ጠቢቡ ሰለሞን ምን አለ፤
“ለሰው ልጆች ሞት አለባቸው፤ለእንስሳትም ሞት አለባቸው። አንድ ሞት አለባቸው፤ አንዱ እንደሚሞት እንዲሁ ሌላውም ይሞታል፤ ለሁሉም አንድ እስትንፋስ አላቸው፣ ሰው ከእንስሳ ብልጫው ምንድን ነው? ሁሉም ከንቱ ነውና ምንም የለውም” (መ.መክብብ 3፣19) ….. አንዳንዴ እኮ ሶል ታመጣዋለች። ሰው ስለ ሞት እና ከሞት በኋላ ስላለው ነገር ከማሰቡ በቀር በእንስሳት፣ በሰው እና በእፅዋት ሞት መካከል ምን ልዩነት አለ። እራሱ የመፅሐፍ ቅዱሱ ሰለሞን እንዳለው፣ ምንም!!
እኚያ ሮማውያንስ ምን አሉ? “ከሞት በኋላ ማንም የለም፣ ሞትም እንኳን”
Transmigration(metempsychosis) እናስታውስ። ትራንስ ማይግሬሽን የነብስ ሽግግር ነው። ሽግግሩ ከሰው ወደ ሰው ብቻ ላይሆን ይችላል። የሰው የነበረችው ነብስ ወደ ውሻ፣ወደ አንበሳ፣ወደ ድመት…ወይም ከእፅዋት ወደ አንዱ ልትሄድ ትችላለች። በሕይወት ሳለ ውሻን የደበደበ፣ ከሞተ ውሻ የመሆን እድል አለው። በውሻ የሰራውን ግፍ፣ ሆኖ ይቀምሰዋል ማለት ነው። የዚህ አስተሳሰብ አራማጅ ከሆኖት ውስጥ አንዱ የሆነው ፓይታጎረስ በአንድ ወቅት ቡችላ የሚደበድብን ሰው አስቁሞታል። ምክንያቱ በውሻው ድምፅ ውስጥ የድሮ ጓደኛዬን ድምፅ ሰማሁ የሚል ነበር።
Empedocles የተባለው ጣልያናዊ ፈላስፋም በዚህ ሂደት የሚያም ነበር። ከማመንም በላይ እንዳለፈበትም ይናገራል። እንዲህ ሲል፤ “I was once in the past a boy, once a girl, once a tree, once too a bird, and once a silen fish in the sea’’
እዚህ ጋር “ከሞት ወዲያ ህይወት(?)” የሚለውን የማሞ ውድነህን የትርጉም መፅሐፍ እናስታውስ። ፀሐፊው በየሀገራቱ ያሉ መንፈስ ጠሪዎች ጋር እየሄደ ጭምር ያዘጋጀው መፅሐፍ ነው። ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ቢልም፣ ከየትኛውም ሃይማኖት/ ፈጣሪ ጋር አያገናኘውም።
እውነት ህንዶች ያቃጠሉት እና አመድ ሆኖ የጠፋው ሬሳ፣ ለምፅዓት ተገጣጥሞ ሰው ሆኖ ይመለሳል ብለን እናምናለን? ጅቦች በልተውት የሞተ ሰው፣ በሰላም ከሞተ ሰው እኩል ለፍርድ ቀን መጥቶ አብሮት ይሰለፋል ብለን እናምናለን? ሞኝ ጥያቄ ጠየኩ አይደል?…

በእርግጥ ሞት እራሱ አለ ወይ?

መልሱ ቀላል ነው። አለም! የለምም! ጥያቄውም መች አለ? መች የለም? ወደሚል ይዞራል። በግለሰቦች ደረጃ ሲሆን ሞት አለ። በማህበረሰብ ወይም በህዝብ ደረጃ ካየነው ደግሞ ሞት የለም። ምን ማለት ነው?
ግለሰቦች ይሞታሉ። ስለዚህ ግለሰቦች ላይ ሞት አለ። ህዝብ ግን በአንዴ አይሞትም- ሞት ህዝብ ላይ ስልጣን የለውም።
የኛ ሰው ሲጠቀስ ይወድ የለ መቼም እንጥቀስለታ፤
“ሕያውነት የማህበረሰብ ባህሪ ነው፣ ማህበረሰብ እንደ ግለሰብ ሟች አይደለም፤ ማህበረሰብ በተከታታይ ትውልዶች ህያው ሆኖ የሚወጥል ነው” (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ የክህደት ቁልቁለት ገፅ 125)
“ሞት እያንዳዳችንን ማሸነፍ ይችላል። ይሁን እንጂ ህዝብ ላይ ስልጣን የለውም” (ዋለልኝ እምሩ፣ “የሕይወት ትርጉም” ገፅ 178)

ወገኖች! ስለ ሞት ከዚህ በኋላ ልፅፍ የምችለው በራሱ በጣም ረዘመብኝ! ሃራኪሪ ማንሳት ፈለኩ፣ ከሞት በኋላ ህይወት ዝም ዝም ነው የሚሉትን nihilistዎች እና Absurdistዎችን ማየት ፈለኩ። ሞት ባይኖር ብዬ ብዙ ነገር መዘርዘር ፈለኩ። ጦርነት ላይ በመድፍ ተመቶ እንዳለመሞት አይነት፣ አየር አጥቶ እንደመኖር አይነት፣ አንገት ተቆርጦ ምንም እንዳለመሆን አይነት። አሁን አዳምና እና ሄዋን ያንን በለስ ባይበሉ(በእርግጥ አልበሉም!) ፣ አንገታችን ቢቆረጥ እንኳን አንሞትም ብሎ የሚያምን አለ? …. ወዘተ ወዘተ ልፅፍ አልኩና ሰፋብኝ። ሞት ከህይወት እንደሚረዝም፣እንደሚወፍር ገባኝ። እናም ሞት መሃል ላይ መኖርን እንደሚያቋርጥ፣ እኔም ስለ ሞት መሃሉ ላይ ላቋርጥ ወደድኩ። ስለሞት ሲፅፉ፣ ሞትን መምሰል ምን ክፋት አለው?


ም!!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

2 Comments

  • yassirmuhanet@gmail.com'
    Yassin mohammed commented on July 10, 2016 Reply

    ሁሌም ሰው መሆኔን ሳስብ መፈጠሬ ይገርመኛል

  • zewudubuze674@gmail.com'
    buzzz commented on February 15, 2022 Reply

    sorry min yagenagnewal kezi gar edatlegn edihu ketyakewoche andu ……….እግዝያብሔር በጥበቡ ከጥቃቅን ነገሮች እስከ ሰው ልጅ ሁሉንም ነገር በምድር ላይ ፈጠረ እናም እርሱ ጥበበኛ ነውና የወደፊቱንም ምን እደሚፈጠር ያውቃል ታዲያ አዳምንና ሔዋንን መጀመሪያ ሲፈትናቸው እደሚሳሳቱ ቀድሞ የሚያውቅ ይመስለኛል ታዲያ እያወቀ ለምን ፈተናቸው ከዚያስ በሗላ ለምን እረገማቸው እርግማን በርሱ ፊት አፀያፊ አይደለምን???? እና ደግሞ የረሳሁት ነገር የበሉት እፅ አሁን ምድር ላይ አለ ወይስ የለም?? ቀኛችሁን ሲመቱአችሁ ግራችሁን ስጡ ወይም በደልን በበደል አትመልሱ ይባላል ግን እኮ ደግሞ እራሱ እነ አዳምን ስለ በደሉት እረግምዋቸዋል ደግሞ እንደ ገና በመርገሙ የተፀፀተ ይመስላል ምክንያቱም እኛን ይቅር ለማለት ተመልሶ በሰው ልጅ አምሳል ይመጣና ያድነናል ለምን??? ////የጥያቄ ገፅ 04/03/2013 ዓ.ም ቡዝዝዝ///////………………..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...