Tidarfelagi.com

ምንሽን

የሰው አገር ሙጥኝ ብየ፥ በወጣሁበት እንዳልቀር
አገሬ ፍቅርሽ ሳበኝ፥ ግና ምንድር ነው ማፍቀር
እንዳስመሳይ አዝማሪ፥ ካልሸነገልኩሽ በቀር
ከተወለድሁ እስከዛሬ፥ ከጣቶችሽ መች ጎርሼ
ወተትሽን መች ቀምሼ
ወለላሽን መቸ ልሼ
ሲርበኝ
ጠኔ በቀኝ በግራ፥ እንደ ጭፍራ ሲከበኝ
የት ነበር የንጀራሽ ሌማት
ሾላ ስለቅም ተሻምቼ፥ ከሽመላ ከማማት
ኑሮየ ሁዳዴ ጦም፥ ፋሲካ አልባ ህማማት።

እና ከድሎት አገር ፥ የሲሳይ ዶፍ ከሚያወርደው
ምን ገፍቶኝ ነው በሞቴ፥ ወዳንቺ የምሰደደው ?
ምን ነክቶኝ ነው? ምንሽን ነው የምወደው?
እኔና ብጤዎቼ፥ እኛ ቅብዝብዝ ልጆችሽ
መስኮት በሩ ተዘግቶብን፥ ተበትነን በደጆችሽ
ይሄው ሶስት ሺ ዘበን፥ ወደ ሰማይ አንጋጠን
በንዝርት እግር ተንበርክከን ፥ በቀይ እንባ ስንማጠን
የለት እንጀራችንን ነፍጎ፥ የእለት ገጀራችንን ሰጠን።

አሁንማ ለመከራሽ ፥ ማን አለና የሚገደው
እሪታሽን እንደዘፈን ፥ ያለም ጆሮ ለመደው
እና ምንሽ ነው እሚስበኝ ፥ ምንሽን ነው የምወደው?
ዛሬም ሆነ ያለፈው
በላባ ብእርም ይሁን በኪቦርድሽ የተጣፈው
ታሪክሽን ሳነበው፥ ደምና አመድ ነው የሞላው
መች ተነቅሎ ከወለልሽ፥ የሾህ ጉንጉን አሜኬላው
ስልጣን ፈልሶ ቢሸጋገር ፥ ካንዱ ጭራቅ ወደ ሌላው ።

እናም እንሆ!
ያለፈውን ዘመን ትቼ፥ የቀረኝን እያሰላሁ
የብርሀን ቅሪት ባጣ፥ አምፖሌን በተስፋ ሞላሁ።
እንጀራየን እንደ ሐሰን ፥ በዳበሳ እየበላሁ።
ከዚህ ወድያ አልልሽም ፥ ወዴት አለ ያንች አለኝታ
ግን ምንሽ ነው እሚስበኝ፥ ልማድ ይሁን ይሉኝታ
እግሬን ከምድርሽ ጋራ ፥ ምንድነው ያስተሳሰረው
ያገር ፍቅር አለኝ ብልስ፥ ምንሽን ነው እማፈቅረው።

(በግጥሙ ውስጥ “ሐሰን “ ተብሎ የተጠቀሰው ዝነኛው አይነስውር የወሎ አዝማሪ ሐሰን አማኑ ነው)

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...