Tidarfelagi.com

ማፍረስ እንደ ባህል

(የመትከል ባህል የሌለው ሕዝብ እንትከል ስትለው አወዳደቁን እየተለመ ይስቃል)

ስሜነህ አያለሁ እና ቢኒያም ሲሳይ የፃፉት፣ «what is in a term? A historical and linguistic examination of the revolutionary terminology:yiwdem, “let it be demolished, down with,” 1974-1977» የሚል ወረቀት አለ። “ይውደም” የሚለው ቃል እንዴት ከዛ በኋላ የመጡ አሰቃቂ የግድያ ተግባሮችን እንደወሰነ ነው ያነሱበት። ይውደም ያልተባለ ነገር አልነበረም።

የባላባቶች ስርዓት ይውደሙ ተብሏል። «ለውጡን የሚቃወሙ ጨርሰው ይወደሙ» ተብሏል። ቀደም ብሎ «ሃይለስላሴ ይወደሙ!» ተዘምሯል። ደርግም፣ «ኢትዮጵያ ትቅደም አቆርቋዧ ይውደም! » እያለ ብዙ አውድሟል። ኢትዮጵያ መቅደሟ ጥሩ ነበር። እያወደምኩ የምትለው ግን እሷኑ ከማድቀቅ ውጪ ምንም አልፈየደም!
ነጥባችን ወዲህ ነው። ይሄ የይውደም ቃልና ድርጊት የፖለቲካ ባህላችን ከሆነ ሰነባብቷል። ቤተኛ ከመሆኑ የተነሳ ችግርነቱ ተረስቶ አባል ሆኗል።

ተጣብቶን የመጣው ይሄ የይውደም ባህል፣ ዘንድሮም ከመገንባት ይልቅ የማውደም ወልፍ ላይ ጥዶናል። ከግለሰብ እስከ ተቋም ኋላፊነቱ ያልተወሰነ አፍራሽ ተቋም የመሆን መንገድ ላይ ተማሚ ሆኗል።
.
ተሻለ ጥበቡ፣ modernism, eurocentrism, and radical politics in Ethiopia,1961-1991 በሚል ስራው፤ «ያ ትውልድ የቀደሙት የነ ሀዲስ ዓለማየሁን የልሂቃን ቡድን እንዴት «ደብተራ» ብሎ ይሰድብ እንደነበር፣ ግን ከነሱ ተሽለው የሀገሪቱንም የአውሮፓንም እውቀት ይረዱ እንዳልነበር» ይነግረናል። ያልተረዱትን ነገር ለማውደም ግን የቀደማቸው አልነበረም።
.
እንዲህ አይነት አባዜ እዛ ዘመን ላይ ቢቆም ጥሩ ነበር። ዛሬ ድረስ ከማህበራዊ ሚዲያው እስከ መንግስት ተቋማት እንደሙያ ይዘው የሚዳክሩበት ባህል ነው።

ሃይለስላሴ፣ ከታህሳሱ ግርግር መክሸፍ በኋላ ተገድሎ የሞተ ሰው ጭምር በአደባባይ እንዲሰቀል አደረጉ። ሬሳን መስቀል ምንን ያሳያል? ነቅሎ አለመርካት? አውድሞ አለመጥገብ?
.
ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ዘነናዊ ትምህርት ሲስፋፋ ባህላዊ ትምህርትን ማንበር አልተቻለም። አንዱ እንዲቆም ሌላው መሞት ያለበት ይመስለናል። ደርግ መጣ። የኢትዮጵያን ባህላዊ አምዶች ሁሉ አወደመ። ንጉሳዊ ስርዓቱን ቀበረ። ንጉሱን ገደለ። እነ መንግስቱ ተነስተው ዳግም ከወንበሩ እንዳይፈነግሏቸው የፈሩ ይመስል በቅርብ ቀበሯቸው።
.
የንግግራችን አካል ይቀነስ እንጂ ይጨመር የለውም። እንትን ክልል ይቀነስ ነው፤ ይገንጠል! ከጀርባ ያለውን ሞቲቭ ትክ ብሎ ላየ ጥያቄው ከፍትህ እና ከነፃነት ጥያቄ በእጅጉ ያንሳል። የቋንቋ ምሁር ነኝ ብሎ መጥቶ፣ ፊደላት ይቀነሱ ይላል። በአማርኛ ፊደላት ውጥት የሌሉ የተለያዩ ድምፆች ይጨመሩ ሲል የሚሰማ ሰው ማግኘት ብርቅ ይሆናል! የግዕዝ ቁጥር ላይ ተስማምቶ አንዲት “ዜሮ ቁጥርን” መጨመር ያቃታው ሁላ፣ በማውደም ወሬ እንጥሉን ያደክማል። ባህል ሆኗላ። መንቀል!
.
በአማን ነጸረ የተባለ የፌስቡክ ወዳጃችን በቅርቡ ይሄን ፅፎ ነበር፤
የፕ/ር መስፍን የ‹‹መክሸፍ …›› ታሪኮች እየገቡኝ የመጡ አሁን ነው። እዚህ ሀገር ሟርት፣ ንግርትና ‹‹ትንቢት›› ለምን እንደሚያዋጣ እየገባኝ የመጣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። የተጀመረ ሁሉ በሚከሽፍበትና አድኃሪነት ሥርዓት በሆነበት ሀገር ሟርት፣ ንግርትና ‹‹ትንቢት›› በጣም አዋጪ ሙያዎች ናቸው። ነገሮችን ሁሉ አስቀድመህ በጨለምተኝነት ፈርጀህ ኋላ ‹‹ብዬ ነበር … ›› ለማለት ሀገራችን እጅግ ምቹ ናት።

ያልመራነው ለውጥ ለውጥ አይደለም እና የለውጥ ጠላት የሚሏቸውን የማጥፋት ሙከራ አሁንም አለ። ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርብ በነበረው የምክር ቤት ውሎ ምን አለ? «መፈንቅለ መንግስት ቢቃጣብን አብረን እንወድማለን እንጂ ምንም አታመጡም» አላለም።
ጎበዝ፣ እኔ ያልተከልኩት አይፀድቅም፣ እኔ ያልነቀልኩት አያምርም ባይነት ባህል ከሆነ ሰነባብቷል!

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሚል እዬዬ አለ። በየትኛውም መንገድ ያለፈውን በማፍረስ መጀመር ነው። አፍርሶ በራስ ቅርፅ መቀየር። ቀጣይ ይመጣል ያፈርሳል። ተካታይ ይመጣል ያፈርሳል— የማውደም ሰንሰለት!

አሳምነው ፅጌ ያደረገው እና ያወራው የዚህ የማውደም ባህል ሰለባነትን የሚያሳይ አዚም ነው።
«ለክልሉ ጥቅም በማይሰሩ አመራሮች ላይ እርምጃ ወስደንባቸዋል» አለመስማማትን በማውደም ነው የምንደመድመው አየህ? አማራጭ ሙግት አይደለም ይዘህ የምትመጣው። ጠመንጃህን ነው የምትመዘው! የሚተከል ነገር ይዘህ ከመምጣትህ በፊት ትነቅላለህ። ችግኝ እንትከል ሲባል፣ ድርጊቱ እና ቁጥሩ ላይ ያለው ማሾም ዝም ብሎ ቀልድ አይመስልህ። የመትከል ባህል ስለሌለ ነው። የንቅል እንቀል ዘመን ውስጥ የኖረ ህዝብ እናቁም ስትለው ሙድ ይይዛል። እንትከል ስትለው አወዳደቁን በምናቡ እየሳለ ይሰቃል!!
.
የቄሮ ትግል ብለው የሚሉት በዚህ የታቀፈ ነበር። ማውደም የሚነዳው ስሜት ነበር። ብዙ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወድመዋል። ለአካባቢው ሕዝብ ያላቸው ጥቅም ግምት ውስጥ አልገባም። ከዛ ወዲህ፣ እዛው ስፍራ ላይ የሚፈጥረው የኢኮኖሚ መፋዘዝ አልታሰበም። «ለትህሉ ሲባል» ብዙ ያልተነገሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን የማጥቃት ድርጊቶችም፣ ነባር ማህበራዊ ትስስርን የሚያወድሙ ተግባራት ነበሩ። ወድሞ አያልቅ ሆኖ እንጂ።
.
ዛሬ እጅግ በግብታዊነት የሚያብዱት፣ በስሜት ሱረት የሚጦዙት የአማራ አክቲቭስቶች ካላወደምን አንቆምም ብለው ሕዝቡን አሳብደውታል። ዲጂታላዊ እብደት ተይዟል። ያለውን ሪፎርም አድርጎ ከመቀጠል ይልቅ፣ ብዙ ለማሻሻል ዝቅ ብሎ የሚለፋ ፓርቲ ላይ እሳት ያዘንባሉ። አዴፓ አይወክለንም/ አዴፓ ይውደም! ይላሉ። ስለመንቀላቸው እንጂ ስለመትከላቸው ግዳቸው አይደለም።
.
ረዘመ እና ተንዛዛ እንጂ ብዙ እያልን መዝለቅ እንችል ነበር። አንድ ቅን ምክር ግን እንመክራለን።
እነቅላለሁ ከማለት በፊት ምን እተክላለሁ ማለት ይቅደም። እንደ ሰፈር ወጠምሻ ነገርን ሁሉ በጡንቻ ከመመዘን፣ መቃጠሉ ለትኋኑ በጀኝ እንዳለችው ሴት አውድሞ ከመደሰት ሚዛን ያጣ ደስታ ለመታቀብ ሰከን ማለት ደግ ነው። ስክነት በማሰብ እንጂ በማሳሰብ እንደማይመጣ ጠፍቶኝ አይደለም። ቢቸግር ነው!
ቢያንስ፣ የራስን የፌስቡክ ግድግዳን ፆም በማሳደር፣ ሀገርን ሰላም ማሳደር ይቻላል!

ከማውደም ልክፍት ምን ያህል ርቄያለሁ ብሎ፣ ስለ ማንበርና ስለመትከል ማሰብ ሊቅ መሆን አይጠይቅም!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...