Tidarfelagi.com

ማዘሎ !!

በእድሜ የገፉ ሰዎችን ማክበር ጥሩ ነው ! ከሞራልም ከሃይማኖትም አንፃር ማለቴ ነው …. ግን እውነታውን እናውራ ከተባለ ስንት የሚያበሳጭ ‹‹ትልቅ ሰው›› አለ መሰላችሁ ምንም የሽምግልና ለዛ የሌለው …ከምር ! አንዳንዴ ወጣት ሁኖ ባጠናፈርኩት ኖሮ የምትሉት እድሜው የትየለሌ የሆነ ሰው አለ ! ለምሳሌ ዛሬ ያየኋቸው ሴትዮ በጣም ነው ያበሳጩኝ …

እድሚያቸው ስልሳውን ያለፈ ሴትዮ ናቸው አለባበሳቸውና የያዙት ቦርሳ ….ዘመነኛ ነገር ….የተሳፈርንባት ታክሲ ውስጥ ገቡ …..ሙሉ ስለነበር ፊት ወንበር ላይ የተቀመጠች ቆንጆ (ከቅድም ጀምሮ እያየኋት ነበር …ቆንጆ ናት በተለይ እግሯ) በአክብሮት ወንበር ለቀቀችላቸው …..እና ትርፍ ሁና በጥግ በኩል ያለ ጣውላ ላይ ተቀመጠች … ሴትዮዋ ልጅቱን ገልመጥ አደረጉና … ሊያመሰግኗት ነው ብየ ሳስብ …..አዥጎደጎዱታ የዱርየ ምክራቸውን ….

‹‹ይሄን የመሰለ እግር …›› አሉ የልጅቱ እግር ጥርት ያለ ውብ እግር በጥቁር ቀሚሷ ቅድ ብቅ ብሏል ….‹‹ ይሄን የመሰለ ቢነኩት የሚፈርጥ የሚመስል ዳሌ …›› አሉ የልጅቱን ዳሌ አየሁ እውነትም ቀሚሱን ሊተረትረው የሚታገል ባሉን ይመስላል …..‹‹ይሄን የመሰለ ጡት …›› አሉ ….የልጅቱ ጡት አለም በቃኝ ያለ ሳይቀር ያሳስታል የሚሉት አይነት ነው …..‹‹ይሄን የመሰረ ቂ*….ይዘሽ ምነዋ ህዝብ ጋር መጋፋትሽ …ይሄ ሁሉ ውሃ የመሰለ መኪና ይዞ ሽው የሚል ወንድ ምን ይሰራል …ነቃ በይ እግዜር ካለነገሩ መልክ አይሰጥም …

ስንቷ አይጥ ናት በግል መኪና የምትምነሸነሸው … ብልጠት እንጅ መልክማ ላንች ‹‹ገረድ›› እንኳ ልትሆን የማይገባት ሁሉ ……አንድ ሁለት ያዲሳባን ልበቢስ ሴሰኛ ሃብታም ወንድ ብትወዳጅ እመቤቴ ብለው እግርሽን ስመው ነው እንደምየ ማሪያም የሚሰግዱልሽ …ውበት ረጋፊ ነው …ካለው ጠጋ እያልሽ ሃብት ቋጥሪ ….ልጀ! አፈር ለሚበላው ገላ ምንድነው መጠራሞት …ኤዲያ ! ራስሽን አትጨቁኝ ….ህዝቡ እንደሆነ ጨዋ ትሁት ይልሻል ላፉ ውሸቱን ነው …አበሻ ውሸታም …አስመሳይ !! ሃብት ስትይዥ …ሸር*ጣ ብትሆኝም ቅድስት ነው የሚልሽ …ወንዱም ስትሸራ*ጭ ….ነው ቀበቶውን ፈቶ እንደውሻ የሚከተልሽ …›› አነበነቡ አይገልፀውም …ታክሲ ውስጥ ያለው ሰው አፍሮ ይሁን ደብሮት ጆሮውን ቀስሮ አይኑን ማሳረፊያ አጥቷል …..ሴትዮዋ ሊያቆሙ መሰላችሁ …

ይች ሁሉ የምታያት ሴት ልብሱን ጌጡን ከየት አባቷ ታመጠዋለች ያው እየሸረ..ች ነው ….የሰባት ደሃ ልጅ …እናት አባቷን ብትመለከችው ዱቄት የነፉባቸው ነው የሚመስሉት … ደሞ ያዲሳባ ሴት ውሎ ይግባ ሃብታም ….እስካሁን ሸራ ጫማዋን ገጥግጣ ቅጫሟ እየረገፈ በየመንደሩ ስትንደፋደፍ በተገኘች አዳሜ ! ያገር ስራ ነው አያሳፍርም ….እወቂበት …እኔ እናትሽ ባለጌ ሁኘ እንዳይመስልሽ ጧት ማታ ቤተስኪያን ዝንፍ ሳልል ነው የምስመው ….ውበት እንዲህ እንዳረባ ነገር በየታክሲው ሲወድቅ እያዘንኩ እንጅ …ማን ያዝናል ዛሬ ወንዱ አቅሙን አያውቅ እንደጥንብ አሳ ቆንጆ መቀራመት ነው …ቁንጅና ሃብት መሆኑን አያውቅ ! የልብሱስ የፀጉሩስ ዋጋ የትና የት ነው? …ይሄን ሁሉ አውጥቶ አምሮ ሰው ያዲሳባን ቆሻሻ አቧራ ሲጠጣ ይውላል? ….!ማንም ጋር ሲጋፋ ይውላል ?…እወቂበት ግዴለም !

‹‹ወራጅ !! ሄይ ወራጅ አልኩህኮ ›› አለ አጠገባቸው የተቀመጠ የባልቴቷ ንግግር የደበረው የሚመስል ወጣት ድምፁ ያስታውቃል …‹‹ደግሞ ይሄ ወራጅ እያልኩት ዝም ብሎ ይነዳል እንዴ …..›› አለ በብስጭት! ታክሲው አለፍ ብሎ ቆመ …ልጁ ሴትዮዋን ገፋ አድርጓቸው ወረደ! …ሴትዮዋ አንገታቸው እስኪቀነጠስ ዙረው እያጨነቆሩ ልጁን ተመለከቱና ….ወዲያው ልጁ ላይ ይወርዱበት ጀመረ …

‹‹ ጥርግ በል ብሽቅ !! …ሰው በዚህ እድሜ ታክሲ ላይ ይጋፋል?… አቁሙልኝ እያለ ይጋፋል? …ወጣት ነህ ብትችል ሰርተህ ካልሆነም ዘርፈህ ለሌላው እንደመትረፍ ‹‹ወራጅ ›› እያለ ጆሮየ ላይ ቡሃቃ አፉን ይከፍትብኛል ….ከድህነት ነው እንዲህ ፎክሮ መውረድ .….ደሃወቹ ረዳትና ሹፌሮች ምድረ ደሃ ሲያጓጉዙ በዋሉ ምን ያርጉህ …..ወራጅ ይላል ደሞ…. እንጥልህ ይውረድ እቴ ….ባቄላ አለቀ ቢሉ አሉ ፈ.. ቀለለ ›› አሁን የታክሲው ሰው ሳቀ …. ሴትዮዋ ግን ተቆጡ ‹‹ተሳቀና ተሞተ ….አዳሜ እንደሰርዲን ታጭቀሽ ትገለፍጫለሽ … ከውጭ ሲያዩሽ እንዴት መሳቂያ እንደሆንሽ …የደሃ ሳቅ መስማት ነው የሰለቸኝ ….ኤዲያ ….ደሞ ይሳቅልኛል ›› ነካ ያደርጋቸዋል ብየ አሰብኩ ….

አንዲት ደልደል ያለች ልጅ ወረደች ….አሁንም አጨንቁረው ተመለከቱና ታክሲው ሲነሳ ጀመሩ ‹‹ ዝም ብለው ጥሬ ከብስል ይወጥቃሉ እንዲህ ፊኛ አክለው …ታክሲ ያጣብባሉ …እስቲ ሰው ይሄን የሚያህል ሰውነት ይዞ ደሃ ይሆናል …ወፍራም ደሃ ! ደሃ እንደለበቅ እጥፍ ዘርጋ ብሎ ካልሰራ ምን ዋጋ አለው …ቦርጭ እና ስኳር ከማጠራቀም ሳንቲም አታጠራቅምም … ይሄን ጊዜ ይችም ባሌ ሌላ ወደደ ብላ ትቆጣ ይሆናል …ነፈዝ እሱስ ይችን ማግባቱ ….ተራራ ….ደሞ ሲለብሱ አይታ …ቦዲ ኡኡቴ …ምን ጠቀማት ሲያጌጡ ይመላጎጡ ….ይሄው ጎንበስ ስትል …..ይሄን በሰገሌ ጊዜ የቀረ ሙታንቲዋን አጋለጠላታ ! ሹፌሩ በሳቅ ድክም አለ …..

ከኀላ ስለኳስ ስለእንግሊዝ ተጨዋቾች ዝውውር ስለተከፈላቸው ፖውንድ የሚያወሩ ጎልማሶች ከታክሲው ወረዱ ….ሴትዬዋ ፊታቸውን አጨፍግገው ሲያዩዋቸው ቆዩና “ደሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ግርጣት ይገለው ነበር አሉ …ደሞ ስለሚሊየን ባውንድ ይወራልኛላ …ሆሆ አሁን ይሄ የፈረስ ጉግስ በማውሪያ እድሜው ኳስ …ሆሆ …አዳሜ እድሜ ልኩን ከተተከለበት ኑሮ መዘዋወር አይሆንለትም እንጅ የተጨዋች ዝውውር እያለ ላንቃው እስኪላቀቅ ይቀባጥራል …ሳቅን ….ወደኔ ዞረው

“ስቀህ ሙተሃል” … ብለው ሊቀጥሉ ሲሉ ‹‹ወራጅ›› አልኩ ድምፄን አለስልሸ …..፡)ከኋላ እየተቦጨኩ ነው ብሎ ማሰብ ያሳቅቃል ለካ …ከወረድኩ በኋላ በቀስታ ወደወረድኩባት ታክሲ ዞር ብየ ተመለከትኩ …..ሴትየይቱ አጨንቁረው እያዩኝ ነው ….ሳቄ አመለጠኝ ! እርግጠኛ ነኝ ላፕቶብ ይዠ ስለነበር ‹‹ማዘሎ ….›› ብለው እንደሚጀምሩ አልተጠራጠርኩም !!‹‹ማዘሎ …. ሰው ቀልጠፍ ያለ ስልክ ይዞ ሽር ብትን ይላል ….እሱ በሰገሌ ጊዜ የቀረ ሳጥን የሚያክል ‹ኮምፐተር› ተሸክሞ ይዞራል ….፡)

 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...