Tidarfelagi.com

‹‹ማርች ኤትን በአዝማሪ››

ሁለት መቶ ሰው ፊት መስሪያ ቤታችን ለሚከበረው የአለም የሴቶች ቀን ዝግጅት አስተባባሪ ሆኜ ስሾም ይህንን ቀን ‹‹ማርች ኤጭ›› እያሉ የሚጠሩት ወንዶች ባልደረቦቻችን እና እኛንም የማያማርር ‹‹ሴቶች ለሴቶች የሚያዘጋጁት አሰልቺ ቀን›› ፣ ሴቶች አበሻ ቀሚስ ለብሰው ፈንዲሻ እየበሉ ወንዶችን የሚረግሙበት ቀን›› ላለማድረግ ሃሳቦችን መሰብሰብ ጀመርኩ።

አዳዲስ ነገሮችን ለማድረግ እና ‹‹እዚያው በጠበላችሁ›› የሚያሰኝ የሻገተ አከባበር ላለማድረግ ወዲህ ወዲያ ጀመርኩ።

አንደኛ፤ ቡናው በወንድ ይፈላል።
ሁለተኛ፤ ዳቦው በሴት ይቆረሳል።
ሶስተኛ፤ መድረኩ በወንድ ይመራል።
አራተኛ ሮዝ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊም ፊኛ ይሰቀላል።

እንዲህ እንዲህ ስንል ለዝግጅቱ ማዳመቂያ አዝማሪ ለመቅጠር ወሰንን።

የአዝማሪዎች ሙዚቃ በተለይ ግጥሙ ሴቶችን ሲሸነቁጥ እንጂ ሲያሞግስ አልተለመደምና፣
ሴቶችን ሲያንጓጥጥ እንጂ ሲያነግስ አይሰማምና፤ አዲስ ነገር ይሆናል ብለን አዝማሪ ለመቅጠር ወሰንን።

ከተማውን ማታ ማታ በአንድ እግሩ ከሚያቆሙት ኮከብ አዝማሪዎች መሃከል አንዱን ለመቅጠር ተስማማን እና ስለ ዘፈኖቹ፣ ስለግጥሙ አይነት፣ ስለዝግጅቱ ስሜት ለማናገር ቢሮዬ ጠራሁት።

‹‹ጌታዬ እንግዲህ ቀኑ ማርች ኤይት ነውና ፣ ዝግጅቱም ቀን፣ በመስሪያ ቤት ሰዎች ፊት ነውና የማታ የማታ ግጥም፣ ይህች ስድቧ፣ ወሲቧ ምናምን እንዳትቀላቀል አደራ!›› አልኩት ትንሽ ካወራን በኋላ።
‹‹አታስቢ። ገብቶኛል። ተስማምተናል እቱ!›› አለኝ ፈገግ ብሎ

‹‹ብትችል ሴትን ብታሞግስ፣ ብታንቆለጳጵስ ደግሞ እንዴት ግሩም ነበር!›› አልኩት ነገሩ ባጭሩ ማለቁ ደስ ብሎኝ።

‹‹ችግር የለም እቴ! ይሄውልሽ አንድ ምሳሌ…›› ብሎ ከወንበሩ ተነሳ።

ማሲንቆውን ሳይዝ ማሲንቆ እንደያዘ ግራ እጁን ገትሮ፣ በቀኝ እጁ አየሩን እየገዘገዘ አንዲህ ብሎ ዘፈነልኝ…
‹‹ እንጀራ እንዳትጋግር ባልትና ቤት መጣ…
ስፌት እንዳትሰፋ ሰፊ ትሪ መጣ…

(ደስ ብሎኝ ፈገግ አልኩ….)
ውሃም እንዳትቀዳ ቤቴ ቧንቧ ገባ…

(በምርጫዬ እየኮራሁ ይበልጥ ደስ ብሎኝ ፈገግ አልኩኝ)

ሸክም እንዳይበዛ ይሄው ኩሊ መጣ….

(መጨረሻው ምን ይሆን ብዬ ሰፍ ብዬ መስማት ቀጠልኩ)

‹‹ባስበው ባልመው ለርሷ ስራ ታጣ…
ትውጣልኝ ከቤቴ ፖሊስ ሳላመጣ››

እሱ እየሳቀ ቁጭ ሲል እኔ አገጬ በድንጋጤ የወደቀ መሰለኝ።

‹‹ቀልድህን ነው አይደል….?›› አልኩት ጉልበት አሰባስቤ፣ ሌላ ሰው ለመቅጠር 12 ሰአት እንደቀረኝ አስቤ።

‹‹መጨረሻው ካልጣመሽ ይቀየራል ነፍሴ….›› አለኝ የኔ መደንገጥ ቅምም ሳይለው።

አውቆ ይሆን ሳያውቅ ነገሩን ሁሉ ጥሬ አደረገብኝ።

‹‹ጌታዬ…አልተግባባንም…እንደገና ላስረዳህ›› አልኩ እና ከመጀመሪያው ጀምሬ አንደገና ላስረዳሁ ለፋሁ።

‹‹እሺ…አሁን ተግባብተናል?›› አልኩ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ።

‹‹በደንብ! ሴቶችን እንዳወድስ፣ እንዳሞካሽ ነው አይደለም?›› አለኝ በተቀመጠበት እየተቁነጠነጠ። ሳላሰለቸው አልቀረሁም።

‹‹እህ…!እንደሱ ነው…ብዙ ሰው ይመጣል…ጉድ እንዳታደርገኝ….››

‹‹ይሄው አሁን የመጣልኝን አንድ ልበልልሽ….››

‹‹እሺ…›› አልኩ በግማሽ ጉጉት በግማሽ ፍርሃት።

‹‹ወፍሬ መስሏችሁ ፊቴ ቢያብጥባችሁ…
ደልቶኝ ነው መስሏችሁ ፊቴ ቢያብጥባችሁ…
ሚስቴ ደብድባኝ ነው እንዲህ የሆንኩላችሁ››

ልቤ ዝቅ አለ።

‹‹ስማኝማ…?›› አልኩት ተስፋ ቆርጨ።

‹‹አቤት…››

‹‹ሴትን ለማወደስ ባሏን ትደብድብ የሚል ህግ የለም…በቃ ..ትዝታ ምናምን ዝፈን…ባለጌ ነገር የሌለው አምባሰል፣ ትዝታ፣ የሚያስጨፍር ምናምን….››

ተጨባበጥን እና ወጣ።

ልቤ ግን አሁንም አላረፈም። ታዋቂ አዝማሪ በመሆኑ ከዚህ በፊት የሰራቸውን ስራዎች ልይ እና ልረጋጋ ብዬ ዩ ትዩብን ማሰስ ጀመርኩ።

የመጀመሪያው ቪዲዮ በመቶ ስልሳ ሺህ ሰዎች ታይቷል።

(በለው! በጣም ታዋቂ ነው!)

ርእሱ ? ‹‹ዳቦ ጉድ አፈላ››

ጉዴ ፈላ!

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...