Tidarfelagi.com

ሚስቴ ፓለቲከኛ ናት

ፓለቲካ አልወድም። የማልወደው፣ ሰዎች የሚያንቀሳቅሱት ሳይሆን ሰዎችን የሚያንቅሳቅሳቸው ስለሆነ ነው። ፓሊዮ እና ዚካ ተቀላቅለው የፈጠረቱ ይመስለኛል።
የጠላሁት ቤቴ ገባ። አትግባ እንዳልለው፣ ይዛው የገባችው ባለቤቴ ናት። መች እንደጀመራት ሳላውቅ ፓለቲካ አተኮሳት። ቀጥሎ አነደዳት። ተቃጠለች። እሳቷ እሳቴ ሆነ።
ፍቅር ከሰራን በኋላ ሁሉ፣የአደረግነውን በተመለከተ፣ የአፈፃፀም ግምገማ ማድረግ ያምራት ጀመረ። ከቤታችን ስንወጣ ብዙ የወደቁ ሰዎች ብናይም፣ በቀን ሶስቴ መብላታችን እንደ ድርጅቷ ስኬት ማስረጃ ሆኖ ተመዘዘ።

ሙሉ ፍቅሯ ለመንግስት ሆነ። እሷም የመንግስት ሆነች። አንዳንዴ፣ የመንግስት ንብረት ቤቴ ሸሽጌ ያስቀመጥኩ ይመስለኛል። እና ድንገት አሰሳ ቢደረግ፣ «የህዝብን ሀብት ቤቱ ሸሽጎ በማስቀመጥ» ብለው ከርቸሌ የሚወረውሩኝ።

ዘር እንተካ ስላት፣ ለድርጅቷ ተተኪ ስላማፍራት ትቆዝማለች። ስለራሳችን እናስብ ስላት፣ «የሀገር ጉዳይ ይቅደም፣ የድርጅቴ ኋላፊነት አለብኝ»ብላ ውይይታችንን ትዘጋዋለች።

መንገስትን ተግቶ የሚጠላ ወንድም አላት። ቤታችን ይመጣል። ሞባይሉ ላይ እንዳፈጠጠ፣
«በዚህ ከተማ ድርጅትሽ ይሄን ያህል ሰው ገደለ። አየሽ እነዚህ ሰዎች የሚሰሩትን» እያለ በጩኸት ይጠይቃታል።
«ለብዙሃኑ ደህንነት ሲባል ጥቂቶች መሰዋታቸው ያለ ነው» ትላለች። እንዲህ ስትል በመገረም አያያለሁ። ሰውነት እንዲህ በአንድ ድርጅት ፍቅር ቀለሙ የሚለቅ አይመስለኝም ነበር።
የማን ሚስት ናት እላለሁ? የመንግስት ናት የኔ? ማን ነው ከማን የነጠቀው? ከኔ ተጋብታ ከመንግስት የምትወሽም ወስላታም ትመስለኛለች።

ፓለቲካ አልወድም። ሚስቴን እወዳታለሁ። ድርጅት ከመሆኗ በፊት ፍቅሬ ነበረች። ሚስቴ ነበረች። ፓለቲካ አሳስቆ ከወሰዳት በኋላ ገላዋ እንደ ቀድሞ አይሞቅም። ሃሳቧ አብሮኝ የለም።
አይገባኝም! ከባሏ በመልካም ማደር ያልቻላች ሚስት፣ ስለ መልካም አስተዳደር ብታወራ ልክ ናት? እወዳታለሁ፤ግን እቅፌ ውስጥ ሆና ድርጅቷ ወስዷቷል።

ሚስቴ የባሏ ዘውድ ናት ይላሉ። የኔ ሚስት ዘውድነቷ ለባለ ዘውዶቹ ነው። ሁለት ዘውድ የደፋ መንግስት ይሄው። ብዙ ታገስኳት።
ፍቅራችን እየደፈረሰ፣ የሕዝቡን ሰላም ስላደፈረሱ ሃይሎች ታወራኛለች።
«በደርግ እኮ፣ ወጣቶች ተገድለው አልቀው አልቀው ሀገሩ፣ ‘የአረጋውያን መጠለያ’ ሊሆን ትንሽ ሲቀረው ነው ድርጅታችን ሀገሪቷን የታደጋት ትለኛለች።
«ወጣቱን አደንዝዞ መግደል፣ በጥይት ከመግደል ያነሰ ጥፋተኝነት ነው? »ብዬ አልጠይቃትም።
«ዛሬ ወጣቱ ቢቃወም፣ ሰዎችሽ አቅፈው የሚያበረታቱት ይመስልሻል? ፝ አልላትም።
አንደኛ፣ ፓለቲካ አልወድም።
ሁለተኛ ሚስቴ ናት።
ሶስተኛ፣ ፓለቲከኛ ሚስቴን እየወደድኩ መቀጠል እችላለሁ ወይ?

ፓለቲካ ውስጥ ፍቅር የለም። ፍቅር የሌለበት ሀገር ይጨንቀኛል። ይሄ ሀገር ለሚስቴ ፍቅሯ ሆኗል።

«እንፋታ!!!!! » አልኳት።
«ምን? » አለች። ደገምኩላት።
«ጥሩ፣ ጥያቄው ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ በመነጋገር ልንፈታው እንችላለን። የሚመላከታቸው አካላት ባሉበት መነጋገሩ የተሻለ ይመስኛል። ለምሳሌ፣ ቤተሰቦችህ እና ቤተሰቦቼ! ለጊዜው ግን የድርጅት ስራ ማስቀደም አለብኝ። ለሁለት ሳምንት ስልጠና ከከተማ ስለምወጣ ስመለስ በሰላማዊ መንገድ እንፈታዋለን»
«እንፈታዋለን ነው እንፋታለን?»
«እሱ በውይይት የሚሆን ነው። በውይይት የማያምን ሰው፣ ጠባብ አመለካከት ያለበት ነው። እንዳንተ የአመለካከት ችግር ያለባቸው ሰዎች ማፍረስን ቀላል ያደርጉታል። ስራቸው ትዳር እና ሀገር ማፍረስ ነው»
«ብዙ ታግሼሻለሁ፣ በቃኝ»
«ይሄ ነዋ ችግሩ። የወዲፊቱ ጊዜ ከኔ ጋር ብሩህ ነው። ያ ደሞ በውይይት፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይፈታል። ጥያቄህ ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ አከብረዋለሁ። ለማንኛውም፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ!»
«እሺ» አልኩ። እሷና ድርጅቷ መወያየት የሚሉት የራሳቸውን ሃሳብ ማሸነፍ እንደሆነ አውቃለሁ።
ሚስቴን እወዳታለሁ። ፓለቲካ አልወድም። መውደድ እና አለመውደድ ሲቀላቀሉ የቱ ያመዝናል? ብወዳትም መለየት ይሻላል። ሁለት ሳምንት …ቀላል ናት። እጠብቃታለሁ።

አቤቱ ወደ ፈተና ዳግም አታግባን፣ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ!!
አሜን!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...