Tidarfelagi.com

“መዶሻህን ብላው”

ወዳጄ (Netsanet) እንደነገረኝ ሰውዬው እሁድ ቀን እቤቱ ጋደም ብድግ ሲል ይቆይና ግድግዳው ላይ የተነቀለች ሚስማር አይቶ ሊመታት ቢፈልግ መዶሻ ያጣል። ጎረቤቱን ሊጠይቀው በሩጋ ከደረሰ በኋላ «ተኝቶ ቢሆንስ» ብሎ ይመለሳል። እቤቱ ከመድረሱ በፊት ግን «እህ የተኛ እንደሆነስ? መዶሻውን ከሰጠኝ በኋላ ተመልሶ ይተኛላ!» ብሎ ተመልሶ ሄደ።

አሁንም በሩጋ ሲደርስ «ሰንበት ነው። በሰንበት እንዴት ትሰራለህ ቢለኝስ?» ብሎ ያስብና ወደቤቱ ይመለሳል። እቤቱ ቁጭ ብሎ ሲያስበው «እንዴ ምንአገባው እኔ ለምሰራው ሰንበትስ ፆምስ ቢሆን መዶሻህን ስጠኝ እንጂ ምታልኝ አላልኩት?» ይልና ተመልሶ ወደጎረቤቱ በር ይሄዳል። «እንግዳ ቢኖርበትስ? ከሴት ጋር አልባሌ ነገር እያደረገ ቢሆንስ?» ብሎ ያስብና ደግሞ ይመለሳል። እንዲህ አንዱን ምክንያት ሲያስብ ሲመለስ ውድቅ ሲያደርግ ደግሞ ሲሄድ ቀኑ ተጋመሰ። መጨረሻ ላይ ጎረቤቱጋ ሄዶ አንኳኳና ሲከፍትለት ምን አለው?
«እንደውም መዶሻህን ብላው እሺ።»🤣🤣🤣🤣
እማጅኑልኝ ሰውየው ባልተሳተፈበት ክርክር ብቻውን ተሟግቶ፣ ከዛ በሰውየው ተናዶ፣ ብቻውን ፀቡን ሲቋጨው።

ከባልተቤትየው ጋር የተጋባን ሰሞን የሆነ ቀን የሚደብረኝን ነገር ተናገረ። በሰዓቱ ትኩረት ያልሰጠሁት ለመምሰል ዝም ብዬ አለፍኩት። በባህሪዬ የቅርቤ የሆነ ሰው አንዴ ሁለቴም ሶስቴም አጠፋ ብዬ የምናገር ሰውም አይደለሁም። በጣም ብዙ አልፌ መቻያዬ ሲሞላ ነው የምፈነዳው! (የማልወደው ባህሪዬ ነው) እናላችሁ ግን ይሄ ከነከነኝ። ብዙም ሳይቆይ እሱ ለስራ ሌላ ሀገር ሄደ። አጅሪቷ ነገር ሳኝክ ሳመነዥክ ስፈትል ስዳውር ሰንብቼ ሲመጣ ተቀባብዬ ጠበቅኩት። ተብላልቶ ተብላልቶ ነገርየው እሱ ከተናገረው በ200% አብዷልኮ እኔ ጭንቅላት ውስጥ።🤷🏽‍♀️🤷🏽‍♀️
«መነጋገር ያለብን ጉዳይ አለ» ብዬ የነገር ጉልቻዬን ስጥድ ተቀመጠልኝ። ያው ቱግ ቱግ ላለማለት ለዘብተኛ ቃል መርጬ እንጂ «መዶሻህን ብላው» ስቴጅ ላይኮ ደርሻለሁ።🤣🤣
«ባለፈው በጫወታ እንዲህ ያልከው ነገር ጥሩ ስሜት አልሰጠኝም።»
«መቼ ነው እንደዛ ያልኩት? ማለቴ ትዝ አይለኝምኮ! ደግሞ በጨዋታ መሃል ከሆነ ያልኩት ለምን በቁም ነገር ወሰድሽው? ጨዋታ ነው ብለሽ አታልፊውም ነበር? ደስ ካላለሽ እዛው አትናገሪም እስከዛሬ እንዴት ነው ጭንቅላትሽ ውስጥ ያስቀመጥሽው?» ብሎ በስንት እርሾና ፓውደር ኩፍ ያደረግኩትን ነገር እፍፍፍ ብሎ ብን አላደረገብኝም? 🙆🏻‍♀️🙆🏻‍♀️🙆🏻‍♀️🙆🏻‍♀️
«እህህ በቃኣ ሲቆይ ነው የከነከነኝ! »
«ይቅርታ እንደዛ ስለተሰማሽ እኔ ጭራሽ አላስታውስም!» ብሎ ስንት ሳምንት ሆ! ምናምን ብዬ የበላሁትን ነገር ኩምሽሽ!!

በኢንቦክስ አንዱ ጭራሽ ያለዛሬም ስሙን ያላየሁት «ጉረኛ ስለሆንሽ ታስጠዪኛለሽ» ብሎኝ ነው ያስታወስኩት!! ደግሞኮ በጣም ትሁት መሆኔ ነው ስልሞሰሞስ «በአካል ተገናኝተን እንተዋወቅ ይሆን?» እለዋለሁ። የመለሰልኝ ይቅርባችሁ ብቻ ያው “መዶሻሽን ብዪው !” ነው ነገሩ🤣🤣🤣🤣🤣🤣🤣🤣🤣

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ!!❤️❤️❤️❤️

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...