Tidarfelagi.com

መቶ ብር ከየት ወዴት?

ትናንት ኣመሻሽ ላይ፤ ከYohanes Molla ጋር ተቀጣጥረን ተገናኘን ፡፡ካልዲስ ገብተን እኔ ኣንድ ፍንጃል ቡና ሳዝዝ ፤ ዮሀንስ ሲያቀብጠው ኣንድ ቡና እና የባራክ ኦባማን ጆሮ የሚያህል ቦምቦሊኖ ኣዘዘ፡፡ በመጨረሻ ኣስተናጋጂቱ የእዳችንን ደረሰኝ ኣምጥታ ጠረጴዛው መሀል ላይ ኣኖረችው ፡፡እሱ እኔ እስክከፍል ሲጠብቅ እኔ እሱ ይከፍላል ብየ ስጠብቅ ካብ ለካብ እየተያየን በጣም እረጅም ጊዜ ተጎለትን ፡፡
በመካከሉ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ርእሰ ጉዳይ ጨርሰን ” ፌንጣ ስንት እግር ኣላት? ስድስት ነው ኣራት?” በሚል ጉንጭ ኣልፋ ክርክር ተጠመድን ፡፡ ወሬ ኣልቆብን ካጠገባችን ከተቀመጡ ተስተናጋጆች ወሬ እየተበደርን ስናወራ ቆየን፡፡ በመጨረሻ ካፌው ጭርር ብሎ ኣስተናጋጆች እንድንወጣላቸው እግራችን ስር መጥረጊያ ኣስገብተው ይጠርጉ ጀመር፡፡
ድንገት በብሄረሰቦች ላይ የሚነገረው ቀልድ እንዴት ኢ-ፍትሃዊነት እንደሆነ ኣንስቼ መከራከር ጀመርሁ፡፡በተለይም ጉራጌን እንደ ቋጣሪ ማየት መሰረት የለሽ መሆኑን ፤ እኔ የማውቃቸው ጉራጌ ጓደኞቼ ባጠቃላይ በጣም ለጋሶችና ኣባ መስጠቶች መሆናቸውን በመጥቀስ በስሜት ነድጄ ጠረጴዛ እየደበደብኩ ተናገርኩ፡፡ የሚቻል ከሆነ ጉራጌን እንደ ንፉግ የሚስሉ ኮሜድያን ባስቸኳይ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ኣሳሰብኩ፡፡
ወድያው ዮሀንስ ሞላ የኣባባሌን እውነተኝነት በተግባር ለማረጋገጥ ከኪሱ መቶ ብር መዥርጦ ሂሳቡን ዘጋው፡፡
2
ኣባቴ ከቅዱስ መጽሀፍ ኣንድ ምእራፍ ሳያነብ እንደማይተኛ እኔ ደግሞ ከ“ ፍቅር እስከመቃብር” ኣንድ ኣንቀጽ ሳላነብ እንቅልፍ ኣይወስደኝም፡፡ከዮሀንስ ጋር ከተሰነባበትን በኋላ እቤቴ ገብቼ “ኣዲስ ኣበባ”የሚለውን ምእራፍ ገለጥሁ፡፡
ብዙዎቻችሁ እንደምታስታውሱት ፤ በዛብህ ቦጋለ፤ ሰብለን ለመጥለፍ ያደረገው ሙከራ ከከሸፈበት በኋላ ከፊታውራሪ መሸሻ ቁጣ ሸሽቶ ኣዲስ ኣበባ ይገባል፡፡ እናም ሱልሉልታ ኣካባቢ ከሲራራ ነጋዴዎች ጋር ይወዳጃል፡፡ኣንድ ቀን ከኒህ ወዳጆቹ ኣንዱ ከሆኑት ነጋድራስ ሁነኛው ጋር እያወራ ነው፡፡
“ኣዲስ ኣበባ የማውቀው ሰው የለኝም፡፡ ምን ማድረግ የሚሻለኝ ይመስልዎታል፡፡እስኪ ይምከሩኝ ” ኣለ በዛብህ፡፡
“ ገንዘብ ካለህ ኣትቸገርም፡፡ገንዘብም የምታውቀው ሰውም ከሌለህ ነው ችግሩ ! እስቲ ለማንኛውም ከኛ ጋር ጉለሌ ስፈርና ስራ እስክታገኝ የምትቆይበትን ስፍራ እንፈልጋለን”ኣሉ ነጋድራስ፡፡
“ገንዘብስ ከእናንተ ጋር ያገጣጠሙኝ ወዳጆች ኣዋጥተው የሰጡኝ ኣንድ መቶ ብር ኣለኝ“
” ኣንድ መቶ ብር ካለህማ ፤ማለፍያ ቤት ተከራይተህ ፤ማለፍያ ቀላቢ ቀጥረህ ብዙ ጊዜ ያቆይሃል…ገንዘብህ እንዳይጠፋብህ መጠንቀቅ ነው”
(ፍቅር እስከመቃብር፤ ገጽ 434)
ኣጀብ ነው!! ኣንድ ኢትዮጵያዊ በመቶ ብር ኣሪፍ ቤት ተከራይቶ ምግብ ኣብሳይ ሰራተኛ ቀጥሮ ለብዙ ጊዜ መኖር የሚችልበት ዘመን መኖሩን ሳስብ፤ በጊዜ መኪና ወደ ድሮ መመረሽ ያምረኛል ፡፡ኢትዮጵያ ከየት ወዴት የሚለውን ለማጥናት ኣቋራጩ መንገድ “መቶ ብር ከየት” ወዴት የሚለውን ማጥናት ኣይመስላችሁም?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • wonde wondey commented on June 7, 2020 Reply

    አንተ የፍቅር እስከ መቃብሩን ጊዜ ትመኛለህ; እኔ አስር አመት ብመለስ በቂዬ ነዉ:: አይ የአሁን መቶ ብር ከአስር አመት በፊት የነበረን አስር ብር አያክልም::

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...