Tidarfelagi.com

መረቅ

(ስሜቴን ለመግለፅ እንጂ፣ እንዳይንዛዛ( እንዳልንዛዛ) ሁለት ወይ ሶስት ጊዜ ቆራርጬ ለመፖሰት እገደዳለሁ)

  1. ክብነት(ሙሉዕነት) በመረቅ

የመፅሓፉ ሀይለኛ ጉልበት እዚህ ጋር አለ።አዳም የህይወትን ክብነት ለማሳየት ገፀባህሪያቱንና ታሪክን በመጠቀም እንጀራውን ይጋግራል።

ሀ. በገፀባህሪቱ፡―

መፅሐፉ አራት ዋና ገፀባህሪያት አሉት።አራት(ምናልባትም “ዐራት”) የምልዑነት መገለጫ ነው። በ “አ ” ከሚፃፍ ይልቅ በ “ዐ ” ቢፃፍ የተሻለ ክብነትንአይገልፅም ብላችሁ ነው?

ምድር ዐራት አቅጣጫዎች አሏት።
ለአላዘር ቴቢ አለችው (ለምስራቅ ምዕራብ አለው)
ለእዝራ ማክዳ አለችው (ለሰሜን ደበብ)

ከነዚህ ገፀባህሪያት አንዱን ብታጎድሉ ጎዶሎ መፅሐፍና ጎዶሎ ህይወት ነው የምታገኙት።
አይደለም የገፀባህሪያቱ መጉደል፣ መቀየር ራሱ ብዙ የሚሰብረው ነገር አለ። ምክንያቱም፣ የመፅሐፉ አንድ ማዕዘን የሆነው “አንፃራዊነት” መሬት የነካው በዐራቱ ገፀባህሪያት ነው።

አዳም በዚህ መንገድ ፍፁም እውነት የሚባል ነገር እንደሌለ በጃዙር ይነግረናል። አላዘር በአላዘር ዐይን ቴቢን ሲነግረን፣ ልክነቱን እንቀበላለን። ቴቢ በራሷ ዐይን ሯሷን ስታሳየን እሷም የራሷ እውነት እንዳላት እንረዳለን። ካላቸው የህይወት ልምድ አንፃር፣ አላዘር ለቴቢ ልፍስፍስ ቢሆንባት፤ ቴቢ ለአላዘር በማያገባት የምትገባ ሰሞነኛ እውር ስሜት የሚጋልባት ድንብር ብትሆንበት ሁለቱም የየራሳቸው እውነት አላቸው (ወይም ማንም እውነት የለውም)
All they are talking abt is their life experience. ማንም ሊያስብ የሚችለው በህይወት ልምዱ ልክ፣ በአስተሳሰቡ ጋት መጠን አይደለምንእ?

በርግጥ ይህ ያተራረክ መንገድ ባማረኛ ውስጥ የመጀመሪያው አይደለም፤ በማውቀው መጠን ሶስተኛው ነው።
የመጀመሪያው፣ የወርቅዬ ደምሴ “የፍቅር ጀርባው ” ሲሆን
ሁለተኛው፣ የእንዳለጌታ “ደርሶ መልስ ” ነው።

ለ. ታሪካዊ ክብነት

ይህ በልቦለዱ ውስጥ ያሉት ታሪኮች ክባዊ ወይም ዙሪያ ገጠም ባህሪን ያሳያል። የሕይወት ክብነት ፍፁም ላይሆን ይችላል። ግን ወደድንም ጠላን በመኖር ዱካ የሚሰመሩ ቀጫጭንዞሮ ገጠም መስመሮች አሏት። ሰነፎች ይህንን አጋጣሚ ይሉታል።

መረቅ እኚህ ዓይነት ክብነቶችን ይዟል። ያንዱ የህይወት መረቅ ተንዠርጎ ከሌላው ጋር ይገጥማል _ ይህንን ገፀባህሪያቱም አይገነዘቡትም ፤ የህይወት እውነት!

ለምሳሌ…
በረከት ነጋሢ እና አላዘር
(አንድ ሴትና አንድ አውሮፕላን ተሳፍረዋል። ሁለተኛውን እንጂ የመጀመሪያውን ሁለቱም አያውቁትም)
አላዘር በረከት ሳያውቀው ደብሮታል። የሚቆጭበትን ድንግልና የወሰደው እሱ እንደሆነ ቢያውቅ ምናባቱ ሊሆን ነበር።

በአያቱ ቤት የታሰረው አላዘር፣ አላዘር የታሰረበት ክፍል የታሰረችው ተባረኪ… የአላዘርን ፅሁፍ ተዘቅዝቃ ስታይ( አላዘርን እንዳልሆነው አድርጋ ዘቅዝቃ እንደምታየው) … ብዙ ዞሮ ገጠም መስመሮች… አንድ የህይወት እንጀራ ላይ…
የቱ ጋር እንደሚጀምር የማይታወቅ መስመር፣ የቱ ጋር እንደሚቆም የማይታወቅ፤ ምናልባትም የማይቆም… የአዳም እንጀራ!

  1. ቅርፅ በመረቅ ውስጥ

አዳም ባንድ ኢንተርቪው ላይ “ቅርፅና ይዘት አይነጣጠሉም ” የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።
ቅርፅ የውበት ጉዳይ ነው። የተፃፈውን ሳይሆን፣ የተፃፈበትን መንገድ ለማየት ይንጠራራል። ምን ተናገርክ ሳይሆን እንዴት ተናገርክ የሚለው ቀልቡን ይገዛዋል።

አዳም ለቅርፅ ተጨናቂ ነው። እውነት አለው፣ ምክንያቱም ይዘት በቅርፅ ይሰራል።
ካህሊል ጅብራን እነወዲህ ይላል፣
“We live only to discover beauty. All else is a form of waiting “(Sand And foam)

ካህሊል በዚህ አባባሉ የአዳም ነብስ አይገልጠውም?
መረቅንስ?
ውበት በመረቅ ውስጥ እንዴት ተሰርቷል?

እዚህ ጋር እልባት እናበጅና ቆየት ብለን እንመለስ
ማለትም…

**************************************************** ክፍል ሁለት ************************************************

አዳም ሁሌም በስራዎቹ ውስጥ ውበት ለመፍጠር ሲጨነቅ ይታያል። ከታሪኩ በበለጠ፣ ውበት የሚያስጨነቀው ይመስላል። ቡዙዎች የተቋጨ ታሪክ ማንበብ ለምደው አዳም ጋር ሲመጡ መፅሐፎቹ የሚበርዱባቸው (የሚበርዷቸው) ለዚህ ይመስለኛል።

እርግጥ ነው እንዳልነው፣ ይዘት ከቅርፅ ይፈለቀቃል። ለዚህ ብርሃኑ ገበየሁ፣ በ “የአማርኛ ሥነ ግጥም መፅሐፉ ” የደበበ ሰይፉን «በቀበሮ ጉድጓድ» የተሰኘ ግጥም የተነተነበትን መንገድ ማየት ደግ ነው።

የሚጮህ የቅርፅ ውበት አለ መረቅ ውስጥ!
አንባቢውን የሚያሰጥም የቃላት ምትሃት፣ የዐ. ነገር አስማት… የሃረግ አዚም…
ማነው እንዲህ አማርኛን ከባድ ቀጠሮ እንዳለባት ሴት አቆንጅቶ የሚያቀርባት ማነው? አዳም አይደለምን?

ቴቢ አላዘር ኳስ ተጫውቶ ሲመጣ የተሰማት ስሜት እንዴት ነበር የተገለፀው?
ማነው በዛ መሰል አገላለፅ የማይነቃነቅ…
ማነው የቴቢ አንጀት መንሰፍሰፍ የማያንሰፈስፈው…
(ያላነበባችሁት ካላችሁ፣ ይህን ክፍል አንብባችሁ ከቤት አትውጡ። ማፍቀርን የሚያስመኝ አገላለፁ ከውስጣችሁ ሳይደበዝዝ ወጣችሁ ከጎረቤት ፉንጋ ላይ እንዳትወድቁ)

በጉርሻ መልክ (በግጥም ቅርፅ የተፃፉ ዐረፍተ ነገሮች ውበት)፣ ፍጡር ቃላት፣ የአገላለፅና የቃላት ሃብት (ወደ ግዕዝም ጎራ እያለ) ፣ የቃላቱ አቻዊነት (ዝርዋዊ ዜማ እንበለው ይሆን?) …የመረቅን ውበት ያደመቁ ቀለሞች ናቸው።
ይህ ማለት ግን ፍፁም ውበት አለ ማለት አይደለም። ዋጋ አልባ የበዙ አገላለፆች፣ እንደ ሌሎቹ መፅሐፎች እዚህም አሉ።

3 . ይዘት

አንድ ልቦለድ ከአንድ በላይ ይዘት ሊኖረው ይችላል። ይዘቶቹ እኩል አቅም ያላቸው ወይም የሚበላለጡ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ወጥ ጭብጥ ላይ መንተራስ ይደላ ይሆናል እንጂ፣ የማሰስ ስንፍና መሆኑ አይካድም።

የመረቅ ይዘት ምንድነው? የዛን ትውልድ ቅሪት; (መረቅ) ማሳያት፣ መለልታውን ጨርሶ የሄደውን ትውልድ መረቅ ማስነበብ?

የመረቅ ጉንጉናዊ ትረካዎችስ ከቅርፅ ባለፈ እንደይዘት አይታዪም? ቅርፅም ይዘትም ሆነው እንዳይታዪ ማን ህከለክላቸዋል?

ፍዝ ተመልካችነት የፈጠረው፣ መንጋነት የልቦለዱ አንዱ ይዘት ነው ብንልስ ማስረጃ ከመፅሐፉ መምዘዝ ይሳነናል? እንሞክርማ

እዝራ እንዲህ ይለናል፣
“እኛ አትኩረን የገጠመንን እናወራለን እንጂ አናጠናም። አዕምሯችን ሰነፍ ሰለሆነ ከሌላ ሰው ምላስ ነው እውነትን የምንቀበለው… ” (ገፅ፣ 513)

እዝራ አጥብቆ ተመልካች ነው። የተነገረውን ሳይሆን የመረመረውን ያምናል። በዚህ ጎኑ ምኑም የቄስ ልጅ አይመስልም። ከልጅነቱ በእምነት ያደገበትን መፅሐፍ ያጠይቃል።

አዳም ይህን የፍዝ ተመልካችነት ብስጭቱን፣ የቴቢና የማክዳን ዐይን በመሳል ሊወጣ ሲሞክር እናየዋለን(ይህ ህፀፅ ቢሆንም)

መንጋነትን ይደበድባል!

የመንጋው ቡድን ወካይ ተደርጋ የቀረበችው ቴቢ በማነው ያልተመታችው(
ከፊት አላዘር፣ ከኋላ እዝራ፣ ከወዲያ ሚሎስ፣ የማክድ ወፍራም ግዴለሽነትና አሁን ትዝ የማይልኝ ንግግር)

የዛን ዘመን አስመሳይነት እንደምን ኮረኮመው፣ ንባብ አልባው፣ ስሜት ጀልባው የሆነውን ሕዝባችንን የጥቂት ገፅ እድሜ ባለው ሚሎስ የተባለ ገፀባህሪ እንዴት እንዴት ነው ያገባለት (ኦ ሚሎስ፣ እንዳንተ በጥቂት ገፅ የገዘፈብኝ ገፀባህሪ ማነው አንተ ራስህ አይደለህምን?)

ከማስታወሻዬ ልጥቀስ፣

” እዛ ዐይነት ድርጅት ውስጥ ገብተው የሚሳተፉ ግለሰቦች ከራሳቸው ልምድ የወጣ ሃሳብና እምነት የላቸውም። አንተንም እሷንም የሚያሸፍታችሁ ምክንያት የለም። ሰበቡ ቅዱስ እንዲመስል “ለተጨቆኑት ነው የቆምነው ” ይሉሃል። ያን የሌሎችን የመጨቆን ታሪክ የሚያውቁበት የህይወት ልምድ የላቸውም…” (162)

የተራራቀ የትውልድ ልብ

ተባረኪ እናቷን አትሰማም። አላዘር አባቱን ይንቃል። እናቱን ይወዳታል፣ ግን ልቡ ከነብሷ አይናበብም። ማክዳ ከቤተሰቦቻ አትገጥምም (አስተዳደጓም አይጋብዛትም) ፣ እዝራ ያባቱ ልጅ አይደለም። የሚንቁት አባቱ ብቻ ሳይሆኑ እሱም አባቱን አይንቅም ለማለት አይቻልም። እኚ ትንንሽ ስንጥቆች እንድናያቸው የተቀመጡልት ጥቂት ቦታ ቢሆንም፣ ሰፍተው የፈጠሩት ገደል እግራችን ስር ነው።

ወሬና በቀል

ተባረኪ፣ ማክዳና እዝራ ወሬ እንደ ምግብ የሚያሰናዳ፣ የሚጎራረስ ሕዝብ ተጠቂዎች ናቸው። እዝራ እና ማክዳ የሚታይ የበቀል ስሜት ያበቅላሉ። ተባረኪ በሞራል ትደሸልቃለች።
የዛ ትውልድ መገዳደል የዚህ ዐይነት የበቀል ስር አለው እያለን ይሆን? በነፃነት ስም በቀል። በተጨቁነሃል የተጠቀለለች ቂም፣ በመሳም ስም መንከስ? በታገልንህ ስም ልጅህን ገደልንልህ?

ችግር!

የተጨቆኑ ገፀባህሪያት!
አዳም የተሳፈረባቸው አተያይና አመለካከቶች!
ነፃነታቸው በጣልቃ ገብነት ቢላ የተገዘገዘባቸው ስብዕናዎች።

ሁሉም ተራኪ ገፀባህሪያት፣
ተመሳሳይ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር፣ ተመሳሳይ ሃብተ ቃላት፣ ተቀራራቢ ጥልቅ ምልከታ አላቸው ( ባይኖራቸውም ተጭኖባቸዋል)

ምን ጠንካራ ገፀባህሪያት ቢሆኑም፣ የፈረሰ ነፃነታቸውን አያቆመውም።

መዓት የአዳም አስማቶች (በነገራችሁ ላይ አስማት ማለት የ”ስም “ብዜት ነው) ቢኖሩበትም ይህን አይሽሩትም።
እያልን
እያልን
እያልን
ብንወርድ ጊዜና ጉልበት አይበቃንም። ጫማ ከመጨረስ ውጪስ ስንቱን ከፍታ እንወጣዋለን።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...