Tidarfelagi.com

ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት

ጥንታውያን የአብነት ሊቃውንት ‹ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት ነው› ይላሉ። መታመሙን ላወቀ፣ መድኃኒቱን ለፈለገ፣ መድኃኒቱንም በትክክል ለወሰደ፣ ወስዶም ለዳነ ሰው ሕመም ለትምህርት ይሆነዋል። ሦስት ነገር ይማርበታልና። አንድም ዳግመኛ እንዳይዘው ጥንቃቄን፣ አንድም ቢይዘው ሊትርፍ የሚችልበትን መፍትሔን፣ አንድም ደግሞ ለሌላው የሚመክረው ልምድን ያተርፋል። ያለበለዚያ ግን የሕመም መጨረሻው ሞት ነውና ላንዱ ትምህርት የሆነው በሽታ ሌላውን ይገድለዋል።

አሁን ታመናል። ሕዝቡ የሚያነሣው ጥያቄ፣ መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ፣ የሃይማኖት ‹አባቶች› የሚያወጡት መግለጫ፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ከግራ ከቀኝ የሚያናፍሰው ነገር፣ ደጋፊና ተቃዋሚው ከወዲህ ወዲያ የሚሠናዘረው ዱላ ሕመም ላይ መሆናችንን የሚገልጥ ነው። አሁን የሚያስፈልገን መታመሙን የሚያምን፣ መድኃኒቱን የሚፈልግና መድኃኒቱንም በተገቢው ሁኔታ የሚወስድ መንግሥትና ሕዝብ ነው።

መጀመሪያ መተማመን የሚያስፈልገው ‹ችግር አለ ወይ?› የሚለው ላይ ነው። አዎን ችግር አለ። እየሆኑ ያሉት ነገሮች የሚነግሩን ችግር መኖሩን ነው። ችግሩ እነ እንትና ያነሣሡት፣ የቀሰቀሱት፣ ያደራጁት ምናምን ማለታችን ችግር መኖሩን አያስቀረውም። በሀገራችን ‹የጥያቄ ክፉ የለውም፤ የመልስ እንጂ› ይባላል። የጥቂቶች ወይም የብዙዎች፣ የእነ አንቶኔ ወይም የነ እንትና መሆኑ ጥያቄውን አይለውጠውም። ለውጥ የሚያመጣው ለጥያቄው ተገቢውን መልስ መስጠቱ ነው። ‹በቅርቡ ያልመለሰ እረኛ በሩቁ ሲባዝን ይውላል› እንደሚባለው በየጊዜው ተገቢ መልስ ሳይሰጣቸው፣ ወይም ደግሞ ይዋሉ ይደሩ እየተባሉ፤ ያለበለዚያም የተፈቱ የመሰሉ ነገሮች እንደገና እያመረቀዙ መሆናቸው እየታየ ነው።

በሽታው ምንድን ነው? ይኼ የምር የሆነ ውይይትና መግባባት የሚጠይቅ ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ለፕሮፓጋንዳ ወይም ለጊዜያዊ ድል ወይም የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ወይም ለዶክመንተሪ ፊልም ወይም ደግሞ ለቁጣ ማብረጃ ከሚሆን ወይይት፣ መግለጫና ንግግር ያለፈ ሁሉን ዐቀፍ፣ ለመፍትሔ ብቻ የቆመና በእውነት የሚደረግን ውይይት የሚጠይቅ። አንድ ዓይነት ሰዎች ተሰብስበው አንድ ዓይነት ንግግር የሚናገሩበት ሳይሆን ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን፣ ወገኖችን፣ አቋሞችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚወክሉ ወገኖች ለአንዲት ሀገር ሲባል ሁሉን ዐቀፍ፣ ግን የምር የሆነ፣ ምናልባትም አንዳንዶቻችንን ሊመረን የሚችል መድኀኒት የሚፈልጉበት ውይይት ነው። በተለመደው መንገድ መጓዛችንን ትተን አዲስ መድኃኒት በአዲስ መንገድ እንፈልግ። በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ሞኝ ብቻ ነውና።

ከያቅጣጫው የሚሰጡ መግለጫዎች ሆድ ለባሰው ማጭድ የሚያውሱ፣ ከሚያረጋጉ ይልቅ የሚያናድዱ፣ ከሚያስታግሡ ይልቅ የሚያባብሱ፣ ከሚመክሩ ይልቅ የሚያነዝሩ ናቸው። ራሳቸው ችግር ናቸው እንጂ ችግር የሚፈቱ አይደሉም። ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት አባቶች እንኳን የሚናገሩት ነገር ሃይማኖት ሃይማኖት የሚል አይደለም።

አሁን የሚታየው የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ነው። ማዶ ያሉትን አካላት የችግሩ መነሻና መድረሻ ማድረጉ መፍትሔ አያመጣም። እንዲያውም ጥያቄ ይፈጥራል። እዚህ አብረውት ከሚኖሩት የመንግሥት አካላት ይልቅ ማዶ ያሉትን ለምን ሰማ? እነዚያስ እዚህ ገብተው ሕዝብ እስኪቀሰቅሱ ድረስ እንዴት ዐቅም አገኙ? ሰው ውጭ ውጭ የሚያየው ቤቱ ምን ሲሆንበት ነው? መልሶ መላልሶ ችግሩ እዚሁ ነው የሚሆነው። የሚያዋጣው ወደገደለው መግባት ነው። ወደ ችግሩ።

ቀጥሎ የሚነሣው ድግሞ ‹መድኃኒቱስ ምንድን ነው?› የሚለው ነው። ሁሉንም ወገኖች የሚወክለውና ለሀገሪቱ ሁነኛ መድኃኒት ለመፈለግ የሚደረገው የምር ውይይት ነው መድኃኒቱን ሊያመጣው የሚችለው። ከአንድ አቅጣጫ የሚመጣ መድኃኒት የሚያድንበት ጊዜ አብቅቷል። አሁን ሁሉን አግባብቶ ሁሉንም ሊያድን የሚችል መድኃኒት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። በዚህ ሂደት የሚፈራም የሚናቅም መኖር የለበትም። የሚገለል የሚጣልም መኖር የለበትም። መድኃኒት አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልግ እንጂ የሚፈለግ ላይሆን ይችላል። የሚያድን እንጂ የሚወደድ ላይሆን ይችላል። መድኃኒት ፍለጋው ይህንን ያገናዘበ መሆን አለበት። በዚህ ሂደት ልናድናት ቆርጠን መነሣት ያለብን ኢትዮጵያን ነው። ሥርዓቶች፣ ፖሊሲዎች፣ አደረጃጀቶች፣ አወቃቀሮች፣ ሊቀየሩ ይችሉ ይሆናል። ከጠላትነት ወደ ተነጋጋሪነት፣ ከአጥር ወደ ድልድይ፣ ከተጻራሪነት ወደ ተደጋጋፊነት መምጣት ያስፈልግ ይሆናል።
በተበታተነ ሁኔታ በየአካባቢው የሚነዱትን እሳቶች ለማጥፋት ከመሯሯጥ ይልቅ ልብን ሰብሰብ አድርጎ የማያዳግም መፍትሔ መስጠቱ ነው የሚሻለው። በተለይም መንግሥት ይህ ይጠበቅበታል። እየሮጡ መስማት እየሮጡ መርሳትን ያመጣልና ቆም ብሎ ሰምቶ ቆም ብሎ መፍትሔ መስጠት ነው ብልሃቱ።

ኮሶ ሲያሽር እየመረረ ነው። ወይ ሁላችን አናሸንፋለን፤ አለያም ሁላችንም እንሸነፋለን። ወይ ሁላችንም ለሕመሙ ትክክለኛውን መድኃኒት አግኝተን ተምረን እንድናለን፤ አለያም መድኃኒቱን አጥተን ሞተን እናርፋለን። ምርጫው ሁለት ነው። ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት ነውና።
‹ሕመምተኛ ሲሻለው የዳነ ይመስለዋል፤ ሕመምተኛ ሲያቃዠው የሞተ ይመስለዋል› ይባላል። አንድ ነገር በትክክል መነሻው ሳይታወቅ፣ ችግሩም ሳይፈታ፣ በራሱ ጊዜ ጋብ አለ ማለት ሕመሙ ዳነ ማለት አይደለም። ብርድ እንዳገኘ የጉንፋን ቫይረስ ሁኔታው ሲመቻችለት እንደገና ይነሣል። ሕመምተኛው ሲሻለው የዳነ እየመሰለን ከምንተወው በሚገባ ሕመሙን መርምረን ተገቢውን መድኃኒት መስጠቱ የተሻለ ነው። ዛሬ የተነሡት ነገሮች ጋብ ቢሉ እንኳን ባንድ በኩል ጥለውት የሚያልፉት ጠባሳ፣ በሌላ በኩል በትክክል ባለመፈታታቸው ምክንያት በባሰ ሁኔታ ዳግም መነሣታቸው አይቀሬ ነው። እንደምናየው ከሆነ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ለውጦች የሰውን አስተሳሰብ፣ አነዋወር፣ መስተጋብርና አሰላለፍ እየለወጡት ነው። ዛሬ እንደትናንቱ የሆነ የለም። ነገም እንደዛሬ የሚሆን አይገኝም።

በሌላ በኩል ደግሞ ‹በሽተኛ ሲያቃዠው የሞተ ይመስለዋል› እንደተባለው ሀገሪቱ ያለቀላት የሚመስላቸው ወገኖች የሀገሪቱን ታሪክ የማያውቁ ብቻ ናቸው። ከዚህ የባሰ ችግርና መከራ፣ ከዚህ የባሰ ውጥንቅጥና ፈተና አሳልፋ የምትኖር ሀገር ናት። አሳልፋ የማታልፍ ሀገር ናት። በየዘመኑ ከሕመማቸው መማር ያልቻሉ መንግሥታትና ኃይላት አልፈዋል። ኢትዮጵያ ግን አሁንም አለች።

ሕመሙን ከማባባስ፣ በሕመሙ ለማትረፍም ከመሮጥ፣ ሕመሙን በትክክል አክመን ከሕመሙ እኛው ተምረን እንውጣ። ካልሆነ ግን ሞተን ለሌሎች የታሪክ መማሪያ እንሆናለን።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...