Tidarfelagi.com

ልጅነቴ…. ልጅነቴ ዱላና ብሶቴ

(ፓለቲካ ልጅነቴ ውስጥ ስትዞር አገኘኋት)

ከመረገዜ በፊት እናትና አባቴ የባልና ሚስት ሙያቸውን እየሰሩ ሳለ አባቴ እናቴን፤

“እስቲ አንድ ስንወጣ ስንገባ ሰፈሩም እኛም የምንደበድበው ልጅ እንውለድ…?” ያላት ይመስለኛል። እናቴም ከአፉ ቀበል አድርጋ፤
“በአንድ አፍ! እኔም እኮ አንዳንዴ ቤቱ በአስፈሪ ፀጥታ ሲዋጥ ምናለ እየደበደብን የምናስጮኸው ልጅ ቢኖረን ብዬ አስባለሁ።” ያለችው ይመስለኛል። ከዛ የተረገዝኩ። እናትና አባቴም እንደሃሳባቸው ልጅ ወለዱ። አባትና እናቴም ምኞታቸው ስለሰመረላቸው ይመስለኛል “አገኘሁ” ብለው ስም አወጡልኝ። በእርግጥ ልጅ ወለድን ከሚሉ፣ ከበሮ ወለድን ቢሉ ይቀላቸዋል። “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ ሲዪዙት ያደናግር” ቢባልም፣ ኮስማና ነገር ስለነበርኩ እኔን ይዞ የሚደናገር ያለ አልነበረም። ባለሁበት ቦታ ሁሉ ጧ……ቷ……ጯ… የሚሉ የምት ድምፆች መስማት የተሳነው ሰው ካልሆነ በቀር አለመስማት አይቻልም ነበር።

ስወለድ ሰፈሩ ሁሉ፣ “የሚመታ ልጅ ተወልዶላችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ” የተባባለ ይመስለኛል። አራሷ እናቴን ሊጠይቁ የመጡ የሰፈር ሴቶች ሁሉ፣ “አንቺ! እንዴት ያለ ምቱኝ ምቱኝ የሚል ልጅ ነው የወለድሽው ባክሽ! ቱ…ቱ…ቱ… እደግ… ለዱላ ድረስ!” ያሉ ይመስለኛል።

በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በሰፈር ውስጥ ታናሽ ልጅ ነበርኩ። የሰፈራችን አባቶች ውትድርና ቆይተው ተመለሱ ይመስል፣ ሚስቶቻቸውን ያስረገዙት በተመሳሳይ ወቅት ነበር። እኔ ግን የሁሉም ታናሽ ሆኜ ብቻዬን ተወለድኩ። ….እድሜዬ ለዱላ ሲደርስ ያገኘ ሁሉ ይመታኝ ነበር። ሳልመታ የዋልኩበት ቀን ትዝ አይለኝም። የሚመታኝ ቢጠፋ ቢጠፋ እንቅፋት ይመታኛል። እንቅፋት ባይመታኝ ብርድ ይመታኛል። ብርድ አዝኖ ቢያልፈኝ ምች ይመታኛል።

አሁን ያ ካልቾአም፣ ጥፊያም፣ ጡጫአም፣ ቡጢያም ታላቅ ወንድሜ የሕይወት ታሪክህን ተናገር ቢባል፣ እድሜውን የጨረሰው እኔን በመደብደብ መሆኑን ከመናገር ውጪ ምን ታሪ አለኝ ብሎ ሊያወራ ነው።
“ ና እስቲ!” ይለኛል ከጨዋታ ስገባ
“ አቤት…” ሁሌም ለምን “ ና ልምታህ እስቲ ደሞ” እንደማይለኝ ጋራ ይገባኛል።
“ይሄ ምንድን ነው?” ጉልበቴ አካባቢ ትንሽዬ አፈር ወደነካው ልብዴ እየጠቆመ
“ብይ ስጫወት….” አያስጨርሰኝም። ድው… ዷ… ጓ….ቷ…. ጧ…. ጯ…. የሚሉ ድምፆችን መስማት ብቻ ነው! ምንም ምክንያቱ አጠጋቢ ባይሆንም፣ እኔን እስክጠግብ መደብደቡ የዘወትር ስራው ነው። እኔም ፊደል በመቁጠሪያ እድሜዬ ሰንበሬን መቁጠር ስራዬ ሆነ!

በነገራችን ላይ ወንድሜ ፌደራል ፓሊስ ሆኗል። መቼም ሲቪው ላይ፣ “የስራ ልምድ” በሚለው ቦታ ወንድሜን ለረዥም ዓመት ሳላጋው፣ ስቆጋው፣ ሳዳፋው፣ ሳጣፋው፣ ስሰርበው፣ ስሰርረው ኖሬያለሁ እንደሚል አልጠረጥርም። ብቻ በፊት ሳይከፈለው እኔን ይደበድብ የነበረው ወንድሜ ዛሬ እየተከፈለው ሰው ይደበድባል። ምን ዱላውን ባልረሳውም መክሊቱን ፈልጎ በማግኘቱ ወንድሜን አደንቀዋለሁ።

********************************************* ክፍል ሁለት *********************************************

 ልጅነቴ ፓለቲካ ውስጥ ስታፏጭ አገኘኋት

አዎ!…. በልጅነቴ ከማጅራት ገትር በሽታ ይልቅ፣ አንዳቸው ማጅራቴን ብለው እንዳይደፉን ነበር ስጋቴ። ሰው የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ ብሎ ሲለምን፣ የእለት ዱላዬን ስጠኝ ብዬ የለምንኩ ይመስል የዱላ እጥረት ገጥሞኝ አያውቅም። አንዱ መትቶኝ ሳለቅስ
“ምን ሆንኩ?” ይለኛል አባቴ። እነግረዋለሁ።
“ታዲያ ምን ሰፈር ሙሉ ያስጮህሃል…” ብሎ ይጨምርልኛል። “ላለው ይጨመርታል” የሚለው የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል ከማንም ቀድሞ የገባኝ ያኔ ነበር።

በእውነቱ የብዙዎቻችንን አስተዳደግ ላየ፣ የቤተሰቦቻችን ፍላጎት በአጭሩ እንድንቀጭ እንጂ እንድናድግ አይመስልም። በነገራችሁ ላይ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በልጆች አስተዳደግ ላይ የራሳቸው የሆነ ተፅዕኖዎች አሏቸው። ለምሳሌ፣ ድሮ ልጆች አጠፋችሁ ተብለው ሚጥሚጣ ይታጠኑ ነበር። ሚጥሚጣው ሲወደድ ግን በፍልጥም፣ በሽመልም….በተገነው ነገር ይነረቱ ጀመር። ቀጥሎ የሀገሪቱ ደን በመመናመኑ የቻይና ሶኬት እና የገበሬ ጠፍር አለንጋ አማራጮች ሆኑ። አንዳንድ ወላጆች ቴክኖሎጂው አልፈቅድ ብሏቸው እንጂ በኤሌቲሪክ ወንበር ከመቅጣትም የሚመለሱ አይመስሉም።

በቅርቡ ሙሉዓለም የተባለው የሰፈራችን ልጅ ብዙ ቦታ ተገባብጦ ቆሞ አየሁት። ከአንበሳ መንጋ ጋር የተፋለመ ነው የሚመስለው። “ምነው?” ስለው…. “አባቴ መትቶኝ” አለ። “አባቴ መትቶኝ ከሚል፣ አባቴ የመግደል ሙከራ አድርጎብኝ” ቢል የተሻለ ይመስለኛል። አባት የተባሉት ሰው ልጃቸውን የሚመቱት በከባባድ የጦር መሳሪዎች ካልሆነ በቀር እንዴት አንድ ሰው እንዲህ እንክትክቱ ይወጣል? “አፍሪካ ብዙ ህፃናት የሚሞቱበት አህጉር ነው” የሚለውን ስሰማ…. ብዙዎቹ ከቤተሰብ አባል አንዱ ባሳረፈባቸው ዱላ የሚሞቱ ነው ይመስለኛል።

ያቺ ዮዲት (ካደኩ በኋላ እሳቶ የምላት)…. ተጣልታ “አሳዳጊ የበደለሽ” ብለው ከሰደቧት፤
“ማን?….ሂሂሂ…. እኔ?…. ማንንም ጠይቂ ተቆንጥጬ ያደኩ ነኝ” ብሎ የመመለስ ልምድ ነበራት። ተቆንጥጦ ማደግ ጥሩ አስተዳደግ ቢሆን፣ በዳዴ ከሚሄደው ህፃን… በከዘራ እስከሚሄዱት አዛውንት ትጋጭ ነበር?

አደኩ። አድጌ ልጅነቴን ፓለቲካ ውስጥ አገኘኋት። ያቺ ልጅነቴ… ከዱላዋ እስከ ማስፈራሪያዋ፣ ከማስፈራሪያዋ እስከ ጨዋታዋ ፓለቲካ አፋፍ ላይ ቆማ ስታፏጭ አገኘሁዋት። ልጅ ሳለን ቤቶቻችን፣ “አዉዉ….መጣልህ!” እያሉ ያስፈራሩን ነበር። ዛሬ አድገን “ፌደራል መጣልህ!” ሲሉን እንደነብራለን። ልጅ ሳለን “ጆሮ ቆራጩ መጣ” እያሉ አስፈራርተውናል። ኸረ ምን ጆሮ ብቻ “ወሸላ ቆራጩ ሰውዬ መጣ” እያሉም አሳቀውናል። አሁን በዚህ ይቀለዳል? ወንድ ልጅ ያለ እንትኑ ምንድን ነው?…. ይሄው በወሸላ መቆረጥ እያስፈራሩ ወሸላ የሆነ ትውልድ አልፈጠሩም? ወሸሎች ሁላ!! …. አድገን እኚያ ሰውዬ፣ “ጣት እንቆርጣለን” ብለውናል። የሚቆረጠው አካል ተቀየረ እንጂ ልጅነታችን ናት ፓለቲካ ሆና የመጣችው።

ልጅ ሳለሁ ዱላ እፈራ ነበር። ሳድግ፣ አባ ዱላ የተባሉ ፓለቲከኛ ፈራሁ። በተለይ ስማቸውን ከላይ የጠራኋቸው የተከበሩ እና የተፈሩ ሰው አፈጉባዬ የሆኑ ሰሞንማ፣ “አፈጉባኤ” ለሚለው ቃል ፣ “ጠረጴዛን በዱላ በመምታት የሚተዳደር ሰው” የሚል ትርጓሜ ሰጠሁ። ጠረጴዛው የማይናገር እኔ ይመስለኛል…. በሰበብ አስባቡ የሚነረት!
ሰዓት አልቋል…. ጓ! ፣ ወንድሜ እኔን አመሸህ ብሎ… ጓ!
ፀጥታ….ፀጥታ….. ጓ!…ጓጓ! …… አባቴ ሰው ፊት አወራህ ብሎ…. ቷ!!
የሆነ ነገር መፅደቁን ለመንገር…. ጓ! …እናቴ ከመታሽው ትፀድቂያለሽ የተባለች ይመስል… ጧ!!
ስብሰባው አልቋል ለማለት….. ጓ! …. “ሱሪውህን የት ስትንፏቀቅበት አለቀ!” ብላ እህቴ ጯ!! ….አቤት ሲያሳዝነኝ ጠረጴዛው!! ቁጭ እኔን እኮ!!
ምስኪን እኔ!
ምስኪን ጠረጴዛ!!
ምስኪን ፓለቲካ!!!

********************************************* ክፍል ሦስት *********************************************

አንዳንዴ የቤተሰቤን ስም፣ “አሰግድና ቤተሰቡ፣ ዱላው ያልተወሰነ የገራፊዎች ማህበር” ብሎ መጥራት ይዳዳኛል። የገደብ የለሽ ዱላቸው ማስታገሻ ነበርኩ። ችግሩ ቤተሰባዊ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራዊ መሆኑን ሳውቅ ግን እተወዋለሁ። ሕዝባችን ጠብ ይወዳል። ከመሬት ተነስቶ ከፈሱ የሚጣላ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ይመስለኛል። ጠብ በመውደዱ….. በላቸው፣ ደም-መላሽ፣ ሺ መክት፣ ጣሰው፣ አሸብር፣ እርገጤ….. የመሳሰሉ ስሞችን ነብስ ያላወቁ ልጆቹ አንገት ላይ ያንጠለጥላል።

አሁን ማንም ያልደረሰበትን ልጅ፣ ገና ነብስ ሳያውቅ “በላቸው” ብሎ ስም መስጠት “ፀብ ባለበት፣ አለንበት” ከሚል ሥነልቦና በቀር ከየት ይመጣል? እነማንን ነው የሚላቸው? ለምንድነው የሚላቸው?… መልስ የለም! አሁን አሁን ሳስበው ብዙዎቹ ባለስልጣኖቻችን ልጅ ሳሉ የቤት ስማቸው “በላቸው!!” ይመስለኛል። አዎ! ሕዝባችን ጠብ ይወዳል። ለዚሕም ነው አብዛኛው ታሪኩ የጦርነት የሆነው። በሰሜን ከእንትን ሀገር ጋር ይዋጣልን ብሎ ተደባድቦ ሳይጨርስ፣ በደቡብ ለእንትን ሀገር “ትፈልጊኛለሽ ልምጣ?” ብሎ የፍልሚያ መልዕክት ይልካል።

የልጅነታችን ችግር ዱላ ብቻ አልነበረም። በነፃነት ማልቀስም አለመቻሉ ነው። ላባቸው እስኪፈስ ደብድበውን፣ እንባችንን እንዳናፈስ ይከለክሉናል።
“ኡስስ!!… ዋጥ አድርጋት ብያለሁ ዛሬ!” እያሉ ትንፋሽ በሰሙ ቁጥር ይጨምሩልናል። የዱላውን ቁጥር ለመቀነስ እጃችንን አፋችን ላይ ጭነን ዝም ለማለት እንሞክራለን! ይህን ትግል በድል ለማጠናቀቅ መተንፈስን ማቆም ይጠይቃል። ለአፍታ መተንፈስ ስናቆም ደም ስራችን ግትርትር ይላል። አምልጣን ትንሽ የሳግ ድምፅ ከወጣች ያቺ እሳት የተነከረች “ጉማሬ አለንጋ” እላያችን ላይ ታፏጫለች።
…..አድጌ ሕዝብ እጁን አፉ ላይ ጭኖ ሲሄድ አየሁ። “ ኡስስ! ዋ ትንፍሽ ትልና” እየተባለ ትንፋሹን ለማፈን በሚያደርገው ትግል ደም ስሩ ተገታትሮ አየሁ። “የት አባቱ… የእጁን ነው ያገኘው” እላለሁ አንዳንዴ! መልሶ ያሳዝነኛል። ምን በልታ እንዲህ እንዳደገች እንጃ፣ ልጅነታችን ነው አድጋ ፓለቲካ የሆነችው። ገራፊውም ተገራፊውም፣ ከዱላ ባህላችን የተቀዱ ናቸው።

ደርግ “ወፌ ላላ” በሚል የዋህ ስም ግርፊያን ብሔራዊ ሹመት ሰጥቷት ነበር። “ወፌም”፣ “ላላም” ሲሰሟቸው ደስ ይላሉ። ሲኖሯቸው ግን ወፍም ወፍ አትመስል፣ ላላም ላላ ለች አይደለችም። ደርግን ማን ፈጠረው ቢሉ፣ ገራፊው ሕዝባችን ነው መልሱ።

ወዲህ ደግሞ የልጅነት ጨዋታዎቻችን ፓለቲካችን ውስጥ ገብተው ሽር ብትን ሲሉ ታገኟቸዋላችሁ። “አኩኩሉ”ን ተመልከቱ። ልጅ ሳለን የተጫወትናት አኩኩሉ ያቹት የፓለቲካው መድረክ ላይ። እንደልጅነታችን መንግስት ሕዝብን ዓይንህን ጨፍን ይለዋል። ሕዝብ ይቆጥራል። 1 ዓመት፣ 2 ዓመት፣ 3 ዓመት፣ ………………….. 23 ዓመት!!
“ነጋ?” ይጠይቃል ሕዝብ
“አልነጋም!” ይመልሳል መንግስት………… መጨፈኑን ይቀጥላል ሕዝብ! አንዳንዴ ተስፋ ቆርጦ ጨዋታው ሳያልቅ ዓይኑን እንዳይገልጥ ነጋ ይሉታል። ዓይኑን ሲገልጥ ድፍን ጨለማ ውስጥ ይነቃል!

“የታል የነጋው” ሲል ይጠይቃል።
“አሃ… ብርሃን እማ ተደብቃለች፣ ፈልጋት እንጂ…… አኩኩሉ ጨዋታ እኮ ነው” ይሉታል። ብርሃንን መፈለግ ይጀምራል።
“እዛ አካባቢ ነው የተደበቀችው” ብለው እራሳቸው ይጠቁሙታል። ሕዝብ ሞኝ አይደለ? ወደመሩት ይሄዳል። ይሄኔ፣
“ ብርሃን ውጪ! ውጪ! አሁን!…” ይሏታል። ብርሃን ከተደበቀችበት ቱርርርርርር ብላ ወጥታ መሳሚያ ቦታውን ትስምበታለች። ሕዝብ ይሸነፋል።
“ተሸንፈሃል ድገም!” ይሉታል። ሕዝብ ድጋሚ ዓይኑን ይጨፍናል። 4 ዓመት፣ 5 ዓመት….. መቁጠሩን ይቀጥላል።
የጨዋታው ኣላማ ብርሃንን መስጠት አይመስልም። ሕዝብ አኩኩሎሹን እየቆጠረ፣ “በነጋ አልነጋም” ተስፋ አንድ፣ ሁለት… እያለ እንዲቆጥር ማድረግ ነው። ሕዝብ ሁሌ ይቆጥራል…. ሁሌ ይሳምበታል። ሕዝብ፣ ወልዶ መሳምም ቆጥሮ መሳምም አልሆነለትም፡፡
አንድ ዓመት!
ሁለት ዓመት!…. ይቆጥራል

“ነጋ?”

“አልነጋም!!”
እዚህም ልጅነታችን ናት

 

*********************************** ክፍል አራት እና የመጨረሻው*******************************

መታለል እና ማታለልን በልጅነታችን ነው የሰለጠንናት።
“ማህረቤን አያችሁ”፣ “አላየንም ባካችሁ!” እየተባባለን። በልጅነታችን ጨዋታ የነበረች አድጋ ሕይወታችን ሆነች።
ዛሬ፤
“ረሃቤን አያችሁ?”
“አላየንም ባካችሁ”
“እቺ ምንድን ናት?”
“ጥጋብ!” …….. ከመባላችን በፊት ዓይን በዓይን የመወሻሸትን “ሀ ሁ” ያጠናነው ያቺ ያላደገች ልጅነታችን ውስጥ ነው። “ማህረብ” እያየን “ኩስኩስ” ስንል፣ የዛሬን ራበን ስንል “ጠግባችሁ ነው”ን እያነፅን ነበር። ይህን የሚያብል አለ? እሱ በውሸት ከሰለጠኑት አንዱ ነው።

የልጅነታችን ጨዋታዎች በዱላ የበለፀጉ ነበሩ። ቤታችንም አጥንት ከሚያጠነክሩ ምግቦች ቀድሞ፣ አጥንት የሚሰብሩ ዱላዎች ነበር የሚያርፉብን። ሰው በሚያውቀው ነውና የልጅነት ጨዋታዎችን ግድግዳ በዱላ የታጠረ ነበር። እርግጫ ነበር ጨዋታችን፣ ቁንጥጫ ለቁንጥጫ ነበር፣ ደስቶ ፊንገር ነበር፣ ሽክክሞሽ ነበር። ያሸነፈ የሚመታባቸው፣ የተሸነፈ የሚወገርባቸው ጨዋታዎች!
ስናድግም ፓለቲካችን እንደዛው ናት!

በሽክክም ጨዋታ፣ ተሸካሚው እስኪያዝንልህ እስከፈለገበት ወይ እስከተስማማችሁት የመሸከም እዳ አለብህ። በፓለቲካ ሽክክምም አሸናፊውን መንግስት የመሸከም እዳ ሕዝቡ ላይ አለ። ሕዝቡ “ሸክሜ ከበደ” ብሎ ከቆረጠ ተሸካሚውን አሽቀንጥሮ ሊጥለው ይችላል። ግን ጀርባው ላይ አዝሎ እንዲህ ዓይነት ጨዋታ ያስፈራዋል- “አናቴን ቢለኝስ?” ብሎ ይሰጋል። በሽክክም ጨዋታ ያደጉ ሁላ ዛሬ የሽክክም ፓለቲካን ፈጥረዋል! ልጅነት በየፓለቲካው ጥጋ ጥግ እግሯን ሰቅላ ትስቃለች።

ዛሬ ዘመናይ ልጆች ተወልደው፣ “what the fu** is እቃቃ” ከማለታቸው በፊት፣ እቃቃ ያልተጫወትሽ አለሽ? በእቃቃ የውሸት ጋብቻ ቅድም ተጋብተሽ፣ አሁን ያልተፋታሽ አለሽ? ከአንዷ ጋር ውሉ ያልታወቀ ትዳር መስርተን ያችኛዋ እያየች ሌላዋን አላገባንም? እቃቃ ነበራ!
ዛሬስ?…. አድገን ብዙ የዕቃቃ ጋብቻ የሆኑ፣ የፓርቲ ጋብቻችን አላየንም? እገሌ ፓርቲ ከእገሊት ፓርቲ ተጋብቶ፣ ስለጋብቻቸው አውርተን ሳንጨርስ “ተፋታን” አላሉንም። “ሎጋው ሽቦ የሚል” ዘፈናችንን ሳንጨርስ፣ ስንት ሎጋ ሎጋ ፓርቲዎች የጋብቻ ገመዳቸውን( ነው ሽቧቸውን?) አልበጠሱም? እንደ ገና ከሌላ ፓርቲ ጋር ሲጋቡ አላየንም? እዚህስ ልጅነታችን አልነበረች አታሞ ትደልቅ የነበረችው?

ብጌ ወይም ብጋራህ የሚለውን ሳትጫወቺስ ያደግሽ ስንትሽ ነሽ?…. ከቤት የሆነ ነገር እየበላህ ስትወጣ ከየት መጣ ያላልከው ልጅ ከሩቅ “ብጌ…… ብጋራህ” እያለ አንጀቱ እስኪወልቅ እየጮኸ ይመጣል። ከያዝከው ላይ ይጋራል። ይሄን ጨዋታ ሳስብ ተመስገን ነው በዓይኔ የሚመጣው። እቤታቸው ብዙ ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ ስለማይኖር ቀርስ እና ምሳውን በብጌ ጨዋታ ነበር የሚሸውደው። ኸረ ውፍርፍር ብሎ አምሮበትም ነበር!

ዛሬስ እቺ ብጌ ጨዋታ አድጋ አድጋ (ማን ቱ ቱ እደጊ ብሎ እንደመረቃት እንጃ እንጂ) “ሙስና” አልሆነችም? አንድ ጠቃሚ ስራ ይዘን ስንወጣ ብጌ የሚሉ የባለጌ ባለስልጣኖች ድምፅ አላሸማቀቀንም? እኛስ ሙስናን እንደ ብጌ ጨዋታ ተገቢ ጨዋታ አድርገን፣ “ብጋራህ” ላለህ የምናጋራውን ይዘን አልወጣንም? ስንቱ እንደ ተመስገን በትልቋ የብጋራህ ጨዋታ ውፍርፍር ብሎ አላማረበትም? ….የብጌ ጨዋታ እንዲህ ትፋፋለች ብሎ ማን ጠበቀ? እዚህስ የምትፎልለው ልጅነታችን አይደለች??

ጊዜ የሰጣት ልጅነት፣ ፓለቲካ ትሆናለች ማለት ይሄኔ ነው። አዳሜ ፓለቲካችንን ለማረም ከሚራኮት ለምን ልጅነታችንን አያፀዳም? በሽታውን ከሚነቅፍ ለምን የበሽታ መፈልፈያ ቦታውን አያፀዳም? ወባን ከሚረግም፣ የረጋውን ውሃ ከሰፈሩ አያጠፋም?
የመናገር መብት አልተከበረም ከማለቱ በፊት፣ ልጆቹን “ዝም በል! ምንድነው በአዋቂ ንግግር መሃል ጣልቃ መግባት” የሚል ንግግሩን አያርምም። “ሰብዓዊ መብቴ ተጣሰ- አልተከበረም!” ከማለቱ በፊት ልጆቹ ላይ የሰነዘረውን ዱላ አይሰበስብም። ነገ እኚሁ ልጆች አይደሉ አድገው የዱላ ሂሳባቸውን የሚዯወራርዱት?

ልጅነት ተገፍታ….ተገፍታ አናት ስትወጣ አይደል አናት የምታዞረው? አያፍርም ባሳደኩ እጄን ተነከስኩ ይላል። ባሳደኩ አትበል፣ ባሳደምኩ በል! እንዲህም አድርጎ ማሳደግ የለ።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...