Tidarfelagi.com

ልጄ -ባዶ ወረቀቴ

ማን ማን ውስጥ እንደገባ፣ የቱ ገላ የማን እንደሆነ መለየት እስኪያስቸግረን ድረስ ተቆላልፈን ከመዋሰብ ያለፈ ነገር አላውቅም ነበር።
የወጣትነት ትኩሳትን ከማዳፈን፣ የቆመን ከማጠውለግ፣ ከግብት- ውጥት እና ግብት- ትፍት ጨዋታ በላይ ደስታ ይሰጠኝ የነበረ ነገር አላስታውስም።
….እንዲህ እንዲህ በየአልጋው ስንወድቅ እና ስንነሳ ፤
ግባችን ወግተህ ንቀል ነው።
ደስታችን በደቂቃ ተሰፍሮ በሰከንዶች የሚጦዝ ነው።
ውጤታችን፤ ሚጢጢ የአልጋ ላይ እሳተገሞራ ነው።
ይሄው ነው።

‹‹ዘለሽ አልበቃሽም..ለምን አትወልጂም?›› ይሉኛል የጸጉሮቼን ሽበት እየቆጠሩ።
‹‹ወልደሽ ክበጂ እንጂ!›› ይሉኛል የግንባሬ ላይ የእድሜ መስመሮች እያመለከቱ።
‹‹ ጊዜው እንዳያልፍ…ዱብ አድርጊው እንጂ›› ይሉኛል እንደ ቦምብ ላይ የተሰካ ሰአት የመውለጃ ጊዜዬ<<ቲክ..ቲክ…>>ማለቱን እንዳላቆመ የሚያዩ።
እኔ ግን…
መቅበጡ ሳያስፈራኝ መውለድ እፈራ ነበር።
መዝለሉ ደስ ብሎኝ ማርገዝ ያሰጋኝ ነበር።
ወይ ዘልዬ አልጨረስኩ ይሆናል። ወይ ሽበቶቼ ቀድመው፣ የእድሜ መስመሮቼ አብለው፣ ‹‹ቲክ ቲክ›› እያለ ጮሆ አላፊ አግዳሚውን የሚጠራው የማህፀኔ ሰአት ቸኩሎ ይሆናል።
የኢትዮጵያዊ ሴት የማህፀን አማካይ የእድሜ ጣሪያ ስንት ይሆን?
መውለድ እፈራ ነበር።
ለዚህም ነው ፤ አንቱ የሚባሉ ሀኪም የሚሆኑ ልጆቼን በኮንዶም ላስቲክ አፍኜ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ስጥል የኖርኩት።
ለዚህ ነው፤ የህዳሴ ግድብን የሚያንፁ ብሩህ መሃንዲሶችን ለሀገሬ እንደመስጠት በየአንሶላው ዘርቼ ለርካሽ ሳሙና ሲሳይ የዳረግኳቸው።
ለዚህ ነው፤ ፓርላማ ገብተው የሚያንቀለፉ ፖለቲከኞችን በመውለድ ፈንታ ከጭኔ እና ከምናምንቴዬ አስደፍቼ በሶፍት የጠረግኳቸው።
ልጅ ተከትሎ የሚመጣ የኑሮ መዘዝን ሽሽት ስንቱን ኮረኮንች ኮብልስቶን ሊያደርጉ የሚችሉ ልጆችን አኮላሸሁ።
ስንት የሱሪውን ቀዳዳ በነጭ ጋወኑ የሚደብቅ ችጋራም የህዝብ ትምህርት ቤት አስተማሪ መፍጠር ስችል ዘር አመከንኩ።
‹‹ልጅ የምትፈሪው በልጅ የሚገኘውን የማይታመን ደስታ ባለማወቅሽ ነው…ቀረብሽ!›› ይሉኛል ወልደው ‹‹ደስተኛ ሆንን››፣ ‹‹ምሉእ ሆንን››‹‹፣ ዛሬ ገና ለህይወታችን ትርጉም አገኘን›› የሚሉ ወዳጆቼ ጓደኞቼ።
እኔ ግን ልጅ ሳስብ የሚመጣልኝ በቀን 30 ብር ዳይፐር ነው።
በቤት ሰራተኛ አገዛዝ ስር መውደቅ ነው።
የአንከር ወተት ወጪ ነው።
እማዬን ‹‹ልጄን ያዥልኝ›› ብሎ መለመን ነው።
ከባሎቼ መቃቃር ነው።
የትምህርት ቤት ወጪ ነው።
እንደው ባጠቃላይ፤ ለሌላ ሰው መኖር ነው።
ራስ ወዳድ እሆን ይሆናል፤ ለሌላ ሰው መኖር ያስፈራኛል።
በየአልጋው ላይ ለደስታ ስሰማራ፣ አርካታን ሳሳድድ የማስበው ይሄን ብቻ ነው፡፤ ምናልባት ያ ነገር የሰራ አካልን ሲቆጣጠር አንጎል ይተኛ ይሆናል። የማስበው በደስታዬ ነው። የማስበው በምናምንቴዬ ነው።
ልጅ የሚወልዱ ሰዎች በአንጎላቸው ያስቡ ይሆናል። ለኔ ግን የዚያ አይነት ጊዜ አልነበረም።

…..በሆነ ሰሞን የቅርብ ጓደኛዬ ለመውለድ ስትዘጋጅ፣ የመውለድ ዱላ ቅብብሎሽ ውስጥ ተሰልፌ ዱላውን ያቀበለችኝ ይመስል ስለ ማርገዝ እና መውለድ አጥብቄ ማሰብ ጀመርኩ።
‹‹ልወለድ…ልክበድ…ዝላዩን ልተው›› ማለት ጀመርኩ።
በይ በይ የሚሉኝም ሰዎች ደስ አላቸው።
ከሳምንታት በኋላ ይህቺው ጓደኛዬ ምጥ የመጣባት ሴት የምትሆነውን ሁሉ ሆና ስታበቃ ወለደች።
ከአሰአታት በኋላ ልጎበኛት ሄድኩ።
ልትቀበር ስትል ያመለጠች መስላ ጠበቀችኝ።
‹‹ምነው?›› አልኳት
‹‹ምነው…?ምነው ትይኛለሽ እንዴ…!በእንትኔ ፅጌረዳ አበባ የወጣ መሰለሽ እንዴ…ልጅ እኮ ነው የወለድኩት››አለችኝ ለመሳቅ እየታገለች።
‹‹ምጥ አድክሟት ነው ልጄ…አንቺ አልወለድሽም…?›› አሉኝ ክፍሏ የተቀመጡት አክስቷ በኡኡቴ ዜማ።
ነገራቸው ገብቶኝ ዝም አልኩ።
ትንሽ ቆየሁና- …‹‹እና አሁን…በእሙሙዬ ከወለድሽ….›› ስላት አክስትየው በቁጣ ተነስተው ወጡ።
ሳቀችና ፤ ‹‹አንቺ ስድ…!የሴት ጓደኞች ወሬ እዚህ ታመጫለሽ…?እታባ እኮ አንዲህ ያለ ነገር አይጥማትም›› አለችኝ።
‹‹ተያቸው ባክሽ በፊትም ጠምደውኛል…!ይልቅ…በእሙሙዬሽ ከወለድሽ….እንዴት ነው…እንደ አዲሳባ አትለጠጥም…አትሰፋም…?.›› አልኳት።
ስቃ ዝም አለችኝ።
‹‹እውነቴን እኮ ነው…ባለሶስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ሆነሽ ተፌ እያመሸ መግባት እንዳይጀመር›› ስላት ቶሎ ብላ…
‹‹አንቺ ሞዛዛ…!ልጅ ከተወለደ እኮ አዲስ ሕይወት ነው…ተፌ <<ልጄ ልጄ>> የሚል ባል እንጂ ቦታ ጠበበ ሰፋ የሚያስፈራው አይመስለኝም›› አለችና ቆም አድርጋ- ‹‹ ግን ዶክተሬ አሪፍ ነበር›› አለችኝ::
‹‹እንዴት?››
‹‹ል…ቅ…ም…አድርጎ ሰፋኝ›› አለች <<ልቅም>>ን እየጎተተች….
ሳቅን።
‹‹ያማል አይደል?›› አልኩ ትንሽ ቆይቼ::
‹‹ምጥን የሚገልፅ የሕመም መለኪያ ቃል የለም ግን…ረሳሁት…ልጄን ሳየው…ረሳሁት››
‹‹ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው እውነት ነዋ›› ፈጠን ብዬ መለስኩላት::
‹‹እህ!…..›› አለች ትራሷን እንዲመቻት እያበጃጀች።
‹‹አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቂያለሽሽ› አልኩ ብዙ ሳልቆይ::
‹‹ምን…?››
‹‹አንደው ይሄ ሁሉ ጣጣ ቀርቶ ልክ እንደ ዶሮ እንቁላል ጣል አድርገን እቅፍ -እቅፍ አድርገን በሙቀት እድግ ቢሉ››
‹‹አንቺ….ሆ….!›› አለች አሁንም እየሳቀች።
ትርሲትዬ እንዲህ ናት። ተለቅማ ተሰፍታም ሳቅ አትቆጥብም።
‹‹ብዙ እትሳቂ..ስፌትሸ እንዳይላላ…ወይ እንዳይበጠስ…››
‹‹ይበጥስሽ ያባቴ አምላክ!››
‹‹የምር ግን ምን አስባለሁ…እንቁላል ብንጥል <<ከሽ ከሽ>> አርገው ውጥት ይላሉ..ምጥ የለ ምን የለ….ወዲያው መራመድ…ወዲያው መሄድ ይጀምራሉ። ከሽ ከሽ…ውጥት…እርምድ…ሰላምታ እየሰጡ ሂድት….ዳዴ የለ…ወፌ ቆመች የለ…ማሳደግ፣ መታገል ዝባዝንኬ የለም። ደስ አይልም?›› ስላት አክስትየው ከመከራ የተሰራ የሚመስል ፊታቸውን ይዘው ተመለሱ።
ግማሹን ሰምተዋል መሰለኝ፤ ››አይ እቴ! ወልደሽ ታይዋለሽ….የልጅ መውለዱ ማእረግ ምን ሆነ እና ታዲያ…!ቀን በቀን ማሳደጉ አይደለም;›› አሉኝ።
አፈርኩና እግሬ ጎማ ኖሮት ቶሎ እንዲወስደኝ እየተመኘሁ ፤ አንደነገሩ ተሰነባብቼ ‹‹ማርያም በሽልም ታውጣሽ›› ብዬ ውልቅ አልኩ።

….በሁለተኛው አመት ልጅ እንደፈራሁ፣ ምጥ አንደጠላሁ፣ በማሳደግ ጭንቀት እንደተጠመድኩ አርግዤ ወለድኩ።
ከዝላዮቹ አንዱ ልጅን ወለደ።
ከእሳተ ገሞራዎቹ አንዱ ልጅ ፈጠረ።
ከሰርክ ውጋ ንቀል ጨዋታ አንዱ ከዚያ ደስታ ለሚልቅ ሌላ ደስታ አለማ ዋለ።
እኔም ተዘርቶብኝ አበቀልኩ።
… የትርሲት እታባ መልእክት የገባኝ ሚጢጢዋ ልጄ፣
እንቁላል ከሽ አድርጋ ያልወጣችው ልጄ፣
አምጬ የወለድኳት ልጄ፣
ዳዴ እና ወፌ ቆመች ገና የሚጠብቃት ልጄ፣
…አመልካች ጣቴን በሚጢጢ አመልካች እና አውራ ጣቶቿ ጥፍንግ አድርጋ ስትይዘኝ ነው።
አየኋት።
ማርና ስኳር ተዋስበው የሰሯት አንጂ ከኔ እና እሱ አሮጌ ዝላይ የተፈጠረች አትመስልም።
አየኋት።
ልጄ ደስታዬ፣
ልጄ ሳቄ፣
ልጀ ሁለንተናዬ።
ልጄ አዲስ እድሌ፣
ልጄ ባዶ ወረቀቴ።
አየኋት።
ለዳዴ ትድረስልኝ።
ለወፌ ቆመች ትብቃልኝ።
አፈር አቡክታ ለማጠብ ያብቃኝ።
በሰርክ ሳቅና ደስታዋ፤
ቀለም አልባ ሕይወቴን ታድምቅልኝ።
የኑሮዬን ምሬት ታጣፍጥልኝ..።
አረ ልጄስ ቀ…..ስ…ብላ ትደግልኝ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...