Tidarfelagi.com

“ሌ ሚዝረብል” እና “ዣንቫልዣ”

=== እንደ መግቢያ ===

እነሆ የቪክቶር ሁጎ ታላቅ ስራ የሆነውን “Les Misérables”ን ልንዘክረው ነው። ይህ ድርሰት የፈረንሳይ ምድር ካበቀለቻቸው የፈጠራ ስራዎች መካከል በጣም ዝነኛው ነው። መጽሐፉ በዓለም ዙሪያ የሚታወቀው “Les Miserables” (ሌ ሚዝረብል) በተሰኘው የፈረንሳይኛው ርዕስ ነው። በበርካታ ቋንቋዎች ሲተረጎምም ርዕሱ ለዛውን ያጣል በማለት ተርጓሚዎች ፈረንሳይኛውን እንዳለ ይተውታል። ለምሳሌ ርዕሱ በእንግሊዝኛ “The Miserable”, “The Wretched”, “The Miserable Ones”, “The Poor Ones”, “The Wretched Poor” and “The Victims” ወዘተ… እየተባለ ለመፍታት ቢሞከርም አንዳቸውም የፈረንሳይኛውን ያህል የሚጥም ሆኖ አልተገኘም። ስለዚህ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትርጉሞችም መጽሐፉ የሚታወቀው Les Miserables በተሰኘው የፈረንሳይኛ ርዕሱ ነው። በሀገራችን ደግሞ “መከረኞች” እና “ምንዱባን” በተሰኙ ሁለት አርዕስት ወደ አማርኛ ተመልሷል።

“ሌ ሚዝረብል” ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ ነው። ትረካውን በ1815 ይጀምርና በሰኔ ወር 1832 በተካሄደው የፈረንሳይ ተማሪዎች አመጽ ወቅት ያቆማል። እግረ መንገዱን ግን ወደ ኋላ ይሄድና ቀደም ያሉ ታሪካዊ ኩነቶችንም ያወሳል። ለምሳሌ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ ድል የተደረገበት የወተርሉ ጦርነት በመጽሐፉ ውስጥ እየተደጋገመ ይነሳል። በሌላ በኩል መጽሐፉ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የፈረንሳይ ህብረተሰብ የአኗኗር ዘይቤ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በዘመኑ የነበረው የፈረንሳይ መንግሥት አወቃቀርና አሰራር፤ የፓሪስና የሌሎች ከተሞች ኪነ-ህንጻ፣ የህዝቡ ሀይማኖታዊ ተዋስኦ፤ የቴክኖሎጂ ደረጃ፤ የፍትሕ ስርዓት፣ የንግድ አሰራር ወዘተ… በመጽሐፉ ውስጥ በግሩም ሁኔታ ተዳስሰዋል።

=== የመጽሐፉ ጭብጥ==

በ“ሌ ሚዝረብል” ውስጥ ሁለት ሀይሎች ይፋጠጣሉ። እነርሱም ህግና ሞራል ናቸው። “ህግ” ገቢራዊ የሚደረገው ለብዙሃን ጥቅም ሲባል ነው። የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ህግ መኖር አለበት። ዕድገትና ብልጽግናን ለመጎናጸፍ የሚቻለው ህግ በአግባቡ ከተተገበረ ብቻ ነው። ነገር ግን ፍትሐዊነት ባልሰፈነበት ሁኔታ ህግና ደንብ አውጥቶ ለመተግበር መሞከር ውጤቱ ጭቆና ነው የሚሆነው። የገዥውን መደብ ጥቅም ለማስጠበቅ የወጣ ህግ ጊዜያዊ ሰላምና መረጋጋት ቢፈጥርም እያደር ብዙሃኑን ህዝብ ለችግርና ለመከራ ይዳርጋል። በሂደትም ይሉኝታን የማያውቅ “መከረኛ” ትውልድ ይፈጠራል። በእንደዚህ ዓይነቱ ህብረተብ ውስጥ ህግ “መከረኛው”ን ትውልድ ከጥፋት ሊታደገው አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን ህብረተሰብ ከጥፋት በመመለስ ቀናውን ጎዳና ሊመራው የሚችለው “ሞራል” (morale ) ብቻ ነው። ክፋትን ለማጥፋት የሚቻለው ሞራል ያለውን ትውልድ በመፍጠር ነው። “ህግ”ን በትክክል መተግበር የሚቻለውም ህብረተሰቡ ለሞራል ወጎችና ደንቦች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ከሆነ ብቻ ነው።

የ“ሌ ሚዝረብል” ዋና ጭብጥም ይኸው ነው! የድርሰቱ ዓላማ ሞራል ጤናማ ህብረተሰብን ለመቅረጽ ያለውን ፋይዳ በስነ-ጽሑፍ ጅረት መግለጽ ነው። ደራሲው ቪክቶር ሁጎ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ስራውን ሲያስተዋውቅ እንዲህ ይላል (ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን ነው የጻፍኩት)።

“So long as there shall exist, by reason of law and custom, a social condemnation, which, in the face of civilization, artificially creates hells on earth, and complicates a destiny that is divine with human fatality; so long as the three problems of the age—the degradation of man by poverty, the ruin of women by starvation, and the dwarfing of childhood by physical and spiritual night—are not solved; so long as, in certain regions, social asphyxia shall be possible; in other words, and from a yet more extended point of view, so long as ignorance and misery remain on earth, books like this cannot be useless.”
መጽሐፉን “መከረኞች” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የመለሱት ሳሕለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም ይህንን አንቀጽ እንዲህ ተርጉመውታል።

“በህግና በልማድ ስም ምድራዊ ኩነኔ የሚፈጥር የፍርድ ውሳኔ እስካለ ድረስ፤ ሰዎች በድህነት ምክንያት መዋረዳቸው፤ ሴቶች በረሃብ ምክንያት ሰብዓዊ ክብራቸውን ማጣታቸው፤ ህጻናት የዕውቀት ብርሃን በማጣት ጎደሎ ሆነው መቅረታቸው፤ እነዚህ የምዕተ ዓመቱ ታላላቅ ችግሮች መፍትሔ እስካላገኙ ድረስ፤ ህብረተሰቡ ነጻ አየር እንዳይተነፍስ የሚያግደው ሁኔታ እስካለ ድረስ፤ ባጭሩ ባለንበት ምድር ድንቁርናና ድህነት እስከ ሰፈኑ ድረስ “መከረኞች”ን የመሳሰሉ መጻሕፍት ተፈላጊነት ሳይኖራቸው ሊቀር አይችልም”
(ሳሕለ ሥላሤ ብርሃነማሪያም፤ “መከረኞች”፤ 1982)
———-
“ሌ ሚዝረብል” አምስት ክፍሎች አሉት። እያንዳንዱ ክፍል በስሩ በርካታ ምዕራፎች አሉት። እነዚህም ምዕራፎች በንዑስ ምዕራፎች የተከፈሉ ናቸው (በጠቅላላው 48 ምዕራፎችና 365 ንዑስ ምዕራፎችን ይዟል)። መጽሐፉ መጀመሪያ በታተመት ቅርጹ 1900 ገጾች አሉት (የእንግሊዝኛው ትርጉም 1500 ገጾች አሉት)።

===ዣን ቫልዣና እና ዣቬር===

“ሌ ሚዝረብል” በርካታ የትረካ ድሮች አሉት። ዋናው ታሪክ ግን “ዣን ቫልዣ” በተሰኘው ገጸ-ባህሪ ዙሪያ ያጠነጥናል። ይህ ሰው በድህነት ነው ያደገው። ከግብርና ውጪ የሚረባ ሙያ አልነበረውም። ለአንድም ቀን የትምህርት ቤት ደጃፍ ረግጦ አያውቅም። በተጨማሪም ሰባት የእህቱን ልጆች ያሳድጋል። ታዲያ አንድ ቀን ለነዚህ ልጆች ሲል አንዲት ቁራሽ ዳቦ በመስረቁ አምስት አመት ይፈረድበታል። ከታሰረ በኋላ ደግሞ ለብዙ ጊዜ የማምለጥ ሙከራ በማድረጉ ተጨማሪ አስራ አራት ዓመት ይከናነባል። ከእስር ሲፈታም “አደገኛ ሰው ነው፤ እንዳታስጠጉት” የሚል ቢጫ መታወቂያ ስለተሰጠው ማንም ሰው ሊያሳድረው ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም (የውሻ ቤት ውስጥ እንኳ ማደር አልቻለም)።

ዣን ቫልዣ በማይረባ ሰበብ መታሰሩ ሳያንሰው ህብረተሰቡ በርሱ ላይ መጨከኑ በጣም ያበግነዋል። በመሆኑም ይህንን የመከራ ስርዓትና መከረኛ ህብረተሰብ ለመበቀል ይቆርጣል። ይሁንና በዚያው ምሽት “እስቲ ካሳደሩኝ እድሌን ልሞክር” በማለት ከአንድ ቤት ሄዶ ሲያንኳኳ እንዲገባ ይፈቀድለታል። በቤቱ ውስጥ ያገኛቸው መነኩሴ እራት ካበሉት በኋላ ባማረ አልጋ ላይ እንዲተኛ ይፈቅዱለታል። በነጋታው ግን ዣን ቫልዣ ሸይጣን ይወሰውሰውና ከቤቱ ውስጥ ያገኘውን ከብር የተሰራ መመገቢያ በመስረቅ መንገዱን ይጀምራል። ነገር ግን ብዙ ሳይጓዝ በፖሊሶች ይያዛል። ፖሊሶቹ እቃው ወደ ተሰረቀበት ቤት አምጥተውት ቄሱን ይጠይቃሉ። ቄሱም “እኔ ነኝ የሰጠሁት፤ አረ እንዲያውም እነዚህን ከብር የተሰሩ የሻማ ማስቀመጫዎችም ሰጥቼው ነበረ” የሚል መልስ ይሰጡና ከፖሊስ ያስጥሉታል። ለዣን ቫልዣም “ትናንትና የገባህልኝ ቃል እንዳትረሳው! በቀሪው ዘመንህ ራስህን ለፈጣሪ ለማሳደር የሰጠኸኝን ቃልኪዳን ጠብቅልኝ” ይሉታል።

“ህብረተሰቡን መበቀል” የሚል የጥላቻ ስሜት በልቡ ላይ ይቀጣጠል የነበረው ዣን ቫልዣ በቄሱ ምግባር በእጅጉ ይደነቃል። በመሆኑም መነኩሴው ያሉትን ለመተግበር ይወስናል። ይሁንና በመንገድ ላይ ቃሉን ረስቶ ከአንድ ትንሽዬ ልጅ ላይ የገንዘብ ሳንቲም ይመነትፋል። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ፀፀት ይይዘውና ሳንቲሙን ለልጁ ሊመልስ ይጠራዋል። ቢሆንም ሊደርስበት አልቻለም። በሌላ በኩል ይህቺ አነስተኛ ስርቆት አንድ አደገኛ አዳኝ ትጠራበታለች።

ያ አዳኝ “ዣቬር” ይባላል። ዣቬር “በየትኛውም ቦታም ሆነ በማንኛውም ሰዓት ህግ መከበር አለበት፤ አንድም ጥፋት በይቅርታ አይታለፍም” የሚል የከረረ እምነት ያለው ሰው ነው። በመሆኑም ዣን ቫልዣልን ወደ እስር ቤት ሊመልሰው ቆርጦ ተነስቷል። ዣን ቫልዣ በበኩሉ “ፍትሐዊነት በጎደለው የቡርዣ ህግ ፊት ቀርቤ ድጋሚ መቀጣት የለብኝም” ባይ ነው። ስለዚህ እስከ መጨረሻው ድረስ ነጻ ሆኖ ለመኖር ይሞክራል። ነገር ግን መንገዱ እርሱ እንደሚመኘው ቀና ሊሆንለት አልቻለም። በአንድ በኩል ዣቬር የሚያደርገው የተጠናከረ ክትትል እንቅልፍ ይነሳዋል። በሌላ በኩል በዘመኑ የነበረው አስከፊ የሞራል ዝቅጠት የወለዳቸው ምግባረ ብልሹዎች ከተራ ዘረፋ ጀምሮ ነፍሲያውን ለማጥፋት እስከ መሞከር የዘለቀ ፈተና ይጋርጡበታል። ለራሳቸው መከረኞች ሆነው እርሱንም ለበለጠ መከራ ይዳርጉታል።

ታዲያ ዣን ቫልዣ እንዲህ ዓይነት ፈተና ተጋርጦበትም ቢሆን ወደ ብቀላ አያመራም። ሁሉንም እንደ አመጣጡ በፍቅር ለመመለስ ይሞክራል። የጎዱትን እንኳ በገንዘብ ይደጉማል። ሊገድሉት ያደቡትን ከመከራ ያድናል። ከዚህም አልፎ በክትትል ብዛት ህይወቱ እረፍት እንዳይኖራት ያደረጋትን ዣቬርን ከሞት ያድናል። ይቅር ባይነቱና ደግነቱ በሌሎች ዘንድ ያልተለመደ በመሆኑ ብዙዎችን መመሰጥ ይጀምራል። ትንታጉ ዣቬር በዣን ቫልዣ አድራጎት ተደንቆ “ከህግና ከሞራል ሰዎችን የመግራት አቅሙ ከፍተኛ የሆነው የቱ ነው?” የሚል ጥያቄ ለራሱ ያቀርባል። ጥያቄውን ለራሱ መመለስ ሲያቅተው ህይወቱን ያጠፋል። ዣን ቫልዣም የተከተለው የፍቅርና የይቅር ባይነት መንገድ በሌሎች ዘንድ ግንዛቤ ማግኘት ሲጀምር ከዚህ ምድር ይሰናበታል።
—–
“ሌ ሚዝረብል” በጣም ተነባቢ እንዲሆን ያደረጉት ሁለቱ ገጸ-ባህሪዎች ናቸው። ዣን ቫልዣ ፍቅርና በጎነትን ነው የሚወክለው። ዣቬር ግን ምድራዊውን ህግ ነው የሚወክለው። በሁለቱ ገጸ-ባህሪያት መካከል ያለው “አባሮሽ” ባልተጠበቀ መልኩ ሁለቱም ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመጡ አድርጎአቸዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት እን ፋንቲን፤ ኮቬት፣ ማሪዩ፣ ቴናርዲዬ፣ ጋቭሮሽ፣ ኢፖኒን፤ ወዘተ… በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮጳ ምድር ሰፍኖ የነበረውን የመከራና የአዝቅት ኑሮ ያንጸባርቃሉ። በአንዳንዶቹ ላይ የሚታየው የጭካኔ ድርጊቶች ስርዓቱ የሚያካሄደው ጭቆና ነጸብራቆች ነው። ፍትሕ አልባ ስርዓት ከሰፈነ ጨካኝና ለሌሎች ደንታ ህይወት የሌለውን ትውልድ ይፈጥራል።

——-
ሚያዚያ 1/2006
አፈንዲ ሙተቂ

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...