Tidarfelagi.com

ላንቺ ግጥም እየፃፍኩ ነበር!

የሆነ የዓለም ጥግ ላይ ህፃናት በረሃብ ሲያልቁ እኔ ላንቺ ግጥም እየፃፍኩ ነበር። ሁሉም ሲያድጉ አንቺን ማግኘት እንደማይችሉ ስለገባችው እንደሚያለቅሱ ይሰማኝ ነበር። እንደዚህ እያሰብኩ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ፈጣሪ ዓለም የሚያጠፋት በቁጣ ነው ሲሉኝ እገረማለሁ። ፈጣሪ ዓለምን ካጠፋ አንቺ ስትሞቺ በሚደርስበት ሀዘን እንደሆነ አምናለሁ። ይህን እያመንኩ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ፀጥታ በነገሰበት ሌሊት፣ እብድ ንፋስ ዛፎችን በሚረብሽበት ምሽት፣ ጣራ ላይ ታንጎ እየደነሰ ፀጥታን በሚረብሽ ሞገደኛ ዝናብ መሃል ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ሕዝቦች እርስ በእርስ የሚዋጉት፣ በጎሳ ተከፋፍለው የሚገዳደሉት አንቺ ጎድለሽባቸው እንደሆነ ይሰማኛል። ይህን እያሰብኩ ግጥም ስፅፍልሽ ነበር።

“ቦኮ ሃራም” ሁለት መቶ ምናምን ሴቶችን አገተ ሲባል ከነዛ ሴቶች መሀል አንቺ ትኖሪ እንደሁ ፈልጎ እንጂ ለክፋት አይመስለኝም ነበር። ይሄንንም እያሰብኩ ግጥም ስፅፍልሽ ነበር።

ከመስጊድ አዛን በሚሰማበት፣ ቅዳሴ ከቤተክርስትያን አቅጣጫ ወደ ቤቴ በሚተምበት ሰዓት ሁሉ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ከማለዳ የወፎች ዜማ በፊት፣ ከጀምበር ስንብት በፊት ሁሉ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ሀገሪቱ ላይ ፍትህ ጎደለ ሲሉ አላምናቸውም። መልካም አስተዳደር ጠፋ ሲሉ አልሰማቸውም። ነፃነት የለም ሲሉ አላደምጣቸውም። ሁሉም የሚነጫነጨው አንቺ ጎድለሽበት እንደሆነ እረዳለሁ። ጠቅላይ ሚኒስረትሩ አንቺን ቢያገኝ የነጋ ጠባ ውሸቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ አንቺን ብቻ እንደሚንከባከብ አውቃለሁ። ሁሉም አሁን የሆኑትን የሆኑት አንቺን ባለማግኘታቸው ነውና አልፈርድባቸውም።

ና ሰልፍ እንውጣ የሚለው ሁሉ፣ አንቺን ቢያገኝ በአንዱ እስር ቤት ተወርውሮ ገላሽን ካለመዳሰስ ጨለማ፣ ከንፈሮችሽን ካለመሳም እርግማን፣ አንቺን ካለማቀፍ ክፉ ዕጣ ለመዳን ጭራውን ጎሽቦ እንደሚቀመጥ አውቃለሁ። ይህንንም እያሰብኩ ግጥም እየፃፍኩልሽነበር።

ፈሪ ነህ ሲሉኝ እስቃለሁ። ሁሉም አንቺን ባለማግኘቱ ለራሱ ግድ ስለሌለው ደፋር የሆነ ይመስለዋል። ደፋር አንቺን አግኝቶ ለራሱ የማይፈራ ነው። አንቺን ሳላገኝማ እኔም ደፋር ነበርኩ፤ እሳት የሚናፍቀኝ፣ ወንድነት የሚፈትነኝ። እዚህም ጋር ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር።

ቀብር ላይ ተገኝቼ የሟች የሕይወት ታሪክ ሲነበብ እኔ በአዕምሮዬ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር። ታክሲ ሰልፍ ላይ ቆሜ ግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር። የቤት አከራዬ የቤት ኪራይ መክፈያ ጊዜዬን እንዳሳለፍኩ ሊነግሩኝ በሬን ሲያንኳኩ ግጥም እየፃፍኩ ነበር። ሳልከፍል ረስቼ የቆየሁትም ላንቺ ግጥም ስፅፍ ነበር።

የምፅፍልሽን ግጥም አሁንም አልጨረስኩም። ገና ብዙ እፅፍልሻለሁ። ጣቶቼ ብዕር መያዝ እስከቻሉበት ጊዜ ሁሉ እፅፍልሻለሁ። ጣቶቼ ቢያቅታቸው በውስጤ እፅፍልሻለሁ። ልቤ ላይ ከትብልሻለሁ።

ፈጣሪ ለፍርድ ሲመጣበግራም ብሰለፍ በቀኝ ግድ ሳይሰጠኝ ግጥም እፅፍልሻለሁ። ገነት የገባሁ እንደሆን ከገነት ብርሃናማ ቅጠሎች ላይ ግጥም እፅፍልሻለሁ።ገነት ውስጥ ከሚኖሩ መላዕክቶች ክንፍ ላይ ላባ መዝዤ ግጥም እፅፍልሻለሁ። ከገነት መግባቴ በላይ ላንቺ የምፅፈው ግጥም ገነቴ ይሆናል።

ሲኦል ብገባ ከሲኦል የእሳት ግግር አለቶች ላይ ከእሳቱ ባህር አጥቅሼ ግጥም እፅፍልሻለሁ። ግጥም ስፅፍልሽ የሲኦልን ንዳድ እረሳዋለሁ። በእሳቱ ባህር ሲቀቀሉ የስቃይ ድምፅ የሚያወጡ ነብሶች ድምፅ እዘነጋለሁ። ይብላኝ አንቺ ለሌለሻቸው። ትኩሳቱ ከሲኦል ቃጠሎ የገዘፈ ግጥም እፅፍልሻለሁ። ይህንንም በግጥም እየፃፍኩልሽ ነበር። ግጥም በስሜታችን መግዘፍ ልክ ሃይሉ እንደሚጨምር አውቃለሁ። የማይበርደው ፍቅርሽም ጣቶቼን የሚፋጅ ግጥም ውስጥ ነክሮት ይውላል። ከፃፍኩልሽ ግን ያልፃፍኩልሽ ይበልጣል። አሁንም ላንቺ ግጥም እየፃፍኩ ነው፤ እንደ ከዚህ በፊቱ! እንደ ወደፊቱ!!

ይህች ፅሁፍ ከልቡ ለሚገጥመውና በቅርብ ማተሚያ ቤት እየተመላለሰ ላለው ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ ትሁን፣ ከተቀበለኝ።

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

3 Comments

 • Anonymous commented on March 28, 2015 Reply

  በጣም የሚገርም ፅሁፍ ነው … ጥልቅ ነው!

 • FIkadutilahun657@gmial.com'
  fikadu tilahun commented on November 3, 2018 Reply

  arif nw

 • Masresha Tilahun commented on August 5, 2019 Reply

  አሪፍ የሚገርም ፅሁፍ ነዉ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...