Tidarfelagi.com

ለቅምሻ የተቀነጨበ

…..ብዙው ኢትዮጲያዊ የራሱን ነፍስ ኑሯት አያውቅም … ከልጅነት እስከእውቀት ለሌሎች ይኖራል ! ወዶ ሳይሆን ተገዶ !! ሙሉ ደሞዙን ደስ ብሎት ተጠቅሞበት የሚያውቅ ማነው ? …. ለዛ ነው ኢትዮጲያ ውስጥ ኑሮ ‹‹መቀማት ›› የሆነው ……የምትረዳውን ሰው ወደድከውም አልወደድከውም መርዳት ግዴታህም ይሁን ውዴታህ ብቻ የሆነ ሰዓት ቁመህ ስታስብ ለራስህ አለመኖርህ ይገባህና ሆድ ይብስሃል

በጣም የሚያበሳጭህ ደግሞ መርዳትህ አይደለም የረደሃው ሰው ከነበረበት ምንም ፈቀቅ አለማለቱ ! ሶስተኛ ክፍል እህትን ረድትሃት አስረኛ ክፍ ትሆናለች …እናትና አባትህን ረድተህ ወደቤትህ ስትመለስ አክስትህ መታመሟን ትሰማለህ ….ባለፈው ስራ ፈልግልኝ ያለችህ በኮምፒውተር ሳይንስ ተመርቃ ቤት ቁጭ ያለችው የአክስትህ ልጅ ደግሞ ትዝ ትልሃለች …..

ፍቅረኛህ ራሷ ሴትነቷን ሰፊ ኪስ አድርጋ እዛ ጋ መቆሟ አይቀርም ….ወንዱም ቢሆን ያው ነው አረብ አገር ትሂድ ወይ እዚህ ስራ ትያዝ ብቻ ‹‹ስራ›› የሚባለው ነገር ካላት ደመወዟ ነው ከልጅቱ ቀድሞ ትዝ የሚለው … በዚህ ኑሮ የፈለገ ብትንጠራራ ራስህ ላይ አትደርስም …ማንም እራሱ ላይ አይደርስም የሆነ ሰው ሲደርስልህ ኑሯል አንተም መድረስ ግዴታህ ነው ….. ህዝቡ ራሱ ይልሃል ስትመረቅ ስራ ስትይዝ ስልጣን ስትይዝ ወላ ስትሰርቅ

‹‹ እሰይ ለዛች ደሃ እናትህ ደረስክላት ….
እሰይ ለአባትህ ደረስክለት እንደዛ ሁኖ አስተምሮ ….
ለትንንሽ እህትና ወንድሞችህ ደረስክላቸው …
ስትሰደድ ሁሉ ደረስክ ትባላለህ ….››

ከዚህ ሁሉ መድረስ በኋላ መንግስት ራሱ አይኑን በጨው አጥቦ በቴሌቪዥን እንዲህ ይልሃል
‹‹ ለአገርህ ደረስክላት !! ››

ብርርር ብለህ ሰው የማይደርስበት አለም መሄድ ያምርሃል ….ቢሆንም ሁሉን ቻል አድርገህ ወደላይ ወደፈጣሪህ ቀና ትልና ‹‹ አንተ ድረስልኝ ›› ትላለህ ! ተደራሽነት የሚለው ቃል ልማታዊ የማይመስለኝ ለዚህ ነው ! ራእያችን ራሱ በምናምን አመት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ላይ …..እ ን ደ ር ሳ ለ ን ! መድረስ ቃሉ ቢወሳሰብም የሆነ ከራስ የመራቅ ነገር በውስጡ አለ !

በቃ ራስህ ላይ መቸም አትደርስም ! መርዳት የሚሰጠው እርካታ አለ መንፈሳዊም ስጋዊም ደስታ አለው …ግን ፈቅደህ ስትሰጥ እንጅ ድህነት ማጅራትህ ይዞ ለሌሎች ስጥ ሲልህ አይደለም !! ይሄ ሰብአዊ ንጥቂያ ነው !! የሕይወትን ትቢያ አንዴ በትምህርት አንዴ በስራ ስትቆፍር የምትኖረው በድህነትህ ከደነደነ ከርሰ ምድርህ ውስጥ የተቀበሩ ተረጅወች ጋር ለመድረስ ነው …

የትምህርት ዶማህ የስራ አካፋህ በበቂ አልቆፍር ሲልህ የሌብነት ትራክተርህን አስነስተህ ትሰቀስቀዋለህ ….እሱን ነው ሙስና የሚሉት ! በአገርህና አገሬ ታሪክ ውስጥ ልብ ብለህ ካየህ ‹‹ ለምን ይሄ ድሪቶና ግትልትል የደረስክለትና ድረስልኝ ሰንሰለት በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አይስተካከልም ›› ብለው የጠየቁ በፈጥኖ ‹‹ደራሽ›› ወታደር ሲቀጠቀጡ ሲታሰሩና ሲገደሉ ትታዘባለህ !

ለምን …..ካልክ
‹‹ ለአገሬ ምን አደረኩላት እንጅ ምን አደረገችልኝ አትበል ›› የሚል የሻገተ ጥቅስ ይመዛሉ ….ለምን እነሱ እራሳቸው አያደርጉላትም …..ማዘለዎች! በአገር ካባ ተጀቡነው ላብህን ጠብ አድርገህ ስልጣን ላይ አሰንብተኝ እንጅ መብት ፍትህ ምናምን አምጣ አትበለኝ የሚል ቅኔ ዘመን በፈጀ ጥቅስ ያጣቅሱብናል …. ስልጣን ከማያዛቸው በፊት ሁሉም ‹‹ደረስንልህ መጣንልህ ›› ሲሉ ኑረው አገር ሲሆኑ ለአገሬ ምን ሰራሁ በል ምናምን ….. እሽ መጀመሪያ ከአገር ከመቀበል በፊት ለአገር መስጠት ከቀደመ ቅምጥልጥል ብለው የሚኖሩት ሁሉ ለአገራችን ምን አድርገውላት ይሄን ሁሉ እንዳደረገችላቸው ይንገሩን …..!!

‹‹አገሬ ምን አደረገችልኝ ›› ትክክለኛው ጥያቄ ይሄ ነው ….አገር ማለት ሰው ነው ብለው የለ እኮ ሰወቿ ….. በኔው በድሃ ላብ ሰው የሆኑት ሰዎቿ ምን አደረጉልኝ ?? !! እውነቱን ለመናገር እንዴት ዘቅዝቀው ኪሴን እንደሚያራግፉት በተረት ነገሩኝ ….እነሱ ኪስ ላይ ድርሽ ብል ግን ፍዳየን እንደሚያበሉኝ በተረት በዛቻ በዜና ሳይቀር ነገሩኝ !! ‹‹ተደራጅተው ስራ በመፍጠር ከጠባቂነት መንፈስ ተላቀቁ ምናምን ›› የሚል ዜናኮ እዛው ስራ ፍጠር ከእኔ አትጠይቅ ማለት ነው …..

እና አንዳንዴ ሁሉ ነገር ከአቅምህ በላይ ይሆንና ወላ ቤተሰብ ወላ አገር አራት እግራቸውን ይብሉ ….የምትልበት ጊዜ ይመጣል ! እንጅ ራስን ሁነህ ብትኖር ስንት ታላላቅ ነገር ትፈጥር ነበር ….አንቱ የሚባል ደራሲ መሆን የሚችል ወገንህ መዝገብ ቤት ተቀብሮ ይቀራል ….ራሱን እንዳይሆን የሚረዳው አላ ….ትልቅ ሰዓሊ መሆን ሲችል የከባድ መኪና ሹፌር ‹ፓ እሱኮ ኮንትሮባንድ ይሰራዋል እንደጉድ › እየተባለ …..ጎረቤቱ ‹‹ጅቡቲ ስትሄድ ዲቪዲ ፕሌየር አምጣልኝ እዛ ርካሽ ነው ብለዋል ›› እያለችው ! ደግሞ ሳይሏቸው የሚተርቱት ተረት አለሃ …”ከራስ በላይ ንፋስ!” ከራስ በላይ ተረጅ ነው ያለው …ንፋስ አግኝተህ መተንፈስማ በምን እድልህ !! ዝም ብለህ ብታስበው እኮ ለሌሎች ሳይሆን ለራስህ ነበር ከንፈርህን የምትመጠው ….

ምርጥ ትዳር ቆንጆ ሚስት የሚያሳሱ ልጆች ምርጥ መኪና ….ቤት ዝና ምናምን ይኖርህ ይሆናል ….ግን አንተን ራስህን ስላጣህ አርቲስት ስታይ አርቲስት የመሆን ስሜት ውስጥህ በለጭ ይላል ….ዘፋኝ ስታይ ዘፋኝ …ሯጭ ስታይ ሯጭ …. የሃይማኖት ሰባኪ ስታይ ሰባኪ ….አየህ ውስጥህ ገና ከምኞት አርፎ እፎይ አላለማ ….እንደተመኘህ ትኖራታለህ ….

ምናባቱ ብለህ ራስህን ፍለጋ እንዳትሄድ አሁንም ጉልበትህ ላይ የተቀመጠ ህፃን የገዛህለትን ብስኩት እየገመጠ ለቀጣይ ብዙ አመት የመረዳት መብቱን አንተ ላይ ጥሏል ….ማን ውለደኝ አለህ !! ጠፍተናል ! የድህነት አስቀያሚ ገፅታ ይሄ ነው … ሰው ሶፋ ሲገዛ ኩንታል ጤፍ ሲሸምት ‹‹ያ ሁሉ አለፈ ›› ይላል እንጅ ድህነት አያልፍም ! አንተን መሻትህን አሳልፎ ነው ከማትፈልገው ተራራ ጫፍ ላይ በተሳሳተ ማንነት አስቀምጦህ የሚሄደው ! ላዛ እኮ ነው ህዝባችን ተች የሚሆነው …ያጣውን ሌላው ላይ ሲያየው እየተበሳጨ ! ህልሙን ሰው ቤት እያለመ ….

2 Comments

  • nebyou1986@gmail.com'
    nebyou commented on August 4, 2016 Reply

    አሌክሶ ተመቸኸኝ፡፡… ሌሎች እንዲኖሩ እኛ መኖር ያቆምን ብዙ ነን፡፡… መቼ እንደምንኖር ፈጣሪ ያውቃል…

  • ወንድሙ ተካ commented on September 10, 2017 Reply

    እግዜአብሕር ይስጥልኝ እድሜህን ያርዝመው

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...