Tidarfelagi.com

ሆያ ሆዬ ድሮና ዘንድሮ

ዘንድሮ እንዲህም ሆነ……..

ሆያ ሆዬ የሚጨፍሩ የዘመኑ ነጋዴ ህፃናት ባላቶሊ ቁርጣቸውን በቄንጥ ተቆርጠው ፣ ደመወዜን የሚያሸማቅቅ ኤር ናይክ ተጫምተው ፣ ዱላቸውን ይዘው ወደ ተቀመጥኩበት ድድ ማስጫዬ መጡ
‹እስቲ ሆያ ሆዬ ጨፍሩልኝ?› ብዬ ስጠይቃቸው
‹ባለስንት?› ብለውኝ በደህንነቶች እንደተከበበ የተቃዋሚ ፓርቲ ቢሮ ደህና አድርገው ቀልቤን ገፈፉልኝ

ድሮ እንዲህ ነበር……

በተረከዙና አውራ ጣቱ ጋር ማስተንፈሻ በሰራው ቀዳዳ ካሲያችን ያደረግነው አሮጌ ሸራ ጫማችን ቦይ ለቦይ ስንከራተት ጨይቅቶ ፣ ቆረቆራም ቆንጮ ፀጉራችን በቅጫማችን ብዛት ደህና የሰርገኛ የጤፍ እርሻ መስሎ እትዬ አሰገደች ቤት በር ላይ ‹መጣና ባመቱ….› ብለን ሆያ ሆዬአችንን መጨፈር ከጀመርን ግማሽ ሰዓት አስቆጥረናል፡፡ ምንም ሳይሰጠን ጉሮሮአችንን ከሰነጠቅን በኋላ ‹ኧረ በቃ በቃ ጉሮሮአችን ነቃ!› ብለን ልንሄድ ስንል….እትዬ አሰገደች ከቤታቸው ወጥተው…….‹ልጆቼ ለዛሬ አድርሰናል ፣ ባይሆን የዛሬ አመት ቀድም ብላችሁ ኑ› ይሉናል፡፡ ማንም እንዳልቀደመን ሰፈሩ ውስጥ እኛ ብቻ ልጆች እንደሆንን እናውቃለን ቢሆንም ፣ 10 ሳንቲም ለመስጠት ለዛሬ አመት ቀጠሮ ይዘን ወደ ሌላ ቤት እንሄዳለን፡፡

ዘንድሮ……

ጩጬ ብራዘሬ አቢ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ የሸቀሉትን ብር ከተከፋፈሉ በኋላ ወደ ቤት ሲመጣ
‹አቢ ስንት ስንት ተካፈላችሁ?› አልኩት
‹ሰባ ሁለት ሰባ ሁለት ብር› አለኝ
‹አቤት ዛሬማ ዘግተሀል ፣ በል ምንም እንዳታጠፋ ቀበሌ ሂድና ዘይት መቷል አሉ ግዛበት› ስለው ገና ባስራ ሁለት ዓመቱ እንዲህ አለኝ
‹ኧረ ባክህ ለኔ ራሱ ብትጨምርልኝ ደስ ይለኛል፡፡›
‹ይሄን ሁሉ ብር ምን ታደርግበታለህ?›
‹ዛሬማ ለስልኬ የ50 ብር ካርድ ነው የምለቅባት…..የቀረችኝን ደግሞ ከእዮባ ጋር አዋጥተን በርገር እንበላበታለን›

ድሮ…..

ከሾላ እስከ ቀበና ፣ ከየካ ተራራ እስከ ሀያ ሁለት ድረስ ‹ክፈት በለው ተነሳ ያንን አንበሳ› ስንል ውለን በጣም ብዙ ከሸቀልን ለ4 (እኔ ፣ ጥሌ ፣ ኤፍ እና ትንሹ ወንዴ…) አስር ብር ነበር፡፡ በሄድንበት ቤት ሁሉ ያኔ እንንቀው የነበረው አሁን ሰማይ ብንቧጥጥ የማናገኘውን የጥቁር ስንዴ ዳቦ ነበር የሚሰጠን፡፡ እኛ ደግሞ ዳቦ ትክት ይለናል ፣ በተለይ የስንዴ! አሁን ልጄ ፍርኖ ዱቄት ጠላቴ ነው!!!! አንዳንዴ 10 ሳንቲም የምትሸጠዋን አቢሲንያ ስኳር ገዝተን ቀፈታችን እስኪቦተረፍ ድረስ እንወጥቀዋለን፡፡ የተቀረውን ደግሞ ሾላ ገበያ መሲ መኮረኒ በፍርፍር የሚሸጥበት ጎን ድሮ ትርፍራፊ ምግብ አድርቃ እየወቀጠች ድርቆሽ ለፍርፍር የምትሸጥ ሴትዮ ነበረች፡፡ በፌስታል በፌስታል የያዝነውን ዳቦ በስሙኒ ሂሳብ እንሸጥላታለን፡፡ (አስቡት አራት ፌስታል ዳቦ በአንድ ብር ማለት ነው)…….ከዛም በጊዜው ለነበረን ጥቁሩ ጌም ወይም በባትሪ ለሚሰራው ትንሽዬው ራዲዮአችን ዱራታ ባትሪ ድንጋይ እንገዛለን፡፡ የተረፈችንን ሳንቲም ሰው ለማስደንገጫ የአስር ሳንቲም ርችት ፣ ዱርዬ ለመሆን ስለምንፈልግ በ35 ሳ ፓስቲ ፣ የጆልጁስ በረዶ በ10 ሳ/የበሶና የአቡካዶ በ 25 ሳ ፣ ያንን ሁሉ ድፎ ዳቦ በስሙኒ ሸጠን ከአደይ ቤት ሽልጦ በስሙኒ ገዝተን እንበላለን ፣ ኧረ ዋናውን ረስቼው ለካ ለእንቁጣጣሽ አበባ መሳያ ቀለምና ሉክ ነበር በቅድሚያ የምንገዛው……..ብቻ ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡
ዘንድሮ እንዲህ ተመረቅን……
‹እዛ ማዶ አንድ ሂፕአፕ እዚ ማዶ አንድ ሂፓፕ
የኔማ ወንዴ ሮናልድ ትራምፕ› (ኧረ ምንሼ ነው በሰላም ሀገር የሰውን ስም ማጥፋት አሁን ምን ይሉታል!)
በዚህ ግጥማቸው ስላናደዱኝ ብር ልሰጣቸው እጄን ወደ ኪሴ ስከትባቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው
‹እዛ ማዶ አንድ ካርሎስ እዚ ማዶ አንድ ካርሎስ
የኔማ ወንዴ ሮቤል ኪሮስ›
(ለካ ሳላውቀው እጄ ኪሴ ውስጥ በጣም መዋኘት አብዝቶ ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች ከዚህ የባሰ ሳይሉኝ ኪስ ያፈራውን ደመወዝ ያሸማቀቀውን ብሬን ሰጠኋቸው)
ታዲያ ሊተዉኝ ነው ፣ እንዲህ ብለው ጭፈራቸውን አሳረጉት
‹በፈረስ አፍንጫ አይገባም ትንኝ
አቶ ወንድማገኝ አይፎን ይግዙልኝ›
ድሮ እንዲህ መረቅን……..
‹…..ማርያም አውጪኝ ከጭንቀቴ
በቦክስ ሳይሆን በካራቴ…..› (አይ ልጅነት! ያኔ ምኑንም ሳናውቀው ለካ እንዲ ብለንም ገጥመን ነበር)
በኛ ጊዜ አብዛኛው ሰፈር ያለ ጨፋሪ እንዲህ እያለ ይመርቅ ነበር….
‹እዛ ማዶ አንድ ብር እዚ ማዶ አንድ ብር
የዚ ቤት ጌታ ባለ ባቡር› (ባቡር ሳናይ የተወለድን ትውልዶች ለካ እንዲህም ተንብየናል)
‹እዛማ ማዶ አንድ ካልሲ እዚ ማዶ አንድ ካልሲ
የዚ ቤት ጌታ ባለTaxi› ( እንዲህ እያለ ሲገጥም ያደገ የኔ ትውልድ ምኞቱ ሁሉ መንጃ ፈቃድ አውጥቶ የታክሲ ሹፌር መሆን ነበር ፣ ህልሙን አብዛኛው የሰፈሬ ልጅ አሳካው)
‹የወፋፋ የወፋፋ
የወለዱት ይፋፋ
የወፍ ደግ የወፍ ደግ
የወለዱት ይደግ
…..እንዲሁ እንዳለን…..ሆ….አይለየን
…..ላመቱ በሰላም…….ሆ……ያድርሰን›

መልካም ቡሄ!

One Comment

  • atetefmelaku29@gmail.com'
    አተረፍ መላኩ commented on September 22, 2016 Reply

    ለማኝ እንጁ በአል የሚያከብር ልጅ የለም. ጥሩ አተያይ እና አገላለጽ ነው::

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...