Tidarfelagi.com

ሄሊ እና የመንዝ ወርቅ

በዚያ ሰሞን ለአጭር ጊዜ ስራ የተቀጠርኩበት አንድ ቢሮ ፈረንጅ አለቃዬን ልተዋወቃት ቢሮዋ ሄድኩ፡፡
‹‹ኦው!አዲሷ ኮንሰልታንት! ማነው ስምሽ?›› አለችኝ አየት አድርጋኝ፡፡
‹‹ሕይወት እምሻው››
እኔን ሳይሆን የምታገላብጠውን የወረቀት ክምር አያየች ‹‹ኦህ…አጠር አድርጊውና ንገሪኝ ›› አለችኝ ፡፡
ግራ ገባኝ፡፡
‹‹ይቅርታ ምን አልሽኝ?›› አልኳት ::
‹‹እዚህ ሀገር ስማችሁ ረጅም ነው…አይያዝም..አጠር አርገሽ ንገሪኝ እስቲ››
ደሜ ሲግል ተሰማኝ፡፡
ይሄ እኮ የሕይወት ታሪክ ወይ ወርሃዊ ሪፖርት አይደለም፡፡ ስም እንዴት ነው አጠር ተደርጎ የሚነገረው!?
‹‹ስሜ አያጥርም፡፡ ስሜ ሕይወት እምሻው ነው፡፡ ሕይወት ልትይኝ ትችያለሽ›› አልኳት የተቀመጥኩበት ወንበር በድንገት እንደ ኮረት እየቆረቆረኝ፡፡
‹‹እህ..ይቅርታ…እኔ የአፍሪካውያን ስሞች አይያዙልኝም…ይቅርታ….ሂዊ…ዎ…ት….›› እያየችኝ መለሰች፡፡
‹‹ሕይወት›› አልኩ ጫን አድርጌ
‹‹ይቅርታ….›› አለች መልሳ፡፡ ይቅርታዋ ከአንገት በላይ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡
ለጥቂት ሰከንዶች ስሜን አንዴ ‹‹ሂዋት›› ሌላ ጊዜ ‹‹ሂዎዎዎት›› እያለች ስሜን ስትገዘግዘው ባለማመን እያየኋት ሳለሁ፤ ትንሽ ቆየችና፤
‹‹በቃ ስራው ትንሽ ጊዜ ስለሆነ ካሁን በኋላ ‹‹ሄሊ ›› ነው የምልሽ…ይቅርታ.. አለችኝ፡፡
ጥያቄ አልነበረም፡፡ ፈቃድ ጥየቃ አልነበረበትም፡፡ ውሳኔ ነው፡፡
ጨስኩ፡፡
ተነስቼ ባንቃት ደስ ይለኝ ነበር፡፡
አብረውኝ የሚሰሩ ፈረንጆች የኔንም ሆነ የኢትዮጵያውያን የስራ ጓደኞቼን ስም ለመጥራት ሲቸገሩ ይሄ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ቢሆንም ትንፋሽ ሰብስበውም፣ አንጋደውም፣ አወላግደውም ቢሆን በስማችን ይጠሩናል እንጂ ዳቦ ሳይቆረስና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሳይታወጅ ስማችንን አይቀይሩም፡፡
ስሜ እንዴት እና ለምን እንደወጣ የማውቀው እኔ ነኝ፡፡
የስሜን ታሪክ የማውቀው እኔ ነኝ፡፡
ዛሬ በእንጀራ ምክንያት ፊቷ የቆምኩ አንዲት አፍሪካ ውስጥ የምትሰራ ግን የአፍሪካውያን ስም ሳይያዝላት ሲቀር የፈለገችውን ስም የምትሰጥ ፈረንጅ፣ ምላሷን በደንብ ማነቃነቅ ሰንፋ ስሜን በደቂቃ ‹‹ሄሊ›› ብላ ስትጠራው ጨስኩ፡፡
በዚያችው ቅፅበት ሳስበው እዚያ ቢሮ ከሷ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ሀበሾች ሁሉ ስማቸው ወይ የፈረንጅ፣ የሀበሻም ቢሆን የፈረንጅ እንዲመስል መስሎ እንደተከረከመ ትዝ አለኝ፡፡
አንተነህ ነኝ ያለኝ ልጅ ‹‹አንቶኒ›› ፣ ስሜ ‹‹አዲስ ›› ነው ያለችኝ ልጅ ‹‹አዲ›› ፣ ‹‹መስከረም›› ብላ የተዋወቀችኝ ልጅ ደግሞ ‹‹ሜሪ›› ተብላ እንደምትጠራ ትዝ አለኝ፡፡
ስማቸው ለርሷ ምላስ እንዲስማማ እና ሳትጨነቅ እንድትጠራቸው ብቻ በፈለገችው ስሞች ተተክቷል፡፡
ይህን ሳስብ ይባስ ጨስኩ፡፡
ራሴን ለመቆጣጠር ሞከርኩና፤ ‹‹እ….ያንቺስ ስም ማን ነበር?›. አልኳት ከወንበሬ እየተነሳሁ፡፡ አውቄ ነው፡፡ ስሟን አውቀዋለሁ፡፡
‹‹ሜሪዴት ሊይን እባላለሁ›› ብላ መለሰች፡፡
‹‹ሜሪ ዳት…?ሜሪ ዴዝ…? እህ….ማሪዳይት……?አይ አልተያዘልኝም.. በቃ ከዚህ ወዲህ ‹‹የመንዝ ወርቅ አለባቸው›› እያልኩ ነው የምጠራሽ›› አልኳት እና ለምላሽ ጊዜ ሳልሰጣት፤ የምሰጣትን ወረቀት ሰጥቼያት ደም ከመሰለው ፊቷ ጋር ትቻት ወጣሁ፡፡
በሶስተኛው ሳምንት ሊታደስ ይችል የነበረው አጭሩ የስራ ውሌ ሲጠናቀቅ ለውሸት የቀረበ ምክንያት ተፈጥሮ ውሌ እንደማይታደስ የሚገልፅ በመንዝ ወርቅ አለባቸው የተፃፈ ኢሜል ደረሰኝ፡፡
አዘንኩ፡፡
ቢያንስ ግን መስሪያ ቤቱን የለቀቅኩት እናትና አባቴ በምክንያት ያወጡልኝ ስሜን ሳልለቅ ስለነበር ደስ አለኝ፡፡

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...